Saturday, 31 May 2014 14:13

“አለ በጅምላ” በመገናኛ ሥራ ጀምሯል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ለሁለት ዓመት ተኩል የአሜሪካ ኩባንያ ይመራዋል
“መንግሥት ከንግድ ሥርዓት ውስጥ እጁን ማውጣት አለበት” - የኢኮኖሚ ባለሙያ

     በመንግስት የተቋቋመው “አለ በጅምላ” የንግድ ድርጅት፣ ከመገናኛ ወደ ቦሌ በሚወስደው መንገድ ላይ የመጀመሪያውን የጅምላ ንግድ ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ባለፈው ሰኞ አስመርቋል፡፡ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነውን ይህን የንግድ ማዕከል ለማቋቋም ከሁለት አመት በላይ ጥናት የተደረገ ሲሆን “A.T. Kearney” የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ድርጅቱን የማቋቋምና የማደራጀት ሃላፊነት እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለሁለት አመት ተኩልም ኩባንያው የስራ አመራሩን ሃላፊነት በኮንትራት የወሰደ ሲሆን ኮንትራቱ ሲጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይተኩታል ተብሏል፡፡
“አለ በጅምላ” የንግድ ማዕከል” ደረቅ የምግብ ሸቀጦች፣ የውበትና ንፅህና መጠበቂያዎች እንዲሁም የፅህፈት መሣሪያዎችን በማቅረብ ስራውን የጀመረ ሲሆን ማዕከሉ ማቀዝቀዣዎች ሲሟሉለት አትክልትና ፍራፍሬዎችንም ማቅረብ እንደሚጀምር የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ፤ ገልፀዋል፡፡
የንግድ ማዕከሉ ከግል የጅምላ ንግድ አስመጪዎች ጋር በትብብር እንደሚሠራ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በዋጋ ረገድ አሁን ካሉት የግል አስመጪዎች ከ5 እስከ 15 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖረው ጠቁመው፤ “አትራፊነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶች ለተጠቃሚው እንዲቀርቡ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ዘመናዊ የንግድ አሠራርና መረጃን መሠረት ያደረገ አገልግሎት እንደሚሰጥ የተነገረለት የንግድ ድርጅቱ፤ የማይነጥፍ አስተማማኝ አቅርቦት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ዋነኛ ተልዕኮው የግብይት ስርአቱን ማረጋጋት ቢሆንም በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ ምርቶች በኢትዮጵያ ገበያ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግና በጥናት ላይ የተመሰረቱ ዘመናዊ የንግድ ስርአቶችና አሠራሮችን መፍጠርም የድርጅቱ አላማ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አቅርቦትን በተመለከተ የተጠየቁት ሚኒስትሩ፤ ከሃገር ውስጥና ከውጭ ፋብሪካዎች በቀጥታ ምርቶችን መቀበልን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡ በዚህ እድል ለሚጠቀሙ የሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች፤ የገበያ ትስስሮሽ በተጠናከረ መልኩ ይፈጠርላቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢንተርፕራይዙ በቀጥታ ምርቱን ከፋብሪካዎች መቀበሉ የግብይት ሰንሰለቱን ያሳጥረዋል፤ የግብይት ስርአቱን የሚረብሹ ደላላዎችም ከጨዋታ ውጪ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
“ጅንአድ” የመንግስት ንግድ ድርጅትና አዲስ የተቋቋመው “አለ በጅምላ”፤ ተልዕኳቸው አንድ ቢሆንም አዲሱ ኢንተርፕራይዝ በዘመናዊነት ለመስራት መዘጋጀቱ ለየት እንደሚያደርገው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ጅንአድ አሁን የተሰጡትን ስኳር፣ ዘይትና የመሳሰሉ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ይቀጥላል፤ “አለ በጅምላ” ሲጠናከር ሁለቱ ተቋማት ሊዋሃዱ ይችላሉ ብለዋል፡፡
“አለ”ን የማቋቋም አስፈላጊነትን አስመልክቶ ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ በሀገሪቱ የንግድ ስርአት ዙሪያ ለሁለት አመታት ሲደረግ በቆየው ጥናት፤ የግብይት ስርአቱና የሸቀጦች ዋጋ መልክ የሌለው እንደሆነ መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ጥናቱን መነሻ በማድረግም በዘመናዊ መልኩ ግብይት መፍጠር እንዲቻል በርካታ አማራጮች መቅረባቸውን ያወሳሉ፡፡ እንደ ዎል ማርት አይነት ድርጅቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው እንዲሠሩ መፍቀድ የሚለውን ጨምሮ፣ የዎል ማርት አይነት ድርጅት ማቋቋም የሚሉ ሃሳቦች ቀርበው እንደነበር የጠቆሙት ሚ/ሩ፤ “መንግስት የዎል ማርት አይነት ስራ ሊሠራ የሚችል ኢንተርፕራይዝ መክፈት የሚለውን ሃሳብ ተቀብሎ እውን አድርጓል” ብለዋል።
ዎል ማርት በቀጥታ ወደ ሃገር ውስጥ ቢገባ ኖሮ፣ በታዳጊ ደረጃ ያለውን የሃገሪቱን ነጋዴ ሊጐዳ እንደሚችልና ከትርፍ የሚገኘው ገንዘብ ወደ ውጭ ፈሰስ እንደሚሆን ያስረዱት ሚኒስትሩ፤ መንግስት የገበያ ጉድለት ባለበት ሁሉ የመግባት ሃላፊነት ስላለበት፣ የግሉን ዘርፍ በማይጐዳና ተወዳዳሪነቱን በማያቀጭጭ መልኩ፣ ይህን ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ ወደ ገበያው መግባት የሚለውን እንደ አማራጭ መውሰዱን ገልፀዋል፡፡
ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር የሆነው “አለ በጅምላ”፤ የሰው ሃይሉን ለማጠናከር አለማቀፍ ልምድ ያላቸውን ዳያስፖራዎች ጨምሮ ከ150 በላይ በዘርፉ ልምድና እውቀት ያላቸው የስራ አመራርና የግብይት ባለሙያዎችን እንደቀጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥም ከፍተኛ የህዝብ ክምችት አለባቸው ተብለው በተለዩ 27 የክልል ከተሞች ውስጥ ወደ 36 የሚደርሱ የማከፋፈያ ማዕከላት እንደሚከፈቱ ተጠቁሟል፡፡
ሰሞኑን መገናኛ አካባቢ ተመርቆ ስራ ከጀመረው የንግድ ማዕከል በተጨማሪ በቅርቡ ቃሊቲና መርካቶ ቢስ መብራት አጠገብ ሁለት ማዕከላት ተከፍተው ስራ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡  
በአለማቀፍ የኢኮኖሚ ተቋም ውስጥ በሃላፊነት የሚሰሩ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት፤ ለዘመናት የሃገሪቱን የጅምላ ንግድ ሲመራ የቆየው ጅንአድ፤ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ አለመፍጠሩን ጠቅሰው፤ ያሁኑም ተቋም የተለየ ተፅዕኖ አይፈጥርም ብለዋል፡፡ “መንግስት ከንግድ ስርአት ውስጥ እጁን ማውጣት አለበት” ያሉት ባለሙያው፤ ማዕከሉ በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ብቻ አተኩሮ ለመስራት መፈለጉ የግል ነጋዴዎችን እምብዛም ላይጎዳ ይችላል፤ ነገር ግን መንግስት በሂደት የጅምላ ንግድ ስርአቱን ሙሉ በሙሉ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች መተው እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
“በተለይ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በብዛት ወደ ጅምላ ንግድ ስርአቱ ገብተው ተወዳዳሪነትን መፍጠር እንዲችሉ መንግሥት ማገዝ ይኖርበታል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ እኔም እንደባለሙያ፣ የጅምላ ንግድ ስርአቱ በጥቂቶች መያዙን እረዳለሁ ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ “የመንግስት በጅምላ ንግድ ስርአት ውስጥ መግባት በሃገሪቱ የንግድ ተወዳዳሪነት ደካማ መሆኑን ያመለክታል”፤ በማለት ተወዳዳሪነት መፈጠር እንዳለበትና መንግስትም ለዚህ ምቹ መደላድሎችንና የፖሊሲ አማራጮችን መፈተሽ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ 

Read 5070 times