Saturday, 07 June 2014 13:52

“ወደ ፊት ትልቅ የመዝናኛ ማዕከል ለመገንባት አስበናል”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አቶ ደረጀ ሺበሺ የወረኩማ ባርና ሬስቶራንት ዳይሬክተር

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ጣፎ ከተማ እንደከተማ ራሷን ችላ መተዳደር የጀመረችው ከ1999 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ በዚህች ከተማ ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ - ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ቀደም ሲል በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰማርተው የነበረው አበባየሁ ከበደ የህንፃ ስራ ተቋራጭ አንዱ ነው፡፡ ባለሀብቶቹ አካባቢውን በማጥናትና ምቹነቱን በማረጋገጥ በሆቴል ኢንደስትሪው የተሰማሩ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት የተመረቀውን “ወረ - ኩማ” ባርና ሬስቶራንት ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ “ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን የተደረገው ከፍተኛ ጥረት፣ እንደ ወረ ኩማ - ያሉ ለከተማ ጌጥ የሆኑ ሬስቶራንቶችን ለማየት አስችሎናል” ብለዋል የከተማዋ ኃላፊዎች፡፡ በከተማዋ እንደተግዳሮት የሚነሱት የውሃና የመብራት መቆራረጥ ሲሆን ውሃውን በተመለከተ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ተደርጐ ከተማዋ በተወሰነ መልኩ ችግሯን እንደቀረፈች የጠቆሙት ኃላፊዎቹ፤ በመብራት በኩል ያለው ችግርም እንዲሁ በቅርቡ እልባት እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡
የዛሬ ሁለት ሳምንት በወረ - ኩማ ባርና ሬስቶራንት የምረቃ ስነ - ሥርዓት ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከባለቤቱና ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ከአቶ ደረጀ ሺበሺ ወ/ማርያም ጋር በአዲሱ የባርና ሬስቶራንት ቢዝነስ ዙሪያ፣ ስለ ኮንስትራክሽን ዘርፉ፣ ስለ ከተማዋና የንግድ እንቅስቃሴው እንዲሁም ስለወደፊት ህልምና ራዕያቸው አነጋግራቸዋለች። እነሆ፡-

እስቲ እንዴት ነው ወደ ቢዝነስ ሙያ የገባኸው?
ቢዝነስ የጀመርነው ከቤተሰብ ጋር ነው፡፡ የቤተሰብ የጋራ ቢዝነስ ነው ያለን፡፡ ኤሌክትሮኒክስ እያስመጣን እናከፋፍላለን፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍም ተሰማርተናል፡፡ አበባየሁ ከበደ የህንፃ ሥራ ተቋራጭ የተባለ ድርጅት አለን፡፡ ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥ ሆቴል አለን - “ኦአሲስ” የሚባል ቃሉ እንግሊዝኛ ሲሆን የ “በረሃ ገነት” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ራሷን ችላ ከተቋቋመች ገና ሶስተኛ አመቷ ነው፡፡ ሆቴላችሁ መቼ ነው የተከፈተው?
ነፃነታቸውን ከማግኘታቸው ከአንድ አመት በፊት ነው ተከፍቶ ስራ የጀመረው፡፡
ዛሬ እዚህ ጣፎ ከተማ የተገናኘነው “ወረ ኩማ” የተሰኘው ባርና ሬስቶራንታችሁን ምርቃት ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ ጣፎ ላይ በዚህ ዘርፍ እንድትሰማሩ ያነሳሳችሁ ምንድን ነው?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በኮንስትራክሽን ዘርፍም ተሰማርተናል፤ ደረጃ ሁለት ተቋራጮች ነን። ይህ ቢዝነሳችን ከአምስት ዓመት በላይ ሆኖታል። እናም ጣፎ የመጣነው በዋናነት ለኮንስትራክሽን ስራ ነው፡፡ በመጀመሪያ የቤተሰብ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ተሰማራን፡፡ የእህቶቻችንና የእናታችንን ቤት ስንገባ፣ የስራችንን ጥራትና ቅልጥፍና ያዩ ሰዎች ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችን አገኘን በኮንትራት ሰጡን፡፡ ለኮንስትራክሽን ስራው ስንንቀሳቀስ ከተማዋን ተዘዋውረን የማየት እድል ነበረን፡፡ እናም አካባቢው አየሩ፣ የመሬት አቀማመጥና ሁሉ ነገሩ ምቹ ሆኖ ታየን፡፡ የከተማ አስተዳደሩም በማንኛውም ኢንቨስትመንት ከተማዋ ላይ ለሚሰማራ አካል የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ማራኪ መሆኑን በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ስንሰማራ ለመታዘብ ቻልን፡፡ ከተማዋ አዲስ በመሆኗ ብዙ ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችሉ ዘርፎች እንዳሉ ተገንዝበናል፡፡ ከዘርፎቹ አንዱም የሆቴልና የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው በመሆኑ እኛም ወደዚሁ ገባን፡፡ በዚህ ዘርፍ መሰማራት እንፈልጋለን ስንል ከተማ አስተዳደሩም በደስታ ነው የተቀበለን። ይሄው ለከተማዋ ድምቀት የሆነውን “ወረ ኩማ” ባርና ሬስቶራንትን አስፋፍተን ዛሬ ምረቃው ነው፡፡
አስፋፍተን ስትል?
መጀመሪያ ከፊት ለፊት የምታያት ቤት ብቻ ነበረች፡፡ ትንሽዬ ምግብ ቤት፡፡ እኛ ይህን ቦታ ተከራይተነው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ጠቅላላ ግንባታ በአንድ ወር ውስጥ ተጠናቆ ነው ስራ የጀመረው፡፡ ፊት ለፊት ካለው ቤት በስተቀር ይህን የምታይውን የመናፈሻ ባር፣ መፀዳጃ እና መሰል ግንባታዎች ከከተማ አስተዳደሩ ባገኘነው ይሁንታ አስፋፍተነው ነው፡፡ አሁን ከባለቤቱ ጋር ለአራት አመት ኪራይ ተፈራርመናል፡፡ የአንድ አመት ክፍያ ቅድሚያ ከፍለናል፡፡ እንደዚህ በማድረግ በዘርፉ አገልግሎት ላይ እሴት ለመጨመር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሌላው በአካባቢው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረናል፡፡ ወረ ኩማንና መስተንግዶውን ሲመለከቱ፣ ሆቴላቸውንና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሳደግና ተፎካካሪ ለመሆን እንዲተጉ ያደርጋል የሚል ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡
ቦታው አስፋልት ዳር ነው፡፡ ሆኖም ተከራይታችሁት እንጂ የእናንተ አይደለም፡፡ የራሳችሁ ለማድረግ ያደረጋችሁት ጥረት አለ?
ይሄ ትልቁ ሀሳባችን ነው፡፡ በዚህ ላይ ትልቅ እቅድ አለን፡፡ ተጨማሪ ቦታ እንዲኖረን በማድረግ ትልቅ ስራ የመስራት ፍላጐት አለን፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስሽው ጥሩ ቦታ ላይ ነው ያለው፤ ለዘርፉ ስራ የሚመጥን ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ከዚህ የተሻለ ስራ መሰራት እንደሚችል እናምናለን፡፡ እና የራሳችን ለማድረግ እንጥራለን፡፡ የጣፎ ከተማ አስተዳደርም ይህንን ያመቻቻል ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ እንደከተማ ራሷን ችላ መተዳደር የጀመረችው ከ1999 ዓ.ም ወዲህ በመሆኑ፣ ከተማ አስተዳደሩ አማራጭ ኢንቨስትመንቶች ወደከተማዋ እንዲመጡ የሚያሳየው ፍላጐት እንድትሰሪ ያበረታታሻል፡፡ ሌሎች ኢንቨስተሮችም መጥተው ቢሰሩ ሁኔታው ምቹና የሚያሰራ ነው ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡
”ወረ ኩማ” ባርና ሬስቶራንት መጀመሪያ ከነበረው ቤት ውጭ ሙሉ በሙሉ የተሰራው አገር በቀል በሆኑ ቁሳቁሶች ነው፡፡ እንደ ቀርከሃ፣ ሸምበቆ እና የመሳሰሉትን ለምን መረጣችሁት? አጠቃላይ የቤቱ አደረጃጀትም ባህላዊ ገፅታው ያመዝናል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
እንግዲህ ሁሉም ነገር ባህልን መሰረት ያደረገ ሲሆን ደስ ይላል፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ቁሳቁሶች ከዚሁ ከጣፎ የወጡ ናቸው፡፡ ቢዝነስ ሲሰራ ጐን ለጐን ባህልንም አብሮ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው። ይህ እንግዲህ ሌሎች በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች እንዲህ አይነት ቢዝነስ ውስጥ ሲገቡ የግድ ውድ ማቴሪያል መጠቀም እንደሌለባቸው ማሳያ ይሆናል። ሸምበቆው እንጨቱ፣ የጐጆዎቹ ክዳን ሳሩ ሁሉ… እዚሁ አካባቢው ላይ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው። ዋናው ነገር ለተስተናጋጅ ምቾት በሚሰጥና በሚያዝናና መልኩ መስራቱ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔና አንቺ እዚህ ተቀምጠን ስናወራ፣ ድባቡ ደስ ይልሻል፤ አየሩ ተስማሚ ነው፤ ለአካባቢው ጌጥ የሆነ ባርና ሬስቶራንት ሆኗል፡፡ ማራኪና የሚያዝናና የሆነው በውድ ቁሳቁስ ስለተሰራ አይደለም፡፡ ባህልን መሰረት አድርጐ በአገር በቀል ቁሳቁሶች በማራኪ ሁኔታ ስለተሰራ እንጂ፡፡
በሬስቶራንቱና በካፌው ዙሪያ ያሉ ቦታዎች በጌጣጌጥነት ከተጠቀማችሁባቸው ባህላዊ አልባሳት ውስጥ የዶርዜ ደንጉዛ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የሃድያና መሰል ብሔሮች አልባሳት ይገኙበታል ለምን ተመረጡ?
ያው የቢዝነስና የመዝናኛ ቦታ የሁሉም ሰው ነው። አሁን ከከተማ ወጣ ብሎ መዝናናት ተለምዷል፡፡ ለምሳሌ ሱሉልታ፣ ዱከም፣ ሰበታ፣ ቡራዩ ብቻ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወጣ ብሎ መዝናናት ተለምዷል፡፡ እዚህ ቦታ የትኛውም ብሔር ብሔረሰብ መጥቶ ይዝናናል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቱሪስቶችም ወደዚህ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ አንድም ኢትዮጵያዊነትን ማስተዋወቅ ነው፤ ሁለትም እነዚህ አልባሳት በጌጥ መልክ ሲታዩ አይንን ይማርካሉ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት ነው፡፡ ህብረ - ኢትዮጵያን ያቀፈ፣ ባህላችንን የሚያንፀባርቅ፣ በአገር በቀል ቁሳቁሶች የተዋበ መሆኑ ቤቱን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንዲሸት ያደርገዋል፡፡
እነዚህ ተጨማሪ የመዝናኛ ቦታዎች ማለትም ጐጆዎቹና ማስፋፊያው በአንድ ወር ተሰርቶ መጠናቀቁ የኮንስትራክሽን ባለሙያ በመሆናችሁ ነው ወይስ ሥራውቀላል ነው?
ብዙ ሰው የተገረመው በዚህ ነው፡፡ “ይሄ የማስፋፊያ ግንባታ አንድ አመት ፈጀ ወይስ ስድስት ወር?” ይሉናል። ነገር ግን በአንድ ወር ነው የተጠናቀቀው፡፡ በአንድ ወር ያለቀው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ስለተሰማራን ብቻ አይደለም። የእኛ ጥረትና ትጋት ነው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ያደረግነው፡፡ እርግጥ በዘርፉ ውስጥ መኖራችን አንዱ ግብአት ሊሆን ይችላል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ባሳየነው የሥራ ጥራትና ፍጥነት ሌሎች ስራዎችንም አግኝተናል። ይሄን ሥራ በአንድ ወር የጨረስነው ግን ትኩረት ሰጥተን በመስራታችን ነው እንጂ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ በመኖራችን ብቻ አይደለም፡፡ በኮንስትራክሽን ውስጥ ኖረው፣ በጥራትና በፍጥነት ስኬታማ ያልሆኑ ብዙ ድርጅቶች አሉ እኮ፡፡ እኛ አሁን ኮንስትራክሽን ላይ ባለን የስራ ብቃት “ቻይኖች ናቸው የሰሩት” የሚሉን አሉ፡፡ ግን ኢትዮጵያውያንም በደንብ መስራት እንደሚችሉ እያሳየን ነው፡፡ ይህም የማስፋፊያ ግንባታ በአንድ ወር ውስጥ ማለቁ የኢትዮጵዊያንን ብቃት ያስመሰክራል፡፡ የራሳችንን ብቃት ስለማናውቅ ነው እንጂ የሚያክለን የለም፡፡ ግን የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በምንም ነገር የላቀ ብቃት አለን፡፡ ነገር ግን በውጭ ባለሙያዎች የማመን ነገር ተጠናውቶናል፡፡
የማስፋፊያ ግንባታው ምን ያህል ወጪ ወጣበት?
ያው እንግዲህ ያላለቁና በመገንባት ላይ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እስካሁን 1.8 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ የተጀመሩት ሲያልቁ ወደ ሁለት ሚሊዮን ይጠጋል፡፡
በከተማዋ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዳለ ነግረኸኛል፡፡ በቀጣይ በምን ዘርፍ ለመሰማራት አስባችኋል?
ተዘዋውረሽ እንደተመለከትሽው ከጀርባው ሰፋ ያለ ቦታ አለው፡፡ ከፊት ለፊት የፓርኪንግ ቦታ ስለሌለው ያንን ቦታ ለፓርኪንግ ልናደርገው አስበናል። እንደነገርኩሽ ቦታውን ለመግዛትና የራሳችን ለማድረግ የጀመርነውና መስመር የያዘ ነገር አለ፡፡ ከዚያ በተረፈ ያሰብነው ትልቁ ነገር፣ በዚሁ አካባቢ ትልቅ የመዝናኛ ማዕከል ለመስራት አቅደናል፡፡ ቀደም ሲል እንደነገርኩሽ፣ በአሁኑ ወቅት ሰው ከከተማ ወጣ ባሉ ትንንሽ ከተሞች የመዝናናት ፍላጐት አለው፡፡ እንደነ ሱሉልታና በመሰል አካባቢዎች ማለቴ ነው፡፡ የህዝቡን ፍላጐት ለማሟላት ጣፎን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚያስጠራ ትልቅ የመዝናኛ ቦታ ለመስራት አስበናል፡፡ አሁን የተለያዩ ጥናቶች እያደረግን በጥሩ ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ ዋና ግባችን የአገር ውስጥ ደንበኛን ብቻ ሳይሆን ቦታው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንም እቅድ አለን፡፡
እንዲህ አይነት ኢንቨትመንቶች ሲካሄዱ ለአካባቢው ነዋሪ የስራ እድሎች ይፈጥራሉ፡፡ ወረ ኩማ ባርና ሬስቶራንት ለስንት ሰዎች የስራ እድል ፈጠረ?
በግንባታው ወቅት መቶ በመቶ ሰራተኛ የወሰድነው ከዚሁ አካባቢ ነው፡፡ በጉልበት ስራም በሙያተኝነትም ማለቴ ነው፡፡ አሁን ሬስቶራንቱ ተከፍቶ ስራ ከጀመረ በኋላም በሰርቪሱና ላይ በተለያየ ስራ ላይ ያሉት 80 በመቶዎቹ የአካባቢው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ለ40 ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ማስፋፊያው ሲያልቅ ለተጨማሪ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡
ባርና ሬስቶራንቱ ስራ ከጀመረ በኋላ ገበያው እንዴት ነው?
በጣም አሪፍ ነው፤ እኛ ደስተኞች ነን፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሰዎች እየመጡ ይጐበኙናል፤ ያበረታቱናል። አሁን ገበያውም ጥሩ ነው፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ሆኑ ከአዲስ አበባ የሚመጡት እየተስተናገዱበት ነው፡፡ ይሄ ለአዲስ አበባ ቅርብ ነው፤ መንገዱም ጥሩና ቀጥ ያለ ነው። ጣፎ ለወደፊት ተስፋ ያላት ከተማ ናት፤ እንደነ ሮፓክ እና ሲሲዲ የመሳሰሉ ትልልቅ ሪል እስቴቶች እዚሁ አሉ። ወደፊት ትልቅ የመዝናኛና የንግድ ከተማ የመሆን እድል አላት፡፡ እኛም ለከተማዋ ማደግ በተለያየ ዘርፍ አስተዋጽኦ እያደረግን እንገኛለን። በነገራችን ላይ የደንበኛ ችግር የለም፡፡ ብዙ ባለሀብቶች ሩቅ ሳይሄዱ እዚሁ ብዙ ነገር መፍጠርና መስራት ይችላሉ ባይ ነኝ፡፡
ለአንተ የሥራ ትጋትና ጥንካሬ አርአያ የሆነህ ሰው አለ?
ታላቅ ወንድሜ አበባየሁ ከበደ ነው አርአያዬ። ለምን ብትይ… በጣም በጣም ጠንካራና አስተዋይ ሰው ነው፡፡ ከምንም ተነስቶ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ የቤተሰባችን ቢዝነስ ያልኩሽ ኮንስትራክሽኑ “አበባየሁ ከበደ የህንፃ ስራ ተቋራጭ ነው” የሚባለው፡፡ ለዚህ ባርና ሬስቶራንት እዚህ መድረስም የእሱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ጠንካራ ሰራተኛና ስራ ወዳድ ስላደረገኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ ሌሎችም ለዚህ ባርና ሬስቶራንት እዚህ መድረስ የበኩላቸውን ያደረጉ በርካታ ሰዎች አሉ በጥቅሉ እናመሰግናለን፡፡

Read 2146 times