Saturday, 24 May 2014 15:01

በማሌዢያው አውሮፕላን ዙሪያ የሚሰራው ፊልም እያወዛገበ ነው

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

የፊልሙ ታሪክ መቋጫ ገና አልተወሰነም
“ጠመንጃ ምናምን አናሳይም፤ ዩፎዎችንም አናስገባም” - (የፊልሙ ዳይሬክተር ሩፒሽ ፖል)

ከወራት በፊት 239 ሰዎችን አሳፍሮ በበረራ ቁጥር ኤም ኤች 370 ከኳላላምፑር በመነሳት ወደ ቢጂንግ ጉዞ ከጀመረ በኋላ፣ ድንገት ደብዛው ጠፍቶ በቀረውና በአለማችን የበረራ ታሪክ በአሳዛኝነቱና በእንቆቅልሽነቱ በሚጠቀሰው የማሌዢያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በህንዳዊው ዳሬክተር ሩፒሽ ፖል አዘጋጅነት የሚሰራው ፊልም እያወዛገበ መሆኑን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተውንና አስፈሪ (ትሪለር) ዘውግ ያለውን ይህን ፊልም፣ በ35 ቀናት ጊዜ ውስጥ በህንድና በአሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች ቀርጾ ለመጨረስ መታቀዱን የዘገበው ቢቢሲ፣ እውነተኛው አውሮፕላን የደረሰበት ባልታወቀበትና ፍለጋው ሙሉ ለሙሉ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ፣ ፊልሙ ለእይታ መብቃቱን ብዙዎች እንዳልወደዱትና ፊልሙ ገና ከወዲሁ ውዝግብ መፍጠሩን አመልክቷል፡፡
ዳይሬክተሩ ሩፒሽ ፖል፤ ከሳምንት በፊት በተከናወነው የኬንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ እንደተናገረው፣ “ዘ ቫኒሺንግ አክት” የሚል ርዕስ በተሰጠውና 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሎ በተገመተው በዚህ ፊልም ላይ ከ200 በላይ ተዋንያን ይሳተፉበታል፡፡
90 ደቂቃ ርዝማኔ የሚኖረው “ዘ ቫኒሺንግ አክት” ፣ በአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ቤተሰቦች ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይፈጥር የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ክስተቱን ተጣድፈው ለገንዘብ ማግኛ የመጠቀም ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በአውሮፕላኑ ዙሪያ ፊልም እየሰሩ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ተከትሎ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘርባቸውን ትችት እያጣጣሉ እንደሆነ፣ ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
“የአውሮፕላኑ ደብዛ ጠፍቶ መቅረትና በየአቅጣጫው ሲካሄድ የቆየው ፍለጋ ዛሬም ድረስ ምንም አይነት ተጨባጭ ውጤት አለማስገኘቱ፣ በአለምአቀፍ ደረጃ የፈጠረው ውዝግብ፣ በተዘዋዋሪ መንገድ የፊልሙን ተፈላጊነት የሚጨምረው ቢሆንም፤ የኛ አላማ ግን፣ ከዚህ አሳዛኝ የበረራ ታሪክ ገንዘብ ማካበት አይደለም” ብለዋል ፖል፤ ለሆሊውድ ሪፖርተር፡፡
“ፊልሙ በከፊል የፈጠራ ስራ ነው፡፡ ቢሆንም ግን በአውሮፕላኑ ነጥፋት ዙሪያ ሲ ኤን ኤንን ጨምሮ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና ግለሰቦች የሰጡትን መላምት እንደ ግብዓት ተጠቅመናል፡፡ የፊልሙ ዘውግ አስፈሪ ቢሆንም፣ አንዳንዶች በአውሮፕላኑ መጥፋት ዙሪያ የሚሰጡትን አጉል መላምት መሰረት አድርገን በፊልሙ ውስጥ አንዳንድ ዝባዝንኬዎችን አናካትትም፡፡ ጠመንጃ ምናምን አናሳይም፤ ዩፎዎችንም አናስገባም፡፡ ታሪኩ ደግሞ የአምስት ወጣት ጓደኛሞችን የበቀል እቅድና አለምን ቀውስ ውስጥ በሚከት መጨረሻቸው ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ እርግጥ የታሪኩ መጨረሻ ምን መምሰል አለበት የሚለውን አሳሳቢ ጉዳይ በተመለከተ፣ ገና አሁንም ድረስ ይህ ነው የሚባል ውሳኔ ላይ አልደረስኩም” ሲሉም አክለዋል፡፡
የፊልሙን ፕሮጀክት በተመለከተ ነቀፌታ የበዛባቸው ተባባሪ ዳይሬክተሩ ስሪታማ ዱታ በበኩላቸው፣ ይሄ ሁሉ ውግዘት አግባብ አለመሆኑን ገልጸው፣ በእውነተኛው አውሮፕላንና በፊልሙ አውሮፕላን መካከል ያለው ግንኙነትና መመሳሰል፣ ሁለቱም መጥፋታቸው ብቻ ነው ሲሉ ጉዳዩን አስተባብለዋል፡፡ ፊልሙን ፕሮዲዩስ ለማድረግ፣ ከእስያ ሃገራት  በተለይ ደግሞ ከጉዳዩ ዋነኛ ባለቤቶች ከማሌዢያና ከቻይና ኩባንያዎች ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ እንደሚገኝ የተናገሩት ፖል፤ እስከ መጪው መስከረም ወር አጋማሽ ድረስ አጠቃላይ ስራው ተጠናቆ በአለም አቀፍ ደረጃ ለእይታ እንደሚበቃ ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ለሙከራ ብለው የቀረጹትና በኬንስ ፌስቲቫል ላይ ለእይታ ያቀረቡት የደቂቃዎች ርዝማኔ ያለው የፊልሙ ክፍል፣ በአንዲት የአውሮፕላኑ ሰራተኛና በአንድ ሽጉጥ የያዘ ተሳፋሪ መካከል የፍቅር ግንኙነት እንደነበር የሚያመላክት ትዕይንት የያዘ ነበር፡፡ ይህ አጭር ትዕይንት በዩቲዩብ ድረ-ገጽ ተለቆ 140 ሺህ ተመልካቾች ያዩት ሲሆን፣ አንዳንዶች ነቀፌታቸውን በመግለጽ ዳሬክተሩን “እብድ!”፣ “ክብር የሌለው!” እና “ጨካኝ!” ሲሉ ነቅፈውታል፡፡
በሚሰሯቸው ወሲብ ነክ ፊልሞች አነጋጋሪ ሆነው እንደዘለቁ የሚነገርላቸው ዳይሬክተሩ፤ የመጀመሪያ ስራቸው የሆነውን ‘ዘ ቴምፕቴሽንስ ቢትዊን ማይ ሌግስ’ ጨምሮ፤ ‘ካማሱትራ’ (በስሪ ዲ የተሰራ) እንዲሁም ‘ሞኖሎግስ ኦፍ ኤ ሴክስ ማኒክ’፣ ‘ዘ ሴክሬት ዲያሪስ ኦፍ ሞናሊዛ’ እና ሌሎች ፊልሞችን አዘጋጅተዋል፡፡

Read 1662 times