Saturday, 07 June 2014 14:37

እግርኳስ፣ ትልልቆቹን አገራት ገና አልማረከም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ቻይና፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዢያ ለእግር ኳስ ባይተዋር ናቸው
በአሜሪካ ክቧ ኳስ ከሞላላ ኳስ ጋር መፎካከር አልቻለችም

የህንድ ቡድን በአለም ዋንጫ የመካፈል ጥሩ እድል ያገኘው ከ64 አመታት በፊት ነው። በብራዚል በተዘጋጀው የያኔው የአለም ዋንጫ ላይ ያለ ማጣሪያ እንዲካፈል የተጋበዘው የህንድ ቡድን፣ እድሉን አልተጠቀመበትም - በሁለት ምክንያቶች። አንደኛው ምክንያት፣ ድህነት ነው። የመጓጓዣና የመሰንበቻው ወጪ ከበዳቸው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኋላቀርነት ነው። የህንድ ቡድን የፊፋን ህግ ለማክበር አልፈለጉም - ያለ ጫማ ነው የምንጫወተው በማለት። ጫማ ካደረግን፣ ጥቃቅን ነፍሳትን ረጋግጠን ልንገድል እንችላለን ብለው የሰጉት የህንድ ተጫዋቾች፤ ሃጥያት ውስጥ መግባት አንፈልግም ብለው ከአለም ዋንጫ ቀርተዋል። እንዲህ፣ ተረት የሚመስል ኋላቀር ባህል ምን ይባላል?
ቻይናን ጉድ ያደረጋት ግን፣ ጥንታዊ ባህል አይደለም። ለነገሩማ፣ እግር ኳስ የሚመስል ጨዋታ የተጀመረው በጥንታዊ ቻይና እንደሆነ ይነገር የለ! ቻይናዊያን ከእግር ኳስ ጋር የተራራቁት በኮሙኒዝም ምክንያት ነው። የድሮዎች የአገራችን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ እነ ደርግና እነ ኢህአፓ ጭምር በአድናቆት የዘመሩላቸው የቻይና መሪ ማኦ ዜዱንግ፣ አገሬውን ሁሉ ሌት ተቀን ፋታ በማይሰጥ ስብሰባ፣ ግምገማና የስራ ዘመቻ ወጥረው ነበር የያዙት። ኳስ ለመጫወት ጊዜ አልነበረም።
ስብሰባውና የስራ ዘመቻውም ጠብ የሚል ነገር አልተገኘበትም - 20 ሚሊዮን ቻይናዊያን በረሃብ ያለቁት በማኦ ዘመን ነው። ከማኦ በኋላ፣ በዴንግ ዚያዎፒንግ ዘመን በመንግስት ተተብትቦ የቆየው ኢኮኖሚ ለግል ኢንቨስትመንት ሲከፈት፣ ከዚያም ሲስፋፋ አገሪቱ በፍጥነት ወደ እድገት መጓዝ ጀምራለች። በመንግስት የተተበተበው ፖለቲካ ግን ብዙም አልተቀየረም። ያለ መንግስት ፈቃድ ከ10 በላይ ሰዎች በአንድ ቦታ ቢሰባሰቡ ይታሰራሉ። ክልክል ነው።
የሰፈር ወጣቶች እግር ኳስ ለመጫወት በየቀኑ ቀበሌና ወረዳ ሊቀመንበር ጋ እየሄዱ የፈቃድ ማመልከቻ ሲያስገቡ ይታያችሁ። “ስፖርት ለአገር ልማትና ለጤናማ ህብረተሰብ ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይታወቃል። እኛ ስማችን ከዚህ በታች የተዘረዘረ የሰፈር ወጣቶች፣ ለአገርና ለህብረተሰብ ልማት በማሰብ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እግር ኳስ ለመጫወት አስበናል። ፅ/ቤቱ ፈቃድ እንዲሰጠን እየጠየቅን፣ ለሚደረግልን ትብብር አብዮታዊ ምስጋና እናቀርባለን...”  
“አብዮት ወይም ሞት!” በሚል መፈክር የታጀበ ማመልከቻ እየፃፉ እግር ኳስ ለመጫወት የሚጓጓ ብዙ ወጣት አይኖርም። በኮሙኒዝም የተሽመደመደው  የቻይና እግር ኳስ፤ እስከዛሬ ገና ቆሞ የመራመድ ብርታት አላገኘም። ደግነቱ፣ እንደ ታሊባን ወይም እንደ አልሸባብ የእግር ኳስ ጨዋታ በቲቪ መመልከት አልተከለከለም። ብዙ ቻይናዊያን እግር ኳስ ባይጫወቱም፣ መመልከት ግን ይወዳሉ። 300 ሚሊዮን ቻይናዊያን በ2010 የአለም ዋንጫ ውድድሮችን በቲቪ ተከታትለዋል።
ህንድና ቻይና ከእግር ኳስ አለም የራቁት በጥንታዊ ኋላቀር ባህልና አኮራምቶ በሚተበትብ የኮሙኒዝም አፈና ሳቢያ ከሆነ፤ አሜሪካ ከእግር ኳስ ጋር ያልተወዳጀችው በምን ምክንያት ይሆን? በሌሎች ተወዳጅ ስፖርቶች ምክንያት ነው። በአሜሪካ ስቴዲየም የሚገባ ብዙ ተመልካች የሚሰበሰበው በሞላላ ኳስ የሚካሄደውን ጨዋታ ለማየት ነው። በአማካይ በእያንዳንዱ ጨዋታ ከ68ሺ በላይ ተመልካች ስቴዲየም ይገባል - ያንን ነው ፉትቦል የሚሉት። እግር ኳስን፣ ሶከር እያሉ ነው የሚጠሩት። ከዚያ በኋላ ደግሞ ቤዝ ቦል አለ። የቤዝ ቦል ጨዋታ ለመመልከት በአማካይ ከ30ሺ በላይ ሰው ስቴዲየም ይገባል። እግር ኳስ ለማየት የሚሰበሰበው ተመልካች፣ ከቅርጫት ኳስ ተመልካቾች ቁጥር ብዙም አይራራቅም - በአማካይ 18ሺ ገደማ ሰው።
በአጭሩ፤ አውሮፓን፣ ደቡብ አሜሪካንና አፍሪካን ያጥለቀለቀው የእግር ኳስ ዝና፣ በአሜሪካ ገና አልተስፋፋም። እንዲያም ሆኖ፣ ከሌሎቹ ትልልቅ አገራት (ከህንድ እና ከቻይና )ጋር ሲነፃፀር፣ የአሜሪካ ሳይሻል አይቀርም። የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ በአለም ዋንጫ ላይ ሲሳተፍ እያየን አይደል?
ሶስቱ ትልልቅ አገራት፤ (ህንድ፣ ቻይና እና ኢንዶኔዢያ) ግን፤ ለአለም ዋንጫ ባይተዋር ናቸው። በእርግጥ፤ ቻይና አንዴ በአለም ዋንጫ ተሳትፋለች። ግን፤ እንደተሳተፈች አይቆጠርም። የቻይና ቡድን አንድም ጊዜ አላሸነፈም። ጨርሶ፣ አንድም ጎል ሳያስገባ ነው በመጀመሪያው ዙር ከውድድሩ የተሰናበተው። እግር ኳስ ለማየት ወደ ስቴዲየም ጎራ ማለት፤ በህንድ፣ በኢንዶኔዢያና በቻይና ገና አልተለመደም።
በዚህ በዚህ ጀርመንን የሚስተካከል የለም። በእያንዳንዱ የቡንደስ ሊጋ ጨዋታ በአማካይ 42ሺ ተመልካች ስቴዲየም ይገባል። በእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ ደግሞ፣ 36ሺ ሰዎች ስቴዲየም ይታደማሉ። በቅርቡ የተጠናቀቀውን የፕሪሚየር ሊግ ለማየት በድምሩ 14 ሚ. ገደማ ቲኬቶች ተሽጠዋል።

Read 3273 times Last modified on Saturday, 07 June 2014 14:57