Saturday, 14 June 2014 11:09

የ“ቤተሰብ አካዳሚ” ተማሪዎች ነገ የፈጠራ ስራቸውን ለእይታ ያቀርባሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

         የ“ቤተሰብ አካዳሚ” ተማሪዎች ነገ በት/ቤታቸው ቅጥር ግቢ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለእይታ ያቀርባሉ፡፡ ከፈጠራ ስራዎቻቸው መካከል በየ45 ደቂቃው ራሱ የሚደውል (አውቶማቲክ) የት/ቤት ደወል፣ አውቶማቲክ ቴለር ማሽን (ATM)፣ አንሰሪንግ ማሽን፣ ቤትን ከሌባ የሚጠብቅ መሳሪያ (ሆም ሶኪዩሪቲ) እና ንፋስን ተጠቅሞ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈጥር (wind turbine) እንደሚገኙበት የትምህርት ቤቱ አክቲቪቲ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም አፈወርቅ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

ከኪንደር ጋርተን እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ 65 ተማሪዎች የፈጠራ ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ የተናገሩት አቶ ዘላለም፤ ተማሪዎች የፈጠራ ስራ ሲያቀርቡ የዘንድሮው ለዘጠነኛ ጊዜ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በነገው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ጀምሮ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለእይታ ለሚያቀርቡ ተማሪዎች እንደ ባለፉት ዓመታት ሁሉ ሜዳሊያና የእውቅና ሰርተፍኬት እንደሚሰጣቸው የጠቆሙት የት/ቤቱ አክቲቪቲ ዳይሬክተር፤ አንዳንዶቹ የፈጠራ ስራዎች የሚያስደንቁና ወደፊት የሰውን ልጅ የሥራ ጫና የሚቀንሱ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

“በአንድ ተማሪ የተሰራው አውቶማቲክ ደወል መምህራን በየጊዜው ደውሉ ጋር እየሄዱ የሚያባክኑትን ጊዜ ይቀንሳል” ያሉት አቶ ዘላለም፤ ATM ማሽኑም ቢሆን በደንብ ተሻሽሎ ከተፈበረከ ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን በመተካት፣ የውጭ ምንዛሬን ያስቀራል ብለዋል፡፡ ቤትን ከዘረፋ ለመከላከል የተሰራው መሳሪያ፤ ሌባ ወደ ግቢ ሲገባ በንዝረት፣ በድምፅና በምስል ለባለቤቶቹ መልእክት እንደሚያስተላልፍ ጠቁመው፤ ይህም የፈጠራ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሌቦች ዝርፊያ ይቀንሳል ሲሉ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ በንፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጨው ማሽንም ቢሆን ትልቅ አገራዊ ፋይዳ እንዳለው የገለፁት አቶ ዘላለም፤ በ65ቱ ተማሪዎች የሚቀርቡት የፈጠራ ስራዎች ወደፊት ለአገሪቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ አልጠራጠርም ብለዋል፡፡ የፈጠራ ስራዎቹን ለመመልከትና እውቅና ለመስጠት የተማሪ ወላጆችና መምህራን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

Read 3176 times