Saturday, 07 June 2014 14:01

እውነተኛውን የሠራዊት ታሪክ ማን ይመዝግበው?

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(0 votes)

ርዕስ…የወገን ጦር ትዝታዬ
የገፅ ብዛት - 497
የሽፋን ዋጋ - አልተገለፀም
የህትመት ዘመን - 2001 ዓ.ም
ጸሐፊ - ሻለቃ ማሞ ለማ
አሳታሚ - ሻማ ቡክስ፣
ህትመት - የተባበሩት አታሚዎች
ቅድመ ኩሉ
የዓለም አገሮች፤ በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ገድሎ ሥልጣን ይይዝና “ደረስሁላችሁ! ከእንግዲህ ጭቆናም ሆነ ድህነት የለም!” ብሎ ይለፍፋል፡፡ ግን አመት ሳይቆይ የድህነቱና የጭቆናው ምንጭ ራሱ ሆኖት ያርፋል፡፡
በህብረተሰቡ መሃል ቅሬታና ስሞታ ሲበዛ፣ በሰበቡ ሌላ አዲስ ጉልበት ያለው አዲስ ጨቋኝ ይነሳል፡፡ በነባሩና በአዲሱ ጨቋኝ መሃል በሚደረግ ፍትጊያም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ህይወት እንደ ቅጠል ይረግፋል፤ በጦርነቱም ድህነት ይበልጥ ይስፋፋል፡፡
በአጠቃላይ “የአፍሪካ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው” ስንል የድህነት ታሪክ ዋና ምንጩ ጦርነትና የእርስበርስ ፍጅት ነው ማለታችን ነው፡፡ አፍሪካዊት እና የአፍሪካ ማዕከል የሆነችው አገራችንም እውነተኛ ታሪኳ የሥልጣኔ፣ የምጣኔ ሃብትና የኪነ ጥበብ ዕድገት ታሪክ አይደለም፡፡ ታሪኳ ጦርነትና ዕልቂት፤ ስደትና ጉስቁልና ነው፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ ተዋናዩ ህዝቡ ነው፤ ብልጣብልጥ ፖለቲከኞች ደግሞ መሪ ተዋንያን። ህዝቡን በተለያየ የፖለቲካ መርዝ ይመርዙትና እርስበርሱ እያጫረሱ ሥልጣናቸውን ማቆየት ይፈልጋሉ፤ ግን አይሆንላቸውም፡፡ አገሪቱንም ህዝቡንም ለከፍተኛ ድህነትና ውርደት ዳርገው በመጨረሻ ራሳቸውም በቅሌት ይሰናበታሉ፡፡
እንዲህ አይነቶቹ ገልቱ ፖለቲከኞች ወገናቸውን ሲጨፈጭፉና ሥልጣን ሲይዙ “ጀግና” የሚል ታርጋ ይለጠፍላቸውና የታሪኩ ሁሉ ቁንጮ ተደርገው ይወደሳሉ፤ ከስልጣናቸው ሲወገዱ ደግሞ ከውድቀታቸው ደቂቃ ጀምሮ የእርግማን ናዳ ይወርድባቸዋል፡፡ ደጃዝማች ተፈሪ፤ ያሳደጓቸውን የአጤ ምኒልክን ልጆች ጨፍጭፈው ሥልጣን ላይ ፊጥ ሲሉ “ፀሐይ ንጉሥ” የሚል የሙገሳ ቃል ከካህናትና አሽቃባጭ ፖለቲከኞች ተቸራቸው፡፡
በሥልጣን መባለግ አብዝተው ዕድሜያቸው ገርጅፎ በመጃጀታቸው እንደ ድሮው ሰጥ ለጥ አድርገው መግዛት ሲሳናቸው ደርግ በቀላሉ ገፍትሮ ጣላቸው፡፡
እሱም በተራው የላቀ የህዝብ ድጋፍ አገኘ፡፡ ንጉሱ በተጓዙበት የመግደል (የሱ በጅምላ ቢሆንም) እርምጃ ሲጀምርም የሀገሪቱን መሪ ኮሎኔል መንግሥቱን “እረፍ፤ ሰውን ያለ ፍርድ መግደል ተገቢ አይደለም” ከማለት ይልቅ በዙሪያቸው የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት “ቆራጡ መሪያችን” እያሉ የግድያ ተግባራቸውን አደነቁላቸው ብቻ ሳይሆን አፀደቁላቸው፡፡ ጊዜያቸው አልቆ ከሥልጣን ሲገለሉ ደግሞ “ከቆራጡ መሪያችን ጋር ወደፊት!” እያለ ግራ እጁ እስከሚዝል መፈክር ያሰማ የነበረው ሁሉ በአንዴ ቆዳውን ገልብጦ “ጭራቁ መንግሥቱ…” ማለት ጀመረ፤ በአንጻሩም ኢህአዴግ ሰራሹንና ህወሃት መራሹን መንግሥት ያወድስ ያዘ፡፡
በሠራዊት ታሪክ ውስጥም የተፈጸመውና የሚፈጸመው ይኸው ነው፡፡ ሠራዊት የአንድ አገርና ህዝብ ህይወት ነው፤ የሰለጠነ፣ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በአግባቡ የተዋወቀ፣ ዘመናዊ የውትድርና ትጥቅ የታጠቀና የሃገር ፍቅር ያለው ሠራዊት በእርግጥም ያገር ህይወት ነው፡፡ እሱ ሞቶ እንደ ክርስቶስ በሞቱ ወገኑን ያድናል፤ አገርን ከውድቀትና ከአሳፋሪ ውርደት ይታደጋል፡፡ ግን እየሞተ፣ አካሉ መጥረቢያ እንደበዛበት ግንድ በፈንጅ እየተጐመደና ዘግናኝ የበረሃ ኑሮ እየተማገደ ነው ይህን በዋጋ የማይተመን መሥዋዕትነት የሚከፍለው፡፡
ሠራዊት ለዚህ አይነት አስከፊ አደጋ የሚጋለጠው በሁለት ምክንያቶች ነው፤ አንደኛው የሃገሩን ዳር ድንበር ከወራሪ ለመታደግ ሲሆን ሁለተኛው ግን የሥርዓቱን ቁንጮ ባለሥልጣናት ህልውና ለመጠበቅ ሲባል ነው፡፡ ሁለቱም ኃላፊነቶች ለሞት፣ ለአካል መጉደልና ለመፈናቀል ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡
አገርን ከወራሪ ለመታደግና የባለሥልጣናትን ወንበር ለመጠበቅ በሚደረግ ግብግብ ውስጥ በሚደረግ ፍልሚያ ለውድቀትም ለድልም የሚያበቁ መሪዎች ሚና ወሳኝ ቢሆንም መሪ ያለ አስተማማኝ ሠራዊት ምንም ሊፈይድ አይችልም። ሠራዊቱ ደምቶና ሞቶ ባስገኘው ድል ተሿሚና ተሸላሚ የሚሆኑት ፊትአውራሪዎች እንጂ ሠራዊቱ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ በየፈፋው በጠላት ጥይት እየተመታ የሚቀረው ጀግና ሠራዊት ካለፈ በኋላ አስታዋሽ የለውም፡፡ የሚታወሰው በህይወት ሳለ ፈፋ ለፈፋ እንደ አንበሳ በጠላቱ ላይ ያገሳ፣ እንደ ዝንጀሮ በየገደሉ ሲዘልና ጠላቱን ሲጥል በነበረበት ወቅት እንጂ ዘንበል ካለ በኋላ የለም፤ አለቃውም፣ ጓደኞቹም፣ አገርም፣ ማንም ሊያስታውሰው አይችልም፡፡
የመጽሐፉ ይዘት በአጭሩ
“የወገን ጦር ትዝታዬ” በሚል ርዕስ ሻለቃ ማሞ ለማ የጻፉት መጽሐፍ ከታሪክ ዘውግ የሚመደብ ሆኖ በተለይ ደግሞ በዚያኔው የኤርትራ ክፍለ ሀገር በተለይ አልጌና በረሃ ውስጥ ለአምስት አመታት በተካሄደ ጦርነት “ሀገሬን አላስገነጥልም” ብሎ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ፍዳውን ሲቆጥር ስለነበረ ድንቅ ሠራዊት ውሎ የሚዘግብ ነው፡፡
መጽሐፉ በሳህል አውራጃ የሚገኙት እጅግ አስፈሪ ገደሎች፣ በጊንጥ፣ በእባብ፣ በዘንዶ፣ በረሃብ፣ በውሃ ጥምና በወገን መሰል ሰብቅ ሠራዊቱ እንዴት መከራውን ሲያይ እንደኖረ፣ የመንግሥትም ሆነ የወታደሩ መሪዎች ልፍስፍስ የውሳኔ አሰጣጥ እንዴት ሲያሰቃየውና የሃገር ክብር እንዴት ለውርደት እንደበቃ በቁጭት ጭምር የሚያብራራ ነው። እርግጥ የ1981 ዱን መፈንቅለ መንግሥት፤ እሱን ተከትሎ ስለመጣው አጠቃላይ ውድቀትም (እስከ ኢህአዴግ አዲስ አበባ መግባት) ያሳያል፡፡ ሆኖም በጥንቃቄ የተሠራውና ከሌሎች ለየት የሚያደርገው የሠራዊቱን ተጋድሎ ጥርት ባለ አቀራረብ ማሳየቱ ነው፡፡
መጽሐፉ ከሌሎች የሚለይበት መንገድ፣ ሻለቃ ማሞ ለማ በዘመቻ መምሪያ መኮንንነት፣ በዘመቻ ጥናትና ዕቅድ መኮንንነት በተለያየ ደረጃ አገራቸውን ያገለገሉ በመሆናቸው አንድ ውጊያ የተሳካ ሊሆን የሚችለው ምን ምን ሁኔታዎቹ ሲሟሉ እንደሆነ በተግባርም ሆነ በትምህርት የዳበረ ልምድ ስላላቸው እያንዳንዷን ጥቃቅን ጉዳይ በሚገባ ዘግበዋል፡፡ የጦር ሜዳ ዘገባዎች በተለያዩ ከፍተኛ መኮንኖች ተጽፈው አንብቤያለሁ፤ ግን የተጻፈው ታሪክ የራሳቸውን ልዕለ ኃይልና መለኮታዊ ባህርይ ለማሳየት እንጂ እንደ ሻለቃ ማሞ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አልሰሩትም፡፡
ጄነራል ተሥፋ ኃ/ማርያም እና ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ የጻፏቸው መጻሕፍት ግለ ታሪኮች ስለሆኑ ከዚህ ጣጣ ውስጥ የሚደመሩ አይደሉም፡፡ በተረፈ ግን በሌሎች መኮንኖች የተጻፉ አብዛኞቹ መጻሕፍት አንድም የጠፋ ስማቸውን በፕሮፖጋንዳ ለመካስ፣ አሊያም በጦር ሜዳ ያልታየን ጀግንነት በወረቀት ላይ ለማሳየት የሚመስሉና መላ የጠፋባቸው ናቸው።
ከዚህ አንጻር የሻለቃ ማሞ ለማን መጽሐፍ ሳየው፣ ሻለቃ የጻፉት የራሳቸውን ጀግንነት ሳይሆን የምስኪኑን ሰራዊት እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ የተለየ  ጀብዱ የሰራውን እያንዳንዱን ወታደር በስም እየጠሩ ስራውን ከህዝብ ጋር አስተዋውቀውለታል። ለምሳሌ ያለማንም ትዕዛዝ ብቻውን ከጠላት ምሽግ ድረስ እየሄደ በመትረየስ ሰው እንደ ገብስ ያጭድ የነበረው ወታደር ከበደ ተሬሳ መትረየሱን ሲተኩስ ስሙን ከእነ አባቱ ይጽፍ ነበር “ከከከ..በበበ…ደደደደ..ተርር እንዲል ያደርገዋል፡፡ የከበደ የመትረየስ ምላጭ አሳሳብ ልክ እንደ ሙዚቃ ምት ወኔ ይቀሰቅሳል፤ ሶምሶማ ያስረግጣል፤ ያስፎክራል፤ ያንደረድራል…” ሲሉ አድንቀውታል (ገጽ 166-181)
በሻዕቢያ ለስድስት ወራት ተከብቦ ለነበረው 15ኛ ሻለቃ ለመድረስ በተንቀሳቀሰ በጥስ ዕዝ ውስጥ የተለየ ታሪክ ስለፈጸመው “ሽመልስ” ስለሚባል ጀግና የገለጡበት መንገድም ሌሉላው ድንቅ ማስረጃ ነው (ገጽ 184-191)፡፡ (ከዚህ ሌላ የበጥስ ብርጌድ አዛዥ ስለነበሩት ኮሎኔል ለሜሳ የሰጡት ምስክርነት ሻለቃ ማሞን ሚዛናዊ ያደርጋቸዋል፡፡ ተራ ወታደር በሆነ ይህ ክብር አይገባውም፤ ባለ ማዕረግ ስሆነ ትንሿ ሥራውም ብትሆን ተጋንና መጻፍ አለባት ሳይሉ ሁሉንም የታዘቡትን እንዳለ ዘግበዋል (ገፅ 197-194)
ስለ ሰራዊቱ ዲሲፕሊን አጠባበቅና ይወሰድበት ስለነበረው ጠንካራ ቅጣትም ሻለቃው ሳይደብቁ የገለጡበት መንገድ መልካም ነው፡፡ ለምሳሌ በ1970 ዓ.ም “ማይሸንኩርቲ” በተባለ ቦታ ሁለት ወጣት ወታደሮች ከአንድ መንገደኛ እጅ ሰዓት አስወልቀው በየተራ ሲጠቀሙበት ተደርሶባቸው በጦሩ ፊት በጥይት ተደብድበው መሞታቸውን፣ ሳይፈቀድላቸው ከአንድ አርሶ አደር ቤት ገብተው በቤት ውስጥ ያገኙትን ዶሮ ወጥ በመብላታቸው ሌሎች ሁለት ወጣት ወታደሮች በአደባባይ በሰራዊቱ ፊት በጥይት መደብደባቸውን የሰጡት እማኝነት ልብን ይነካል (ገፅ 225-228)፡፡
ይህ ደግሞ “ሥርዓት አልባ ነበር” እየተባለ በአንዳንድ ወገኖች የሚታማውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ያሳይ ይመስለኛል፡፡ ሰራዊቱ በበነነ በተነነው አዛዦች እንደ ዶሮ የሚያርዱት፤ ሲፈልጉ ጠላት በሌለበት ጭው ያለ በረሃ ልከው በውሃ ጥም የሚፈጁት፣ ሲያሻቸው ደግሞ በብዙ ዙር በተጠመደ የጠላት ፈንጅ ላይ ወጥቶ ምንም አይነት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ የሌለው ተራራ እንዲይዝ ሞት ሲፈርዱበት የነበረ ያ ጀግና ሰራዊት ከሞተ በኋላ እንኳ በአጥንቱ ላይ ቤታቸውን፣ ታሪካቸውን ሊገነቡበት ሲንደፋደፉ ማየት ልብን በእጅጉ ያደማል፡፡
በአጠቃላይ “የወገን ጦር ትዝታዬ” በእርግጥም የጦሩን ድንቅ ብቃት፣ የአዛዦችን (በከፍተኛ አመራር እና በመንግስት ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የነበሩትን ማለት ነው) ዝርክርክነት፣ እጅግ ፈጣንና ተለዋዋጭ ውሳኔ የሚጠይቀውን የውጊያ አመራር በጊዜው አለመስጠት፣ ብቃት የሌለውን ሰው አንስቶ በአዛዥነት መመደብ፣ በሰባራ ሰንጠራው ምክንያት ለክፉ ቀን ይሆኑ የነበሩ ጀግኖችን በጠራራ ፀሐይ በጥይት እየደበደቡ የሰራዊቱን ሞራል መግደል፣ የተራዘመ ጦርነት፣ የስንቅና ትጥቅ በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ፤ በጦርነት ሰዓት ድጋፍ ሰጭ ጦር ሲጠየቁ ፈጥኖ መልስ አለመስጠት፣ ወዘተ ያንን የመሰለ ታላቅ ሰራዊት ቅስሙ እንዲሰበር መደረጉን መጽሐፉ በቁጭት ጭምር ገልጿል፡፡ በአልጌና ግንባር የነበረው ሰራዊት ታሪክ እንደዚህ ተጽፏል፤ የሌላው ግንባርስ?
የእኔ ጥያቄ የሚነሳውም በዚህ ምክንያት ነው፤ በየእሳቱ ሲማግዱት የኖሩትን ትልቅ ሰራዊት ቢቻል በአግባቡ መርተው ለውጤት ባበቁት ነበር፤ ካልሆነስ ለምን አሁን ድረስ የእነሱ ሽንፈትና ወኔ ቢስነት መሸፈኛ ለማድረግ በየ “መጽሐፎቻቸው” ይሞክራሉ? የተፈታ ቦንብ በራኬት እየቀለበ ከጠላቱ ምሽግ ላይ መልሶ ሲጥል የነበረና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተአምር የሰራ የዚያን ሰራዊት ታሪክስ ማን ይጻፍለት?

Read 2267 times