Saturday, 07 June 2014 13:11

የማተሚያ ማሽን መገጣጠሚያ ፋብሪካ በባህርዳር ተከፈተ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(3 votes)

ኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች የራስዋ ብራንድ እንዲኖራት በጋራ እንሰራለን - የጣና ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ

ጣና ኮሙኒኬሽን ከሳምሰንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር፣ በባህር ዳር ከተማ የማተሚያ መሳሪያ (ፕሪንተር) መገጣጠምያ ፋብሪካ የከፈተ ሲሆን በቅርቡም ምርቶቹን ወደ ጎረቤት አገራት ለመላክ መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡
የማተሚያ ማሽን (ፕሪንተር) አካላትን ከዋናው የሳምሰንግ ኩባንያ በማስመጣት፣ የተለያዩ ሞዴል ያላቸውን ማተሚያ ማሽኖች የሚገጣጥመው ፋብሪካው፤ የተሻለ የጥራት ደረጃ ያላቸው የሳምሰንግ ፕሪንተሮችን ከኦሪጂናል የማተሚያ ቀለም ጋር ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡
የጣና ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ስዩም አዳሙ እንደተናገሩት፤ ከሳምሰንግ ኩባንያ ጋር በፈጠሩት ትብብር የጥሬ እቃ አቅርቦትና የባለሞያ እገዛ ያገኙ ሲሆን የተለያየ መጠንና ዋጋ ያላቸው የሳምሰንግ ማተሚያ ማሽኖች (ፕሪንተሮች) በሃገር ውስጥ ተገጣጥመው ለገበያ ሲቀርቡ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው፡፡
ፋብሪካው በደቂቃ 20 ገጾችን ከሚያትመው 20/60 የተባለው ትንሹ ማተሚያ መሳሪያ ጀምሮ የተለያየ መጠን ያላቸው ማተሚያዎችን እየገጣጠመ በሳምሰንግ ብራንድ ለገበያ እንደሚያቀርብ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
“ጣና እና ሳምሰንግ ትብብራቸውን የጀመሩት የማተሚያ መሳሪያዎች አካላትን በመገጣጠም ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ ተወስኖ አይቆምም፤ በሀገሪቱ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ትብብራቸው የሚቀጥል ሲሆን ጣና ኮሙኒኬሽን በሀገር ውስጥ ያሉ ግብዓቶችን በመጠቀም ሁሉንም ማተሚያ አካላት እዚሁ ለመፈብረክ አቅዶ እየሰራ ነው፡፡” ብለዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡  ሳምሰንግ ለምርት ለጥራት ባለው ከፍተኛ ግምት፣ ፋብሪካው በቴክኖሎጂ ምርት የልቀት ማዕከል እንዲሆን የሚሰራ ሲሆን በኤሌክትሮኒክስ ምርቶችም ኢትዮጵያ የራስዋን ብራንድ ፈጥራ ወደአለማቀፍ ገበያ እንድትገባ ትብብሩ ይቀጥላል ተብሏል፡፡ ሳምሰንግ ስማርት ፎኖችን፣ ፍሪጆችን፣ ፍላሾችን፣ ታብሌቶችንና ካሜራዎችን በማምረት በዓለም ላይ ስመገናና ሲሆን ማተምያዎችን (ፕሪንተሮች) በማምረትም በዓለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ፣ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ አቶ ታዲዮስ ሃወል ገልፀዋል፡፡

Read 3008 times