Saturday, 31 May 2014 14:00

የአፍታ ቆይታ ከዳንኤል ክብረት ጋር

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(14 votes)

“በጐ ሰዎችን በመሸለምና በማክበር ሌሎች በጐ ሰሪዎችን እንፍጠር” በሚል ዓላማ በሀገራችን በጐ የሠሩትን የማመስገን ባህልን ለማበረታታት፣ ሀገራዊ አርአያዎችን ለመፍጠርና ለጀግኖቻችንም ዕውቅና የመስጠት  ልማድን ለማጐልበት በሚል የተጀመረው “የበጐ ሰው ሽልማት” የዘንድሮ ተሸላሚዎችን ግንቦት 30 እንደሚያሳውቅ ኮሚቴው ገለፀ፡፡
የ“በጐ ሰው ሽልማት” ዙር ሥነስርዓት በኢሊሌ ሆቴል እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡ የዘንድሮው ሽልማት በሰባት ዘርፎች የሚሰጥ ሲሆን በሰላም፣ በሀገራዊ ዕርቅና ማህበራዊ አገልግሎት፣ በእርዳታና ሰብዓዊ ሥራ፣ በኪነ ጥበብ፣ በግብርናና ኢንዱስትሪ፣ በመንግስታዊ የሥራ ተቋማት ኃላፊነት፣ በቅርስ፣ ባህልና ቱሪዝም፣ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዘርፎች ከመቶ በላይ እጩዎች ቀርበው፣ 35 እጩዎች ተመርጠዋል፡፡
በየዘርፉ በተመደቡ ዳኞችም ሰባቱ የሽልማቱ አሸናፊዎች ይለያሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በሽልማቱና አጠቃላይ እንቅስቃሴው ዙሪያ ከሽልማት ኮሚቴው ሰብሳቢ ከደራሲ ዳንኤል ክብረት ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጋለች፡፡


“የበጐ ሰው ሽልማት” እንዴት ነው የተጀመረው?
“የበጐ ሰው ሽልማት” የተጀመረው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነው፡፡ ምክንያት የሆነው ደግሞ “የዳንኤል እይታዎች ጦማር” ሲከበር የነበረው ኮሚቴ፣ “ለአገር በጐ የሠሩ ሰዎችንስ ለምን አንሸልምም?” የሚል ሃሳብ በማንሳቱ ነው፡፡ እናም አምና በ2005 አምስት ሰዎች ከተለያዩ ዘርፎች ተሸለሙ፡፡ እነዚያ ሰዎች መሸለማቸው በብዙዎች ዘንድ መነቃቃትን ፈጠረ፡፡ እሱን መሰረት አድርጐ ኮሚቴው በተጠናከረ ሁኔታ ከጦማር ውጪ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ተደረገ፡፡ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የሽልማት ሥነስርዓቱን የሚያካሂደው፡፡
የዳንኤል እይታዎች ጦማርና “የበጐ ሰው ሽልማት” የሚያገናኛቸው ነገር አለ?
የሚያገናኛቸው በምክንያትነት ያስጀመረው የጦማሩ በዓል በመሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የተለያዩ አንባቢያን ለእጩዎች ድምፅ እንዲሰጡ ቅስቀሳ የተደረገው በጦማሩ ነው፡፡ በእርግጥ በማህበራዊ ድረ ገፆች፣ በኤፍኤም የሬዲዮ ጣቢያዎችና በህትመት ውጤቶችም ተካሂዷል፡፡ ከዚህ በቀር ግን ሁለቱን የማያገናኛቸው ነገር የለም፡፡
የ2005 “የዓመቱ በጐ ሰው” ተሸላሚዎች እነማን ነበሩ?
አምስት ናቸው፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን መዓዛ ብሩ ስትሸለም፣ በእርዳታና ሰብዓዊ ስራ ቢኒያም፣ (የመቆዶኒያው  ስራ አስኪያጅ) ተሸልሟል፡፡ ንባብን በማበረታታትና በተለይ መጽሐፍ ገዝተው ማንበብ የማይችሉ ሰዎች በቀላሉ ማንበብ የሚችሉበትን መንገድ በመፍጠሩ፣ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በኪነጥበብ ዘርፍ ሊሸለም በቅቷል፡፡ አዲስ የንግድ አሰራር ዘዴን በመቀየስና በመምራት ዶ/ር እሌኒ      ገ/መድህን፣ የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል፣ እንዲሁም ጥንታዊ ቅርሶች በመጠበቅ በሰሩት ስራ ደግሞ ንዑረድ ተፈራ መልሴ ተሸልመዋል፡፡
ሽልማቱ የመንግስት ባለስልጣናትንና ፖለቲከኞችን ያካትታል?
ሽልማቱ እስከ አሁን ባለስልጣናትንና ፖለቲከኞችን አላካተተም፡፡ ግን በመንግስት ስራ ላይ ተመድበው ያከናወኗቸውን ሥራዎችና የተሰጣቸውን ሃላፊነት ምን ያህል ተወጥተዋል የሚለውን በማየት፣ ማህበረሰቡን ያገለገሉ ሰዎች የሚሸለሙበት ዘርፍ አለ፡፡
የባለፈው ሽልማት ምን ነበር? የዘንድሮስ? የገንዘብ ምንጫችሁ ምንድነው?
ዓምና “የበጐ ሰው ዓመታዊ ሽልማት” የሚል ሰርተፍኬት ነበር የሰጠነው፡፡ ዘንድሮ ግን ራሱን የቻለ ሽልማት ተዘጋጅቶለታል፡፡ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ናቸው የበጐ ሰው ሽልማት የሚል እንደ ኦስካር ዓይነት ሽልማት በራሳቸው ዲዛይን ሰርተው ያዘጋጁት፡፡ እስከ አሁን ድረስ ስራውን እየሰራን የነበረው የኮሚቴው አባላት በምናዋጣው ገንዘብ ነው፡፡ አሁን ግን ዳሽን ቢራ ሥራችንን እንደሚደግፈን ቃል ገብቶ ከእኛ ጋር እየሰራ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሽልማቶች የአንድ ጊዜ ዜና ብቻ ሆነው ይቀራሉ፣ ቀጣይነቱ ታስቦበታል?
አዎ!! በቀጣይ “የበጐ ሰው ሽልማት” የበጐ አድራጐት ድርጅት ፈቃድ አውጥቶ፣ ራሱን ችሎ እንዲቀጥል ለማድረግ አስበናል፡፡ አምና በጠባቡ ሰራነው፤ ዘንድሮ ከፍ አደረግነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ አገር አቀፍ ሆኖ የሚካሄድበትን መንገድ እያጠናን ነው፡፡
የ2006 “የበጐ ሰው ሽልማት” እጩዎች
በኪነጥበብ ዘርፍ
ሙላቱ አስታጥቄ፣
ተስፋዬ አበበ
አባባ ተስፋዬ ሳሕሉ
ይልማ ሀብተየስ
ታደሰ መስፍን
በማኅበራዊ አገልግሎት
ዶ/ር አበበ በጂጋ
ዶ/ር ሚናስ ኅሩይ
ቄስ አሰፋ ሰጠኝ (ትግራይ)
ብጹዕ አቡነ ዮናስ (አፋር)
ደበበ ኃይለ ገብርኤል
በእርዳታና ሰብአዊ ሥራ
ዶ/ር ተዋበች ቢሻው
ዶ/ር በላይ አበጋዝ
ወ/ት ሮማን መስፍን
ሲ/ር ዘቢደር ዘውዴ
ወ/ሮ አበበች ጐበና
በግብርና፣ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕርነርሺፕ
ቤተልሔም ጥላሁን
ዶ/ር ኢንጂነር ዳንኤል ቅጣው
ዶ/ር ወሬታው በዛብህ
አሶሴሽን ኦፍ ውሜን ኢን ቢዝነስ
ካፒቴን ሰሎሞን ግዛው
መንግሥታዊ ኃላፊነትን በመወጣት
አምባሳደር ቆንጅት ሥነ ጊዮርጊስ
ኢንጅነር ስመኘው በቀለ
አቶ በድሉ አሰፋ
አቶ ይርጋ ታደሰ
አቶ አድማሱ ታደሰ
በቅርስ፣ ባሕልና ቱሪዝም
አቶ ዓለሙ አጋ
አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ
ሼህ አብዱላሂ ሸሪፍ
ዶ/ር ዘረ ሠናይ ዓለም ሰገድ
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር
በጥናትና ምርምር ዘርፍ
አምባሳደር ዘውዴ ረታ
ፕ/ር አሠራት ኃይሉ
ፕ/ር ዓለም ፀሐይ መኮንን

Read 4755 times