Saturday, 31 May 2014 13:53

ሁሉም የየራሱን “የግንቦት 20 ፍሬዎች” ይናገር!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(7 votes)

“የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች፣ ከእኛ የግንቦት 20 ፍሬዎች ይለያሉ” ተቃዋሚዎች
የግንቦት 20 አከባበር ጥበባዊ ፈጠራ ይጎድለዋል ተባለ

     የግንቦት ልደታ ከጠባች ጀምሮ ኢቴቪ የግንቦት 20 ፍሬዎችን እያስኮመኮመን ይገኛል - አንዳንዴ በግጥም አንዳንዴ በዜማ፡፡ ይሄስ ባልከፋ፡፡ ሁሌም ግርም የሚለኝ ግን በየግንቦት 20ው በዓል ስማቸው ሳይጠቀስ የማይታለፈው የኃይለሥላሴና የደርግ መንግስታት ናቸው፡፡ (እንዴት ዕድለኛ ቢሆኑ ነው?!) እኔ የምለው…በዓሉ የእነሱ ነው ወይስ የኢህአዴግ? (የእኛ ማለቴ ነው?)
ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ? የበዓሉ አከባበር የፈጠራ ድርቀት ይታይበታል፡፡ አዎ ጥበባዊ ፈጠራ ይጐድለዋል፡፡ የደርግ ዓይነት ሥርዓት ተመልሶ እንዳይመጣ ቀኑን መዘከሩ ተገቢ ነው። ነገር ግን በፕሮፖጋንዳ የተሞላ በዓል መሆን የለበትም። እንደኔ እንደኔ ፕሮፓጋንዳውን ኪነ-ጥበብ ብትተካው ይሻላል፡፡ በፊልም፣ በትያትር፣ በስዕል፣ በሙዚቃ ወዘተ… ቢዘከር የበለጠ ውጤታማ በዓል እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ (በቀይ ሽብር ዙሪያ የረባ ፊልም እኮ አልተሰራም!) የአሁኑ አንዴ አልፏል፡፡ ለመጪው ግንቦት 20 ማለቴ ነው፡፡
እስቲ አስቡት… ከመጀመርያው የግንቦት 20 በዓል ጀምሮ ሰዎች ያለፉትን ጨቋኝ መንግስታት ሲረግሙና በቁጭት ሲብከነከኑ ብቻ ነው ኢቴቪ የሚያሳዩ፡፡ (ድብቅ አጀንዳ አለው እንዴ?) ከተገረሰሰ 23 ዓመት የሞላው ደርግና ከንግስናቸው ከወረዱ 40 ዓመት ያለፋቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እየተኮነኑና እየተረገሙ ነው ግንቦት 20 የሚከበረው - ዛሬም ከ20 ዓመት በኋላ!! (ቀላል የCreativity ችግር አለ?!) ቀኑ የእርግማን ነው የምርቃት? የምናከብረው የትላንትናን ጭቆና ነው ወይስ የዛሬን ነፃነት? ፈጣን የካድሬ መልስ አልቀበልም፡፡ ጥያቄው በደንብ ማሰብ ይፈልጋል፡፡ መበሻሸቅ ሳይሆን መወያየት ባህላችን ሊሆን ይገባል፡፡ (ብሽሽቅ ለፌስቡክ ፖለቲከኞች!)
መቼም ሰዎች (ያውም አዛውንቶች!) በኢቴቪ እየቀረቡ…. ተበድለን፣ ተገርፈን፣ ተጨቁነን፣ ታስረን፣ ታፍነን፣ ተገድለን ወዘተ … እያሉ የደረሰባቸውን ሲተርኩ ወደድንም ጠላንም ሃዘንና ድብርት ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡ በየራሳችን ክፉ ትዝታም መቆዘም እንጀምራለን፡፡ (ይሄ ሁሉ ቅጣት በየትኛው ኃጢያታችን ነው?)
እኔ የምለው… ግንቦት 20ን በተሻለ የደስታና የመነቃቃት ስሜት መዘከር አንችልም እንዴ? (ድሉ እያለ አከባበሩን አልቻልንበትም!) ኢህአዴግ፤ “አመለካከት ላይ መሰራት አለበት” የሚለው ለካ ወዶ አይደለም! (የግንቦት 20 አከባበራችን የአመለካከታችን ውጤት ነው!) ይኸውላችሁ… ኢትዮ ቴሌኮም በቴክስት ሜሴጅ የላከው የግንቦት 20 የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንኳን “…Wishes all Ethiopian People a Happy Ginbot 20 Anniversary, the downfall of Dergue regime!” ነው የሚለው (ፍርጃ እኮ ነው!)
እንግዲህ 23 ዓመት ሙሉ “ደርግ የተገረሰሰበት የግንቦት 20 በዓል” እንጂ “ኢህአዴግ ድል ያደረገበት የግንቦት 20 በዓል” ሲባል ሰምተን አናውቅም፡፡ (ድል ላይ ሳይሆን ጠላት ላይ የማነጣጠር አባዜያችን እኮ ነው!) ምናለበት ክፉው ላይ ሳይሆን በጎው ላይ፣ ድህነት ላይ ሳይሆን ብልፅግና ላይ፣ ድንቁርና ላይ ሳይሆን ትምህርት ላይ፣ ነውጥ ላይ ሳይሆን ሰላም ላይ ኋላቀርነት ላይ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ወዘተ ብናተኩር?!!
እኔ የምናፍቀው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ኢህአዴግ አንድም የጠላት ስም ሳያነሳ (የጥንትም የዛሬም ማለቴ ነው!) ግንቦት 20ን በሰላምና በፍቅር ስሜት የሚያከብርበትን ዕለት ነው!! (“ፀረ - ልማት ሃይሎች” ሳይባል እኮ ግንቦት 20ን ማክበር ይቻላል!)
የእስካሁኑን መንደርደርያ እንደ ግንቦት 20 ዲስኩር ቁጠሩልኝና ወደ ዋናው የዕለቱ ርዕስ ጉዳይ ልግባ፡፡ ለነገሩ የዕለቱም ርዕሰ ጉዳይ በግንቦት 20 ዙርያ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በግንቦት 20 ፍሬዎች ላይ ያነጣጥራል፡፡ እናላችሁ…23ኛውን የግንቦት 20 በዓል አስመልክቶ ኢህአዴግ “የግንቦት 20 ፍሬዎች” በሚላቸው ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች (ኧረ ተቃውሞዎችም ናቸው!) እየተሰነዘሩ ነው። መሰንዘር ብቻም ሳይሆን የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች ለራሱ እንጂ ለእኛ ምናችን ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። እናም እነዚህ ወገኖች… “ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች ለምን አይናገርም?” ባይ ናቸው፡፡ ያው በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች በኢቴቪ መናገር የሚችልበት ዕድል እንደሰበዝ የሰለለ መሆኑ ይታወቃል (ለአውራው ፓርቲም አልበቃ እኮ!) ይሄንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሁለት ከተቃዋሚው ጐራ፣ ሁለት ደግሞ ከመንግስት ጐራ የተሰለፉ ወገኖች የግንቦት 20 ፍሬዎች የሚሏቸውን በዛሬው ፅሁፌ አቀርባለሁ (ይሄም ራሱ የግንቦት 20 ፍሬ መሆኑን ልብ ይሏል!) እናም ከእስከዛሬው ንግግራቸውና አቋማቸው ተነስቼ፣ የግንቦት 20 ፍሬዎቻችን የሚሏቸውን እንዲህ ከትቤላቸዋለሁ፡፡ (በእውነታ ላይ የተመሰረተ ምናብ ወለድ ልትሉት ትችላላችሁ!)
ከአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እጀምራለሁ፡፡
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለተቃዋሚዎች
መቼም እዚች ምስኪን አገር ላይ ከሚያስማሙን ነገሮች ይልቅ የማያስማሙን ነገሮች ይበዛሉ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ሰሞኑን ኢቴቪና ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፤ የግንቦት 20 ፍሬዎች እያሉ የሚደሰኩሩት ነገር እምብዛም የሚያስማማን አይደለም፡፡ (“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አሉ!) እርግጥ ነው ኢቴቪ የግንቦት 20 ፍሬዎች የሚላቸው…ለራሱ ለኢቴቪና ለኢህአዴግ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ (ኢቴቪ ብቻ ለሚያውቃት ኢትዮጵያም ይሰራል!) እኛንና ህዝባችንን ግን ጨርሶ ሊወክል አይችልም፡፡
ኢቴቪ ለምን ጐበዝ ከሆነ… ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች እንዲናገር ዕድሉን አይሰጥም? (የእነሱን ፍሬዎች እንደማንጋራ ያውቀዋላ!) ሃቁን ለመናገር ኢቴቪ እስኪታክተን ድረስ የሚደሰኩርልን ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዜጐች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ የህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ልማት፣ ብልፅግና፣ ወዘተ ሁሉ የሚገኙት በኢቴቪ ስክሪንና በኢህአዴግ “የምኞት ቋት ውስጥ” ብቻ ነው፡፡ የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች አይመለከተንም ብንልም የራሳችን የግንቦት 20 ፍሬዎች የሉንም ማለት ግን አይደለም፡፡ በደንብ አሉን እንጂ! (የራሳችን እያለን የሌላውን አንጋራም!) እናም እነ ኢህአዴግ የሚሰማ ጆሮ ካላቸው… የእኛንም የግንቦት 20 ፍሬዎች ይስሙልን (ከእነሱው የተገኘ በረከት ነውና!)
ለህዝባችን ፕሮግራማችንን ለማስተዋወቅ አቅደን፣ ህዝባዊ ስብሰባ እናደርጋለን ብለን ካወጅንበት ዕለት አንስቶ የሚደርስብን ወከባ፣ ድብደባና እስር እንዲሁም የዕቅድ መስተጓጐል …ከግንቦት 20 ፍሬዎቻችን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ (እነዚህን ነው ስንኮመኩም የኖርነው!) የተቃውሞ ሰልፎችን በልማት ሰበብ ባሰብነው ቀንና ሥፍራ እንዳናካሂድ በየጊዜው መደናቀፋችንም ሌላው የግንቦት 20 ፍሬያችን ነው፡፡ በየክልሉ በወረዳና በዞን ኃላፊዎች የሚፈፀምብን ድብደባና እስር (ሞባይል መንጠቅን ይጨምራል!)፣ የዲሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብቶች ጥሰት… የግንቦት 20 ፍሬዎቻችን እንደሆኑ ስንገልፅ በታላቅ ሃፍረት ነው፡፡ የኢህአዴግ “ፀረ - ሰላም፣ ፀረ - ልማት፤ ፀረ - ዕድገት፣” ወዘተ… ፍረጃም ለእኛ የግንቦት 20 በረከታችን ነው፡፡
ለዚህ ነው ሁሉም የየራሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች እንዲናገር ዕድል ይሰጠው የምንለው፡፡ ለዚህ ነው የኢህአዴግ የግንቦት 20 ፍሬዎች፣ ከኛ የግንቦት 20 ፍሬዎች ይለያሉ የምንለው፡፡ እነ ኢህአዴግ የእኛን የግንቦት 20 ፍሬዎች በግድ እንዲቀበሉን አናስገድድም (“ህልም እንደፈቺው ነው” ብለው ይለፉት)፡፡ እኛንም ግን የእነሱን የግንቦት 20 ፍሬዎች እንድንቀበል አያስገድዱን (የሌሎችን መብት ማክበር ከዚህ ይጀምራል!)
ድል ለሰፊው ህዝብ!!
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለዳያስፖራ ተቃዋሚዎች
ስለ ግንቦት 20 ፍሬዎች መናገር ያለባቸው የወያኔ (ኢህአዴግ ሊሉ ፈልገው ነው!) ሹማምንት እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ (የፍሬው ተጠቃሚ እኮ እነሱ ናቸው! እንኳንስ እኛ በርቀት ያለነው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ቀርቶ፣ እዚያው አገር ቤት ያለው ምስኪኑ የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን  የግንቦት 20 ፍሬዎች ምኑም እንዳልሆኑ መናገሩ አይቀርም (ነፃነት የለም እንጂ!) “የባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት” ተጠቃሚው ድሃው ህዝብ ሳይሆን የወያኔ (ኢህአዴግ ለማለት ፈልገው ነው!) ባለስልጣናት ናቸው፡፡ ድሃው ህዝብማ አሁንም ድሃ ነው፡፡ ለእሱ የግንቦት 20 ፍሬው የበለጠ ድህነት ሆኗል፡፡
ወያኔ በፈጠረው የኢኮኖሚ ሥርዓት ኑሮው የተመሰቃቀለው የከተሜው ነዋሪ፤ በታክስና በቫት ወገቡ ተቆርጦ መንቀሳቀስ አቅቶታል፡፡ ገበሬው በብድር በወሰደው ማዳበሪያ በእዳ ተቀፍድዶ፣ የፖለቲካ ነፃነቱን ተነጥቋል፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ የግንቦት 20 ፍሬዎች!! ወያኔ ነገ ጠባ የፈረደበትን ኮብልስቶንና የባቡር ሃዲድ እያሳየ፣ አገሪቷን እያለማ እንደሆነ ይደሰኩራል፡፡ (ድንጋይ ዳቦ ይሆናል እንዴ?) ህዝቡ ግን የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ይሰቃያል፡፡ (እንኳን በቀን ሶስቴ አንዴም መብላት ተስኖታል!)
ለእነ ጅቡቲና ሱዳን የኤሌክትሪክ ሃይል እየሸጠ ዶላር ወደ ካዝናው የሚያስገባው የወያኔ መንግስት፤ (የኢህአዴግ መንግስት ለማለት ፈልገው ነው!) ህዝቡን ጨለማ አውርሶት ወደ 16ኛው ክ/ዘመን መልሶታል፡፡ አሁን አሁንማ አራት ኪሎ ቤተመንግስትና የባለስልጣናት መኖርያ ቤት ካልሆነ በቀር መብራትና ውሃ ማግኘት ዘበት ነው እየተባለ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለዓመታት በታክሲ እጦትና ወረፋ ከመሰቃየቱ የተነሳ፣ ጋሪና ባጃጅ ቢገቡለት ደስታውን አይችለውም፡፡ (ድንቄም የአፍሪካ መዲና!) የወያኔ ባለስልጣናት ግን በህዝብ ገንዘብ በተገዙ የሚሊዮን ብር አውቶሞቢሎች ይንፈላሰሳሉ። (የግል አውሮፕላን አለመጠየቃቸውም እነሱ ሆነው ነው!) እኒህ ናቸው እንግዲህ የህዝቡ የግንቦት 20 ፍሬዎች!!
ከሁሉም የሚያስገርሙትና የሚያሳዝኑት ደግሞ የወያኔን መንግስት በምርጫ እንጥላለን ብለው አገር ቤት የተቀመጡት አብዛኞቹ ተቃዋሚ ተብዬዎች ናቸው፡፡ (ሰልፍ እንኳ አይፈቀድላቸውም እኮ!) ጥቂቶቹ ተቃዋሚ ተብዬዎች ደግሞ ከወያኔ ፓርቲ ጋር የጋራ ምክር ቤት አቋቁመው፣ የሚጣልላቸውን ድርጐ እየጠበቁ፣ የወያኔ መንግስት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆነዋል፡፡ (ከወያኔ ቅንጣት ሥልጣን የሚገኝ መስሏቸው እኮ ነው!)
ግራም ነፈሰ ቀኝ አገር ቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚታገሉ የቁርጥ ቀን ልጆች (ተቃዋሚ ፓርቲዎች) እንደሌሉ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች የተረዱት ዛሬ አይደለም፡፡ በ97 ምርጫ ማግስት ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ራሱ የወያኔ መንግስት “ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ለማግኘት አልታደልኩም” እያለ የሚያፌዝባቸው! የሆኖ ሆኖ ወያኔን በሰላማዊ ትግል መጣል አንድም ቅዠት አሊያም ጅልነት እንደሆነ የዳያስፖራ ተቃዋሚ ያምናል፡፡ ምርጫ ለወያኔ፣ የስልጣን ዕድሜውን ማራዘምያና ለጋሽ አገራትን ማጭበርበርያ መሳሪያ መሆኑ አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ እናም የዳያስፖራው ተቃዋሚ በዚህ ፈጽሞ ሊሸወድ አይችልም፡፡
በመጨረሻ የወያኔን የስልጣን አልጠግብ ባይነት ለመግታትና ሥልጣን ለባለቤቱ ለሰፊው ህዝብ እንዲመለስ ለማድረግ፣ የዳያስፖራው ተቃዋሚ የሚከተለውን ባለ 5 ነጥቦች የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ለወያኔ የሚያደርጋቸውን ማናቸውም የገንዘብ ድጋፎችና እርዳታዎች እንዲያቆም መጠነ-ሰፊ ሎቢ ይደረጋል!
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኘውን ኤምባሲውን ዘግቶ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን እንዲያቋርጥ ከፍተኛ ግፊትና ጫና እንጀምራለን፡፡
አሜሪካውያንም ሆኑ የዳያስፖራ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ መረር ከረር ያለ ቅስቀሳ እናካሂዳለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ጭቁን ህዝብ!!
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለመንግስት ሚዲያ
ግንቦት 20 ይዞልን ከመጣው ዕልፍ አዕላፍ በረከቶች አንዱና ዋነኛው የፕሬስ ነፃነት መሆኑ አሌ የማይባል ሃቅ ነው፡፡ ዛሬ ዜጐች ያሻቸውንና የመሰላቸውን ሃሳብ ያለምንም ገደብ የመግለጽ ሙሉ ነፃነታቸው ተከብሮላቸዋል - ዕድሜ ለግንቦት 20 ፍሬዎች! የመንግስት ሚዲያዎች ምንም እንኳን ይሄን የግንቦት 20 ፍሬ ተጠቅመው መስራት የሚገባቸውን ያህል በስፋት ሰርተዋል ባይባልም ቢያንስ የህዝብ አጋርነታቸውንና ልማታዊነታቸውን ለማሳየት ተግተዋል ማለት ይቻላል፡፡ በጥፋት ጐራ ከተሰለፈው የግሉ ፕሬስ የሚለያቸውም ይሄው ህዝባዊነታቸውና ልማታዊነታቸው እንደሆነ እሙን ነው፡፡
በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ጨለምተኝነት፣ መርዶ ነጋሪነት፣ ዕድገትን የመካድ አባዜ፣ የፅንፈኛ ተቃዋሚዎች አፈቀላጤነት፣ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞችን እንደዘገባ ምንጭ መጠቀም፣ ህገመንግስቱን የመናድ እንቅስቃሴ… ወዘተ የግል ፕሬሱ መለያ ባህርያት ሆነዋል፡፡ በአንፃሩ የመንግስት ሚዲያ፤ ልማታዊ መንግስታችን ያስመዘገባቸውንና እነ IMF ሳይቀሩ ያመኑባቸውን የእድገት እመርታዎች በትክክል በመዘገብ፣ በመላ አገሪቱ ወደርየለሽ መነቃቃትን ፈጥረዋል፡፡ በዚህም የግሉን ፕሬስ የጥፋት ብዕር በልማት ብዕራቸው በመመከት፣ የህዝብና የመንግስት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
የግሉ ፕሬስ፣ በአመፅና ሁከት የአገሪቱን ሰላም ለማደፍረስና ህገመንግስቱን በሃይል ለመናድ የተንቀሳቀሰውን ያህል፣ የመንግስቱ ሚዲያም ሰላምና ልማትን እንዲሁም ህግና ስርዓትን በመስበክ ለህገመንግስቱ ዘብ ቆሟል፡፡ በአጠቃላይ የግሉ ፕሬስ (ከጥቂቶች በቀር) ለአገር ጥፋት፣ የመንግስት ሚዲያ ደግሞ ለአገር ልማት የቆሙ እንደሆኑ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብም ማን የህዝብ አፈቀላጤ፣ ማን ደግሞ የፅንፈኛ ተቃዋሚ ልሳን እንደሆነ በግልፅ ይመሰክራል፡፡
እስከአሁን ድረስ የግሉ ፕሬስ ከጥፋት ተግባሩ እንዲታረም ልማታዊ መንግስታችን ለምን ህጋዊ እርምጃዎችን ሳይወስድ በትዕግስት እንደቆየ በቅጡ እንገነዘባለን፡፡
የግንቦት 20 ፍሬ የሆኑት የግል ፕሬሶች እንዲያብቡ ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄንን የመንግስት ትዕግስት የግሉ ፕሬስ ከፍርሃት በመቁጠሩ፣ ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰበት እንጂ እየተሻለው አልመጣም፡፡ ስለዚህም ለህዝብና ለአገር ደህንነት፣ እንዲሁም ግንቦት 20 ያጐናፀፈንን የፕሬስ ነፃነት ለመጠበቅ ሲባል፣ ልማታዊው መንግስታችን ህጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ እናሳስባለን፡፡ (የፕሬስ ነፃነት እሳት ማንደድ አይደለም!)
በተጨማሪም የአንዳንድ የግል ፕሬሶች የገንዘብ ምንጭ በአግባቡ ተጠንቶ፣ ከጀርባቸው ማን እንዳለ ሊታወቅ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ (አገራችን የቀለም አብዮተኞች ሰለባ እንዳትሆን ለመታደግ!) ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እዚህና እዚያ ማጣቀሱን ትተው ሚናቸውን መለየት ይኖርባቸዋል፡፡ መፃፍ የቻለ ሁሉ “ጋዜጠኛ ነው” ሊባል ስለማይችል፣ የጋዜጠኝነት መስፈርት የሚያወጣና የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥ ተቋም በአፋጣኝ እንዲቋቋም እናሳስባለን፡፡
በሌላ በኩል፤ ብዙም ወደ ጥፋቱ ጐዳና ያልገቡ የግል ፕሬሶችን በድጎማና በማበረታቻ በመማረክ፣ ወደ ልማታዊ ጋዜጠኝነት የመቀየር ጥረትም ቸል ሊባል እንደማይገባው እናሳስባለን፡፡
ለግንቦት 20 ፍሬዎች - ዘብ እንቆማለን!!!
የግንቦት 20 ፍሬዎች - ለኢህአዴግ ካድሬዎች!
ዛሬ በአገራችን ላይ የምናያቸው መልካም ነገሮች ሁሉ የግንቦት 20 ፍሬዎች መሆናቸውን ራሳቸው ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ሊክዱት አይችሉም፡፡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት፣ ልጄ ለጦርነት ይማገድብኛል ከሚል ስጋት ተላቆ መኖር፣ ንግድ አቋቁሞ ማትረፍ፣ በፈለጉት ሃይማኖት ማመን፣ በብሄር ማንነት ከሚደርስ ጭቆናና አድልኦ ተላቆ በእኩልነት መኖር፤ ወዘተ… የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት ያስመዘገብነው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገትም ከግንቦት 20 ፍሬዎቻችን በተቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡
በመላ አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተዘረጋ ያለው መሰረተ ልማትም የግንቦት 20 ፍሬዎቻችን አካል ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድባችንም በፊታውራሪነት የሚሰለፍ የግንቦት 20 በረከታችን ነው፡፡ የገዢውን ፓርቲ መንግስትነት ክደው፣ ነጋ ጠባ በክፉ የሚያብጠለጥሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የእነሱ አፈ ቀላጤ የሆኑት የግል ፕሬሶችም ቢሆኑ… የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡ (እነሱ ወፍ ዘራሽ ነን ቢሉም!)
አረረም መረረም እኒህን አያሌ የግንቦት 20 ፍሬዎች ተንከባክቦ ሊጠብቃቸው የሚችለው ከመጀመሪያም መኖራቸውን አምኖ የተቀበለ ወገን ብቻ ነው፡፡ እናም ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችና የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች እንዲሁም የእነሱ ልሳን የሆኑት የግል ፕሬሶች፣ የግንቦት 20 ፍሬዎቻችንን (ሰላማችንን፣ ዕድገታችንን፣ ልማታችንን፣ ዲሞክራሲያችንን፣ ወዘተ…) እንዳይንዱብን ከህዝባችን ጋር በመሆን በዓይነ ቁራኛ መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡ በተለይ ደግሞ ለህገመንግስታችን ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ ዛሬ የምናጣጥመውን መብትና ነፃነት ለማምጣት ስንት ዘመንና የስንቶችን መስዋዕትነት እንደጠየቀ አንዘነጋውም፡፡ እናም በግንቦት 20 ፍሬዎቻችን ፈፅሞ አንደራደርም (የቀረው ይቀራል እንጂ!)
ድል ለልማታዊ መንግስታችን!!

Read 3340 times