Saturday, 07 June 2014 13:14

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በግብጽ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ላይ ይገኛሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በነገው ዕለት በካይሮ በሚከናወነው የአዲሱ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በዓለ ሲመት ላይ እንደሚገኙ አህራም ኦንላይን ዘገበ፡፡ኢትዮጵያና ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግንኙነታቸው መሻከር ከጀመረ አንድ አመት ያህል እንዳለፈው የጠቀሰው ዘገባው፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ካይሮን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያው እንደሚሆን አስረድቷል፡፡
የቱርኩን የዜና ተቋም አናዶሉ ኒውስ ኤጀንሲን ጠቅሶ አህራም ኦንላይን ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ የግብጽ መንግስት ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ በተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ በሆኑት አል ሲሲ በዓለ ሲመት ላይ እንዲገኝ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት በላከው ግብዣ መሰረት ነው፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተመራ የከፍተኛ ባለስልጣናት ልኡክ በበዓሉ ላይ የሚገኘው፡፡
የከፍተኛ ባለስልጣናቱ በበዓለ ሲመቱ ላይ መገኘት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን እየሻከረ የመጣ ግንኙነት በማሻሻል ረገድ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
የግብጽ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው የምርጫ ውጤት መሰረት፣ የቀድሞው የአገሪቱ የጦር ሚኒስትር አል ሲሲ በምርጫው 96 ነጥብ 9 በመቶ ድምጽ በማግኘት የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን በይፋ በሚረከቡበትና በሄሊፖሊስ በሚገኘው ብሄራዊ ቤተመንግስት በሚከናወነው በዓለ ሲመት ላይ የ22 አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራንና ሩሲያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ለተመራጩ ፕሬዚዳንት የደስታ መልዕክቶቻቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፤ የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ ደጋፊ የሆነው ‘ዘ ናሽናል አሊያንስ ቱ ሰፖርት ሊጂቲሜሲ’ የተባለው ቡድን በበኩሉ፣ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ፣ ህዝቡ በአል ሲሲ መሾም ላይ ያለውን ተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ እንዲገልጽ ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 2735 times