Saturday, 07 June 2014 13:34

ፖለቲከኞቻችን የእስከዛሬ ሃሳባቸውን “ዲሊት” ያድርጉት!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(7 votes)

አዲሱ ንቅናቄ - የምስጋና አብዮት ነው!

     ለሁሉም ጊዜ አለው ተብሏል… አሁን ጊዜው የምስጋና አብዮት ነው፡፡ የአረቡን ህዝባዊ አመፅ አይተነዋል፡፡ የቀለም አብዮት የተባለውንም በቲቪ መስኮት በእነ ዩክሬን ታዝበነዋል፡፡ እና ምን ቀረን? ሁሉም ተሞክሯል እኮ! ሰላማዊ ሰልፉም፣ የእሪታ ቀኑም፣ ቦይኮት ማድረጉም ወዘተ… ኧረ ምን ያልተሞከረ አለ!
አሁን በአንድ ነገር እንስማማ፡፡ በድሮው መንገድ እየሰራን አዲስ ውጤት (ለውጥ) መጠበቅ ጅልነት ነው፡፡ አሰራራችንን ሳይቀይር ለውጥ ሊመጣ ጨርሶ አይችልም፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ እንደሚለን፤ “ይህ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡” (It is a must! ብያችኋለሁ) እናላችሁ.. ዛሬ ስለምስጋና አብዮት እናወራለን፡፡ ምስጋናና አብዮት ምን አገናኛቸው ይሆን? በነገራችሁ ላይ ይሄ ስብከት አይደለም፡፡ እንደ ዕውቀት (መረጃ) ሽግግር ብትመለከቱት ደስ ይለኛል፡፡ የምስጋና አብዮት አመንጪዋ ማን መሰለቻችሁ? ታዋቂዋ አውስትራሊያዊት ደራሲ ርሆንዳ ባይርኔ ናት፡፡ The secret እና The power የተባሉ መፃህፍቷን በሚሊዮን ቅጂዎች የቸበቸበችውን ደራሲ ማለቴ ነው፡፡
እናላችሁ… ችግር ለገጠመው ግንኙነት፣ (የቤተሰብ፣ የትዳር፣ የፖለቲካ፣ የፍቅር፣ የማህበራዊ ኑሮ፣ የጓደኝነት ወይም የሁሉም ሊሆን ይችላል!) እንዲሁም ለጤና፣ ለገንዘብና ለደስታ እጦት መድኃኒቱ ምስጋና (gratitude) ነው ባይ ናት- The Magic የተባለውን መፅሃፍ የፃፈችው ርሆንዳ ባይርኔ፡፡ (ምስጋና ስትል ግን የአበሻን “ተመስገን እቺንም አታሳጣኝ” ማለቷ አይደለም፡፡) ምስጋና ፍርሃትን፣ የሌሎችን ችግር  መረዳትን፣ ጭንቀትን፣ ሃዘንን እና ድብርትን በማጥፋት ደስታን፣ የሃሳብ ግልፅነትን፣ ትዕግስትን፣ ደግነትን፣ ርህራሄን፣ የአዕምሮ ሰላምን ያመጣል ትላለች ፀሃፊዋ፡፡ ምስጋና ለችግሮቻችን መፍትሄ ይሰጠናል፡፡ ህልማችንን ወደ ተግባር የምንለውጥባቸውን ዕድሎችና መንገዶችም ይከፍትልናል - ባይርኔ እንደምትለው፡፡ በሃሳቡ ጥርጣሬ ቢጤ ከገባችሁ ቀላል ነው፡፡ አመስግናችሁ ውጤቱን ማየት ትችላላችሁ፡፡ እንኳን በፖለቲካ ጎዳና (በሚያሙለጨልጨው ማለቴ ነው!) በሌላውም እንኳን በሂሳብ የተሰላ እርግጠኛ መንገድ የለም፡፡ መንገዱ የሚገኘው በሙከራና በፍተሻ ነው፡፡
ከእያንዳንዱ ስኬት ጀርባ ጥረትና ትግል ብቻ አይደለም ያለው፤ ምስጋናም ጭምር እንጂ! ምስጋና ለአዳዲስ ሃሳቦችና ግኝቶችም በር ይከፍታል የምትለን ደራሲዋ፤ ይሄንንም ታላላቆቹ ሳይንቲስቶች ኒውተንና አንስታይን አረጋግጠውታል ስትል እማኝ ታደርጋቸዋለች፡፡ ሁሉም ሳይንቲስት የእነሱን ዱካ ቢከተል ኖሮ ዓለም ወደ አዲስ ግንዛቤ፣ እድገትና ምጥቀት ትወነጨፍ ነበር ስትል ተቆጭታ ታስቆጨናለች፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በፊዚክስ፣ በህክምና፣ በሥነ-ልቦና፣ በህዋ እና በሁሉም የሳይንስ መስኮች ህይወትን ለዋጭ ግኝቶች እውን ይሆኑ  ነበር … (የምስጋና ንፍገት ስላለብን ግን አልተሳካም!)
እስቲ ምስጋና እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት (ኮርስ) በት/ቤቶች ቢሰጥ ብላችሁ አስቡ፡፡ ስልጣኔያችንን በአስደናቂ ስኬቶችና ግኝቶች ወደ ሰማይ የሚያስወነጭፉ፣ ውዝግብን የሚያስወግዱ፣ ጦርነትን የሚያስቆሙና ሰላምን የሚያበስሩ አንድ ትውልድ ህፃናት ይፈጠር ነበር፤ባይ ናት፤ ደራሲዋ (ግዴለም እንመናት!)
ወደፊት ዓለምን የሚመሯት እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? አመስጋኝ መሪዎችና ህዝቦች ያሏቸው አገራት ናቸው፡፡ (“የሚመሰገን ሳይኖር?” ብሎም ማማረር ይቻላል!) አንድ ህዝብ በምስጋና ሲሞላ አገሩን በሃብትና በዕድገት ያንበሸብሸዋል (ሥራ ትቶ ምስጋና አልወጣኝም!) ችግርና ደዌን ድምጥማጡን ያጠፋዋል፡፡ ቢዝነስና ምርት እንዲመነደግ፣ ሰላምና ደስታ አገሪቱን እንዲያጥለቀልቁትም ያደርጋል - ተዓምራዊ ምስጋና! (በተዓምራት የማያምኑ በጨረታው አይገደዱም!)
እንደባይርኔ አባባል፤ እንቅልፍ አጥቶ እየተጉ ማደር ብቻ በጥጋብ አያትረፈርፍም፡፡ “ተመስገን” የምትለዋ ቃልም ልትታከልበት የግድ ነው፡፡ ያኔ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው የእኛና የመንግስታችን ህልም እውን ይሆናል፡፡ (ትጋት የሌለበት ምስጋና ግን ውጤት አልባ ነው!) ሳይሰሩ ምስጋናማ በእነ አዳምና ሄዋን ጊዜ ቀረ!!
እንግዲህ አሁን ወደ ዋናው ፍሬ ጉዳይ እንግባ።  እንዴት ነው ቅስቀሳው የሚካሄደው? በቴክስት ሜሴጅ፣ በፌስ ቡክ፣ በትዊተር… በህዝባዊ ስብሰባ፣ በሰላማዊ ሰልፍ? በነገራችሁ ላይ ለቅስቀሳ በሚጠቀምበት የሚዲያ ዓይነት ከሌሎቹ አብዮቶች ብዙም አይለይም - የምስጋና አብዮት!!
አብዮቱ በመላው ዓለም ከዳር እስከ ዳር እንዲጥለቀለቅ የምንሻ ከሆነ ትለናለች ባይርኔ፤ የምስጋናን ተዓምራዊ ኃይል (magical power) ብዙዎች በጥልቀት እንዲያውቁትና እንዲገነዘቡት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ (ያልነቃ ህዝብ ይዞ Revolution የለም!) ይኼውላችሁ…የሃይማኖት ስብከት አይደለም የያዝኩት (ሃይማኖትና ፖለቲካን እያጣቀሱ መጓዝ አይፈቀድም!)  ምስጋናው ወይም ተመስገን የሚለው የእርካታ ስሜት የግድ የሰማዩ ፈጣሪ ጋ መድረስ የለበትም፡፡ ወዳሻችሁ ቦታ መላክ ትችላላችሁ፡፡ ዋናው ነገር ምስጋና ማቅረባችሁ ነው - ተመስገን ማለታችሁ!! እርካታችሁን መግለፃችሁ፡፡ ሆኖም ግን ምስጋና ለማቅረብ ሎተሪ እስኪወጣላችሁ ወይም በብልጽግና እስክትንበሸበሹ መጠበቅ የለባችሁም፡፡ “ቡና በሰከነ ቁጥርማ ተመስገን አልልም” የምትሉ ከሆናችሁ መልካም በረከቶቻችሁን እያባረራችሁ ነው፡፡ (ቡናውም እኮ ላይሰክን ይችላል!)
እናላችሁ…በየደቂቃው ስንትና ስንት ሺ ሰው በሚሞትባት ዓለማችን፣ በህይወት መኖራችን ራሱ ተመስገን ሊያሰኘን ይገባል፡፡ ዓይንና ጆሮአችን ያለ እክል በማየታቸውና በመስማታቸውም ተመስገን ብንል አይበዛባቸውም፡፡ (የማይሰሙና የማያዩ አሉ እኮ!) ለ1 ሚሊዮን ብር የቋመጠ ህልመኛ (ባለራዕይ) ኪሱ ውስጥ ላለችው 100 ብር ተመስገን ሊል ይገባል። (ለማንም አይደለም ለራሱ!) 100 ብር ብቻ ናት  እያለ ዘወትር ከተነጫነጨ ግን እንኳንስ 1ሚ.ብር 100 ብሯንም ሊያጣት ይችላል፤ ትላለች ርሆንዳ ባይርኔ። BMW አውቶሞቢል ማለም ክፋት የለውም፡፡ ዛሬ ለምታገለግለን ቮክስ ዋገን ግን ተመስገን ልንል የግድ ነው፡፡ ከእሷም በፊት ለጤናማው እግራችን ምስጋና ይገባዋል (ብርድ ቢሸመቅቀንስ!)
ይቺ አውስትራሊያዊት ደራሲ ምን ትላለች መሰላችሁ? በህይወት ስትኖሩ ለሚገጥማችሁ ደስታና መከራ፣ ችግርና ውጣ ውረድ፣ ስኬትና ውድቀት፣ ማግኘትና ማጣት…ወዘተ ተጠያቂው ራሳችሁ ናችሁ፡፡ እርግጥ ነው ሰበብ አናጣም፡፡ የምንከሳቸው ብዙ ሰዎችም ይኖሩናል፡፡ ክፋቱ ግን ማንም ለማንም ህይወት ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ለምን መሰላችሁ? የየራሳችንን ህይወት የምንፈጥረው ራሳችን ነን፡፡ እንዴት? በሃሳባችን!! እናም ህይወታችን የሃሳባችን ውጤት ነው፡፡ ባይርኔ እንደምትለው፤ የዛሬ ህይወታችን የትላንት ሃሳባችን ውጤት ሲሆን የዛሬ ሃሳባችን ደግሞ የነገ ህይወታችን ነው፡፡
Thoughts become things ትላለች - ደራሲዋ። ሃሳባችን ህይወት ሆኖ ይከሰታል እንደማለት ነው። አባቶቻችን ሲተርቱ “ደግ ተመኝ ደግ እንድታገኝ” ይላሉ፡፡ ያሰብነውን፣ ያለምነውን፣ የተመኘነውን እናገኛለን ማለት ነው፡፡ እሷ ደግሞ Like attracts like ትለዋለች፡፡ (ሁሉም ቢጤውን ይስባል እንደማለት) ባይርኔ በመጀመሪያው ዝነኛ መጽሐፏ The secret ላይ ዓለም የሚመራው በስበት ህግ ነው ትለናለች - the law of Attraction. በቀላል አነጋገር ደግነት - ደግነትን፣ ጠላትነት - ጠላትነትን፣ ክፋት - ክፋትን፣ መስጠት -መቀበልን …ይስባል ወይም ይጎትታል እንደማለት ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ የስኬትና የብልጽግና መፃህፍት፤ ሁሉም የዘራውን ያጭዳል በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ይስማማሉ፡፡ እስካሁን ያልናቸው ነገሮች ሁሉ ለግለሰብም፣ ለቤተሰብም፣ ለህዝብም፣ ለፓርቲም፣ ለአውራ ፓርቲም…ይሰራሉ፡፡ ለአንዱ እየሰራ ለአንዱ የማይሰራበት ምክንያት የለም፡፡ የዩኒቨርስ ህግ (The law of attraction ማለቴ ነው) አድልዎ አያውቅም (በዚህስ ተማመን ነው!)
አሁን ለምሳሌ ኢህአዴግ የአቅሙን ያህል ወይም የአቅማችንን ያህል ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው ልንል እንችላለን (“እያንዳንዱ ህዝብ የሚገባውን መንግስት ያገኛል” አሉ!) “የለም፤ ኢህአዴግ የለየለት አምባገነን ነው” የምትሉ መብታችሁ ነው፡፡ እኔን የሚያሳዝነኝ ግን ስለምስጋና እስካሁን የሞካከርኩት ቅስቀሳ ፍሬ አልባ መሆኑ ነው፡፡ ደርግን ያህል ፍፁም አምባገነንና ጨካኝ መንግስት የሚያውቅ መቼም ለኢህአዴግ ተመስገን ይላል ብዬ አስባለሁ (በልቡ እኮ ነው!) ከኢህአዴግ የተሻለ ወይም የበለጠ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዳናገኝ ግን የረገመን የለም፡፡ ችግሩ እኛም ራሳችን አሁን ካለው ዲሞክራሲያዊ መንግስት የበለጠ ይገባናል ብለን አናስብም፡፡ (ህይወታችን የሃሳባችን ውጤት ነው ይሏል ይሄ ነው!) ነገር ግን እኛ የሚገባን የአሜሪካ ዓይነት ዲሞክራሲያዊ መንግስት (ሥርዓት) ነው ብለን ማሰብ ብንጀምርስ? በእርግጥ ማሰቡ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አሜሪካውያን የደረሱበት የሥልጣኔና የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ ልንደርስ ይገባል፡፡ የግለሰብ መብት፣ የሰለጠነ የፖለቲካ ውይይት፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ወዘተ… ሁሉ ያካትታል፡፡ ሚስትን መደብደብ እንደ ነውር በማይታይበት አገር ውስጥ እየኖርን የአሜሪካ ዓይነት ዲሞክራሲ ልናስብ አንችልም፡፡ ብናስብም ቅዠት ነው፡፡
ቆይ ለምን ይመስላችኋል…የዜጐች መብትና ነፃነት የሚሸራረፈው? ኢህአዴግ የዜጐችን መብት ስለማያከብር ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ደራሲዋ ርሆንዳ ባይርኔ ግን በጄ ብላ አታዳምጣችሁም፡፡ ለዚህ ተጠያቂ የምታደርገው ኢህአዴግን ሳይሆን እኛን ነው - ህዝቦችን ወይም ዜጐችን፡፡ ተሸራርፋ የምትደርሰን ነፃነት ትበቃናለች፤ ጐመን በጤና ብለን ስለምናስብ እኮ ነው መጀመሪያውኑ የሚሸራርፍ የጣለብን፡፡ (“ማንኛውም ህዝብ የሚገባውን መንግስት ያገኛል” የምትለዋን አትዘንጉ!)
በኢህአዴግ በኩልም ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ እንደማያገኝ አምኖ የተቃዋሚን ሚና ራሱ ሊጫወት ወስኗል - በአውራ ፓርቲነት። ነገር ግን እውነት ጠንካራ ተቃዋሚ ጠፍቶ ነው? ያሉትንስ ማጠንከር አይቻልም ነበር? (ያውም ነፃነታቸውን በመስጠት ብቻ!) ግን ኢህአዴግ አዕምሮ ውስጥ ስለተቃዋሚ ያለው ሃሳብ … ፀረ ዲሞክራሲያዊ፣ ፀረ ልማትና ፀረ ሰላም የሚል ብቻ  ነው፡፡ ከዚህ አዙሪት ሃሳቡ ሆን ብሎ ራሱን ካላወጣ መቼም ጠንካራ ተቃዋሚ አይፈጠርም። (እሱማ ደስታው ነው!) ህዝብ ግን እንደ 97ቱ ምርጫ እንኳን የሚያኮርፍበት ተቃዋሚ ያጣል፡፡ (ይሄ ሁሉ ልማት እኮ የ97 ምርጫ ፍሬ ነው!)
እኔ ለኢህአዴግ የምፈራለት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ክፉ ክፉውን ስለሚያስብ በክፉ ነገሮች እንዳይከበብ ነው! ባለፉት አስርት ዓመታት ደጋግሞ “ጠላቶቻችን” በማለት ኢህአዴግ ምን አተረፈ? ደርዘን ሙሉ ጠላቶች! በአገር ቤትና በዳያስፖራ፡፡ ይሄ የሆነው ግን በኢህአዴግ ተንኮል ሳይሆን በዩኒቨርሳል ህግ ነው፡፡ ደጋግመህ የምታስበውን ታገኘዋለህ በሚለው፡፡
መቼም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መግለጫ ሳትሰሙ ወይም ሳታነቡ አትቀሩም ብዬ እገምታለሁ። በአብዛኛው አዲስ ፕሮግራም የማያስተዋውቅ አይደለም፡፡ ስሞታ ነው - እሮሮና አቤቱታ፡፡ አንድም አዎንታዊ ዓ.ነገር አታገኙበትም - በአሉታዊ ቃላትና ሃረጐች የታጀበ ነው፡፡ ሁሌም ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ ከመቼውም ይበልጥ እየጠበበ መምጣቱን እንጂ የስንዝር ያህል እንኳን መስፋቱን አይገልጽም፡፡
እዚህ ላይ ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው… አውራው ፓርቲ የተሻለ ነው እያልኩ አለመሆኔን ነው፡ ግን ሁለቱንም ለየብቻ ስትፈትሿቸው “ተመስገን” ከሚለው ተዓምራዊ ሃይል በፈቃዳቸው የተጣሉ መሆናቸውን ትረዳላችሁ፡፡ ይሄ ብቻም አይደለም። ሙሉ ትኩረታቸውን ያደረጉት በጐ በጐው ላይ ሳይሆን ክፉው ላይ ነው፡፡ እናም ምን እሰጋለሁ መሰላችሁ? የአሁኑ ዘመን ተቃዋሚ ከመሰናበቱ ወይም ጡረታ ከመውጣቱ በፊት የፖለቲካ ምህዳሩ አሁን ካለበት ቅንጣት ታህል ንቅንቅ አይልም የሚል ስጋት አለኝ፡፡ (ሟርተኛ ሆኜ እንዳይመስላችሁ!) የተቃዋሚው ጐራ ዝም ከማለት እያለ “ምህዳሩ ይስፋ” የሚል ጥያቄ ቢያሰማም፣ ይሰፋል በሚል ልባዊ እምነት ግን አይደለም፡፡ “ኢህአዴግ ማጥበብ እንጂ ማስፋት የት የለመደውን ነው” ብሎ የደመደመ ይመስለኛል፡፡ በባይርኔ ህግ  ተቃዋሚዎችም እንደኢህአዴግ  ናቸው። ኢህአዴግን አጋር ከማድረግ ይልቅ በጠላትነት ፈርጀው በማውገዝ ምን አተረፉ? ምናልባት የበለጠ ጠላትነት፣ እስር፣ ወከባ፣ መፈናፈኛ ማጣት--- ይሄም ግን እንደ እርግማን ራሳቸው ላይ የወረደባቸው ጉድ አይደለም፡፡ ሥራዬ ብለው በትኩረት በማሰብ ያመጡት ዕዳቸው ነው፡፡
ባይርኔ እንደምትለው፤ ሰዎች የማይፈልጉትን ችላ ብለው የሚፈልጉት ላይ ቢያተኩሩ ነገሮች ይለወጣሉ፡፡ ሥራ ማርፈድ የማይወድ ሰው ማተኮር ያለበት በጊዜ ሥራ መግባት ላይ እንጂ ማርፈድ ላይ ሊሆን አይገባም፡፡ እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ (ተቃዋሚዎችንም ይመለከታል!) ተቃዋሚዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚፈጁት የራሳቸውን ፖሊሲ የተሻለ በማድረግ  ነው ወይስ የኢህአዴግን ፖሊሲ በማጣጣል? እንደኔ ግምት ተቃዋሚዎች በትኩረት የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ስኬት ሳይሆን ስለ ኢህአዴግ ውድቀት ነው፡፡ ስለሌላው ውድቀት እያሰቡ ስኬትን መቀዳጀት ደግሞ ፈጽሞ የማይታለም ነው፡፡ የዓለም  ባለፀጐች በየዓመቱ በሃብት ላይ ሃብት የሚጨምሩት የሌሎች ድህነት ላይ በማተኮር እኮ አይደለም፡፡ !አሁንም ግን ተስፋ አለን፡፡ የዩኒቨርሳል ህግ የሰዎችን ያለፈ ሃጢያት አይቆጥርም፡፡ ትላንት ምን ክፉ ቢያሰቡ፣ የቱንም ያህል በአሉታዊ ሃሳቦችና ስሜቶች ቢሞሉ፤ ዛሬ በጐ በጐውን ማሰብ ከጀመሩ እንደ አዲስ ቀን ነው የሚቆጠርላቸው፡፡ እናም ያለፈውን ዘመን ያረጀ ያፈጀ ጐጂና አይረቤ ሃሳብ ሁሉ “ዲሊት” አድርጋችሁ በጐና የሰለጠነ ሃሳብ ላይ አተኩሩ፡፡ የአገራችን ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ ማንን ይመስላል ቢሉ? የፖለቲከኞቻችንን ሃሳብ ነው መልሱ፡፡
እባካችሁ ኢህአዴጐችና ተቃዋሚዎች፡- ለአዲሱ ትውልድ (ለልጆቻችሁም ጭምር) ስትሉ በጐ በጐውን አስቡ፡፡ ከምንም በላይ (ከፓርቲያችሁም  ቢሆን) አገርን አስቀድሙ! ጦቢያ ትቅደምልን!  

Read 2885 times