Print this page
Saturday, 07 June 2014 13:41

አማዞን ሰው አልባ ሚኒ ሄሊኮፕተሮቹ ሊያሰማራ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
  • ዋና ቢዝነስ፡ መጽሐፍ፣ ሲዲ፣ ዲቪዲ፣ የኤሌክትሮኒስ እቃ፣ ልብስ፣ ምግብ በኢንተርኔት መሸጥና በአካል ማድረስ
  • በአመት የ74 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ይሸጣል
  • አምና ሩብ ቢሊዮን ዶላር አትርፏል
  • የኩባንያው ሃብት 40 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል
  • 120ሺ ገደማ ሰራተኞች አሉት

በኢንተርኔት ጎብኚዎች ብዛት በአለም 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል
ከሳምንት በኋላ፣ አዲስ ታሪክ ይሰራል የተባለለትና “3ዲ” ስክሪን ያለው ሞባይል ስልክ ለገበያ እንደሚያቀርብ ያበሰረው አማዞን ዶት ኮም፤ እቃ የሚያደርሱ ሰው አልባ በራሪዎችን ሰርቶ እንዳጠናቀቀ ገለጿል።
አመት ሙሉ ሲወራለት የነበረው የአማዞን አዲስ ሞባይል ስልክ በወሬ አልቀረም።  አይፎን እና ጋላክሲ ከመሳሰሉ ስማርትፎኖች በምን እንደሚለይ በዝርዝር ባይገለፅም፤ በስክሪን ቴክኖሎጂው የላቀ እንደሚሆን ተገምቷል። ምስሎችን በአካል የማየት ያህል አንዳች የ3ዲ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዳዋለ ኩባንያው ጠቁሟል። ዋጋው ገና አልታወቀም።
የተለያዩ ሸቀጦችን በኢንተርኔት በመሸጥና ሸቀጦቹን ለደንበኞች በአካል በማድረስ የሚታወቀው አማዞን፤ አዲሱን የሞባይል ስልክ ለሚገዙ ደንበኞች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠቱ አይቀርም።
የቀረ ነገር ቢኖር፣ እቃዎችን ለደንበኞች የሚያደርስ ሰው አልባ በራሪ (ድሮን) ብቻ ነው። አማዞን እንደሚለው፣ ያለ አብራሪ እቃ ለማጓጓዝ የተሰሩት ሚኒ ሄሊኮፕተሮች በተግባር ተሞክረዋል። አደጋ የማድረስ ወይም የመጋጨት ስጋት የለባቸውም። በራሪዎቹ ሚኒ ሄሊኮፕተሮች ለአገልግሎት ዝግጁ ናቸው። እና ምንድነው የሚጠብቁት? የአውሮፕላን በረራዎችን ለመቆጣጠር በመንግስት የወጡ ህጎች እስኪሻሻሉ ድረስ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችንም ሆነ ሄሊኮፕተሮችን በብዛት መጠቀም አይቻልም። ህጎች እስኪሻሻሉ እየጠበቅሁ ነው የሚለው አማዞን፤ “ፕራይም ኤር” የተሰኙት ሚኒ ሄሊኮፕተሮች በአመት ውስጥ ለደንበኞች እቃ የማመላለስ አገልግሎት ይጀምራሉ የሚል ተስፋ እንዳለው ገልጿል።
ታዲያ የእቃው ክብደት ከ2 ኪሎ ግራም መብለጥ የለበትም። ቦታውም  ከ17 ኪ. ሜትር በላይ መራቅ አይኖርበትም። እናም በኢንተርኔት አማካኝነት ያዘዙት እቃ በግማሽ ሰዓት ውስጥ ከቤትዎ ደጃፍ ከች ይላል - በሰው አልባ ሚኒ ሄሊኮፕተር።

Read 3300 times
Administrator

Latest from Administrator