Saturday, 07 June 2014 14:25

ሀገር ቋንቋ፣ ሀገር የሰው ምስጢር ናት?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

የሀገር ነገር - የራስ ነገር!

የዓለም ዋንጫን ተከትሎ - የጋዜጠኛ አበበ ግደይን የብራዚላዊያን እግር ኳስ አፍቃሪነት ባደመጥኩ ጊዜ፣ ዋንጫ የተነጠቀችውን ሀገራቸውን አደባባይ ጭርታ ከማዳመጥ ይልቅ የሞትን ጨለማ በቴስታ መግጨት መርጠው፣ ከስቴዲየም ጫፍ እየተፈጠፈጡ መሞታቸው ሲያስደንቀኝ ከርሞ ነበር፡፡ ግን ደሞ እዚህች አየር የተሞላች ኳስ የሚሏት ቅሪላ ውስጥ የምትንከባለል ሀገር የምትባል ፍቅር፣ ባንዲራ የምትባል ክብር እንዳለች አሰብኩ፡፡ ኳስ ብቻዋን በቁጭት ቆንጥጣ ለሞት አታጐርስም። ሀገር የምትባለው የማንነት መልክ ናት ነፍስ የምታሰጠው፡፡ ሀገር ጦስህን ልውጣልህ አትልም፣ ጦሴን ውሰድልኝ እንጂ…!ለዚህ ነው የብራዚል ኳስ ወዳጆች የአንቺን እምባ የተሞላ ዓይን፣ የፈረሠ ልብ ከምናይ የኛን የፈረሠ ሕይወት ትቢያሽ አድርጊው ብለው የለፉላት!
ሀገር በየሀገሩ አፍቃሪ አላት፡፡ በሕይወት ያለች ሀገር ሕይወት እንዲኖራት እልፍ ሕይወት ተገብሮላታል፡፡ ሰንደቅዋ እንዲቆም፣ የሀገር ንፋስ በከንፈሩ እየሳመው እንዲያልፍ በርካታ ጐበዞች ከሞት ጋር ተሳስመዋል፡፡ ለሀገር ሕይወት ብዙዎች የሞትን ጽዋ ጨልጠዋል፡፡
ሀገር ምትሀትዋ ምንድነው? ብዬ የምጠይቀው እኔ ብቻ ነኝ - አልልም፡፡ ሁሉም ልብ ውስጥ ሀገር አለች፡፡ ሀገር ውስጡ የሌለች ሰው ልብ - ሬሣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሀገር ከሌለች ሰው በምን ተስፋ ይኖራል? በፈጣሪ ብንል እንኳ ፈጣሪ አምላክ እንጂ ሀገር አይደለም፡፡ ስለዚህም ለሰው ሀገርን ሰጥቶታል። ሀገር ሰንሰለት አላት፤ ታሥራለች። ፍቅሯ እንደ ልጃገረድ ፍቅር፣ ከከንፈር፣ ከአይን፣ ከገላ፣ ከጠባይ የሚወለድ አይደለም፡፡ ሳይታወቅ ከልጅነት ጀምሮ ቀስ እያለ ልብ ውስጥ የሚገነባ የልዩ ልዩ ገጠመኞች ጡብ ነው፡፡
እንዲያውም ሀገር ጠንካራ ልብ ውስጥ የምታድገው በልጅነት ይመስለኛል፡፡ ልጅነት ሥንል በንፁህ ልብ ፣ በቤት ውስጥ፣ በጓደኝነት፣ በበዓላት አከባበር፣ በትምህርት ቤት ውስጥ፣ በሠፈር ጨዋታ፣ ቀለበት ታጠልቃለች፡፡ ብዙ ሰዎች ከልጅነታቸው ጋር በፍቅር ይወድቃሉ፡፡ ለምሣሌ እኛ ሀገር በቡሄ፣ እንቁጣጣሽ፣ መስቀል ደመራ፣ ማለትም በሆያሆዬ በችቦ ልኮሳ፣ በቡሄ ጢቢኛ ወዘተ… ልባችን ውስጥ የሀገራችን መልክ ይቀመጣል፡፡ ስናድግ ታዲያ እነዚህ ሁሉ የሀገር መልክ ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡ ዓመድ ሊለብሱ ሲሉ ትዝታ እየመጣ አመዱን ሲገፍፈው፣ የፍቅር ፍሙ ትርክስ ይልና ይሞቀናል፡፡
ይሄኔ ነው ታዲያ ሀገርህ ተነካች ሲባል ውስጣችን የተከመሩትን የፍቅር ጉንጉኖች የበጣጠሱብን፣ ሕልውናችንን ያፈረሱብን ሲመስለን እንዴት ተብሎ የምንለው! የሀገራችን ወካይ የሆነው ትዕምርት ሰንደቃችን ሲነካ የምንቆጣው፡፡ ምናልባትም ለዚያ ነው የሀገር ልጅ ካገር ልጅ ጋር የቋጠረውን ቂምና የሚያናድደውን ቁጣ ወዲያ ብሎ ለአንድ ሀገር አንድ አፈር ላይ የሚወድቀው፡፡ ለዚህ ምስክር የሚሆነን ሌላ እማኝ አንጠራም፤ የዐድዋ ድልና ሌሎችም የጦር ግንባሮች እማኝ ይሆኑናል፡፡
ታዲያ ሀገር አንዳንዴ ታናድዳለች፡፡ መሪዎችዋ አልመች ሲሉ፣ ወይም ጥበብ ጐድሏቸው፣ የሠላምዋን ምድር በኑሮ ውጣ ውረድ ጦር ሜዳ ሲያደርጓት “ይቺ ሀገር” ታሠኛለች፡፡ ይሁን እንጂ ሀገር ከልብ አሽቀንጥረው የሚጥሏት ምናምንቴ አይደለችም። ሀገር ትርጉሟ ብዙ ነው፡፡ እስቲ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ለሀገር ምን ትርጉም ይሰጣታል? መቼም ገጣሚ ልቡ ለጥበብ ብቻ ሣይሆን ለፍቅር ቅርብ ነውና ፍቅርና ጥላቻውን፣ ጥልቀቱንና ቅርበቱን፣ እንዴት እንደተረከው እንይ ፡-
ሀገር ማለት ለገጣሚው በድሉ ዋቅጅራም ቀላል ትርጉም የሰጠው አይመስልም፡፡ እንዲህ ይላል፡- ገፀ ባህሪው ለልጁ በዜማ ሲተርክ፡-
ሀገር ማለት ልጄ፣ ሀገር ማለት፣
እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ፣
የተወለድሽበት አፈር፤
እትብትሽ የተቀበረበት፣ ቀድመሽ የተነፈስሽው
አየር
ብቻ እንዳይመስልሽ፡፡
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ፤
በድሉ - አፈሩ፣ የአፈሩ ጠረን፣ ጧት ከቤትሽ ስትወጪ አዘውትረሽ የምታይው ተራራ፣ ያይንሽ ጓዳ የልብሽ ሥዕል፣ ዕትብትሽ የተቀበረበት የሠፈርሽ አፈር፣ የሠፈርሽን ቆርቆሮ እያንኳኳ የሚያልፈው ንፋስ ወይም ከዛፎች ሽው እያለ የምትተነፍሺው አየር አይደለም… ይላል፡፡ ግን ደሞ መልሱን በቀላሉ አልመለሰውም፤ በቀላሉ ቃላት ተሸክመው ልብሽ የሚያደርሱት ቀላል ኪሎ ያለው ነገር አይደለም ይላል! ረቂቅ ነው፤ ውስብስብ ነው፡፡ ጥልቅ ምስጢር እንደማለት፤
እና ደሞ ሊመልስ ይዳዳዋል፣ እንዲህ
ሀገር ማለት ልጄ፣
ሀገር ማለት ምስል ነው፣ በህሊና የምታኖሪው፤
ከማማ ማህፀን ከወጣሽበት ቀን ጀምሮ፤
በጠባሽው ጡት፣ ወይም ጡጦ
በዳህሽበት ደጃፍ፣ በወደቅሽበት ፈፋ፡፡
በተማርሽበት ትምህርት ቤት፣
በተሻገርሽው ዥረት
በተሳልሽበት ታቦት፣ ወይ በተማፀንሽው ከራማ፤
በእውቀትሽና በሕይወትሽ፣
ለእውነትሽና በሕይወትሽ፣
ለእውነትሽና በስሜትሽ፣
የምትቀበይው ምስል ነው፤ በሕሊናሽ
የምታኖሪው፤
ስትወጅ ሰንደቅ ታደርጊው፡፡
ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው፡፡
ሀገር ማለት ረቂቅና ተጨባጭ ሥዕሎች፣ የነፍስ ዜማዎች፣ የአእምሮ ሀውልቶች ድምር ናት - የሚል ይመስላል፡፡ ግን ደግሞ ስለወደድሽ ከፍ አድርገሽ፣ ቢያስጠላሽ ወግጂልኝ - የማትያት -ቁርኝት አላት - ይላል፡፡ እውቀት፣ ስሜት፣ ቦታ፣ እምነትና ሌሎችም የተደመሩ ነገሮች ውጤት ናት፡፡
ግን ደግሞ ይላል - ቋንቋ ብትሆንም ባንደበት የሚናገሯት፣ በጆሮ የሚያደምጧት ምትሀት ናት። አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ ቅማንትኛ፣ ጉራጊኛ፣ ትግርኛ ብለው የማይፈርጇት፣ ግን ቋንቋ ናት ሀገር!
አንዱ የአንዱን ቋንቋ እንኳ ባያደምጥ፣ ሀዘንና ደስታውን የሚጋራበት የጋራ ምስጢር አለው ይላል - ገጣሚ በድሉ፡፡
የኔ ልጅ
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞውና ሲዳማው፣
ጉራግኛሽን ባይሰማ፣
ያልገባሽው እንዳይመስልሽ፣ ሀዘን ደስታሽን
ያልተጋራ፡፡
የየልቦናችንን ሀቅ፣ ፍንትው አድርጐ እያሳየ፡፡
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ፡፡
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስተዋት፡፡
ሲከፋሽ ትሸሸጊበት፣ ሲደላሽ ትኳኳዪበት፡፡  
ሀገር ቋንቋ ነው፣ ሁለንተናን ያሳያል ይልና “ሲከፋሽ ቀን ታሳልፊበታለሽ፡፡ ሲመችሽ ደግሞ ትደምቂበታለሽ” በማለት ልጁን ስለሀገር ሊያሳያት ይሞክራል፡፡ ቀጥሎም ለዚህች ሀር ለምትባል ምትሀት - አያት ቅድመ አያትዋ- “አትንኩብኝ” ብለው፣ ጦር ሰብቀው፣ የሀገር ልጆች ሁሉ አጥንታቸውን ማግረው፣ እንዳትደፈር አጥር እንደሆኑዋት የኋሊት ያሳያታል፡፡ ቀጥሎም እንዲህ ይላል፡-
ሀገር ይሉት መግባቢያ ሰንደቅ ይሉት መለያ፣
ሲያቆይልሽ
በጉራጊኛ ማትገልጪው፣ በጎጥ የማትገድቢው
ስንት ታሪክ አለ መሰለሽ!
ባንቺ ብሔር ቋንቋ ብቻ የማትተነትኚው፣ እዚህ ድረስ ነው ብለሽ ወሰን የማታበጂለት እልፍ ታሪክ፣ ብዙ ድርሳን አለ… በማለት የአድማሱን ርቀት፣ የምስጢሩን ጥልቀት በቃላት ይተርክላታል፡፡
የዶክተር በድሉን “ሀገር ማለት የኔ ልጅ” ግጥም ጥቂት ስንኞች ዘልላችሁ ስትሄዱ ደግሞ “መሬት ሀገር አይደለም” የሚል ሀሳብ ታያላችሁ፡፡
መሬትማ የኔ ልጅ፤
በእምነትና እውቀትሽ ከልለሽ ካላበጀሽው
ለእድገትሽ ውጥን ካልሆነ፣ ለተስፋሽ ካልተመገብሽው
መሬትማ ባዳ ነው ላለማው የሚለማ
ለተስማማው የሚስማማ፡፡
ዥረቱም ግድ የለውም፣ ቦይ ለማሰለት ይፈሳል
ተራራውም ደንቆሮ ነው፣ ለቦረቦረው ይበሳል፡፡
ስትቸገሪ ታድጎ፣ ስትታመሚ አስታሞ፣ ስትሞቺ
አፈር የሚያለብስሽ
ወገን ነው ልጄ ሀገርሽ፡፡
ሀገር ቋንቋ ቢሆንም የቋንቋው ምንጭ ደግሞ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ሀገር ነው፡፡ ወገን ነው ሀገር።
ከላይ መነሻዬ ላይ እንዳልኩት ለሀገር ጦስ የሆኑ ጎበዞች ለአፈሩ ብቻ አይደለም የሞቱት፡፡ አፈሩን ሀገር ያደረገውን ሕዝብ ክብር ለመጠበቅና ነፃነቱን ለማስጨበጥ ነው፡፡ ሀገር የቋንቋ ልዩነት አይሽረውም፤ ጎሣ አይበትነውም! የኛ ሀገር ኢትዮጵያ ደግሞ ብዙ ጊዜ ሕልውናዋ ተፈትኗል፤ ጠላቶችዋ ሊያፈርሷት መጥተዋል፡፡ ግን ሕዝቧ-ስለ ሕዝቧ ሞቷል፡፡ እናም ታሪኳና ነፃነቷ ሕያው ሆኖ ዛሬን ደርሷል፡፡ ብዙዎች እንደሚናገሩት የሀገር ጉዳይ የሚያንገበግበው ሰው ሀገር ሲሄዱ ነው፤ የባዕድ መሬት ሲረግጡ “ሀገርህ የት ነው? ከወዴት ነህ ሲባል?” ያኔ - ሰው ያለ ሀገሩ ክብር እንደሌለው፤ ሥር እንዳጣ ይገባዋል፡፡
የገጣሚና ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ “ሀገሬ” የምትሰኝ ግጥም - ይህንን ሀቅ ፍንትው አድርጋ ታሳያለች፡፡ ለምሳሌ የራስ ሀገር ቆሎ፣ ከባዕድ ሀገር ጮማ እንደሚበልጥም በናፍቆት ጠቅልሎ ስንኝ ቋጥሯል፡፡
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎው ክትፎ ሥጋ፣
ድርቆሽ ፍትፍት ነው፣ ቃሪያው ሙክት ሠንጋ፡፡  
ጠጅ ነው ወለላ
ከኮኛክ ይነጥቃል የመንደሩ ጠላ፡፡
እህሉ ጣዕም አለው እንጀራው ያጠግባል
    በዓሉ ይደምቃል
    ሙዚቃው ያረካል፣
ጭፈራው ዘፈኑ ችግርን ያስረሳል፡፡
እዚያ ዘመድ አለ፡፡
ሁሉም የናት ልጅ ነው፣
ሁሉም ያባት ልጅ ነው
ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር
ባላጋራም ቸር ነው “ያገር ልጅ” ሲቸገር፡፡
ሀገር እንዲህ ፀበኛን፣ ዕድርተኛን፣ ምግብና መጠጥን ሁሉን ይጠቀልላል፡፡ ግን የዚህ ሁሉ ባለቤት ሰው ራሱ ነው ያገር ልጅ፡፡ ገብሬም-ሁሉም የናት ልጅ ነው፣ ሁሉም ያባት ልጅ ነው ያለው ለዚህ ነው፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ አይባልም፡- ወገን ነው፣ አካል ነው፡፡ የሀገር ምስጢርም የሀገር ምትሀትም ይህ ነው፡፡ የተበታተነ ልብ፣ የጐሪጥ የሚተያይ አይን ሳይሆን ለአንድ ራዕይ፣ በአንድ መሥመር የሚጓዝ፣ መንገደኛ ነው ወደ ማለት ያስጠጋናል፡፡
በተለይ በተለይ የፖለቲካ ልዩነት፣ በዘር ሊመነዘር አይገባም፡… እንደዚያ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያን ሶማሌ የሀገር ሽማግሌዎች “ከሊ” በተባለው ስፍራ እንግሊዞች ውሳኔ ሕዝብ እንዲያደርጉ በጠየቋቸው ጊዜ ጥቅማቸውን መርጠው ኢትዮጵያዊነታቸውን ይሸጡ ነበር። እነዚያ አባቶች ግን ያንን አላደረጉም!” ምሥጋና ይግባቸውና! ቀድሞም ኢትዮጵያዊ ነበርን፣ አሁንም ኢትዮጵያዊ-ወደፊትም እንደዚሁ ነበር ያሉት፡፡ ሀገር አትገፋም፣ ሀገር አትጣልም!...
እኔ እንዲያውም ሀገር ከኃይሌ እና ደራርቱ እግር ጋር የምታስሮጠን፣ ከኳስ ጋር የምታንከባልለን፣ ባንዲራ ስናይ አንጀታችንን እንደቅቤ የምትንጥ ብቻ አይደለችም፤ በደማችን ውስጥ የምትፈስስ ወንዝ ናት እላለሁ፡፡
ልብ በሉ ከሰውነታችን ጠቅላላ ክፍል ሦስት አራተኛው ውሃ ነው፡፡ ውሃ ደግሞ ከደም ጋር ይኖራል፡፡ ቅዱስ መፅሐፍ” ደም ውስጥ ሕይወት አለ ይላል፡፡ እኛ ውስጥ ያለው ደም ደግሞ ከኢትዮጵያ ከርሠ ምድርና ገፀ-ምድር የጠጣነው ነው፡፡ እና ሀገር ማለት እኛው፣ እኛ ማለት ሀገር፣ መሆንዋ አይደል! መዝጊያውን ለዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ልተውለት፡-
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ፡፡ የሀገር ነገር የራስ
ነገር ነው!

Read 3203 times