Saturday, 07 June 2014 13:37

የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

የድሬዳዋው ገፅ ለገፅ ውይይት
“የመገፋፊያ ሳይሆን የመደጋገፊያ ውይይት!”
   የብሾፍቱው የጉዞ ማስታወሻ የተጠናቀቀው፤ በአንደኛ ደረጃ ት/ቤትና በውሀ ችግር ዙሪያ የተነሱትን ነጥቦች በመነቆጥና አገልግሎት ሰጪዎች (የመንግስት አካላት) እና አገልግሎት ተቀባዩ (ህዝብ) ተማምነው፣ የሥራ ድርሻ ተከፋፍለው ከዚያም ከየቀበሌው የተመረጡ አራት አራት ሰዎች ተመርጠው፣ የድርጊት ኮሚቴ ፈጥረው፣ የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ለመከታተል ቃል ገብተው ነው፡፡
የብሾቱ ከንቲባ ሲያሳርጉ ባደረጉት ንግግር “የዛሬውን መድረክ ልዩ የሚያደርገው፤ በባለሙያዎች የተጠና፣ ብዙ ጊዜ የወሰደ፣ ናሙና ተወስዶ የተሰራና በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው፡፡ የተኛ ህዝብ ሲኖር የተኛ አመራር ይፈጠራል፤ የነቃ ህዝብ ሲኖር የነቃ አመራር ይፈጠራል” ያሉት ተጠቃሽ አባባል ነው፡፡”

   ሚያዚያ 28 2006 ከድሬዳዋ ኤርፖርት ወደ ራስ ሆቴል ተጓዝኩ፡፡ ወደ ስብሰባው ቦታ፡፡ የድሬዳዋ ኮሚኒቲ አክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ የስብሰባውን አላማ አብራሩልን። “የኢትዮጵያ ሶሻል አካውንቴቢሊቲ ፕሮግራም እየተካሄደ ነው” አሉ “በኢትዮጵያ በ39 ቦታ ይካሄዳል። እኛ ደግሞ በድሬዳዋ እናካሂዳለን፡፡ በ4 ቀበሌዎች ነው የምናካሂደው፡፡ 01 02 04 እና 05። በት/ቤቶች በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ላይ፡፡ አገልግሎት ሰጪ የምንላቸው በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃና ፍሳሽና በግብርና ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ዋና ትኩረቱ ደግሞ የት/ቤቶች ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ያወጣውን የትምህርት መስፈርት ተከትለን ነው የምንሄደው፡፡ ግምገማ አካሂደናል - በአገልግሎት ሰጪዎች እና አገልግሎት ተቀባዮች ላይ፡፡ በአገልግሎት ሰጪዎች ማለት የአስተዳደር ሥራ ላይ ያሉና መምህራን ናቸው፡፡ ሌላው ህብረተሰቡ ነው፡፡ በአግባቡ አገልግሎት እየተሰጠን ነወይ? ልጆቻችን በትክክል እየተማሩ ነወይ? የሚለው ህዝብ፡፡
በቀበሌ ደረጃ ተገምግመዋል፡፡ ከዚያ 4ቱንም ቀበሌ የሚመለከት ግምገማ ተካሂዷል፡፡ የደረሰቡበትን ደረጃ አይተናል፡፡ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ውይይት ማካሄድ ነው ዓላማችን፡፡ የገፅ ለገፅ ውይይት ነው! በአገልግሎት ሰጪዎች በኩል፤ ከምክር ቤት አባላት፣ የቀበሌ ሹማምንት፣ ከመንግሥት የትምህርት ክፍሎች ወዘተ ሲኖሩ፤ ከማህበረሰቡ ደግሞ ከወጣቱ፣ ከሴቶች፣ ከአረጋውያን ወዘተ የተወከሉ አገልግሎት ተቀባዮች አሉ፡፡ ሁለቱም አሉ፡፡ የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ድሬደዋ ኮሙኒቲ አክሽን ማህበር (ዲዲካ) በአጋርነት ነው የሚተገበሩት፡፡
ምዝገባ ተካሂዷል፡፡ ፕሮግራሙ ተዋውቋል። የመግቢያ ንግግር ተካሂዷል፡፡ አቶ ብርሃኑ ሰቦቃ ብሾፍቱ እንዳደረጉት ሁሉ ማብራሪያ ሰጡ፡፡ የሶሻል አካውንቴቢሊቲ (ማህበራዊ ተጠያቂነት) ጥናት ኮሚቴ ውጤት ቀርቧል፡፡ የትምህርት ሂደቱ ክፍተቶች ምንድናቸው? ይህን ተወያይተን የምንፈታበት የጋራ መድረክ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ነቅሶ ያወጣቸውና አገልግሎት ሰጪው ነቅሶ ያወጣቸው፤ ብዙ ልዩነት የላቸውም አሉ፡፡ እንዴት እናስተካክለው ነው ዋናው፡፡ አንኳር አንኳሮቹን ለይተን የማስፈፀም ዕቅድ ይወጣላቸዋል፡፡ ይህን ዕቅድ የሚያካሂዱ ከየቀበሌው አራት አራት ሰዎች ይመርጣሉ። የስብሰባው መንፈስ ይሄ ሲሆን በትምህርት ቢሮ ተወካይ ንግግር ተዘግቷል! የድሬዳዋ ኢህማልድ (ጄክዶ) ሥራ አስኪያጅ  አቶ አበበ ናቸው ለመክፈቻ የተናገሩት፡፡ ዋና ዋና ጉዳዮቻቸው፡-
ጄክዶ ህፃናት ላይ ሲሰራ ቆይቷል
የከፋ ችግር ያለባቸው የዝቅተኛ ደረጃ ህብረተሰብ አባላት ላይ ያተኩራል፡፡
የማህበረሰቦችን ችግሮች የመሥፍታት ሥራ ስንሰራ ቆይተናል
አደረጃጀትና አቀነጃጀት ላይ ሰርተናል፡፡
በሂደት በጤና፣ በፅዳት በተለይም በትምህርት ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት አገልግሎት ሰጪና ተቀባይ ተገናኝተው እንዲወያዩ ማድረግ አንዱ ተግባራችን ነው። ውጤትም አምጥቷል፡፡ የተሻለ ውጤት በህብረተሰቡ። እንዲመጣ ነው ዓላማችን ዛሬም ለዚህ ነው እዚህ የተገኘነው፡፡
በትንሽ ትንሹ፣ ባዋጣነው ያህል ለውጥ እናመጣለን እንላለን፡፡ ለትምህርት ቢሮ ምሥጋና ይገባል፡፡
ዲዲካ በባለቤትነት የሚመራው ውይይት ነው፡፡
በመሠረቱ ከጠራ ዕቅድ እንኳ ውጤት ማምጣት ያስቸግራል እንኳን ከተዛነፈ፡፡
ሁላችንም ለቀና ውጤት በቀናነት እንሳተፍ!
ይሄ የመንግሥት ፕሮግራም ነው፡፡ ጊዜው ደግሞ የመገፋፊያ ሳይሆን የመደጋገፊያ ነው - የጋራ ውጤት ማምጫ!
“ችግርን መለየት ግማሽ ሥራ ነው” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ዛሬ ያንን እየሰራን ነው፡፡  
“ማህበራዊ ተጠያቂነት - ማንም ኃላፊ ለሆነበት ነገር ተጠያቂ ነው፡፡ ሁለት ዓይነት የማመዛዘኛ ካርዶች አሉ። ሲቲዝን ሪፖርት ካርድ አንዱ የሚሞላው ፎርም ነው። በተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሞላ ካርድ ነው፡፡ አሳታፊነቱ አጭር ነው፡፡ ስኮር ካርድ ግን የአገልግሎት ሰጪንም ተቀባይንም የሚያሳትፍ ካርድ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ካርዶች የውይይታችን መሰረት ናቸው” አሉ ሰብሳቢው፡፡ “ነዋሪው ያለውን ግንዛቤ በተጨባጭ የሚያሰፍርባቸው ናቸው፡፡ መታረም ያለበት ምንድን ነው? ነው የሚለው ኮሙኒቲ ስኮር ካርድ! ግብዓት መለየት፣ ቅደም ተከተል ማውጣት፤ ከዚያ በነጥብ አሰጣጥ ደንብ የትኛው የበለጠ ቅድሚ ሊሰጠው ይገባል? የሚል ነው። ተቀዳሚውና የተለየው ችግር ላይ ርብርብ ይደረጋል! ጥናቶቹን ህብረተሰቡ ያውቃቸዋል!” የዕድር አመራሮች፣ የማህበር አመራሮች፣ ከማህበረሰብ የተውጣጡ በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ ለዚህ ነው ህዝባዊ/ማህበራዊ ተጠያቂነትን የሚያመላክተን! ከዚያ ነው ጥናቱ የመነጨው…” ብለዋል፡፡
“ከየቀበሌው የተውጣጡ በተጨማሪም 32 ሰዎች የስኮር ካርድ አጠቃቀም ኤክስቴንሲቭ ትሬኒንግ ተሰጥቷል” ብለዋል፡፡ የማህበራዊ ተጠያቂነት ምክር ቤት Social Accountability Council ተቋቁሞ በትምህርት ቢሮ ተወካይ መሪነት ተቋቁሞ፤ መለኪያ አስቀምጧል፡፡ እነሱን ይዘን ተጉዘናል፡፡ አመቻችተንም አሰልጥነናል፡፡ Focus Group Discussion በየቀበሌው አካሂደናል፡፡ አካል ጉዳተኞች፣ በኤች አይ ቪ የተጠቁ ትምህርት ቤት ገብተው ያለተፅዕኖ ይማራሉ ወይ? ዓይነት ውይይት አድርገናል፡፡ የትምህርት ማቴሪያል ተሟልቷል ወይ? የሚለው ተብራርቷል፡፡ ወጣት፣ ሴት፣ አረጋውያን ህፃናት ተሳትፈውበታል፡፡ ልዩ ምክክር ተደርጓል፡፡    
በመጨረሻ እስኮር ካርድ ተሞልቶ የተገኘውን ውጤት በየቀበሌው እንዲገመግሙ አድርገናል፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች ሁሉ ባሉበት የተካሄደ ነው፡፡ እዚህ የመጣነው ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው፡፡
ሁለቱም አካላት ዛሬ ተገናኙ!
ውይይቱ በሰፊው ተካሄደ፡፡ ቀድመው የሚያውቁት ጉዳይ ስለሆነ አገልግሎት ሰጪዎችም፣ አገልግሎት ተቀባዮችም በሚገባ ችግሮቹን ተወያይተው፣ ተሞራርደው፣ ተማምነው፤ ወደ ተግባር ኮሚቴ ምሥረታ ተሸጋግረዋል፡፡
የህብረተሰብ ተወካይ ውጤቶቹ - በየት/ቤቱ ያልተሠሩ ሥራዎችና የቤተመፃሕፍት አለመሟላትና እጥረት፣ የላቦራቶሪ አለመሟላት፣ የመፀዳጃ ቤት ከፍተኛ ዕጥረትና አለመጽዳት፣
ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ማጣትና አቅም ማጣት፣ የመጠጥ ውሃ እጥረት፣ የመዝናኛ ክበብ ችግር ወዘተ ናቸው፡፡
ለነዚህ የተሰጠውም ነጥብ ተዘረዘረ፡፡ የጋራ ችግሮች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ ተሰብሳቢውም ተስማምቶባቸዋል።
የታወቁና የተለመዱ ችግሮችን በማንጠር ተጀመረ፡፡
አሁንስ ስብሰባውን አቶ በኃይሉ የጄክዶ ፕሮግራም አስተባባሪ ነው የሚመሩት፡፡ “ወደፊት በምን መልኩ እንፍታው የሚለው (approach) ላይ ነው እምንወያየው” አሉ፡፡
ውይይቱ ቀጠለና አብዛኞቹ ለኢህማልድ (ጄክዶን) ያላቸውን አድናቆት ገለጡ፡፡ የመንግሥት ት/ቤትን ብቻ እንደሚመለከት አጽንኦት ተሰጠ፡፡ አንጥረው ሲያወጡትም ውስን የሰው ኃይል መኖር እሱኑ በአግባቡ አለመጠቀም አሟጦ አለመጠቀም፤ የስታንዳርድ አለመኖር፣ ተረባርቦ ችግርን መፍታት ላይ በሁለቱም ወገን ሀሳብ ተሰጥቶበታል። ተማምነውበታል፡፡ በአብዛኛው የአቅም ጉዳይ እንደሆነ ተሰምሮበታል፡፡
ርዕሰ መምህሩ ብቻውን አይችለውም አጋዥ ይፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡ መሳተፍ ይገባዋል፡፡ የስፖርትና መዝናኛ ቦታ ሊታሰብበት ይገባዋል፡፡ የቆሻሻ መብዛትን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ የልጃገረዶች መምከሪያ ክፍል ተዘጋጅቷል፤ በጀት ተመድቦ ፓንትና ሞደስ ሳይቀር ያደራጀ ትምህርት ቤት እንደምሳሌ ተጠቅሶ ተወድሷል። የግቢ ጥበት የብዙ ትምህርት ቤቶች ችግር በመሆኑ ተወስቷል። በመጨረሻም ሦስት መፍትሔ ሰጪዎች ተጠቁመዋል 1) ራሱ ት/ቤቱ 2) ህብረተሰቡ 3) መንግሥት፡፡ የሦስቱ መረባረብ ተጠቁሟል፡፡
እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ለመፍታት ዕቅድ አውጥቶ የሚደረገውን ሂደት የሚከታተል የተግባር ቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ኃላፊነቱ ተሰጥቶት መንግሥትም ድርሻውን ሊወስድ ተስማምቶ ስብሰባው አብቅቷል፡፡ ገፅ ለገፅ በመላው አገሪቱ ቢካሄድ የት በደረስን እያልኩ ነው ቁጭቴን ይዤ ወደ አዲስ አበባ የተመለስኩት!    

Read 1794 times