Saturday, 31 May 2014 14:10

ኤክስፖርት ንግዱ ዘንድሮም አልተሳካለትም

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

          ቡና፣ ዛሬም የውጪ ንግድ ዘርፉን ገቢ ይመራል። በዚህ ሳምንት አጋማሽ የንግድ ሚ/ር ሚኒስትር ክቡር አቶ ከበደ ጫኔ፤ የመ/ቤታቸውን የዘንድሮ ዓመት የ10 ወራት ዕቅድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሲያቀርቡ፣ ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ በገቢ ከፍተኛ ድርሻ የያዘውን የቡና የወጪ ንግድ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ የድጋፍ ክትትልና ቁጥጥር ተግባራት ለማጠናከር በቡድን ደረጃ የነበረውን አደረጃጀት ወደ ዳይሮክተሬት ደረጃ ማሳደጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ክትትልና ድጋፍን አስመልክቶ ሚ/ሩ እንደገለጹት፤ ባለፉት 10 ወራት 206,825 ቶን ቡና በመላክ፣ 822.08 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 136ሺ (65.8%) ቶን ቡና በመላክ፣ 489.28  (53.3%) ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል፡፡ ይህ አኀዝ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ለዚህም ምክንያቱን ሲገልጹ፣ የሚፈለገው የቡና መጠን ወደገበያ ባለመቅረቡ፣ በቡና ዋጋ መዋዠቅ የተነሳ የሚጠበቀውን ያህል ቡና ባለመላኩ፣ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ፈጻሚ ቅንጅታዊ አሠራር በመጓደሉ፣ በነባርና በአዳዲስ ገበያዎች ሰብሮ ለመግባት በቂ የገበያ ማስፋፊያ ባለመሠራቱ፣ የኤክስፖርት ቡና በሕገወጥ መንገድ በሀገር ውስጥና ወደ ጐረቤት አገር በመውጣቱና ይህንንም የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል የተደረጉ ጥረቶች ውሱን በመሆናቸው እንደሆነ ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ እየተሻሻለ በመምጣቱ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት የሚቻልበት አዝማሚያ መኖሩን አመልክተዋል፡፡
ባለፉት 10 ወራት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል፣ የእርሻ ምርቶች የሆኑትን  ቡና፣ ሰሊጥ፣ ነጭ ቦሎቄ 515,827 ቶን ማገበያየታቸውን የገለፁት ሚ/ሩ፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 43,961 (9%) ሜትሪክ ቶን ዕድገት ማሳየቱን፣ 519,152 ሜትሪክ ቶን ቡና፣ ሰሊጥ፣ ነጭ ቦሎቄና ማሾ ወደ ምርት ገበያው መጋዘኖች ማስገባታቸውንና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 45,945 (10%) ሜትሪክ ቶን ጭማሪ እንዳሳየ ጠቁመዋል፡፡
ሚ/ሩ በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ምርቶቻቸውን በብዛትና በጥራት አምርተው ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን ገልፀው፤ ባለፉት 10 ወራት ከግብርና ምርቶች፣ ከማኑፋክቸሪንግና ከማዕድን ዘርፎች በአጠቃላይ 4.25 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 2.61 ቢሊዮን ወይም የዕቅዱ 67.39% መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ይህ አኅዝ ከዕቅድ በታች ቢሆንም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 2.49 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር፣ በ120.11 ሚሊዮን ዶላር ወይም (4.82%) ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡
መ/ቤታቸው ክትትል የሚያደርግባቸው የግብርና ምርቶች የኤክስፖርት አፈጻጸም በተመለከተ፣ ባለፉት 10 ወራት 1.16 ሚሊዮን ቶን የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ 2.026 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ነበር። ነገር ግን 776,006 ቶን ወይም የዕቅዱን 67% ቶን የተለያዩ ሰብሎችን ለዓለም ገበያ አቅርቦ 1.54 ቢሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 76% ገቢ አግኝቷል፡፡
947,557 የቁም እንስሳትን ለዓለም ገበያ በማቅረብም 223.71  ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 515, 140 ወይም የዕቅዱን 54.37% የቁም እንስሳት በማቅረብ፣ 164.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 73.4% ገቢ አግኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የሰብል ምርቶችና የቁም እንስሳት ለዓለም ገበያ አቅርቦ፣ 2.24 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 1.71 ቢሊዮን ዶላር ወይም 76.34% ገቢ ተገኝቷል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የሰብል ምርቶች መጠን 0.8 በገቢ ደግሞ 22% ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል፤ በቁም እንስሳት በመጠን 11.24% ሲቀንስ በገቢ ደግሞ በ15.68% ጨምሯል፡፡ በአጠቃላይ የንግድ ሚ/ር ክትትል በሚያደረግባቸው የግብርና ምርቶች፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በገቢ 10.8% ጭማሪ ተመዝግቧል፡፡
ከኤክስፖርት ክትትልና ድጋፍ አንፃር የቅባት እህሎች ምርት ባለፉት 10 ወራት 335,958 ቶን የቅባት እህሎች ለማቅረብ ታቅዶ፣ 226,640 ወይም የዕቅዱ 67% ግዢ ተፈጽሟል፡፡ 222,727 ቶን ሰሊጥ ለምርት ገበያ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር (70%) ብቻ ተሳክቷል፡፡ ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ ያልተሳካው አምራች አርሶአደሮች፣ ባለሀብቶችና አቅራቢዎች ምርትን በወቅቱ ለገበያ ባለማውጣታቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የአቅርቦት መጠኑ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 163,160.73 ሰሊጥ ጋር ሲነፃፀር የ36.51% ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከጥራጥሬ ምርት፣ ክትትልና ድጋፍ አንፃር 66,605 ቶን ነጭ ቦሎቄ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲቀርብ ታቅዶ፣ 59,028.6 ቶን ወይም የዕቅዱ 88.6% ቀርቧል፡፡
ባለፉት 10 ወራት 41,054.9 ቶን ጫት በመላክ፣ 235.4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 39,970.8 ቶን ወይም የዕቅዱን 92.5% በመላክ፣ 216.8 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 92.1% ገቢ ተገኝቷል። በበጀት ዓመቱ 10 ወራት 920,173 የቁም እንስሳት በመላክ፣ 242.58 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የተሳካው የዕቅዱን 60 በመቶ፣ 548,664 የቁም ከእንስሳት በመላክ 163.916 ሚሊዮን ዶላር ወይም የእቅዱ 67.6% ገቢ ተገኝቷል፡፡ በሀገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች ከሚገኙ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች 23,262,022 ጥሬ ቆዳና ሌጦ ለተለያዩ ፋብሪካዎች ለማቅረብ ታቅዶ፣ ማሳካት የተቻለው 16,109,240 ወይም የእቅዱ 69.25% ብቻ ነው፡፡
ንግድ ሚ/ር ባቀረበው የ10 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፤ ከእቅድ በላይ የላቀ አፈጻጸም የታየው በአዲስ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ነው። 202,236 አዲስ የንግድ ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 208,728 መስጠቱን ሚ/ር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡ እንዲሁም 176,581 አዲስ የንግድ ምዝገባ ለማካሄድ ታቅዶ 157,803 ምዝገባ መካሄዱን፣ 840,991 የንግድ እድሳት ለማካሄድ ታቅዶ 731,665 መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
ሌላው የሚ/ሩ ከፍተኛ ስኬት የንግድ ስም ማጣሪያ ክንውን ነው፡፡ 21ሺ የንግድ ስም ለማጣራት ታቅዶ 53,210 የዕቅዱ ማከናወን ተችሏል፡፡ የዚህ ስኬት ምክንያት ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ጨምሮ ወደ ንግድ ሥርዓቱ የሚገባው ማኅበረሰብ ቁጥር በመጨመሩ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት 10 ወራት ለተጠቃሚው የስንዴ ዳቦ እንዲቀርብ፣ ለክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሚሆን 5.73 ሚሊዮን ኩንታል ጥሬ ስንዴ፣ ለዱቄት ፋብሪካዎችና ዳቦ ቤቶች ቢቀርብም ፍላጐትና አቅርቦት አልተመጣጠኑም፡፡ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በእህል ንግድ ድርጅት በኩል ስንዴ ከአገር ውስጥ 150ሺ ኩንታል ቢገዛም የስንዴ ፍሰትና አቅርቦት በቂ ባለመሆኑና የስንዴ ዋጋ እየጨመረ በመሄዱ፣ ግዢው በተፈለገው መጠን ሊሳካ እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ መንግሥት 400ሺ ቶን ስንዴ ከውጭ እንዲገዛ በወሰነው መሠረት ግዢው ተፈጽሞ ስንዴው በሐምሌ ወር እንደሚገባ ታውቋል፡፡ የሸቀጦችን ገበያ ለማረጋጋት ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችንና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችን ከውጭና ከአገር ውስጥ አምራቾች ግዢ መፈፀሙን የጠቀሱት ሚ/ሩ፤ ከዚህ ወር ጀምሮ በአዲስ አበባ በሦስት ክፍለ ከተሞች ለመክፈት ካቀዳቸው መጋዘኖች ውስጥ የመጀመሪያውን መገናኛ አካባቢ ከአምቼ የመኪና መገጣጠሚያ ፊት ለፊት “አለ በጅምላ” የጅምላ ንግድ ሸቀጦች መደብር መከፈቱን ገልፀዋል። በክልል ከተሞችም ተመሳሳይ ሥራ ለመጀመር በቀጣይ 3 ዓመታት በ27 ከተሞች 36 መደብሮች ለመክፈት የቅድመ ጥናት ዝግጅት መጀመሩን ሚኒስትሩ ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡
የንግድ ዘርፉን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ከመ/ቤታቸው ሠራተኞችና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ማከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡ በፌዴራል፣ በክልል መስተዳድሮችና በከተማ አስተዳደሮች፣ በንግዱ ዘርፍ አመራርና ፈጻሚ እንዲሁም በንግዱ ኅብረተሰብ ዘንድ በንግድ አሠራርና ውድድር ላይ የጠራ ግንዛቤ አለመኖር፣ የመፈፀም አቅም ውሱንነት፣ ቅንጅታዊ አሠራር ያለመዳበርና ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች በወቅቱ መታየታቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሠሩባቸው አመልክተዋል፡፡
ንግድ ሚ/ር በበጀት ዓመቱ ለመደበኛ ወጪዎች ብር 63.23 ሚሊዮን፣ ለካፒታል በጀት 31,645,832 ብር እንደመደበለት ጠቅሶ፣ ባለፉት 10 ወራት ከመደበኛ በጀት ብር 41.96  ሚሊዮን፣ ከካፒታል በጀት ብር 13.83 ሚሊዮን ወጪ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ከንግድ አሠራር ቋሚ ኮሚቴና ከም/ቤቱ አባላት በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው ሚ/ር ዴኤታው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ቋሚ ኮሚቴው፣ ለውጪ ንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል እንዲሰጠው አሳስቧል፡፡   

Read 2181 times