Saturday, 31 May 2014 14:02

ገፅ ለገፅ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

ተፋጠጥ፤ ተገላለጥ፣ ተሞራረድ፣ ችግር ፍታ!

          ባለፈው ሳምንት የጀመርኩት የደብረዘይት ገፅ ለገፅ (Interface meeting) ዛሬም ቀጥሏል። ህዝብና መንግስት ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሚወያይበትና መሬት ላይ ላሉ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥበት በጣም ያስገረመኝ ውይይት ነው ብዬ ነበር፤ ባለፈው ሳምንት ጉዞ ማስታወሻዬ ላይ፡፡ ፕሮግራሙን የሚመሩት  
አቶ ግርማ ከበደ ለ16 ዓመት የማኔጅመንት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ የነበሩ ሲሆኑ፤ ቆመው ሲናገሩ ቆይተው በኋላ ወንበር ይገባኛል ብለው ውይይቱን ተቀምጠው ሊመሩ ተሰየሙ፡፡ (ሁላችንንም ፈገግ አሰኙን) የእየሩሳሌ የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢህማልድ) (የጄክዶ) የፕሮግራም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ገፅ ለገፅ የመንግሥት የሪፎርም አጀንዳ መሆኑን ገለጡ፡፡ በዚህ ጉዳይ ኢህማልድ (ጄክዶ) ከፍተኛ ልምድ እንዳለው አብራሩ፡፡
በባህር ዳር መሰል ፕሮግራም መካሄዱንና በድሬደዋ፣ ከዚያም በአጄ ሻሸመኔ እንደሚካሄድ ገለፁ፡፡ የዕለቱን ጥናታዊ ማብራሪያ የሰጡት፤ አቶ ብርሃኑ ሰቦቃ ስለማህበራዊ ተጠያቂነት ፅንሰ-ሃሳብ እንደሚገልፁም አሳወቁ፡፡
አቶ ብርሃኑ ሰቦቃ የቢሾፍቱ ተሰብሳቢ ኦሮሚፋ ተናጋሪ ነው በሚል እሳቤ ይመስለኛል፤ “አርካፉኔ” በሚል ጀመሩና ቆይተው ይቅርታ ጠይቀው በአማርኛ ተያያዙት፡፡ “ሆኖም ያዘጋጀሁት በእንግሊዝኛ ነው” ብለው ቀጠሉ። ዛሬ፤ ትንሽ አዝናኑኝ፡፡ ኦሮሚፋ፣ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ ዞሮ ዞሮ የምሁራን የጥናት ቋንቋ ናቸው፡፡
“የማህበረሰብ ተጠያቂነት ምንድነው? ለምንስ ይጠቅማል? የሚል ነው ነገሬ፡፡ በቀላሉ ስናየው ስልጣን በእጃቸው ያለ አካላት ለህዝቡ ለሚሰጡት አገልግሎት ተጠያቂ የሚሆኑበትና ምላሽ የሚሰጡበትን ኃላፊነት የሚያስቀይር ነገር ነው፡፡
ስለዚህም የህዝቡን ተሳትፎ የሚያሳይ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ መብቱን የመጠየቅና ግዴታውን የመወጣት ነገርን ያካተተ ነው ማለት ነው፡፡
በዲሞክራቲክ አሠራር ለመሄድ የህገ መንግሥት አንቀጽ 12፤ መሠረቱ ይሄ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ “የመንግሥት አሠራር በሙሉ ግልፅ ይሆናል፡፡ ጥሩ የሰራ ሊሸለም፣ መጥፎ ቢሰራ ሊጠየቅ ይገባዋል” ነው የሚለው መንፈሱ፡፡ ‹አንቀፅ 50 ላይ ደግሞ፤ አተገባበሩ ወደ ህዝቦች እንዲሆን ይደረጋል› ይላል፡፡ እነዚህን ወደመሬት ለማውረድ የተለያዩ ህጐች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች ወጥተዋል፡፡”
ይህንን መመርመር ነው እንግዲህ - የዚህ ስብሰባ ዋና ደርዝ፡፡
ሥራዎች ሲሰሩ በቅድሚያ ሰዎች አብረዋቸው መቀጠር አለባቸው፡፡ አለዛ ሥራ አይሠራም፡፡ አዕምሮን የማቃናት ፕሮግራም ያስፈልጋል፡፡ 10 ዓመቱ ነው ሲቪል ሰርቪስ ፕሮግራም! ከተጀመረ
ለተገልጋዩ ቀና አገልግሎት መስጠት ነው ሲቪል ሰርቪስ፡፡ ይሄን ሁሉ ግን መንግሥት ነው እየተቆጣጠረ ያለው፡፡ ህዝቡስ እንዴት ነው? ነው ጥያቄው፡፡ የተጠያቂነት ሁኔታ ለ18 ወራት ፓይለት (የፕሮጀክት ሙከራ) የነበረው እዚህጋ ይመጣል፡፡
ጥሩ ተሞክሮ ነበር፡፡ ተሞክሮውን ትመርጡታላችሁ? ተብሎ ነበር በ2008ቱ የኢሲኤ ስብሰባ የቀረበው፡፡ “የት ሄዳችሁ ነው ተሞክሮውን ማየት የምትፈልጉት?” ተባሉ ተሰብሳቢዎቹ፡፡ ግማሹ ካናዳ፣ ግማሹ አሜሪካ፣ ሌላው እንግሊዝ አለ፡፡ የፕሮግራም መሪዋ፤
“ግዴላችሁም እዚሁ አለ፡፡ እሩቅ አትሄዱም፡፡ ሻሸመኔ ሂዱ!” ነው ያለቻቸው፡፡
17 ዓመት ሙሉ የተተኛበት የትምህርት ለውጥ በ2 ዓመት ውስጥ ውጤቱ ታየ፡፡
የማህበራዊ ተጠያቂነት ጉዳይ፤ ውጤታማ፣ ፈጣን፣ ተጠያቂነት ያለበት አገልግሎት ለህዝቡ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር አካል መሆኑን ነው ይሄ የሚያሳየው፡፡”
በአቶ ብርሃኑ ሰቦቃ በቀረበው ትንተና መሠረት፤ መላ ጨመቁ (essence) በሚከተሉት 5 ነጥቦች ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡
1) መሬት ላይ ያለውን ነገር አንስቶ መወያየት ማለትም ችግሩን ለመፍታት ተሳታፊነት 2) ምላሽ መስጠት 3) ግልፅነት፤ ለምሳሌ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ወዘተ የተመደበውን ባጀት ማሳወቅ፣ የሚታይ ቦታ መለጠፍ 4) ተጠያቂነት 5) ውጤታማና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት ማግኘት፡፡ ምሁሩ ነጥቦቹ የሚሰጡትን ውጤቶች ሲነቁጥ እነዚህን አምስት ፍሬ ጉዳዮች ህዝብና መንግስት አንድ ላይ ሆኖ ከተወያየባቸው፣ ከተፋጠጠባቸው፣ ከተሞራረደባቸውና ወደ ተግባራዊ መፍትሄ ከተሸጋገረባቸው፤ ሀ) ህዝብና መንግስት አንድ ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ ድህነትን ለማስወገድም ይቆራኛሉ ለ) መረጃ ለሁሉም ይዳረሳል ሐ) ህዝብን ማብቃት (empower ማድረግ) ይቻላል፤ መ) ግልፅነትና ተጠያቂነት ወደ ልማት ያመራል፡፡

የትምህርት ነገር
ሌላው በከፍተኛ ደረጃ ለውይይት የቀረበው ጉዳይ “በትምህርት በኩል ያለው ችግር ምንድን ነው” የሚለው ነው፡፡ “የተማሪዎች የማንበብ ባህል መዳከምና የትምህርት ውጤታቸው በዚያው መጠን መጓተቱ ነው” የሚል ድምዳሜም ቀርቧል። Readers are great leaders (አንባቢዎች ታላላቅ መሪዎች ይሆናሉ እንደማለት ነው)
“የትምህርት ውጤትን በተመለከተ በተለይ ቋንቋና ሂሳብ ላይ ዝቅተኛ እርካታ ነው ያለው፤ ተብሏል፡፡ Transition rate (የማለፍ ዕድል መጠኑ ግን ጥሩ ነው፡፡) ከ8ኛ ወደ 9ኛ ማለት ነው። ትምህርት ሚኒስቴር 50 እና ከዚያ በላይ አቬሬጅ ያመጣ ነው የሚያልፈው እሚለውን ልብ አርጉ። ያንን አምጥቶ አደለም ያለፈው፡፡ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማለፊያ ሲቃረብ ወገቤን ሊል ይችላል። ብሾፍቱ እንደብሾፍቱ በትምህርት ዙሪያችን ካሬ አለው ግን የበለጠ መሠራት አለበት፡፡ በተለይ ከላይ ብራሪ፣ ከንባብ አጋዥ ማቴሪያሎችና ከመፃህፍት አኳያ መጠናከር አለበት፡፡ 1ኛ ደረጃ የብሾፍቱ የትምህርት ችግር የመፃህፍት ቤት አገልግሎት ነው፡፡ 2ኛ ደረጃ ጥራት ያለው መፃህፍት ዕጥረት ነው፡፡ 3ኛ ደረጃ ያስቀመጠው የሳይንስ ላቦራቶሪ እጥረትና የማቴሪያልም አለመኖር ነው፡፡ ስለዚህ የመማር አግባብ ተጎድቷል፡፡”
የጋራው ውይይት ሲቀጥል ችግር ብቻ ሳይሆን መፍትሔም መነሳቱ ደስ ይላል፡፡ በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታ እንዲህ በግልፅ ገፅ በገፅ ነገሮች ቢነሱ እንዴት መልካም ነበር አልኩኝ፡፡ አንዱ አንዱ ላይ ጣት መጠቆም አይደለም፡፡ ችግሩን በጋራ አንስተን በጋራ ኃላፊነታችንን እንዴት እንወጣ የሚል መንፈስ እንዳለው” የፕሮግራም መሪው ገለፁ፡፡

የውሃ ነገር
የውሃ ችግርን በተመለከተ ሪዘርቯየር መተከል አለበት፡፡ በትምህርት ቤት ረገድ ከባለ ሀብቶችም ጋር ተወያይቶ የገንዘብ ማሰባሰብ መፍትሔ ይደረግ፡፡ በት/ቤት ቅፅር ስላሉ የመኖሪያ ቤቶች መንገድ ቢፈለግ፣ ከንቲባችንም እዚህ ስላሉ፣ መፍትሄ እንሻለት፡፡ በውሃ አለመኖር ምክንያት በትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የፅዳት ችግር አለ፡፡ መልካም አስተዳደር ቃሉ ብቻ ሳይሆን ተግባሩም መኖር አለበት፡፡ የውሃ ችግር… የውሃ ችግር… (ብዙ ተወሳ፡፡) የቆሻሻ አንሺ መኪናን ችግር ለመፍታት የባለሀብቶች ተሳትፎ ምን መሆን አለበት?... የትምህርት ቤት ጉዳይ ላይ ከእኛስ ምን ይጠበቃል? የሚል መልዕክት ተላለፈ፡፡ ባለመብቶቹ አገልግሎት ተቀባዮች ናቸው መነሻችንም እነሱ ናቸው አሉ አቶ ብርሃኑ፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች Defense አይደለም የምታካሂዱት፡፡ ይሄን ለመፍታት ምን ዝግጅት እያደረግን ነው፣ ካላደረግንስ በጋራ ምን ማድረግ አለብን? ወደሚል ነው መሄድ ያለብን፡፡ እየተገመገሙ ያሉት አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው! ሀሳብ በነፃ እናንሸራሽር፡፡ አንዱ ጠያቂ አንዱ መላሽ መሆን የለበትም አሉ የፕሮግራም መሪው፡፡ ቀጥሎ ከመንግስት ወገን ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች መናገር ጀመሩ፡፡ “አገልግሎት ሰጪው ምን እያደረገ ነው ህዝቡስ ምን ምላሽ እየሰጠ ነው እንድንባባል መቻላችን ትልቅ ነገር ነው” ብለው ጀመሩ፡፡
ይቀጥላል


Read 1693 times