Saturday, 31 May 2014 13:59

‘የጎንዮሽ ጣጣ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

ማስታወቂያዎች ከመተላለፋቸው በፊት “ብታምኑም ባታምኑም” ተብሎ ይፃፍልን

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… ሀዲዱን እየነቀሉት ነው የሚባለው እውነት ነው እንዴ? ለነገሩ መገረም ስለተውን “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም…” ምናምን አይነት ተረት ትተናል፡፡ አሀ፣ ልክ ነዋ… አምናና ካቻምና “ጉድ!” ያሰኙ የነበሩ ነገሮች ዘንድሮ ልዩ መለያዎቻችን (“ከአፍሪካ ቀዳሚ…” ምናምን የሚባለው አይነት) እየሆኑ ነዋ!
ይሄ የዓለም ዋንጫ መጥቶ ለጥቂት ሳምንታት ለ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲያኖች’ ብቻ የሚሆኑ ዜናዎች ከመስማት ትንሽ ተንፈስ ባደረገን! እኔ የምለው…ይሄ የኳስ ፍቅር ነገር…ይቺን ስሙኝማ…
የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ ነው፡፡ ያው እንግዲህ ትኬቶች የወንበር ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ አንዱ የተከዘ ሰውዬ ከተቀመጠበት ጎን ያለ ወንበር ባዶ ነው፡፡ በወዲያኛው ወገን ያለው ተመልካች “ምን አይነት ሰው ነው በዚህ የፍጻሜ ጨዋታ ዕለት የሚቀረው!” ይላል፡፡ የተከዘው ሰውዬም “ለሚስቴ የተያዘ ቦታ ነበር፡፡ ያለፉትን አምስት የዓለም ዋንጫዎች የፍጻሜ ጨዋታዎች አይተናል፡፡”
“አሁን ታዲያ ምነው አልመጣችም?”
“ህይወቷ ስላለፈ ነው፡፡”
በጣም አዝናለሁ፡፡ ግን ሌላ የቤተሰቡ አባል ወይም ጓደኛ መምጣት አይችልም ነበር?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አይችልም፣ ሁሉም እሷ ቀብር ላይ ናቸው፡፡”
የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ዓለም ባለቀች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው፡፡ በመንግሥተ ሰማያትና በገሀነም መካከል የድንበር ውዝግብ ይነሳል፡፡ ነገሩን በሰላም ለመጨረስ እግዚአብሔር ዲያብሎስን ለጠረዼዛ ዙሪያ ድርድር ይጋብዘዋል፡፡ ዲያብሎስም በመንግሥተ ሰማያትና በገሀነም መካከል የእግር ኳስ ግጥሚያ እንዲደረግ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
እግዚአብሔርም… “እሱ እንኳን ቢቀርብህ አይሻልም! ጎበዝ ተጫዋቾች በሙሉ መንግሥተ ሰማያት እንደሚገቡ አታውቅም?” ይለዋል፡፡
ዲያብሎስ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“እሱስ ልክ ነህ፣ ግን የእግር ኳስ ዳኞች በሙሉ ገሀነም ናቸው፡፡”
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የመድኃኒቶች አጠቃቀም ዝርዝር ላይ ‘ሳይድ ኢፌክትስ’ ምናምን የሚባል ሊከሰቱ ስለሚችሉ የጎንዮሽ ውጤቶች (‘የጎንዮሽ ጣጣ’ ማለትም ይቻላል፣) የሚጻፉ ነገሮች አሉ አይደል…በሌላውም ነገር ሁሉ እንዲሁ ይደረግልን፡፡ ነገሮች የሚያስከትሉትን ‘የጎንዮሽ ጣጣ’ ሳናውቅ እየቀረን ተቸገርና!
ሀሳብ አለን…“ተከታዩን ዜና በመስማት፣ በማንበብ ወይም በመመልከት ለሚከተሉ ‘የጎንዮሽ ጣጣዎች’ ኃላፊነት የማንወስድ መሆናችንን እናስታውቃለን፣” ምናምን የሚባል ነገር አብሮ ይተላለፍልንማ!
እናማ… “ሊከሰቱ ከሚችሉ የጎንዮሽ ጣጣዎች መካከል…
የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣
ዜና አቅራቢውን ጠምዶ መያዝ…” ምናምን እየተባለ ቢዘረዘርልን፡፡
የምር እኮ ዘንድሮ አንዳንድ ‘ዜና’ እየተባሉ የሚቀርቡ ነገሮች… አለ አይደል… ገና ስንሰማቸው ወይም ስናነባቸው የኦክሲጅን እጥረት ሊገጥመን ይችላል!
“ማስጠንቀቂያ፡— ይህን ጽሁፍ ከምግብ በፊት ማንበብ በምግብ መፈጨቱ ሂደት ላይ ለሚፈጥረው ማንኛውም አይነት ችግር የማንጠየቅ መሆኑን እናስታውቃለን፣” የሚልም ይካተትልን፡፡
ደግሞላችሁ… ‘ዘጋቢ’ ፊልሞችን በተመለከተ ሀሳብ አለን፡፡
“ማስጠንቀቂያ፡— ይህን ዘጋቢ ፊልም በማየት ለሚፈጠረው ድብርት ወይም ሕይወትን የመጥላት ስሜት…ኃላፊነቱ የተመልካቹና የተመልካቹ ብቻ ነው፣” ተብሎ ይጻፍልንማ! እንዲህ ብሎ መገላገል እያለ ‘ዘጋቢ ፊልም’ ባየን ቁጥር እኛም “እነዚህ ሰዎች አሁንም ዋሻ ግድግዳ ላይ ስዕል ይስሉ ከነበሩ ቅመ አያቶቻቻን የተሻለ ላያስቡ ነው!” ምናምን እያልን ባልተዘባበትን ነበር፡፡
ስሙኝማ…መቼም እዚህ አገር ‘ተመሳስሎ’ ያልተሠራ ነገር ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ምነዋ እስካሁን ድረስ “እነ እከሌ የእንትንን ምርት አስመስለው ሲሠሩ ስለተገኙ ሀግ ፊት ቀርበው…” ምናምን የሚባል ነገር የማንሰማሳ!
እናላችሁ…‘ተመሳስለው ከተሠሩ ፈገግታዎችና ሳቆች ራስን መጠበቂያ አሥር ዘዴዎች’ የሚል የስነ ልቡና መጽሐፍ ይውጣልንማ! ልክ ነዋ…ጠቅላላ ህዝቤ እንደ ፕላስቲክ ተለጥጦ ድርግም የሚል ፈገግታ እያሳየ ‘የጎንዮሽ ጣጣዎቹን’ እንዳናይ እየተሞኘን ነዋ! አንድ በጣም ፈገግ የሚሉ ሰዎች ሲገጥሙት አንድ ሺህ አንድ ጥርጣሬዎች የሚሰፍሩበት ወዳጅ አለን፡፡ በደህናው ዘመን “ጨለምተኛ!” ምናምን ይባል ነበር፡፡ እንደ ዘንድሮ አያያዛችን ከሆነ ግን… “እውነቱን ነው፣ እንኳንም ተጠራጠረ!” የሚያሰኝ ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ተመሳስለው ከተሠሩ ‘ታሪኮች’ ራሳችሁን ጠብቁ…” የሚል ማሳሰቢያ በሆነ ነገር ላይ ታትሞ ይውጣልን፣ ወይ እንደ ‘ሲንግል’ ይለቀቅልንማ! አሀ…ሌሎች ያሉትን እየሰሙ፣ የጻፉትን እያነበቡ… አለ አይደል… የራስን ታሪክ ‘ቆርጦ መቀጠል’ በዛ!
“የማንበብ ፍቅር ያሳደረብኝ የአምስተኛ ክፍል የአማርኛ አስተማሪዬ…” (‘የማንበብ ፍቅር’ የተባለው እኮ በዓመት ሁለት ሙሉ ለሙሉ የተነበቡና ሁለት ግማሽ ላይ የተቋረጡ መጽሐፍት ናቸው!)
“የባዮሎጂ አስተማሪዬ የሳይንስ ፍቅር አሳድሮብኛል…”
“በልጅነቴ የሻኪራን ዘፈኖች እወድ ነበር…” (ያኔ እኮ ሻኪራ፣ አይደለም ልትወለድ እናትና አባቷ በእሷ ወደዓለም መምጣት ስለሚጠናቀቀው እነሆ በረከት ጉዳይ ገና ድርድር እንኳን አልጀመሩም፡፡)
ደግሞላችሁ…“ተመሳስለው ከሚገቡ እንግሊዘኛ ቃላቶች ራሳችሁን ጠብቁ…” ይባልልንማ! አለ አይደል…
“ኢንተረስቲንግ ነኝ…”
“ኮንፊዴንሺያል ነኝ…”
የመሳሰሉትን ለማለት ነው፡፡ የምር ግን አንዳንዴ፣ አይደለም በየድራፍቱ ላይ.. በኤፍ ኤሞች ላይ የምንሰማቸው ተመሳስለው የሚገቡ የ‘እንግሊዝኛ’ ቃላት ነገር…‘የፈረንጅ አፍ’ የሚያውቁት ሰዎች እንዴት እንደሚሸማቀቁብን እነሱ ብቻ ናቸው የሚያወቁት፡፡
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፣ ከዚህ በፊት ተብሎ ከነበረም ልድገመው…አንዳንድ ሙያዎች የማህበራቱ ብዛት ከባለሙያዎቹ ብዛት ጋር ሊስተካከል ነው እንዴ!! ልክ ነዋ…ለምሳሌ ጋዜጠኝነትን ውሰዱልኝ፡፡ አለ አይደል…እንደ ማህበራቱ ብዛት ቁጥራችንም ያን ያህል ከሆነ…ለእኛ ብቻ እኮ ራሱን የቻለ ‘የህዝብ ቆጠራ’ ነገር ሊያስፈልገን ነው!  አሀ… አንድ  ግለሰብ ፌስቡክ ላይ አምስት ሺህ ፍሬንዶች ካሉት አንድ ማህበርም መቼም አንድ ሦስት ሺህ ያህል አባላት አያጣም፡፡ እናማ…በአሥር ሺዎች ብንገባ አይገርምማ!
ሀሳብ አለን…ይሄን ቦታ ይከለልልንማ! (የስፖርት ጋዜጠኞች የራሳቸው ‘ቁራጭ መሬት’ ይሰጣቸዋል— ከግዴታ ጋር፡፡ አሀ…ልክ ነዋ…  ማንቼ፣ አርሴ የሚባሉትን ነገሮች ከድንበራቸው ካሳለፉ በሌሎች ጋዜጠኞች ላይ እንደ ጥቃት ተቆጥሮ በእነሱ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ይቋረጣል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ኢንተርኔት ቢቋረጥ ምን እንደሚውጠን አንድዬ ይወቀው!)
ማስታወቂያ ላይ ሀሳብ አለን…ማስታወቂያዎች ከመተላለፋቸው በፊት በትልቁ ‘ብታምኑም ባታምኑም’ ተብሎ ይጻፍልን፡፡
እናማ…በሁሉም ነገሮች ላይ ‘የጎንዮሽ ጣጣዎች’ ይነገሩንማ!
“እንትና የተባለውን ቦተሊከኛ ዲስኩር በመስማት ለሚፈጠረው የአእምሮ ብቃት ማነስ ‘የጎንዮሽ ጣጣ ተጠያቂ አለመሆናችንን እያስታወቅን ‘የቦተሊከኛው ንግግር ትልቁን አንጀቴን ከነበረበት ወዴት እንደሰወረብኝ ይጠየቅልኝ…’ አይነት አቤቱታ የማንቀበል መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
‘የጎንዮሽ ጣጣ’ ከሚያስከትሉ ነገሮች አንድዬ ይሰውራችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1483 times