Saturday, 24 May 2014 14:33

በመፃህፍትና በጋዜጣ ካርቱኖች የተደገፈው የግብፅ ተቃውሞ

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(9 votes)

አሁንም የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲቆም መወትወቷን ገፍታበታለች

ግንባታው ከተጀመረ ሦስተኛ ዓመቱን የያዘውን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ አሁንም ድረስ የግብፅ አቋም አልተለወጠም፡፡ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ፈጣን ግስጋሴ እያሳየ ያለውን ያህል፣ ግብፅም ግንባታው እንዲቋረጥ የከፈተችውን ዘመቻ በየአቅጣጫው አጠናክራ ገፍታበታለች፡፡ ግብፅ ከግድቡ መገንባት ልታገኘው የምትችለውን ጥቅም ፈጽሞ ማሰብም ሆነ ማሰላሰል የምትሻ አትመስልም፡፡ እንደውም የግድቡን መገንባት የሰው አገር ልዕልናን እንደመዳፈር የቆጠረችው ነው የሚመስለው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ፖለቲከኞቿ የግድቡ ግንባታ የማይቆም ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይሉ በአደባባይ ሲዝቱ የሚሰማው፡፡ አንዳንዴ የግብፅ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች አኳኋን ሲታይ፣ የአባይ ወንዝ 11 አገራት የሚጋሩት የጋራ ሃብት መሆኑን  የዘነጉት ይመስላል፡፡
ግብፃውያን አባይን የግል ሃብታቸው አድርገው የማሰብ ዝንባሌያቸው እንዲህ በቀላሉ እንደማይለቃቸው ሁነኛ ማስረጃው፣ በቅርቡ በፀደቀው አዲሱ የአገሪቱ ህገመንግስት አንቀፅ 44 ላይ የአባይን ወንዝ በተመለከተ የሰፈረው ሃሳብ ነው።
የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች እንዲሁም ምሁራን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በመቃወም በቃላት ከከፈቱት ዘመቻ ጐን ለጐን፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች የህትመት ውጤቶቻቸውም በጥናትና ትንተና መልክ እንዲሁም በካርቱኖች ተመሳሳይ ተቃውሞ ማንፀባረቃቸውን ቀጥለውበታል፡፡
በግብፅ የቀድሞ የመስኖ እና የውሀ ሀብቶች ሚኒስትር መሀመድ ናስር ኤልደን፤ በአረብኛ ቋንቋ ተፅፎ ሰሞኑን ለንባብ የበቃው “የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ቀውስ” የተሰኘው መፅሐፍ ለዚህ አንዱ አብነት ነው፡፡ 242 ገፆች ያሉት መፅሀፉ፤ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ በግብፅ ዘንድ ያለውን አመለካከት ቁልጭ አድርጐ እንደሚያሳይ በመፅሀፉ ላይ ቅኝት የሰራው “አል አህራም” ጋዜጣ አመልክቷል፡፡  
የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተከትሎ ግብፅ ከባድ የውሀ ቀውስ እንደሚገጥማት በመፅሃፋቸው ያወሱት የቀድሞው ሚኒስትር፤ የግብፅ የውሀ ድርሻ በ1959 ዓ.ም የተወሰነ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረው የህዝብ ብዛቷ፣ እንዲሁም የእርሻ መሬትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከፍተኛ የሆነ የውሀ ፍላጎት መፍጠሩን ይገልፃሉ፡፡ “የደቡብ ሱዳን አንድ አገር መሆን ቀደም ሲል ከሱዳን ጋር ተደርጎ በነበረው ስምምነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳርፍ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ የሰሜን ሱዳን ግብፅን ተወት አድርጎ ከኢትዮጵያ ጋር መወገንም ሌላው ፈተና ነው” ሲሉ ስጋታቸውን የፃፉት መሀመድ ናስር ኤልደን፤  ባለፉት አስርት አመታት በጉዳዩ ላይ የእስራኤል ሚና የጎላ እንደነበር በመጥቀስ እስራኤልንም ተጠያቂ ያደርጓታል፡፡
“ሶማሊያ ፈራርሳለች፤ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ራሳቸውን የቻሉ አገሮች ሆነዋል፤ ኢትዮጵያና ኡጋንዳም የአካባቢው ሀያል አገሮች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ሁለቱ አገራት ከታላላቆቹ ምእራባውያን በሚያገኙት ድጋፍ ሳቢያ፣ የአካባቢው ወሳኝ ሚና ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡” ሲሉ የቀድሞው ሚኒስትር ተስፋ በመቁረጥ የታጀበ ፖለቲካዊ ትንተና ያቀርባሉ።
የመሀመድ ናስር ኤልደን “የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ቀውስ” መፅሃፍ፤ ግብፅ እስከዛሬ ከምታንፀባርቀው አቋም ቅንጣት ታህል የተለየ አዲስ ሃሳብ ይዞ አልመጣም፡፡ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ማቆም እንዳለባት ነው አበክሮ የሚሞግተው፡፡ “ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ አቁማ ጥናት እንዲካሄድ መፍቀድ አለባት፤ ይህ ካልሆነ ግን ግብፅ  ጉዳዩን ለአፍሪካ ህብረትና ለመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት  ከመውሰድ ውጭ አማራጭ የላትም” ይላሉ - ፀሐፊው፡፡

Read 3243 times