Monday, 26 May 2014 10:11

የሸጎሌው ፍንዳታና አሰቃቂው እልቂት 23ኛ ዓመት ሲታወስ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(17 votes)

          “ትዝ ይለኛል… ዕለቱ ማክሰኞ ነበር፡፡ ማለዳ ላይ የኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ኢህአዴግ አገሪቱን መቆጣጠሩንና የመንግስት ለውጥ መደረጉን መናገሩ አካባቢያችን የፍርሃት ድባብ አጥልቶበታል፡፡ ት/ቤታችንም ከተዘጋ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ቤተሰቦቼ ከቤት እንድወጣ አይፈቅዱልኝም ነበር፡፡ ቤት መቀመጥ በጣም ቢሰለቸኝም አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ከቤታችን በራፍ ላይ ባለችው ገላጣ ሜዳ ላይ የሰፈር ልጆች ለጥቂት ደቂቃዎች ሰብሰብ ብለን የቆምን እንደሆነ ‘ተበተኑ’ የሚል ፈጣን ትእዛዝ ይደርሰናል፡፡ ያኔ እንዲህ እንዳሁኑ ቴሌቪዥንም ሆነ ሌሎች መዝናኛ ነገሮች እንደልብ ባለመኖራቸው እቤት እምንውልበት ጊዜ በጣም አሰልቺ ነው፡፡ በአካባቢያችን የሚገኙ በርካታ የመንግስት ተቋማት እየተሰበሩ ይዘረፉ ነበር፡፡ ፈጥኖ ደራሽ እየተባለ የሚጠራው የፖሊስ ማሰልጠኛ ማእከል ከተዘረፈ በኋላ አብዛኛው የሰፈራችን ነዋሪ ባለመሳሪያ ሆነ፡፡ የማሰልጠኛው እቃ ግምጃ ቤት ተሰብሮ የተዘረፈ እለት ከዘራፊዎቹ መካከል እርስ በርስ ተታኩሰው የሞቱ የሰፈር ልጆችም ነበሩ፡፡ በርካታ አዳዲስና ያገለገሉ የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች፣ በንጉሱ ጊዜ ለማሰልጠኛው የተገዙ የተለያዩ ውድ እቃዎችና የጦሩ አልባሳት በዘራፊዎቹ ከመወሰዳቸውም በላይ ለጦሩ ደመወዝ የመጣ በሚሊዮን የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ የዘራፊዎች ሲሳይ ሆኗል፡፡ ግርግርና እረብሻ በአካባቢያችን የተለመደ ጉዳይ ነበር፡፡

አብዛኞቻችን (የሰፈራችን ሰዎች) ቤተሰቦች ስለሆንን የነበረው ውጥረት ከሌሎች አካባቢዎች ሁሉ በእኛ መንደር የባሰ ይመስለኛል፡፡ ቤተሰቦቼ ወደ እነዚህ የረብሻና የዘረፋ ቦታዎች እንድሄድ ፈፅመው አይፈቅዱልኝም፡፡ ለቤቱ ብቸኛ ወንድ እኔ በመሆኔም፣ ከሴቶቹ ይልቅ በእኔ ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር ይደረግብኝ ነበር፡፡ የኢህአዴግ ሰራዊት ከተማውን በይፋ መቆጣጠሩ በሬድዮን ከተነገረ በኋላ፣ ሁኔታዎች ይበልጥ እየተለወጡ ሄዱ፡፡ ግንቦት 19 ምሽትና ሌሊቱን ከሆለታ መስመር ወደ አዲስ አበባ ከገባው የኢህአዴግ ሰራዊት ጋር የመንደራችን ወጣቶች ተጋጭተው፣ አንድ ወጣት ከኢህአዴግ ታጋይ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱን አጣ፡፡ አባቴ በማግስቱ ከጥቂት የሰፈራችን ሰዎች ጋር ወጣቱን ለመቅበር ወደ ፊሊጶስ ቤተክርስቲያን ሄደ፡፡ እኔም እግሩን ተከትዬ ከቤት ወጣሁ፡፡ የሰፈሬ ልጆች፣ የሸጎሌ ጥይት ማምረቻና ማከማቻ መጋዘን ተሰብሮ እየተዘረፈ እንደሆነና ወደዚያው ሊሄዱ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ ከእነሱ ጋር ሄጄ ሁኔታውን የማየት ጉጉት አደረብኝ፡፡

ለቀናት በቤተሰቦቼ የተነፈግሁትን ነፃነት በአጋጣሚ በማግኘቴ፣ ሳልጠቀምበት እንዲያመልጠኝ አልፈለግሁም፡፡ ታዲ፣ ስዩም፣ ፈቃዱ፣ ዮሐንስ፣ ዘካርያስ፣ ግሩሜ፣ አሌክስና እኔ ስምንት ሆነን ወደ ስፍራው ጉዞ ጀመርን፡፡ ሁላችንም እድሜያችን ከ18 ዓመት በታች ነበር፡፡ ወደ ስፍራው እየተቃረብን ስንሄድ ምድር ቀውጢ ሆናለች፡፡ በየሜዳው የተበታተኑ የጥይት ቀለሆች፣ የተቀዳዱ ካርቶኖች በብዛት ይታያሉ፡፡ የዊንጌትን ዳገታማ መንገድ ጨርሰን በስፍራው ስንደርስ በሜርኩሪ ዘረፋ ላይ ነበሩ የተባሉ ሰዎች በጥይት ሲታኮሱ በማየታችን እጅግ ፈራን፤ ግን ሁኔታውን ለማየትና ከተገኘም የተራረፈ ነገር ለመለቃቀም አስበን ተጠጋን፡፡ ሁላችንም አንድ ላይ እንድንሆንና እንዳንለያይ ተነጋግረን ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል ሰዓቱ ወደ ምሳ ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ወደ ስፍራው ተጠግተን ጥቂት እንኳን ሳንቆይ አካባቢውን የሚነቀንቅ ኃይለኛ ፍንዳታና የእሳት ብልጭታ ከአንድ ስፍራ ተነሳ፡፡ ከዛ በኋላ ምኑን ልንገርሽ… ምድር ቀውጢ ሆነች፡፡ እዚህም እዚያም ሃይለኛ ፍንዳታና ጩኸት ብቻ ሆነ፡፡

ካየሁ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግን የሆነውን አላውቅም፡፡ ራሴን ያወቅሁትና የነቃሁት ከ32 ቀናት በኋላ ባልቻ ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡ በሆስፒታሉ ለ4 ወራት ባደረግሁት ህክምና ህይወቴ ከሞት ቢተርፍም ዘላቂ አካል ጉዳተኛ ከመሆን አልዳንኩም፡፡ በደረሰብኝ አደጋ የጀርባዬና የፊቴ ግማሽ ክፍል እንዲሁም የግራ እጅና እግሬ ስጋዎች ሙልጭ ብለው ተገፈዋል፡፡ በጭንቅላቴ ላይ ፀጉር የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ በሚገባ መንቃቴንና ራሴን ማወቄን የተገነዘቡት ቤተሰቦቼ በደረሰብኝ ጉዳት እንዳላዝንና እንዳልከፋ፤ ይልቁንም በህይወት በመትረፌ መደሰት እንደሚገባኝ እየነገሩ እንድፅናና ያበረታቱኝ ጀመር፡፡ ከሰፈራችን ተጠራርተን አብረን ከሄድነው ስምንት ጓደኞቼ መካከል በህይወት የተረፍኩት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ሰባቱ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ህይወታቸውን እንዳጡ ተነገረኝ፡፡ የደረሰብኝን የጉዳት መጠን ሳየው በሞቱት ጓደኞቼ ቀናሁ፡፡ በባልቻ ሆስፒታል አራት ወር ሙሉ ፍዳዬን አየሁ፡፡ ሀኪሞቹ የተበላሸውን የፊት ገፅታዬን ለመመለስ ያደረጉት ጥረት በጥቂቱም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል፡፡ ከመቀመጫዬና ከእግሬ እየተወሰደ በፊቴና በአንገቴ ላይ በተለጣጠፉት ስጋዎቼ ሰው መምሰል ቻልኩ፡፡

በአጋጣሚ እኔን ያክመኝ የነበረው ሩሲያዊ ወጣት ዶ/ር፣ ወደ ሀገሩ ለእረፍት ሄዶ ሲመለስ፣ የፊቴን ቆዳ ለማስተካከል የሚረዱ ቅባቶችና መድኃኒቶች ይዞልኝ መጣ፡፡ ይህን ፊቴን የተሻለ ለማድረግ በእጅጉ ጠቅሞኛል፡፡ በባልቻ ሆስፒታል ቆይታዬ ወደተኛሁበት ክፍል እየመጡ አደጋው በደረሰብኝ ስፍራ ላይ ያገኘሁትን ሜርኩሪ በውድ ዋጋ እንደሚገዙኝ እየነገሩ የሚያግባቡኝ ፈረንጆች ነበሩ፡፡ እኔ ግን እንኳንስ ሜርኩሪ ላገኝ ቀርቶ፤ በቦታው እየተካሄደ የነበረው ምን እንደሆነ እንኳን በቅጡ ሳይገባኝ ነበር ለአደጋ የተጋለጥኩት፡፡ ከሆስፒታሉ ከወጣሁኝ በኋላ ከአንድ አመት በላይ ከቤቴ ተኝቼ ህክምናዬን ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ ምክንያትም ትምህርቴ ለሁለት ዓመት ተቋርጧል፡፡ ቀስ በቀስ አደጋው ያደረሰብኝ የአካል እና የአእምሮ ጉዳት እየቀነሰ ሄዶ ሳገግም፣ ትምህርቴንም ካቆምኩበት ቀጠልኩና አሁን ላለሁበት ደረጃ ልደርስ ቻልኩ፡፡ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር ግን የደረሰብኝ አደጋና እስከ ወዲያኛው ያጣኋቸው ጓደኞቼ ትዝ ይሉኛል፡፡ ለእኔ የግንቦት 20 ፍሬዬ የአመታት ህመምና ስቃይ እንዲሁም አካል ጉዳተኝነት ነው፡፡” ይህንን ያለኝ በአንድ ስመ ገናና ኤንጂኦ ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ ተመድቦ በመስራት ላይ የሚገኝና የ37 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ፍፁም ኃ/ኢየሱስ ነው፡፡ ፍፁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪውን በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቆ ከተመረቀ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተማረበት የትምህርት መስክ በተለያዩ ድርጅቶች ለዓመታት ሰርቷል፡፡ አሁን በሚሰራበት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ጠቀም ባለ ደመወዝ ከተቀጠረ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡

ምንም እንኳን ኑሮው የተደላደለ ቢሆንም ውስጡ ደስተኛ እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ የብቸኝነት ስሜት ያሰቃየዋል የፊት ገፅታውን ለመመለስ መስዋዕትነትን የከፈሉት መቀመጫው፣ ዳሌውና የእግሩ ባቶች በጨርቅ ካልሆነ በስተቀር ለእይታ ሊያጋልጣቸው እንደማይደፍርም አውግቶኛል፡፡ በአደጋው ከደረሰበት የአካል ጉዳት ቢያገግምም የአእምሮው ጉዳቱ ግን እያደር እየባሰበት እንደሄደና ኑሮውን የብቸኝነትና የሰቀቀን እንዳደረገበት አልሸሸገኝም፡፡ ለም ሆቴል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተገንብተው ለከተማዋ ውበት ከሰጡት ህንጻዎች አንዱ ባለቤት ነው፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም በሸጎሌ የጥይት ማምረቻና ማከማቻ መጋዘን ላይ በደረሰው የፍንዳታ አደጋ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአደጋው ግራ እጁንና አንድ አይኑን አጥቶ በህይወት ለመትረፍ ችሏል፡፡ ወደ ሥፍራው የሄደው ከሶስት ጓደኞቹ እና ከታላቅ ወንድሙ ጋር ቢሆንም በህይወት የተመለሱት እሱና አንድ አብሮ አደግ ጓደኛው ብቻ ነበሩ፡፡ ቴዎድሮስ (ለፅሁፉ ስሙ የተቀየረ) ከአደጋው ያተረፈው አካል ጉዳተኝነቱን ብቻ አልነበረም፤ ህይወቱን ለመቀየር ያስቻለውን ሀብቱን ጭምር ነበር፡፡

መኖሪያ ቤታቸው በጥይት ፋብሪካው አካባቢ በመሆኑ መጋዘኑ ተሰብሮ ዘረፋው ሲጀመር ከስፍራው ከደረሱት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ እሱና ጓደኞቹ ይገኙበታል፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲወራ ይሰሙ የነበሩትንና ከመጋዘኑ ህንፃ በታች (አንደር ግራውንድ) ውስጥ የተቀበረና ለጥይት ማምረቻው የሚያገለግል ሜርኩሪ የተባለው ማዕድን ይገኝበታል የተባለውን ስፍራ የቅድሚያ ኢላማቸው አደረጉት፡፡ እንደሀሳባቸው ሆኖም ውድ ማዕድኑ ያሉበትን ቦታ በማግኘታቸው ዕድል የሰጣቸውን አፍሰው ወጡ፡፡ ያገኙት ማዕድን እጅግ ውድ ዋጋ እንደሚያወጣ ሲነገራቸው፣ ተጨማሪ የማግኘቱ ጉጉት አደረባቸውና በድጋሚ ወደስፍራው አመሩ፡፡ ሆኖም ለሁለት ጓደኞቹና ለታላቅ ወንድሙ ሞትን፣ ለእሱ ከፍተኛ የአካል ጉዳትን እንጂ ተጨማሪ ሜርኩሪን አላስገኘላቸውም፡፡ ቴዎድሮስ በአሁኑ ወቅት የ47 ዓመት ጎልማሳ ነው፡፡ “ዛሬ በሆነ አጋጣሚ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ላይ በተሰራ የቀለበት መንገድ በመኪና ሳልፍ ያኔ የነበረው ሁኔታና ድርጊቱ ሁሉ አሁን የተፈፀመ ያህል ይታየኛል፡፡ ግንቦት 20 ለእኔ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜትን የሚፈጥርብኝ ቀን ነው፡፡ እውነቱን ተናገር ካልሽኝ፣ እለቱ ፍፁም ባይታወስና ባይከበር ደስ ይለኛል፡፡” አለኝ ስሜቱ ተረብሾ፡፡ ወ/ሮ ሽታዬ ሰሙንጉስ በሸጎሌው አደጋ ሶስት ልጆቻቸውን ያጡ እናት ናቸው፡፡ በ18፣በ16ና በ12 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የነበሩት ሶስት ወንዶች ልጆቻቸው ወሬ እንመልከት ብለው ከቤት እንደወጡ በዛው መቅረታቸውን ነግረውኛል፡፡

ሁለቱ ልጆች እዛው አደጋው በደረሰበት ስፍራ ህይወታቸውን ሲያጡ፣ አንደኛው ልጃቸው ግን ለአንድ ወር በባልቻ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ከቆየ በኋላ፤ ህይወቱ አልፏል፡፡ ወ/ሮ ሽታዬ፤ በእለቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱት አይኖቻቸው በእንባ ይሞላሉ፡፡ ለረባ ቀብር እንኳ ያልታደሉት ልጆቻቸውን በከፋ ችግርና እንግልት ማሳደጋቸውንና ልጆቹም በባህሪያቸው አስቸጋሪዎችና ረባሾች እንዳልነበሩ ይናገራሉ፡፡ “በአንድ ጀንበር ከወላድነት ወደ መካንነት ተሸጋግሬ በህይወት መኖር መቻሌ እንኳንስ ለተመልካች ለእኔም ትንግርት ነው፡፡ ግን ላያስችል አይሰጥ አይደል እሚባለው? ይኸው የሰጠኝን በፀጋ ተቀብዬ 23 ዓመት ለመኖር ችያለሁ፡፡ አደጋው የደረሰ ሰሞን እራሴን ሁሉ ስቼ ነበር፤ እራሴን ለማጥፋትም ብዙ ሙከራ አድርጌያለሁ ግን አልሆነልኝም፡፡ ፈጣሪ ለምን እንደፈለገኝ ባላውቅም ይኸው ቁጭ አድርጎኛል፡፡ አንድ ጊዜ በቀበሌያችን በተደረገ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ አደጋው ለደረሰባቸው ሰማእታት ለምን ሀውልት በቦታው ላይ አይሰራም ብዬ ብጠይቅ፣ አንዱ የቀበሌያችን ተመራጭ ‹ልጆችሽ ያለቁት እኮ ለአገራቸው ደህንነት ሲታገሉ አይደለም፤ መጋዘን ሰብረው ሲዘርፉ ነው› አለኝ፤ ምን እላለሁ? “እኔን ሆነህ እየው” ብዬው ወጣሁ፡፡ ይኸው 23 ዓመት ሙሉ ግማሽ ህይወቴን እኖራለሁ፡፡

አሁን ግንቦት 20 ምኑ እሚያስደስት ቀን ሆኖ ነው… በዚህ ሁሉ ቸበርቻቻና በዚህ ሁሉ ግርግር የሚከበረው፤ እለቱ ያመጣብን መዓትና መከራንና ችግርን ብቻ ነው፡፡” ወ/ሮ ሽታዬ የልጆቻቸው ሀዘን ዛሬም የወጣላቸው አይመስሉም አይኖቻቸው በእንባ ብዛት እየሟሙና እየደከሙ መሄዳቸው ያስታውቃል፡፡ ዛሬም በእነዚሁ አይኖቻቸው ያነባሉ፡፡ ኑሮዋቸው ተስፋና ጉጉት አልባ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደሳቸው ሁሉ በእለቱ በደረሰው የፍንዳታ አደጋ ህይወታቸውን ባጡ ልጆቻቸው ኑሮዋቸው በሀዘንና ሰቀቀን የተሞላ በርካታ እናቶች ሸጎሌ እና አካባቢዋን በከፋ ሀዘን ያስታውሱታል፡፡ የዛሬ 23 ዓመት ግንቦት 20 ከቀኑ 5 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በደረሰው የፍንዳታ አደጋ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ህጻናትና ጎልማሶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በአደጋው ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ታዳጊዎችና ህፃናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶችም ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አካባቢው ለወራት በመጥፎ ሽታና በአሞራዎች ተወርሮ ነበር፡፡ ዛሬ አካባቢው ታርሶ በተገነቡ ቤቶች ውስጥ በርካታ ነዋሪዎች ሰፍረውበታል፡፡ ከዊንጌት አዲሱ ገበያ ድረስ የሚዘልቀው የቀለበት መንገድ የተሰራውም በዚሁ ፍንዳታ በደረሰበት ቦታ ላይ ነው፡፡ የሸጎሌውን ፍንዳታና በፍንዳታው ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን የሚያስታውስና እንደ ወ/ሮ ሽታዬ ያሉ እናቶችን የሚያፅና ምንም ነገር በስፍራው የለም፡፡

Read 7768 times