Saturday, 31 May 2014 14:32

ከህፃናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤት የሚሰናበቱ ወጣት አርቲስቶች ቀጣይ ህይወታቸው እንደሚያሳስባቸው ተናገሩ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“ችሎታና ብቃት ካላቸው ወደ ትልልቅ ቴአትር ቤቶች ይገባሉ”

እድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላ ከህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት የሚሰናበቱ ወጣት አርቲስቶች የምንሰናበተው ያለ ሰርተፍኬትና ያለምስጋና በመሆኑ ቀጣይ እጣፈንታችን ያሳስበናል ሲሉ ስጋታቸውን ገለፁ፡፡ “በቅርቡ 50 ያህል በቴአትር ቤቱ ስናገለግል የቆየን ባለሙያዎች ልንሰናበት ቀናት ቀርተውናል” ይላሉ፡፡
የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀጋነሽ አይናለም በበኩላቸው፤ “ህፃናቱ ችሎታና ብቃት ካላቸው ወደ ትልልቅ ቴአትር ቤቶች ይገባሉ፤ በድምፅ፣ በውዝዋዜና በመሰል ዘርፎች ማስታወቂያ ሲወጣ የድጋፍ ደብዳቤ እንፅፍላቸዋለን፤ የትም አይወድቁም” ብለዋል፡፡
“18 ዓመት ሲሞላን ከቴአትር ቤቱ እንደምንለቅ እናውቃለን” ያለው የዛሬ አራት ዓመት በ14 ዓመቱ ቴአትር ቤቱን የተቀላቀለ አንድ ወጣት፤ “ስንሰናበት ግን ቢያንስ ምስጋናና የምስክር ወረቀት እንኳን አለመሰጠቱ በቀጣይ ህይወታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ ይህንን ከእኛ በፊት በተሰናበቱ ወጣቶች ላይ አይተነዋል” ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡
“ቴአትር ቤቱ 18 ዓመት ሞልቷቸው የሚሰናበቱ ወጣቶችን መድረሻ ማዘጋጀት አለበት” ያለው ሌላው ወጣት፤ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በትያትር ቤቱ ውስጥ በድምፃዊነት ሲያገለግል እንደቆየ ጠቁሞ፤ ወጣቶቹ እንደ “ብሄር ብሄረሰቦች”፣ “አባይ”፣ “ላብ ደምን ይተካል”፣ “ምነው ሞት” የተሰኙ በአገር አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ያተረፉ መዝሙሮችን በመዘመር፣ ህብረተሰቡን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው ብሏል፡፡ ሆኖም ሲሰናበቱ በየቲያትር ቤቶቹ እንዲመደቡ አልያም እንደ እድሜያቸው መጠን ሙያቸውን እንዲቀጥሉ የሚደረግበት መንገድ ባለማመቻቸቱ ወጣቶቹ ለስነ-ልቦናና ማህበራዊ ቀውስ መጋለጣቸው እንደማይቀር ከዚህ ቀደም ከተሰናበቱ ወጣት ባለሙያዎች ተሞክሮ አይተነዋል ብሏል፡፡
“ከዚህ ቀደም በጥረታቸው ትልልቅ ቦታ ከደረሱ ጥቂት የቴአትር ቤቱ ወጣቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ የት እንደደረሱ አይታወቅም” ያለው ሌላው የ17 ዓመት ታዳጊ አርቲስት አንዳንዶቹ በተለያዩ ሱስ ውስጥ ወድቀው ሳንቲም ሲለምኑ የምናይበት አጋጣሚ አለ ይላል፡፡
“ስናገለግል የነበረው ለድምፃዊያን 40 ብር፣ ለተወዛዋዥ 20 ብር በወር እየተከፈለን ነው” ያለው ወጣቱ፤ ይህም ቢሆን አሁን ቀርቷል፣ አይከፈለንም ሲል አማሯል፡፡ “ባለን ብቃት፣ በምናሳየው እንቅስቃሴ ተወደን ቆይተናል፤ ይህን በማየት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ደሞዛችን 380 ብር እንዲሆን ከአንድ አመት በፊት ቢወስንም እስካሁን ተፈፃሚ አልሆነም” ብሏል - ወጣቱ፡፡
የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ፤ በብቃታቸው በመደነቅ ለእያንዳንዳቸው 10ሺህ ብር ሽልማት እንዳበረከቱላቸው የገለፁት ወጣቶቹ፤ ይህን በማግኘታችን ኃላፊዎች “እኛ እንሰራለን እናንተ ትጠቀማላችሁ” በማለት ሞራላችንን ጐድተውታል ብለዋል፡፡ “ቴአትር ቤቱ እስከዛሬ በብቃት ስናገለግል የቆየነውን ሙያተኞች ያለምስጋና፣ ያለ ምስክር ወረቀትና ከአመት በፊት የተወሰነልንን ደሞዝ ሳይከፍል፣ እንደሸንኮራ መጥጦ ሊጥለን ስለሆነ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠን እንጠይቃለን” ሲሉ ተማፅነዋል፡፡
ለልማት ሲባል በትምህርት ቀን ሳይቀር እስከ አባይ ድረስ ሄደን በረሀ ሳይበግረን ስናገለግል ቆይተናል የሚሉት ወጣቶቹ፤ ከቴአትር ቤቱ ከወጣን በኋላ የምናርፍበት ቦታ አለመመቻቸቱ ያሳስበናል፤ የተከታዮቻችን ህፃናት ጉዳይም ያሰጋናል ይላሉ፡፡
የቴአትር ቤቱ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀጋነሽ ህፃናቱ ቀድሞውንም ቢሆን በቅጥር ሳይሆን ሙያ እንዲቀስሙ ተመልምለው የሚሰለጥኑ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
“እስካሁን ባለው ተሞክሮም ከህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ወጥተው ትልልቅ ቦታ የደረሱ እንጂ ወድቀው ለመጥፎ ነገር የተጋለጡ አላውቅም” ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ችሎታና ብቃት ካላቸው ወድቀው የሚቀበሩበት ምክንያት እንደሌለና የስራ ማስታወቂያ ሲወጣ የድጋፍ ደብዳቤ እንደሚፃፍላቸውም ተናግረዋል፡፡ ቴአትር ቤቱ እስከ ዛሬም ለትልልቅ ቴአትር ቤቶች ሲመግብ ቆይቷል፤ ቴአትር ቤቶችም ከህፃናትና ወጣቶች ወጥቶ ችሎታና ብቃት ካለው እንደማይጥሉ አብራርተዋል፡፡
በቅርቡ አዲስ መመሪያ እንደወጣ የተናገሩት የወ/ሮ ፀጋነሽ ከዚህ በኋላ ህጻናቱ እንዴት ይተዳደሩ፣ ስራቸው ከትምህርታቸው ጋር እንዴት ይጣጣም፣ ከቤተሰባቸው ጋር እንዴት ግንኙነት ይኑረን እና እንዴት እናንጻቸው” በሚለው ላይ እንደሚያተኩር ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ ለሚሰናበቱትም ሰርተፍኬት ለመስጠት እንደታሰበ ተናግረዋል፡፡
ወጣቶች መዝሙር እንዲያቀርቡ በየመስሪያ ቤቶች ሲጠሩ ከ200-250 ብር በአንደ መድረክ እንደሚከፈላቸው የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ የቀድሞው ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ሊሸልሟቸው ሲያስቡ አሁን ያሉትን ብቻ ሳይሆን በፊት እዚህ የነበሩትንም ፈልገው እንዲሸለሙ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
የወጣው መመሪያ ለተተኪዎቹ ህፃናት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር የገለፁት ወ/ሮ ፀጋነሽ፤ አሁን ከሚሰናበቱት ወጣቶች ለተነሱት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በዳይሬክተርነት የተቀጠሩት በ2006 መስከረም ወር ላይ በመሆኑ እንደሚቸገሩ ገልፀዋል፡፡ “አሁን ስለሚሰናበቱት አብረዋቸው የነበሩትን መጠየቅ ትችላለችሁ፤ በቀጣይ አብሬያቸው ለምዘልቀው ግን በመመሪያው መሰረት በቁርጠኝነት ለመስራትና ህፃናቱን ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ጥረት እያደረግሁ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የወጣቶቹ የቅርብ ኃላፊ፤ የወጣቶቹ ችግር ወደ ቴአትር ቤቱ ሲመጡ ለተጨማሪ ሙያ ሳይሆን ህይወታቸው እዚህ ቴአትር ቤት እንደተመሰረተ አድርገው ማሰባቸው እንደሆነ ገልፀው፣ በጥረታቸው አንድ ነገር ላይ ለመድረስ መጣር እንጂ ብዙ ነገር ከቴአትር ቤቱ መጠበቅ እንደሌለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ቴአትር ቤቱ የአቅም ውስንነት አለበት ያሉት እኚሁ ኃላፊ፤ ደሞዛቸው 380 ብር እንዲሆን ከዓመት በፊት መወሰኑን አምነው፤ ያልተከፈለበት የራሱ የሆነ ምክንያት እንዳለውና መግለፅ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡   

Read 2297 times