Saturday, 24 May 2014 14:41

ራሱን ከመምህርነት ወደ ኢንቨስተርነት የቀየረው ህንዳዊ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

በትምህርት፣ በሆቴልና  በአስጎቢኝነት ዘርፎች ተሰማርቷል
በአፍሪካ ስመጥር ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት አቅዷል

የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘው በአካውንቲንግ ነው፡፡ በአገሩ ሕንድ በዚሁ ሙያ አስተማሪ ነበር። ሁለተኛ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ ከማስተማር በተጨማሪ የማማከር አገልግሎትም ይሰጥ እንደነበር ገልጿል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በ2001 (እ.ኤ.አ) ሲሆን የያኔው ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመምህርነት ቀጥሮት ነበር፡፡ ሆኖም በኮሌጁ ከሦስት ዓመት በላይ አልቆየም፤ ጥሎ ወጥቶ የራሱን ቢዝነስ ጀመረ፡፡
ታሪኩን የማወጋችሁ ህንዳዊ፤ የስሪ ሳይ (SRI SAI) ኮሌጅ፣ ደንበል ሲቲ ሴንተር ፊት ለፊት አበሩስ ህንፃና ኦሎምፒያ አካባቢ የሚገኙት ስሪ ሳይ የእንግዳ ማረፊያና ሆቴል እንዲሁም በተመሳሳይ ስም የሚጠራው የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ሚ/ር ረዲ ኤል ጂ ነው፡፡
የ41 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ሚ/ር ረዲ፤ አዲስ አበባ መኖር ከጀመረ 13 ዓመት አስቆጥሯል፤ የ28 ዓመት ወጣት ሳለ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው፡፡ አገሪቷ ከሰሩባት ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለእንግዶችም ትመቻለች ማለት ነው ያሉት የቀድሞ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ መምህር ስለ ሚ/ር ረዲ ሲናገሩ፣ “ሚ/ር ረዲ የሚደንቅ ሰው ነው፡፡ ከእሱ ብዙ መማር ይቻላል፡፡ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የለቀቀው ከኮሌጁ ባለቤት  ከዶ/ር ፍስሐ እሸቱ ጋር ባለመስማማቱ አባርሮት ነው፡፡ እሱ ግን ኢትዮጵያ ለቢዝነስ ምቹ መሆኗን ተገንዝቦ ስለነበር፣ አገሩ ሄዶ በራሱ መንገድ ተመልሶ መጣ፡፡ ይኼው አሁን ጥሩ እየሰራ ነው፡፡ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአገርና ለዜጎችም ጥቅም ፈጥሯል፡፡ ያኔ አገሩ እንደተመለሰ በተሸናፊነት ስሜት ቀርቶ ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ የለም፡፡ ሚ/ር ረዲ መጥፎ አጋጣሚን ወደ መልካም እድል የለወጠ ሰው ነው፣ ከእሱ ብዙ መማር ስለሚቻል ላማክረው አስቤአለሁ” ብለዋል፡፡
ሚ/ር ረዲ እንዴት ወደ ቢዝነስ እንደገባ ሲያስረዳ፣ “በወቅቱ መንግሥት የውጭ ኢንቨስተሮች መጥተው በአገሪቷ እንዲሰሩ ይፈልግ ነበር፡፡ ይህም ጥሩ አጋጣሚ ሆነኝ፡፡ በፊትም የማማከር ልምዱ ስለነበረኝ፣ ከአገሬና ከመላው ዓለም ኢንቨስተሮች አምጥቼ ቢዝነስ እንዲጀምሩ ለማድረግ በእንቅስቃሴያቸው ልረዳቸው የምችልበትን የአማካሪ (ኮንሰልተንሲ) ድርጅት በ2004 (እ.ኤ.አ) በ50ሺ ዶላር ከፈትኩ” ብሏል፡፡
በማማከሩ ሥራ ሁለት ዓመት ከሠራ በኋላ ሌላ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ቀደም ሲል ሲያስተምራቸው የነበሩ ጎበዝ ተማሪዎች “የማስተርስ ፕሮግራም መቀጠል እንፈልጋለን፣ ለምን አትጀምርም?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ የማስተርስ ፕሮግራም መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ቁጥር ብዙ ስለነበር “ገበያው ጥሩ ከሆነ ለምን አልጀምርም?” የሚል ሐሳብ መጣለት። ማሰብ ብቻ ሳይሆን “መክፈት ካለብኝ፣ በአገሬ በትምህርት አሰጣጥ ጥራት በጣም ጥሩ ስም ካለው ዩኒቨርሲቲ ጋር ነው መሥራት ያለብኝ” በማለት ወሰነ። ከዚያም በሕንድ ታዋቂ የሆነውን ስኪም ማኑፖል ዩኒቨርሲቲን አነጋገረ፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሙም በአዲስ አበባ በስሙ ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ስለተስማማ፣ በ2006 (እ.ኤ.አ) ሴሪ ሳይ ኮሌጅን በመክፈት የማስተርስ ፕሮግራም መጀመሩን ሚ/ር ረዲ ይናገራል፡፡
ኮሌጁ ትርፋማ እየሆነ ሲመጣ፣ ለምን በሌላስ ዘርፍ አልሞክርም? በማለት የእንግዳ ማረፊያና ሆቴል በ2008 ዓ.ም ከፈተ፡፡ ከዚያም ኮሌጁን በማስፋፋት ከማስተርስ ፕሮግራም በተጨማሪ በመጀመሪያ ዲግሪ የሚያስተምር ኮሌጅ አቋቋመ። ቢዝነሱ እየሰመረለት ሲሄድ የበለጠ ማስፋፋት ፈለገ። ስለዚህ ከእንግዳ ማረፊያና ከሆቴሉ ጋር የሚሄድ ነገር አሰበና፣በቀጣዩ ዓመት አስጎብኚ ድርጅት ከፈተ፡፡ አሁን ሚ/ር ረዲ በትምህርት፣ በሆቴል፣ በእንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ ዘርፎች ተሰማርቶ እየተጋ ይገኛል፡፡
ኮሌጁ በመጀመሪያ ዲግሪ አካውንቲንግ፣ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽንና ኮምፒዩተር ሳይንስ እያስተማረ ነው፡፡ የትምህርት መርሐ ግብሩ ያነሰው የተለያየ ትምህርት የሚሰጡ ተፎካካሪ ኮሌጆች በየጊዜው ስለሚከፈቱ እንደሆነ ሚ/ር ረዲ ይናገራል፡፡
ስሪ ሳይ ሲኪም ማኑፖል ዩኒቨርሲቲም ለማስተርስ ፕሮግራም መደበኛና የተልዕኮ ትምህርቶችን ይሰጣል፡፡ በመደበኛው ማስተርስ ኦፍ ኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ማስተርስ ኦፍ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ያስተምራል፡፡ በተልዕኮ ደግሞ ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (ኤምቢኤ)፣ማስተርስ ኦፍ ኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ማስተርስ ኦፍ ኢንፎርሜሽን ሳይንስ፣ ማስተርስ ኦፍ ጆርናሊዝም ኤንድ ማስ ኮሙኒኬሽን ይሰጣል፡፡ ለማስተርስ ዲግሪ የምናስከፍለው ዋጋ ተመጣጣኝ ነው ያለው ሚ/ር ረዲ፤ ለመደበኛ ማስተርስ ዲግሪ 38ሺ ብር፣ ለተልዕኮው ደግሞ 48 ሺህ ብር መሆኑን ገልጿል። ኮሌጁ ቀደም ሲል ለበርካታ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድልና የኪስ ገንዘብ (ፖኬት መኒ) መስጠቱን የጠቀሰው ባለሀብቱ፤ አሁንም ሁለት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ በነፃ ለማስተማር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ አንደኛው መስፈርት ከፍተኛ ውጤት ኖሯቸው በድህነት ወይም በሌላ ችግር ምክንያት ከፍለው መማር ለማይችሉ ወጣቶች ነው፡፡ ሌላው በሚሰለጥኑበት የትምህርት ሙያ ማኅበረሰባቸውን ማገልገል ለሚፈልጉ የገጠር አካባቢ ወጣቶች ነው፡፡ ሚ/ር ረዲ መመዘኛውን የሚያሟሉ ገርጂ በሚገኘው የኮሌጁ ጽ/ቤት እንዲመዘገቡ ጠቁሟል፡፡
የአስጎብኚነት ስራው አትራፊ ባይሆንም አክሳሪ ግን አይደለም፡፡ የቱሪዝም ሥራ ከመሰረተ ልማት መሟላት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መንገድ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መብራት፣ የቴሌኮሙኒኬሽን መገናኛ፣ ንፁህ ማረፊያ ሆቴል፣ ጥራቱን የጠበቀ ምግብ፣ … ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ነገሮች የተሟሉ አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ በአሁኑ ወቅት የዓለም ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ከድቀት ስላልወጣ፤ የቱሪስቶችን ቁጥር ለማሳደግ  እያላመድን ነው ብሏል፤ ሚ/ር ረዲ፡፡
ኢንቨስተሩ ወደፊት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ስመ ጥርና ገናና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመገንባት እቅድ አለው፡፡ ለዚህ ዩኒቨርሲቲ መገንቢያ የሚሆን ቦታ ከመንግስት ጠይቋል፡፡ “መንግስት የጠየቅሁትን ቦታ ከሰጠኝ እሰየው ነው፡፡ ባይሰጠኝ እንኳ መሬት ከግለሰብ ገዝቼ እሰራለሁ እንጂ እቅዴ አይቀርም” በማለት ቁርጠኝነቱን ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ብትሆንም ከተቀሩት የአፍሪካ አገራት የዕድገት ማነቆዎች የፀዳች አይደለችም ይላል ሚ/ር ረዲ። ብዙ ችግሮች ቢኖሩም የካፒታል አቅርቦትና የባለሙያ እጥረት፣ የምርታማነት ማነስ፣ ወጥ ፖሊሲ ያለመኖር፣… በዋናነት እንደሚጠቀሱ ገልጿል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማለፍ የሚቻለው ሁሉም ሰው ለዚህች አገር ቀና አስተሳሰብ ሲኖረው ነው ብሏል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁሉም ሰው በተገኘው ለውጥ ረክቶ ከመቀመጥ ይልቅ ለተሻለና ለበለጠ ለውጥና ዕድገት በርትቶ  መስራት አለበት ሲልም ምክሩን ለግሷል፡፡
ሚ/ር ረዲ በአሁኑ ወቅት ከ120 እስከ 150 ላሉ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ገቢውም እያደገ መሆኑን ተናግሯል፡፡            

Read 2491 times