Saturday, 24 May 2014 14:19

“ቀን ሲሰጥ የውሻ ደም ትበቀላለህ ቀን ሲከለክል ያባትህን ደም ትተዋለህ” - አገርኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(10 votes)

“ዳኞች አጥፊን ባህር ውስጥ ይጥሉታል፡፡
ከሰመጠ ንፁሕ ነው ይሉታል፡፡
ካልሰመጠ ጠንቋይ ነው ብለው ይቀጠቅጡታል፡፡”
                 - የግብፅ ፍርድ
አንድ የጥንት የኢትዮጵያ ጀግና ወደ ጦር ሜዳ ሊሄዱ እየተዘጋጁ ሳሉ፤ ሠፈር - ጐረቤቱ መጥቶ የበኩሉን የስንብት፣ የድጋፍና የማበረታታት መንፈስ ያላብሳቸዋል፡፡
“እርሶ የገቡበት ጦርነት መቼም ሁሌ ድል ነው፡፡ ሁሌ ጉሮ ወሸባዬ ነው! ሁሌ ምሥራች ነው” አሉ አንድ ጐምቱ የሰፈሩ ሰው፡፡
“መጠርጠሩስ!” ይላሉ ሌላው፡፡
ቀጠሉ ሌሎቹ፤
“እንዲያው እርሶ ጦር ሜዳ ታይተው ጠላት እፊትዎ ሊቆም? አይደረግም!”
“እረ ጠላት አይደለም ሣር ቅጠሉ ያረግዳል! የጌቶችን የሚያህል ጀግንነት እግር እስኪዝል ቢሄዱ አይገኝምኮ!”
“እረ በዓለም በታሪክ ሲነገር የሰማነውም እሳቸውን የሚያህል ጀግና የለም!”
በመጨረሻ አንድ ትንሽ ልጅ፤ “አጐቴ አሁን ሁሉንም ተዉትና ንግግር አድርጉልንና ሂዱ”
ሁሉም፤ “ይናገሩ! ይናገሩ” አሏቸው፡፡
“እስኪ እንዳፋችሁ ያድርግልኝ፡፡ እኔ ስገባበት ውስጡ ሆኜ የማደርገውን አላውቀውም። ያኔ በቦታው የማደርገውን አሁን በንግግር መግለፅ አይሆንልኝም፡፡ እንዲያው ‘ይቅናህ!’ ያላችሁኝ ምርቃት ብቻውን ብዙ ስንቅ ይሆነኛል፡፡ የጣሊያን ጥላቻዬ ሁለተኛ ስንቄ ነው። ሌላውን ስንመለስ እናወራለን” ብለው ሁሉን ተሰናብተው ወጡ፡፡ የሚሸኟቸው፤ መንገድ ድረስ ሸኝተዋቸው ተመለሱ፡፡
ጀግናው ሲደርሱ፤ ጦር ሜዳው ቀውጢ ሆኗል፡፡ ከዛም ከዚህም ወገን፣ ሰው ይረፈረፋል። ጀግናውም እንደገቡ ጥይቱን እንደጉድ ያንጣጡት ጀመር፡፡ ጦርነቱ በጣም ተፋፋመ፡፡ ጀግናው እጅግ በርካታ ጠላት ረፈረፉ፡፡ ግን አልረካ አሉ፡፡
አልረካ ያሉበት ምክንያት “የምገለው ጠላት ሁሉ ራሱ ፈረንጅ በሠራው ጥይት ነው እየወደቀ እማየው፡፡ ከዚህ ደቂቃ በኋላ ግን፤ ፈረንጅ በሰራው ጥይት አልገድልም፡፡ የራሴን እጅ ነው መቅመስ ያለበት” አሉ፡፡ ጠመንጃቸውን ወርውረው በጨበጣ ገቡበት፡፡ “ተዉ ጌታዬ ሌላው በጥይት ይመታዎታል!” ቢባሉ፤ “በጭራሽ! እጄን ይቅመስ!” አሉ፡፡ በኋላ ግን፤ ሰው ናቸውና ወደቁ፡፡
*       *       *
በስሜታዊነት፣ በዕልህና በግትርነት የትም አንደርስም፡፡ ግትርነት ለማመዛዘን እድል አይሰጥም፡፡ ግራ ቀኝ ለማየት ጊዜ አይሰጥም፡፡ የአብዛኞቻችን ዓይነተኛ ችግር ከስሜታዊነት የሚመነጭ ኃይለኛ ግትርነት ነው፡፡ ግትርነት እያለ ዲሞክራሲ ይፋፋል ማለት ደግሞ ዘበት ነው፡፡ ከግትርነት በላይ ቃል ቢኖር እንጠቀምበት ነበር፡፡ (እንግሊዞች የግትር ግትር ለማለት “Stiff upper lip” የሚሉት አይነት መሆኑ ነው፡፡) ሌላ ብዙ ቅፅል፣ ብዙ ጭራና ቀንድ እየቀጠልን ለግትርነታችን ምክኑ ያ ነው እንበል እንጂ አብረን ያደግነውን ግትርነት የሚያክል ባላንጣ የለንም፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል ማለት፤ ግትርነት ነው፡፡  ጠላቴ ያለበት አንድ ጥግ፣ እኔ ያለሁት ሌላ ፅንፍ፣ ብሎ መፈጠምም ግትርነት ነው፡፡ ሀብትን ማከማቸት አልጠግብ ማለትና ምንም ጥቅም ላይ ባላውለውም በእኔ እጅ ይሁን፤ ማለትም ግትርነት ነው። “ሀብት ሲሰበስብ ከርሞ ሳይጠቀምበት የሚቀር በርሀብ ይሞታል” የሚል የአፍሪካውያን አባባል ይሄንኑ ይነግረናል፡፡ በአንፃሩ ሁሌ በማባከን መለከፍም ግትርነት አለበት፡፡ “አባካኝነት ለድህነት ይዳርጋል፡፡ ድህነት፤ ዕውነተኛ ድህነት፣ ሞት ነው” (የኦዞ ዘፈን) የሚለውንም ልብ ይሏል፡፡ በሀገራችን ጉዳይ ግልፅ በግልፅ እንነጋገር ሲባል በፍፁም እምቢኝ ብሎ ድርቅ ማለትም ግትርነት ነው፡፡
በአንድ ወቅት በብሾፍቱ “ገፅ ለገፅ” የሚባል የብሾፍቱን የውሃና ትምህርት ችግር የሚያይ ፕሮግራም ላይ፤ ባንድ በኩል ህዝብ፣ በሌላ በኩል ከንቲባውን ጨምሮ የከተማይቱ ባለስልጣናት የታደሙበት፤ አስገራሚ ስብሰባ ተካሂዶ፤ ከንቲባው የሚገርም ግልፅ ንግግር አድርገው ነበር፡- “መንግስት ባላችሁዋቸው ችግሮች አንጻር የበኩሉን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ህዝቡስ? ለመሆኑ ውሃ ሲፈስ ብታዩ የምትጠቁሙ እነማን ናችሁ? አለቃ ሲሰርቅ እምቢ አይደረግም (No!) የምትሉ እነማናችሁ? የሚሰረቀው ’ኮ የራሳችሁ ሀብት ነው! እንደዛ ከቀጠለኮ ብሾፍቱ የጥቂት ሰዎች ብቻ ናት ማለት ነው! ከህዝብ የማያስፈልገን ሰው የለም! አቅም ትሆኑናላችሁ! እንደምታውቁት፤ ያደግንበት አካባቢ ለዕድገት አመቺ አልነበረም። አይፈቅድም ነበር፡፡ መለወጥ አለበት፡፡ አንዱ አንዱን አይርገም! ዛሬ ማይክሮ -ሰከንድ ሚሊዮን ያሳጣል፡፡ እንፍጠን፡፡…” ብለዋል፡፡
እርስ በርስ የመረጋገም ልክፍትም ግትርነት ነው ፡፡ ፊት ለፊት በመወያየት የጋራ መፍትሄ ማምጣት ያዋጣናል፡፡ የሆነውን ለመሸፋፈን ከመሞከር በግልፅ ማፈንዳት ወደፍሬ ያደርሰናል!
ለግልፅነትም፣ ለተጠያቂነትም፣ የሁሉ እናት - ክፍል ለሆነው ዲሞክራሲም፤ ዞሮ ዞሮ መጠቅለያው ጊዜ ነው፡፡ ለጊዜ በመገዛት ጊዜን መግዛት ነው ጥበቡ፡፡ ጊዜን ካወቁ (The right timing) እንዲሉ ስኬት ቅርብ ነው፡፡ መቼ ማፈግፈግ እንዳለብህ ዕወቅ - ጊዜው አልበሰለምና። መቼ አጥብቀህ መምታት እንዳለብህ ዕወቅ - ካረፈድክ ትጠቃለህና፤ ይላሉ ፀሀፍት፡፡ የመጨረሻዋን ሶስት ደቂቃ ተጠቅምባት (Last three minutes እንዲል የቅርጫት ኳስ ህግ)፡፡ እንደጥንታዊው የግብፅ ፍርድ ‹ውሃ ውስጥ ልትጣል ትችላለህ - ከሰመጥክ ንፁህ ልትባል፤ ካልሰመጥክ ጠንቋይ ነው ተብለህ ልትቀጠቀጥ!!› ጊዜን አለማወቅ ቅጣቱ ብዙ ነው። ይህን ጉዳይ፤ መረርና ከረር ያለው አገርኛ ተረት በወጉ ይደመድመዋል፡-
“ቀን ሲሰጥ የውሻ ደም ትበቀላለህ፤
ቀን ሲከለክል ያባትህን ደም ትተዋለህ!”

Read 5767 times