Saturday, 24 May 2014 14:55

ይዘት የለውም’ ነው ‘ዘይት የለውም’?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ዮናስ አብርሃም - የ“ትንንሽ ፀሀዮች” ደራሲና አዘጋጅ    

  “የትንንሽ ፀሐዮች” ተከታታይ የሬድዮ ድራማ በድንገት መቋረጡን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ ዕትም“ጥበብ” አምድ ላይ ቃለ-መጠይቅ እንደተደረገልኝና የጣቢያው ተወካይም ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
በቅድሚያ ሀሳባችንን ለማስተናገድ ዕድል ስለተሰጠን አዲስ አድማሶችን ላመሰግን እወዳለሁ። በማያያዝም፣ ከጣቢያው የተሰነዘረው ምላሽ ከዕውነታው የራቀ በመሆኑ መልስ ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡
ድራማውን ማቋረጥ ያስፈለገው በሁለት ምክንያቶች መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ አንዱ ምክንያት፡- “እንደማንኛውም ድራማ የሆነ ጊዜ ተጀምሮ ማለቅ ስላለበት ነው” ተብሏል፡፡ ይህ ምክንያት በመልስነት መቅረቡ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ታስቦበት የተጀመረ ስራ በታሰበበት መንገድ መጠናቀቅ ነበረበት። ‘ማለቅ’ የሚለው ቃል ደስ አይልም፡፡ ለሕዝብ የቀረበ ትልቅ ስራ እንዲያልቅ ስለተፈለገ በጣቢያው ውሳኔ ብቻ ‘ማለቅ’ የለበትም፡፡ እንዲቋረጥ ከተፈለገ ብዙ ቀና መንገዶች አሉ፡፡ ጊዜውንና ፈቃዱን ለሰጠ አድማጭ ስሜት ማሰብ ግድ ነው፡፡ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሕዝቡ ባለቤት መሆኑ አይካድም፡፡ እኔ በማይመቹ ሁኔታዎች ውስጥ ስሰራ የቆየሁት፣ አድማጩንና የሙያ ስነምግባርን አክብሬ እንጂ የሚያጓጓ ጥቅም ስላገኘሁ፣ ወይም ሌላ ዕድል አጥቼ አልነበረም፡፡
የከፈልኩትን መስዋዕትነት፣ ያደረግሁትን ልዩ ጥረት… በቅርብ ያሉ ሁሉ ይረዱታል፡፡ ሠፊው አድማጭም የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡ ‘ማለቅ ስላለበት’ ብቻ ‘አልቋል’ ተብሏል፡፡ ለነገሩ “ጉመደው፣ አስወግደው” የሚሉ ቃላት አዲስ አይደሉም፡፡
ሁለተኛው ምክንያት፡- “ድራማውን ከአድማጭ በሚመጣ አስተያየት እንገመግመዋለን፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይዘት አልባ ሆነ የሚሉ አስተያየቶች ተበራከቱ” የሚል ነው፡፡ ‘ይዘት አልባ’ የሚለው ግምገማ ግልፅ አይደለም፡፡ ከጣቢያው ምስረታ ማግስት ጀምሮ በጋዜጠኝነትና በድራማ ፀሐፊነት (Playwright) የሠራ ሰው ‘ይዘት አልባ’ ስራ ይዞ አድማጭ ፊት አይቀርብም፡፡ ድራማዎች ሁሉ አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡ አስተያየቱ አንድ ናቸው ከሚል ድምዳሜ የመጣ ይመስላል፡፡ የዚህ ዓይነቱን አፃፃፍ በራሴ ጥረት አንብቤ የጀመርኩት እንጂ ቴክኒኩና ፈጠራው ከጣቢያው አልተሰጠኝም፡፡ ድራማው በእኛ ካላንደር (ቀን መቁጠሪያ) ከእኛ ጋር የሚራመድ ታሪክ ስለሆነ እንጂ ዝግ ብሎ መሄዱ በስንፍና የመጣ አይደለም፡፡
በገፀ-ባህርያት ላይ የተመሠረተ ወቅታዊ ድራማ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ‘ይዘት አልባ’ ፕሮግራም መስራትን ጣቢያው አላስተማረኝም፡፡ ሚዛናዊነት አንዱ የጋዜጠኝነት ማዕዘን ነው፡፡ ሚዛናዊነቱ ለእኔ ካልሰራ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሌላ ምክንያት ቢፈለግ ጥሩ ነበር። “በቃ! አልፈለግነውም” ማለት ከባድ አይደለም። በመላ ሀገሪቱ ድራማውን በጉጉትና በአድናቆት የሚከታተሉት አድማጮች ጊዜያቸውን የሠጡት ‘ይዘት አልባ’ ለሆነ ነገር ከሆነ፣ በዕድሜና በዕውቀት የሚበልጠንን ሠፊ አድማጭ አለማክበር ነው፡፡
በመሠረቱ፣ እኔ የአለቆችን ስሜት እያነበብኩ የምሰራ ሰው አይደለሁም፡፡ እንደ ጣቢያው ሁሉ፣ የእኔም መለኪያ ሕዝብ ነው፡፡ ፈራጁ ተደራሲው ስለሆነም ስሜቱን በትኩረት እከታተላለሁ፤ ባለኝ መረጃ መሠረትም በጥሩ አቋም ላይ ነበርኩ፡፡ እነማን ምን እንዳሉ እኔ አላውቅም፡፡ በእኔ በኩል ግን… ሕዝብ ያልወደደውን ነገር በግድ ለመጋት ምን ምክንያት ይኖረኛል? ብዙ የጥቅም ዕድሎችን ሰውቼ ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ የቆየሁት፣ ደመወዝ ከፋዩ ሕዝብ ስለሆነ ውዴታውን አክብሬ፣ ለፍላጎቱ ተገዝቼ ነው፡፡
‘ይዘት የለውም’ ከሚባል ‘ዘይት የለውም’ ቢባል በአክብሮት እቀበል ነበር፡፡ ያለ እረፍት ለአምስት ዓመታት በየቀኑ እየፃፉ፣ በየሣምንቱ እየቀረፁ መዝለቅ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማሰብ አለመፈለግ ለደራሲው ያለውን ስሜት ያሳያል፡፡ ሕዝብ ግን ያውቀዋል፤ አድናቆትን ብቻ አይደለም ምርቃትም ስቀበል ኖሬአለሁ፡፡
“ተዋንያኑ እየለቀቁ በመሄዳቸው ድራማው ተዳከመ” የሚል አስገራሚ አስተያየት ተሰንዝሯል። ብቸኛው ደራሲና አዘጋጅ ችግር ገጥሞኛል ብሎ ካላመለከተ፣ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ አይደለም ማለት ነው፡፡
ተመስገን መላኩ (ቅቤው) ወደ አሜሪካ እንደሚሄድ የተነገረው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር። በተለያየ ምክንያት ዘግይቶ ከስድስት ወራት በፊት ለስራ ሄደ፡፡ ስለዚህ ድራማው እንዳይጎዳ በቂ ጊዜ ነበረኝ ማለት ነው፡፡ እኔ ደራሲ ነኝ፣ ደራሲ ችግሮቹን ለመፍታት ብዙ መንገድ እንዳለው የሚፅፍ ሰው ያውቀዋል፡፡ የሚወደዱ ገፀ-ባህርያት ከስራው ገለል ሲሉ መናፈቃቸው ያለ ቢሆንም ገፀ-ባህርያቱ ግን ከደራሲው ሀሳብ ስር ናቸው፡፡ ከተፈለገ፣ ግድ የሚል ችግር ቢመጣም - ባይመጣም ከድራማው የሚወጡበት አሳማኝነት ያለው ጥበባዊ መብት በደራሲ እጅ እንዳለ ይታወቃል፡፡
በረከት በላይነህ (አመዶ)፣ ‘ድራማው አይመጥነኝም ብሎ መውጣቱን’ የሰማሁት ጣቢያውን ወክለው ከተናገሩት ኃላፊ ነው፡፡ እሱ፤ አላለም - አይልም፤ ለዚህ ደግሞ መላው የድራማው አባላት ምክንያቱን ያውቃሉ፡፡ ድራማው በጥድፊያ ‘አለቀ’ ተብሎ በተነገረ በሣምንቱ በረከት (አመዶ) የሰጠውን አስተያየት ማድመጥ ይቻላል፡፡
ለጥቂት ሣምንታት ድም    ፁ ባይኖርም፣ እኔ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሜ በማሰብ ጥንቃቄ ስለማደርግ፣ ሲጀመር ከነበረው ታሪክ ጋር ተያይዞ እንዲሄድ ተደርጓል፡፡ “አመዶ የት ሀገር ነው የሄደው… ለምንድነው የሄደው?” ብዬ በመጠየቅ ‘ይዘት አልባ’ ሆነ የሚሉትን ትዝብት ውስጥ ለመክተት አልፈልግም፡፡
ዋናዋ እና ተወዳጇ ገፀ-ባህሪ ሠብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ) ለስራ ጉዳይ እንግሊዝ ስትሄድ፣ ድራማው ጣዕሙን እንደጠበቀ አቆይቼዋለሁ፡፡ ይህንን አድማጮች ይመሰክራሉ፡፡ የእማማ ጨቤን ክፍተት ለመሙላት በጥንቃቄ ተቀርፀው የገቡት እህታቸው (እትየ ጩጩባ) በጥቂት ሣምንቶች ውስጥ ተወዳጅ መሆን የቻሉት ስላላሰብኩበት አይደለም፡፡  
እውነቱን ለመናገር ጣቢያው በእኔ ስራዎች ላይ እምነት አጥቶ፣ ጥርጣሬ አድሮበት አያውቅም። እኔ የሚጠላ ባህርይ አለኝ ብዬ ባላስብም አልተወደድኩም ብዬም አላዝንም፡፡ እንዴት መወደድ እንደሚቻል ግን አውቃለሁ፡፡
“ድራማው ካለቀ ዓመት አልፎታል” ተብሏል። ለእኔ ሲባል ከሆነ የቆየው ስህተት ነው፡፡ አንድ ግለሠብ ከመላው አድማጭና ሕዝብ አይበልጥም። ዓመት ሙሉ በሕዝብ ጆሮ ላይ ‘ይዘት አልባ’ የሆነ ድራማ ማስተላለፍ የማይመስል ነገር ነው።    ሌላው፡- “ዓመቱን ሙሉ ደብዳቤ እየፃፍን ቆይተናል” ለተባለው ደብዳቤውን ማን እንደተቀበለልኝ አላውቅም፡፡ ሁለት መልስ መስጠት ያልፈለግሁባቸው ደብዳቤዎች በግዳጅ እንደተሰጡኝ አልካድኩም፡፡
“… በነገራችን ላይ ተከታታይነት ያለው ታሪክ የያዘ ድራማ አይደለም፡፡ በየሣምንቱ አዳዲስና የተለያዩ ታሪኮችን ይዞ የሚመጣ ድራማ ነው። ስለሆነም እርሱ ቅን ቢሆንና ቢያስብበት በሦስት ሣምንት ለማጠቃለል የሚያስቸግር ነው ብዬ አላስብም” ብለዋል - የጣቢያው ተወካይ፡፡ ለዚህ ምን መልስ መስጠት ይቻላል? ብዙ ዓይነት ድራማዎች አሉ፡፡ የእኔ ድራማ ምን ዓይነት ባህሪ እንዳለው አድማጭ በሚገባ ይረዳል፡፡ “አዳዲስ ሃሳቦችን ይዞ የሚመጣ ድራማ ነው” ከተባለ በኋላ ‘ይዘት አልባ’ ነው መባሉን አትዘንጉብኝ፡፡
በሀገራችን አዲስ ባህሪ ያለው ረጅምና ተከታታይ ድራማ መሆኑን ማድነቅ ባይቻል በአግባቡ ማወቅ ግን ተገቢ ነበር፡፡ “ቅን ቢሆንና ቢያስብበት…” ለተባለው ለማቋረጥ ምን ቅንነት ያስፈልጋል፡፡ ማሰብ የነበረብኝስ ምንድን ነው?
በበኩሌ ሀሳቤን ለመሰንዘር የተነሳሁት ባሰብኩት መንገድ አልጨረስኩትም ለማለት ብቻ ነው፡፡ ቅንነትን ልጠየቅ የምገባው እኔ አልነበርኩም። ለእያንዳንዱ ነገር መልስ መስጠት ቢቻልም ቃለ ምልልሶቹን ያነበቡ ሰዎች ራሳቸው ስለሚፈርዱ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቤያለሁ፡፡
በጣም ያስገረመኝ ነገር ግን አለ፤ ለእኔ መልስ ለመስጠት የተወከሉት የፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሆኑን አስምሩልኝ፡፡ አንድ ድምፅ ይዘው የመጡ የጣቢያው አፍ መሆናቸውን “እኛ” እያሉ በሰጡት ምላሽ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ስለ ስራው የሚያውቀው ማን ነበር? በስተኋላ የመጡት የአስተያየት ሰጪው የስራ ድርሻ ከዚህ ጉዳይ ጋር ባይገናኝም፣ “እኛ… የድራማው ደራሲ እሱ መሆኑን አናውቅም ነበር። … ያኛው ሰው ደራሲ ነኝ ብሎ መጥቶ ገንዘብ ይወስዳል… ይህንን ሁሉ ያወቅነው ከጋዜጠኝነት ስራው ከፋና ከለቀቀ በኋላ ነው፡፡” የሚያሳፍር ስህተት ብቻ አይደለም፡፡ ስምን አጉድፎ ስብዕናን ዝቅ ለማድረግና ለመወንጀል የታለመ ንግግር ነው። የባለቤትነትን መብት ለማጣረስ የተፈበረከ ውዥንብርና ውንጀላ ነው፡፡
የዚህ መልስ አጭርና ግልፅ ነው፡፡ “ያ-ሰው” የሚባል ፀሐፊና ገንዘብ ወሳጅ አልነበረም። የለፋሁበትን ፈርሜ የምወስደው እኔው ራሴ ነበርኩ፡፡ ይህንን ድራማ ለማስጀመር ከብቸኛ ስፖንሰር አድራጊው ዲኬቲ ኢትዮጵያ ጋር ድራማውን በተመለከተ ብዙ ስብሰባዎች የተካሄዱበትን ድርድር ከሽያጭ ክፍል ሠራተኞች ጋር በመሆን የተወጣሁት እኔ ነኝ፡፡ ሲኖፕሲስ (አፅመ-ታሪክ) አቅርቤ፣ የድራማውን ባህሪ አስረድቼ፣ ድራማው ተደማጭና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርቼ … አየር ላይ ውሏል፡፡ ድራማው ካለቀና አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ በዚህ ዓይነት ስም ማጥፋት በአደባባይ መቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡  
ድራማው እንዴት እንደተጀመረ፣ በምን መንገድ እንደተጀመረ፣ ሲጀመር ለትንሽ ጊዜ በብዕር ስም ለምን እንደፃፍኩ… እዛው ቢጠይቁ ኖሮ መልስ ያገኙ ነበር፡፡ በብዕር ስም ፅፌ ክፍያዬን ስቀበል ይኼ የመጀመሪያዬ ነው እንዴ? እኔስ የመጀመሪያው ሰው ነኝ?! አይደለሁም፡፡
ምንም እንኳን ለውስጥ ሰራተኞች ተጨማሪ ክፍያ የማይታሰብ ቢሆንም በጋዜጠኝነት እየሰራሁ ለድራማው ‘በደቂቃ 20 ብር’ ይከፈለኝ የነበረው ልዩ ተሰጥዖን የሚጠይቅ ስራ ስለሆነ ነው፡፡ የመስሪያ ቤቱ  ባልደረባ የመዝናኛ ክፍል ኃላፊ ሆኜ ድራማውን መፃፍና ማዘጋጀት ስጀምር፣ ከደመወዜ በተጨማሪ 1,800 ብር የሚከፈለኝ በጋዜጠኝነት እንጂ በደራሲነት ስላልተቀጠርኩ ነው፡፡ ከ70ኛው ክፍል በኋላ ድርጅቱን ለቅቄ ስወጣ፣ በደቂቃ 80 ብር እንዲከፈለኝ ተስማምተናል፡፡ የመጨረሻዎቹን አስራ ስድስት ወራት አካባቢ ደግሞ ክፍያዬ በደቂቃ 100 ብር ደርሷል፡፡ በጠቅላላ በወር 10 ሺህ ብር ማለት ነው፡፡
ለተሰጥኦ (Talent) ብዙ እንደሚከፈል መንገር አይገባኝም፡፡ ተወካዩ ከፍተኛ ገንዘብ ያሉት ይህንን ከሆነ፣ ውጪ ያለውን ገበያና ክፍያ አያውቁትም ማለት ነው፡፡  
ሠብለ ተፈራ በእማማ ጨቤ ገፀ-ባህሪ ተዋናይነቷ፣ በኋላ ላይ ጭማሪ ተደርጎላት እንኳ በወር የምትወስደው 2 ሺህ ብር አይሞላም፡፡ ሁላችንም ስለ ገንዘብ ሳይሆን ስለ ሙያው ፍቅር እንደምንሰራ ጣቢያው አልተረዳም፡፡
“ድራማው የኛ ነው” ማለት በጣም ያስገምታል፡፡ ጣቢያው በድራማው ላይ ያለውን ባለቤትነት ማወቅ ካስፈለገ… ወጪ ስላወጣበት እና ገንዘብ ከፍሎ ስላሰራ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ እስካሁን በተቀረፁት ላይ ሙሉ ባለቤትነት እንዳለው ግልፅ ነው፡፡ መረዳት የሚያስፈልገው ነገር የአንድ ደራሲ የአዕምሮ ፈጠራ ውጤት እንደመሆኑ፣ ቢያስፈልግ ፅሁፉን በሌላ ስቱድዮ በራስ ወጪ በመቅረፅ መጠቀም ይቻላል፡፡
በቀጥታ ያልተዋዋልንበት የስራ ግንኙነት ተቋርጧል፡፡ ለአመታት የተላለፉትን መደምሰስ ከተፈለገ ችግር የለም፡፡ ገፀ-ባህሪያቱን ግን ማክሰም አይቻልም፡፡ የአዕምሮዬ ውጤት የሆኑት ገፀ-ባህሪያት ባለቤት እኔው ብቻ ነኝ፡፡
ጣቢያው ትልቅ ቢሆንም ከዕውነትና ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ አሁንም እላለሁ፡- “በእኔ በኩል ድራማውን ፅፌ አልጨረስኩም!!”          

Read 1564 times