Saturday, 24 May 2014 15:15

ታይላንድ፡ በመፈንቅለ መንግስት ብዛት ወደር የላትም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ታይላንድ የገዢ ፓርቲ ባለስልጣናትና ተቃዋሚዎች ሐሙስ እለት ታስረዋል

ገዢውን ፓርቲ የሚደግፉና የሚቃወሙ ቡድኖች በሚያካሂዱት አመፅ ስትታመስ የከረመችው ታይላንድ፤ በዚህ ሳምንት ለወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተዳርጋለች። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ማክሰኞ እለት የገለፀው የአገሪቱ የጦር ሃይል፣ ውሳኔው የመንግስት ግልበጣ አይደለም በማለት ደጋግሞ ተናግሯል። “የጦር ሃይል፣ የመንግስት ግልበጣ ሳያካሂድ በአገሪቱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጫን ስልጣን አለው” ሲልም ከመቶ አመት በላይ ያስቆጠረና የተረሳ ጥንታዊ የሕግ አንቀፅ በመጥቀስ ለማስረዳትና ለማስተባበል ሞክሯል። ማስተባበያው ግን ከሁለት ቀን በላይ አልዘለለም። ሐሙስ እለት፤ ወደለየለት መፈንቅለ መንግስት ተሸጋግሯል።
ስልጣን የተቆጣጠረው የጦር ሃይል፤ የተቃውሞ ሰልፎችን በማገድ ወታደሮችን ለቁጥጥር ካሰማራ በኋላ የዋና ከተማዋ ጎዳናዎች ፀጥ ረጭ ብለዋል። ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ጎራ ለይተው ቀውሱን ያባብሳሉ የተባሉ 14 የቴሌቪዥን ቻናሎችና 3000 የሬዲዮ ቻናሎችም ለጊዜው ታግዳችኋል ተብለዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን፤ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች እንዲሁም ከፓርቲዎቹ ጋር ጎራ ለይተው የተሰለፉ ተቀናቃኝ ቡድኖች ለውይይት እንዲሰበሰቡ ወታደራዊው ሃይል ማክሰኞ እለት በቴሌቪዥን ማሳሰቢያ አሰራጭቷል። ለአመታት ሲወዛገቡ የቆዩትና በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት በየአደባባዩ ሲጋጩ የከረሙት ተቀናቃኝ ፓርቲዎችና ቡድኖች፤ አንድም ጊዜ ተቀራርበው ለመነጋገር ፈቃደኛ አልነበሩም።
ወታደራዊው ሃይል ማሳሰቢያ ባሰራጨ ማግስት ግን፣ ለውይይት ፈቃደኛ ሆነው ተሰብስበዋል። ሁለት ሰዓት ተኩል በፈጀው ውይይት አንዳች የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ባይደርሱም ጥሩ ጅምር ነው ብሏል የወታደራዊው ሃይል ቃል አቀባይ። ፓርቲዎቹ እንደገና ሃሙስ እለት ለመገናኘት ተቀጣጥረው ነበር - በስልጣን ክፍፍልና በምርጫ ዝግጅት ላይ ለመወያየት።
የሃሙሱ ስብሰባ የተካሄደው በጦር ሃይሎች ክለብ ውስጥ ነው። ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በጊዜያዊነት ስልጣን የያዘው ገዢ ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲ፤ እንዲሁም ጎራ ለይተው ከሁለቱ ፓርቲዎች ጋር የተሰለፉ ተቀናቃኝ ቡድኖች ለስብሰባው መጥተዋል። ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የፖለቲካ ቡድኖ ተወካዮች፤ ማክሰኞ እለት እንዳደረጉት ሃሙስ እለትም ወደ ሁለት ሰዓት ገደማ ተነጋግረዋል። ግን፤ ሊስማሙ አልቻሉም። ገዢው ፓርቲ ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደለም። ተቃዋሚው ፓርቲ ስልጣን ካልተሰጠኝ ሞቼ እገኛለሁ ይላል።  ይሄኔ ነው፤ የጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ ጄነራል ፕራዩዝ ቻንኦቻ፤ ትእግስታቸው እንዳለቀ የገለፁት። ተሰብሳቢዎቹም ሆኑ ውይይቱን ለመዘገብ የመጡ ጋዜጠኞች ምን እየተፈጠረ እንደሆነ አላወቁም። “የናንተ ንግግር ማለቂያ የለውም” ሲሉ የተናገሩት ጄ/ል ፕራዩዝ፤ “ከአሁን ጀምሮ፣ ስልጣን በኔ እጅ ውስጥ ገብቷል” በማለት ነገሩን በአጭሩ ቋጩት። ለውይይት የተሰባሰቡት ሚኒስትሮች፣ ተቃዋሚዎች፣ የፖለቲካ ቡድን መሪዎች በዚሁ የሚሰነባበቱ መስሏቸው ነበር። ነገር ግን እዚያው እንደተሰበሰቡ ወደ ምድር ጦር ካምፕ ተወስደው እንዲታሰሩ ነው ጄነራሉ ትዕዛዝ የሰጡት። ፖለቲከኞች ሲወያዩ ለማየት የሄዱ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች ሲታሰሩ አይተው ተመለሱ። በስብሰባው ላይ ያልተገኙ ሚኒስትሮችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ በአንድ ቀን ውስጥ እጃቸውን እንዲሰጡ በሚዲያ ማስጠንቀቂያ ተሰራጭቷል።
የጦር ሃይል ዋና አዛዥ ጄ/ል ፕራዩዝና ምክትላቸው፤ እንዲሁም ኤታማዦር ሹም፣ የባህር ሃይል፣ የአየር ሃይልና የፖሊስ ዋና አዛዦችን ያካተተ የአምስት ጄነራሎች ኮሚቴ፤ የመንግስትን ስልጣን እንደተቆጣጠረ ጄ/ል ፕራዩዝ ገልፀዋል። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ሁሉም የሚዲያ ተቋማት፤ የግል የቴሌቪዢንና የሬድዮ ጣቢያዎችም ጭምር፤ ከወታደራዊው ጁንታ ከሚመጣላቸው ነገር ውጭ ምንም እንዳያሰራጩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ተከልክሏል። የማታ ሰዓት እላፊ ታውጇል።
በአጠቃላይ፤ ከመፈንቅለ መንግስት ጋር ተያይዘው የሚመጡ እርምጃዎች በሙሉ በፍጥነት ተከናውነዋል። ፍጥነታቸው አይገርምም። ታይላንድ በመፈንቅለ መንግስት በኩል፤ ከፍተኛ ልምድ የተከማቸባት አገር ናት። በመቶ አመታት ውስጥ 19 የመፈንቅለ መንግስት ታሪኮችን በማስተናገድር በአለም ቀዳሚ አገር ናት ተብሎላታል።

Read 2559 times