Print this page
Saturday, 24 May 2014 14:56

የዝነኛ ፀሐፍት አስገራሚ እውነታዎች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ዊሊያም ዎርድስዎርዝ (1770-1850)
እንግሊዛዊው ገጣሚ ዎርድስዎርዝ  ገና 15 ዓመት ሳይሞላው ነበር ወላጆቹን በሞት ያጣው፡፡ እንዲያም ሆኖ በእንግሊዝ የተሳካላቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ገጣምያን ተርታ ከመሰለፍ ያገደው ነገር አልነበረም፡፡ ግጥሞችን መፃፍ የጀመረው ገና ተማሪ ሳለ ቢሆንም 23 ዓመት እስኪሞላው ድረስ ግን አንድም የግጥም ሥራው አልታተመለትም ነበር። ዎርድስዎርዝ  የፃፋቸውን ግጥሞች የሚያነበው ለውሻው ሲሆን  ውሻው በተነበበለት ነገር ከጮኸ ወይም ከተበሳጨ፣ ዎርድስዎርዝ ግጥሙን ማሻሻልና እንደገና መፃፍ እንዳለበት ተገንዝቦ ወደ ሥራው ይገባል፡፡
ዲክ ኪንግ-ስሚዝ (1922-2011) በእንስሳት ላይ የተመሰረቱ የህፃናት መፃህፍትን በመፃፍ ይታወቅ የነበረው እንግሊዛዊው ደራሲ ዲክ ኪንግ- ስሚዝ፤በሙያ ዘመኑ ከ100 በላይ መፃህፍትን ፅፏል፡፡ ዝናን ያጎናፀፈው መፅሃፉ The Sheep Pig የተሰኘው ሲሆን ይሄ ሥራው Babe በሚል ርዕስ ወደ ፊልም ተቀይሮለታል፡፡ የመጨረሻ መፅሃፉ በ2007 እ.ኤ.አ የታተመለት ሲሆን The Mouse Family Robinson ይሰኛል፡፡ ደራሲው የፃፋቸው ታሪኮች አሁንም ድረስ በመላው ዓለም በሚገኙ ህፃናት ዘንድ በፍቅር እንደሚነበብለት ይነገራል፡፡


ከ800 ሚሊዮን በላይ መፃሕፍቶችን የቸበቸበችው የረዥም ልብወለድ ፀሐፊዋ ዳንኤላ ስቲል፤ የመጀመርያ ረቂቅ ፅሁፏን እስክታጠናቅቅ ድረስ በጥንት የትየባ ማሽን ላይ በቀን ለ20 ሰዓታት ትፅፋለች፡፡ በአንድ መፅሃፍ ላይ አተኩሮ ከመስራት ይልቅ በአንድ ጊዜ ከ4-5 የሚደርሱ መፃሕፍት ላይ በመስራትም ትታወቃለች፡፡
ጥቂት የማይባሉ የደራሲዋ ልብወለዶች ወደ አማርኛ ተተርጉመው ለአገራችን አንባቢያን መቅረባቸው የሚታወቅ ሲሆን ወደ ፊልም የተቀየሩ ሥራዎቿም በቅዳሜ የታላቅ ፊልም ፕሮግራም ላይ ለተመልካች  ይቀርቡ ነበር፡፡


ስቲፈን ኪንግ
ከ350 ሚሊዮን በላይ ኮፒዎች የተሸጡለት ይሄ አሜሪካዊ ደራሲ፤ ምንም ሳያስተጓጉል በየቀኑ ስድስት ገፆች ገደማ  ይፅፋል፡፡ በቀን ከ4 እስከ 6 ሰዓታት ማንበብና መፃፍ የማይችል ሰው ታላቅ ፀሐፊ የመሆን ህልሙን ይርሳው ሲልም ደራሲው ያስጠነቅቃል፡፡  
የድርሰት ትምህርት አንድን ሰው የመፃፍ ክህሎት ያስታጥቀዋል ብሎ የማያምነው ስቲፈን ኪንግ፤ ደራሲነት ከተፈጥሮ የሚገኝ ፀጋ ነው ባይ ነው፡፡ የመጀመርያ ድርሰቱን በ7 ዓመት እድሜው የፃፈው ኪንግ፤ ይሄን ድርሰት በ18 ዓመቱ ለአንድ መፅሄት እንደሸጠው ተዘግቧል፡፡ Carrie የተሰኘውን የመጀመርያ ልብወለዱን ከፃፈ በኋላ በተወዳጅ አስፈሪ (horror) ልብወለዶቹ እየታወቀ የመጣ ሲሆን የመጀመርያ አስፈሪ መፅሃፉም The Shining ይሰኛል፡፡  

አሜሪካዊው የልብ አንጠልጣይ ረዥም ልብወለዶች ደራሲ ዳን ብራውን፤ በሳምንት ለ7 ቀናት ሳያሰልስ በመፃፍ ይታወቃል - ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ፡፡  ይሄ የቀድሞ የእንግሊዝኛ መምህር፤ ዳቪንቺ ኮድ በተባለው ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ ልቦለድ መፅሐፉ የሚታወቅ ሲሆን ይሄ ልቦለድ  በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ እየተተረጎመ ሲወጣ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

Read 3512 times
Administrator

Latest from Administrator