Saturday, 24 May 2014 14:37

ራስ - በራስ - ለራስ

Written by  ተስፋዬ ይሁኔ
Rate this item
(0 votes)

አገራችሁን የአፍሪካ ቀንድ ሳይሆን
የአፍሪካ ጭንቅላት ማድረግ እየቻላችሁ አላደረጋችሁም”

እውነት እውነት እላችኋለሁ… በምድር ላይ እንዲህ ያለ ቦታ አለ ብሎ ሰው ቢነግረኝ፣ ከቶውንም አላምንም ነበር፡፡ አልጠብቅማ! አልገምትማ! ምክንያቱም እንዲህ አድርጎ መስራት የሚችል ፈጣሪ ብቻ መሆኑን ስለማምን ነው፡፡
አንድርው መንደር ትባላለች፡፡ በካናዳ፣ በኞቫ ስኮሽያ ክ/ሃገር የምትገኝ መንደር ናት፡፡ የሃገራችን ከተሞች አንድ ቀበሌ ያህል ህዝብ ይኖርበታል፡፡ አንድርው መንደር፣ አረንጓዴ ስጋጃ የተነጠፈበት የሚመስል መልክዓ ምድር ያላት ሲሆን ሊኖሩባቸው ቀርቶ ሊዳብሷቸው የሚከብዱ መኖሪያና መስሪያ ቤቶች ያሉባት፣ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ የሆነባት ምድራዊት ገነት ነች፡፡ በመንደሩ ውስጥ ያሉ የውሃ፣ የመብራት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የመዝናኛ፣ የማህበራዊ መስተጋብር ወዘተ… አገልግሎቶች በፈጣሪ ተሰናድተውና ተቀናጅተው፣ በሰው እጅ ለሰዎች የሚቀርቡ ይመስላሉ፡፡ ከመንደሩ ለምነት የተነሳ የሚተነፈሰው አየር፣ ከኦክስጅንም በላይ የሆነ ኦክስጅን ነው፡፡ በጸደይ ወራት ፀሐይ ጨረሯን ሳታሳርፍበት ላስተዋለ አንድርው መንደር፣ በህብረ ቀለማት ከማሸብረቋ የተነሳ፣ በውስጧ የሚንቀሳቀሱ አናፍስት ሁሉ ከቶ የምድር አይመስሉም፡፡
በአንድርው መንደር ውስጥ ሆኜ ያደግሁበትን አካባቢ ሳስብ አነባሁ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተዘዋውሬ ያየኋቸውን የሀገሬን አካባቢዎችና መንደሬን ባሰብኩ ጊዜም ቆዘምኩ፡፡ በቦታው ድንቅነት፣ በማህበረሰቡ ኑሮ አይነፀሬነት በመደመም፣ ስለ አንድርው መንደር ለማወቅ ጓጓሁና ወደ አንድ የ71 ዓመት አዛውንት ጠጋ አልኩኝ፤ ራሴንም አስተዋወቅኋቸው፡፡ እሳቸውም ኢትዮጵያን ቀድመው ያውቋት ነበርና “ሀበሻ ነሃ!” አሉኝ፤ እኔም የሃበሽነት ወኔዬ መጣና “እንዴታ!” አልኳቸው፡፡
ፈገግ ብለው “ያች ሃገር ተለውጣለች ማለት ነው… ኮራ ብለህ እንዴታ የምትለኝ?” ሲሉኝ፣ ቅስሜ ስብር አለ፡፡ የተለመደ ቁስሌን ሊነኩት እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ “ኢትዮጵያን የማውቃት ያልተገባትን ድህነት ወድዳና ፈቅዳ የለበሰች፣ በዚህ የድህነት ልብሷም የምትመካ ሃገር ሳለች ነበር፡፡ ይሄ ነገር ተቀይሯልን?!” አሉኝ፤ በጥርጣሬ ስሜት ተሞልተው፡፡
አዛውንቱ፤ በጠየቁኝ ጥያቄ የተነሳ፣ ጸጉሮቼ ሲቆሙ፣ አንዳንዶቹም ሲሰባበሩ በማስተዋላቸው  “ሀበሻ፤ የእኔውን ተወውና ወዳንተ ጥያቄ እንግባ” አሉኝ፡፡ እኔም እንደምንም ስሜቴን ለማረጋጋት ሞከርኩኝና፤
“አባት፤ ይህን መንደር ፈጥሮና አሰናድቶ የሰጣችሁን ፈጣሪ አግኝቼው በተማጸንኩትና የኢትዮጵያን መንደሮች በሙሉ እንዲህ ባደረገልኝ” አልኳቸው፡፡ እሳቸውም ፈገግ አሉና፤ “መንደሩን የሰራውና እንዲህ የምታየውን አይነት ኑሮ እንድንኖር ያደረገው ሰው የሚሉት ፍጡር ነው፡፡ አዎ! እኛው ራሳችን ነን እንዲህ አድርገን የሰራነው፡፡” ሲሉ መለሱልኝ፡፡
አዛውንቱ የሚሉትን አምኖ ለመቀበል ስለከበደኝ፤ “አምላክ ሆይ፤ እባክህ አለማመኔን ገስፀው” አልኩና “እንዴት?” አልኳቸው፡፡
“ይህ አካባቢና እኛው ራሳችን ከዓመታት በፊት በጠኔ፣ በርዛት፣ በተመጽዋችነት፣ በበልቶ አላዳሪነት፣ በበይ ተመልካችነት ….ነበር የምንኖረው። ከጊዜያት በኋላ ግን በተወሰኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተነሳሽነት፣ የአካባቢን ሃብት መሰረት ያደረገ የማህበረሰብ ልማት ስራ ውስጥ ገባን፡፡ አየህ! በተለመደው መንገድ ችግሮቻችን ከመለየትና ድጋፍ ፍለጋ ከመሄድ ይልቅ ጥንካሬዎቻችንንና መልካም አጋጣሚዎቻችንን በሙሉ ለየን፡፡ የማህበረሰባችንን አጠቃላይ ተሰጥኦዎች በሙሉ ነቅሰን አወጣን፡፡ የማህበረሰቡ አባላትን ክህሎቶችና ችሎታዎች በሙሉ ዘረዘርን፤ በአካባቢያችን ያሉ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ማናቸውንም ነገሮች በሙሉ ለየን፡፡ እናማ በጊዜ ሂደት ያለማንም ድጋፍ በራሳችን አነሳሽነት፣ በራሳችን ቀያሽነት፣ በራሳችን አስተዳዳሪነት፣ በራሳችን ውሳኔ ሰጭነት፣ የራሳችንን ማለትም የማህበረሰባችንን ህይወት ቀየርነው፤ ራስ በራስ ይሏል ይህ ነው፡፡
“ዛሬ ድፍን ካናዳ እየመጣ ተሞክሯችንን ይጋራል፣ መንግስት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የሲቪል ማህበራቱም የእኛን ሞዴል በመጠቀም የተለያዩ አካባቢዎችን ቀይረዋል፤ እየቀየሩም ነው፡፡”
“ሀበሽ! ይህ መንደር ልጆች በታላቅ ስነ ምግባር፣ በእምቅ እውቀትና ክህሎት የሚታነጹበት፣ ወጣቶች ለሌሎች አርአያ በመሆን የሚወደሱበት፣ … የመሬት ገነት ነው፡፡”
እኔም በአካል አንድርው መንደር ሆኜ በህሊና ሀገር ቤት ስለነበርኩ “የሚያውቋትን ኢትዮጵያ ለማሻሻል ምን ማድረግ ይቻላል?” አልኳቸው፡፡
“አይ ሀበሻ! እናንተ እኮ ባላችሁ ዕምቅ ማህበረሰባዊ እሴት ከማንም ቀድማችሁ ማደግ የነበረባችሁ ህዝቦች ናችሁ፡፡ አየህ! እኛ እርስ በርሳችን አንተዋወቅም፡፡ የሚያገናኘን ማህበረሰባዊ እሴትም ልል ነው፡፡ ነገር ግን መሻቱ ስላለ፤ መንደርን፣ ክ/ሀገርን ብሎም ሀገርን ቀይረናል።
እናንተ ግን ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር፣ በርካታ የማህበረሰብ አውታሮች እንዲሁም ተሰፍሮና ተለክቶ የተሰጠ አየር ንብረት፤ ሊሰራ የሚችል ትኩስ ጉልበት እያላችሁ፣ ሀገራችሁን የአፍሪካ ቀንድ ሳይሆን የአፍሪካ ጭንቅላት ማድረግ ሲገባችሁ አላደረጋችሁም፡፡ ስማ በዚያ ላይ በቅኝ ገዥዎች ላይ ድል የተቀዳጃችሁ ታላቅ ታሪክ ያላችሁ ህዝቦች ናችሁ፡፡ ያላችሁን አስተባብራችሁ ችጋርን ድል መንሳት ግን አልቻላችሁም፡፡
“ስማ ሀበሻ! ለእንዲህ አይነት በጎ ስራ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ ላይነሳ ይችላል፡፡ ጥቂት ሰዎች ብቻ ተነሳሽነቱን ቢወስዱ ሁሉም ይቻላል፤ ጥቂት ሰዎች ሀገርን ይቀይራሉና፡፡
ተነሳሽነቱ፣ ታታሪነቱ፣ ትጋቱ፣ የእኔ ባይነቱ፣ ቅንነቱ፣ ዓላማው፣ ሩቅ አሳቢነቱ፣ መተሳሰቡ፣ ከራስ በፊት የማህበረሰብ ጥቅምን ማስቀደሙ ወዘተ… ካላችሁ፣ የራሳችሁን ምድራዊ ገነት መፍጠር ትችላላችሁ፡፡ ለሀበሻ ምድር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዓላማት የሚበጁ ዜጎች የማፍራት ዕድሉ በእጃችሁ ነው…” እያሉ እያወጉኝ ሳለ፣ ሰዓት አልቋል የሚል ፊሽካ ከወደ አስተባባሪዎች ተነፋና ትቼአቸው ሄድኩ፡፡

Read 1959 times