Saturday, 31 May 2014 13:50

ድምፅን ከፍ አድርጐ በመጮህ ቤት የሚሠራ ቢሆን አህያ በቀን በቀኑ ሁለት ቤት በሠራ ነበር አንጋረ - ፈላስፋ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ገመድ ዝላይ ከሚዘሉ ልጆች ጋር ሊጫወት ከቤቱ ይወጣል፡፡ አባቱ ከፎቅ ሆኖ የስተውለዋል፡፡
አባትየው የሚያየውን ለማመን አልቻለም፡፡
ልጁ ገመዱን የሚያዞሩትን ልጆች፤
“እኔንም ገመድ ዝላይ አጫውቱኝ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
“እሺ ዝለል” አሉት፡፡
ልጁ መዝለል ጀመረ፡፡
ልጆቹም ገመዱን ማዞር ቀጠሉ፡፡
አስገራሚው ነገር ግን ልጁ የሚዘለው ሌላ ቦታ ነው፤ ልጆቹ ገመዱን የሚያዞሩት ሌላ ቦታ ነው፡፡ ልጁ መዝለውን ቀጠለ፡፡
ልጆቹ ይቀልዱበታል፡፡ ይስቁበታል፡፡ እሱ መዝለሉን ቀጥሏል፡፡ አይፎርሽም፡፡ ደስ ብሎታል፡፡
አባትዬው በሁኔታው አዝኖ ከፎቅ ወርዶ መጥቶ ልጁን መዝለሉን አስቆመውና ወደቤት አስገባው፡፡ ልብሱን አስቀይሮ ወደ ሐኪም ቤት ወሰደው፡፡ ሐኪሙም፤
“ምን ችግር ገጠማችሁ፤ ምን ልርዳችሁ?” አለ
አባት ልጁ ሲጫወት ምን ያደርግ እንደነበረ ገለጠለትና “ምናልባት ልጄ አንድ ዓይነት የአዕምሮ ወይም አካላዊ ችግር እንዳይኖርበት ብዬ ነው” ሲል አስረዳ፡፡
ሐኪሙ ለልጁ ብዙ ምርመራ ካደረገለት በኋላ የዓይን ችግር እንዳለበት አረጋገጠና መነፅር አዘዘለት፡፡
ልጁ መነፅር ተገዛለት፡፡ መነፅሩን አድርጐ ወደ ገመድ ዝላይ ጨዋታው ሄደ፡፡
አሁን በትክክል ገመዱ ማህል ገባ፡፡ አዞሩለት፡፡ በትክክል መዝለል ጀመረ፡፡ አንዳንዴ ነው እንጂ አልፎረሸም፡፡ ቀጠለ ዝላዩን!!
*    *    *
ገመዱ በሌለበት የምንዘል አያሌ ነን፡፡ ሐኪም ያላየ ዐይን ያለን በርካታ ነን፡፡ በትክክል እንዳልዘለልን እያዩ፣ እየታዘቡ፤ እየሳቁ፣ እየተሳለቁ የሚያዩንም ብዙ ናቸው፡፡ ገመድ ማዞሩን እንደስራ ቆጥረው ዕድሜ - ልካቸውን ቢሮክራሲው ውስጥ የሚኖሩም የትየለሌ ናቸው፡፡ እንደ መልካም አባት ያለ መልካም መሪ፣ መልካም ኃላፊ፣ መልካም አለቃ የልጁን ችግር ተረድቶ ወደሀኪም ዘንድ ይወስዳል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ይፈጥራል፡፡
የሚስቁ፣ የሚሳለቁትን ሁሉ ኩም ያደርጋቸዋል፡፡ “የሚሠሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው” ይላቸዋል፡፡
በገመድ ዝላይ መፎረሽ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ግን የፉረሻውን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። ከገመዱ ውጪ መዝለል ከጨዋታው ውጪ ነው ቢባልም፣ ልምዱ ግን ቀላል አደለም ብሎ መከራከርም ይቻላል፡፡ የልጁ የዕይታ ችግር (Sight problem) የሁላችንም ችግር ቢሆንስ ብለን ማሰብ አለብን (myopic or farsighted እንዲል ፈረንጅ - የአፍንጫ ሥር ማየትና አርቆ - ማስተዋል እንደማለት)፡፡ ማመን ነው እንጂ አለማመን ምን ያቅታል፤ ይላል አንድ ፀሐፊ
ዕውነትን መሠረት ካደረግን ውሸትን መናቅ ቀላል ነው፡፡
“ሐሰተኞች ሰዎች ቢምሉ ቢገዘቱ ነገራቸውን በአየር ላይ በሚበሩና ፍለጋቸው በማይገኝ ዎፎች መስለው፡፡ ለመብረራቸው ፍለጋ እንደሌለው፤ ሐሰተኞች ሰዎች ለሚናገሩትም ነገር ሥር መሠረት የለውምና” ይላሉ የአገራችን ፈላስፎች፡፡
በነባራዊነትና በህሊናዊነት አንፃር ከተመለከትን የማይዋሹ ነገሮችን መዋሸት ጅልነት ነው። አንድ አዛውንት “እንዴት ፖለቲከኛ ለመሆን ቻሉ?” ተብለው ቢጠየቁ፤ “የዕውቀት ማነስ ነው ፖለቲከኛ ያደረገኝ!” አሉ፤ አሉ፡፡ “አንተስ የአገራችን ምሁር ያደረገህ ምንድነው?” ብለው አዛውንቱ ቢጠይቁት “ያው መማሬ ይመስለኛል ሌላ ሰበብ አይሰማኝም” አለ ምሁሩ፡፡ አዛውንቱም “አንተን ምሁር ያረገህ ደሞ ምን መሰለህ?...የዕውነት ማነስ!” አገራችን ከእኒህ አዛውንት ዕሳቤ ውጪ አይደለችም፡፡ የዕውነትና የዕውቀት ማነስ ፖለቲከኛም፣ ምሁርም አድርጐናል፡፡ ያወቀ ያውቀዋል። ያለቦታው ገመድ መዝለልም ክህሎት ይሆናል፡፡ በዛሬ ግንቦት ሃያ ማግስት ሆነን፣ “አንጋረ - ፈላስፋ” የሚለው መፅሐፍ የሚለንን ብናስብ ፀጋ ነውና እነሆ:-
“ዕውነትን መናገር፣ በሐሰት ከመማል መራቅ፣ ሰውን ፊትን አብሮቶ መቀበል፣ እንግዶችን አክብሮ መቀበል፣ በጐ ሥራ መሥራት፣ ጐረቤትን ተጠንቅቆ መያዝ፣ Uዕቢትን አለማድረግ፣ ሁልጊዜ ሰውን ማክበር፣ ትህትናን ማዘውተር፣ አንደበትን ክፉ ከመናገር መግታት፣ ቀናውን ነገር መናገር፣ ለሁሉም በቅንነት መመለስ፣ የወንድምን ኃጢያት መሠወር፣ ሽንገላን (ምሎ - መክዳትን) መተው፣ ጉባዔ ፊት ጮክ ብሎ አለመናገር” እነዚህን ቃላቶች ሁሉ ገንዘብ ያደረገ ሰው በዕውነት አዋቂ ነው፣ ዐዋቂ ይባላል”
ትርጓሜውም፤ ባጭሩ፤
“ዕምነትህን አትካድ፡፡ ከጐረቤት ጠንቅ መጠበቅ፡፡ የፖለቲካ አቀባበልና አያያዝን ማወቅ። በፓርላማ ፊት አለመፎከር፡፡ መሬት ላይ ምን እንደሚጠብቀን አናውቅምና፡፡” ይሄ የወቅቱ መልዕክት ይሁነን፡፡
ነብሳቸውን ይማረውና አባ ጳውሎስ ረዥም ፍትሐተ - ፀሎት ያደረጉለት፤ ነብሱን ይማረውና የአድዋው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር፤
“ግንቦት ሃያን እንዴት ታየዋለህ?” ሲባል፤
“እንደሰኔ ሃያ” ያለው አይረሳንም፡፡
ድሎቻችንን አንረሳም፡፡ ሌላ ድል ለማስመዝገብ የቀደሙት ድሎች ከትውስታነት ባሻገር አገልግሎት የላቸውም፤ እንደ አድዋ ድል ሁሉ፡፡ ወሳኙ የዛሬ ዝግጁነታችን ነው፡፡ የዛሬ ማንነታችን ነው፡፡ የሚከፈለን ካሣም በወቅቱ ፍሬ ነበረ፡፡ ወደ ሰላማዊ ትግል ስንዘዋወር ምርቱ ለሌላ ዕድገት መስፈንጠሪያ - ድልድይ (Spring Board) ሆኗል፡፡ ስለዚህም ጊዜው ብዙ መናገሪያ ሳይሆን ማድረጊያ ሆኗል ማለት ነው፡፡ መስከረም ሁለትን ከግንቦት ሃያ የሚለየው ይሄ ነው፡፡ ድፋትና ቅናት ነው በያሬድኛ፡፡ ትንሽ ምላስ እና ብዙ እጅ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ለተቃዋሚም፣ ለአልተቃዋሚም፣ ለአዘቦት - ሰውም ዕውነት ነው፡፡
ለዚህ ነው ከምዕተ - አመታት በፊት የነበሩ ፈላስፎቻችን፤ “ድምፅን ከፍ አድርጐ በመጮህ ቤት የሚሠራ ቢሆን፤ አህያ በቀን በቀኑ ሁለት ቤት በሠራ ነበር!” ያሉት፡፡   

Read 6299 times