Print this page
Saturday, 24 May 2014 14:19

የግንቦት 20 መልዕክቶች - ለገዢው ፓርቲ ለኢህአዴግ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(3 votes)

ሲፒጄ፣ የጋዜጠኞች ማህበር፣ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ… ምን ይላሉ?

ውድ የፖለቲካ በፈገግታ አንባቢያን - በመጀመሪያ እንኳን ለ23ኛ ዓመት የግንቦት 20 በዓል አደረሳችሁ!  (አይመለከተኝም የሚል ይዝለለው!) ከዚህ በታች ሦስት በአካል ወይም በቲቪ አሊያም በዝና የምናውቃቸው ድርጅቶች  የግንቦት 20ን በዓል ምክንያት በማድረግ ለኢህአዴግ ማስተላለፍ የሚሹትን መልዕክት እንዲፅፉ እድል ሰጥቻቸው የተፃፈ ነው፡፡ (እነሱ የፃፉት ነው አልወጣኝም!) ይልቁንም በእነሱ ቦታ ሆኜ ምን ሊፅፉ እንደሚችሉ በመገመት፣ተከታዮቹን ምናባዊ መልዕክቶች ለመፃፍ ሞክሬአለሁ፡፡  

ይድረስ ለምስራቅ አፍሪካው የኢህአዴግ መንግስት -
23ኛውን የግንቦት 20 የድል በዓል ምክንያት በማድረግ፣ይህቺን የደስታ መልዕክት ለመፃፍ ዕድል በማግኘቴ ደስታዬ ወደር የለሽ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እኔና የምመራው ተቋም፣ዓይናችንን ወደ ጥንቷ ገናና አገር ኢትዮጵያ የጣልነው፣ኢህአዴግ ሥልጣን ይዞ የፕሬስ ነፃነትን ባወጀ ማግስት ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በጦቢያ ምድር ስለ ፕሬስ ነፃነት ማውራት አይቻልም።  ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ እኛን የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾችን እንደጭራቅ ነበር የሚቆጥረን፡፡ ነፃ ጋዜጠኞች ከሥልጣኑ ፈንቅለው የሚጥሉት ይመስለው ነበር፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት ፍራቻ እንደሌለበት በእርግጠኝነት ልናገር እችላለሁ፡፡ (“የቀለም አብዮት” የሚባለው ነገር  ከመምጣቱ በፊት ማለቴ ነው!)  
 በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ታሪክ ውስጥ ግንቦት 20 ጉልህ ሥፍራ እንዳለው ማንም አይክድም። የፕሬስ ነፃነት መታወጅን ተከትሎ፣በአገሪቱ የተበራከቱትን የፕሬስ ውጤቶች ወደ ኋላ በምናብ ተንሻትቼ ሳስብ ቁዘማ ውስጥ እገባለሁ፡፡ አሳይቶ መንሳት ማለት እኮ ሌላ አይደለም - ይኸው ነው። እኔና ተቋሜ በዚህች አገር ላይ የፕሬስ ነፃነት እንዲያብብ፣የጋዜጠኞች መብት እንዲከበር በትጋት ስንሰራ ቆይተናል፡፡ (እጃችን አመድ አፋሽ ቢሆንም!)
አንዳንድ የፕሬስ ነፃነት መከበር የሚያስበረግጋቸው ወገኖች በተደጋጋሚ እንደሚሉት፤ እኔም ሆንኩኝ የምመራው ተቋም  የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ጥላሸት የመቀባት አንዳችም ድብቅ ዓላማ እንደሌለን በዚህች አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ኢህአዴግ ለዓመታት ከታገለላቸው ውድ የሰው ልጆች መብቶች መካከል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አንዱ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን፣የፕሬስ ነፃነትን እንደ ቅንጦት የሚመለከቱ፣ ጋዜጦችንና ጋዜጠኞችን እንዳሻቸው መዝጋትና ማሰር የሚቋምጡ (የ97ቱን የምርጫ ቀውስ የሚመኙ) አንዳንድ የኢህአዴግ አምባገነን ሹማምንት እንዳሉ ኢህአዴግም ራሱ አያጣውም። (አምባገነንነት በአንድ ጀምበር አይጠፋም!) ለዚህም ነው የምመራው ተቋም፣የኢትዮጵያን ጋዜጠኞች ስደት፣ ወከበና እስር  በተመለከተ መረር ከረር ያለ ዓመታዊ ሪፖርት ባወጣ ቁጥር፣ ያለ ስሙ ስም እየሰጡ የሚያብጠለጥሉትና የሚፈርጁት፡፡ (ስም ማጥፋት መብታቸው የሚመስላቸው አሉ!)
ከሁሉም የሚገርመኝ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስም ማህበር አቋቁመው፣ስለ አገሪቱ ፕሬስና የጋዜጠኞች መብት ሁኔታ  ትንፍሽ የማይሉት የጋዜጠኞች ማህበራት ጉዳይ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ተሰደዱ - ጭጭ፡፡ ጋዜጦች ተዘጉ - ጭጭ፡፡ ጋዜጠኞች ታሰሩ - ጭጭ፡፡ ማተምያ ቤት ውጣ ውረድ በዛ - ጭጭ፡፡ እኔ የምለው--- አንደበት የሌለው ማህበር እንዴት ለሌሎች መብት ሊሟገት ይችላል? (የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!) እነዚህ ማህበራት ድምፃቸው የሚሰማው የእኔ ተቋም ወይም ሌላ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚሰራ ድርጅት፣ ኢትዮጵያን የተመለከተ ጠንከር ያለ ሪፖርት ሲያወጡ ብቻ ነው። ሪፖርቱ በወጣ ማግስት ሰብሰብ ብለው ሆቴል ይከራዩና ሪፖርቱን አውግዘው ወደየቢሯቸው- በቃ!    
ለምሳሌ የእኔ ተቋም በቅርቡ ያወጣውን ሪፖርት አስመልክተው ባወጡት የአቋም መግለጫ “በኢትዮጵያ አንድም በሙያው የታሰረ ጋዜጠኛ የለም፤ እገሌ ስለ ኢትዮጵያ ፕሬስና ጋዜጠኞች አያገባውም” አሉና  ወደ የጉዳያቸው ተመለሱ፡፡ (የሙያ ማህበራት እኮ የመንግስትን መግለጫ ቃል በቃል የመኮረጅ ግዴታ የለባቸውም!) የሆኖ ሆኖ ግን የእኔ ተቋም ለጋዜጠኞች መብት የሚቆመውና የሚሟገተው የእነሱን ፈቃድ ወይም ይሁንታ እየጠየቀ አይደለም፡፡ ለፕሬስ ነፃነት መታገል፣  ለጋዜጠኞች መብት መከራከር የቆምንለት ዓላማችን ነው፡፡ የምንሟገተው ደግሞ  ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ብቻ አይደለም፡፡ ለኤርትራ፣ ለሱዳን፣ ለኢራን፣ ለካዛኪስታን፣ ለኢራቅ፣ ለሶሪያ ወዘተ…ለመላው የዓለም ጋዜጠኞች መብትና ነፃነት መከበር ነው! እንደሚመስለኝ እኒህን ማህበራት ነፃ የሚያወጣቸው ሌላ ነፃና ጠንካራ እንዲሁም ቁርጠኛ ማህበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ (የግንቦት 20 ፍሬ የገባቸው አልመሰለኝም!)
አምባገነኑን ወታደራዊ አገዛዝ ገርስሶ ሥልጣን በተቆናጠጠ ማግስት፣ የፕሬስ ነፃነትን በይፋ ላወጀው የምስራቅ አፍሪካው የኢህአዴግ መንግስት ግን፣ እኔና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቴ፣ ከወገባችን ዝቅ ብለን አክብሮታችንን ልንገልፅለት እንወዳለን፡፡ እንዲያም ሆኖ የፕሬስ ነፃነትና የጋዜጠኞች መብት ጉዳይ አሁንም እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ  መጥቀስ ይኖርብኛል፡፡ እናም በዚህ የድል በዓል ዋዜማ ላይ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፣ ጋዜጠኞች ለስደት እንዳይዳረጉ እንዲሁም መንግስት ራሱ አርቅቆ ያፀደቀውን  የፕሬስ ነፃነት አዋጅ  ሳይሸራረፍ እንዲያከብር በራሴና በተቋሜ ስም በጥብቅ አሳስባለሁ፡፡  
መልካም የግንቦት 20 በዓል ለኢህአዴግ!
(የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት- ተጠባባቂ ዳይሬክተር)

ይድረስ ለኢህአዴግ መራሹ ልማታዊ መንግስት-
እንኳን ለ23ኛው ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓል አደረሳችሁ ስል በታላቅ ደስታ ነው - ግንቦት 20 የእኛም ድል ነውና! እንደቻይና ኮሙኒስት ፓርቲነታችን፣ ኢህአዴግ በርካታ የግንቦት 20 ፍሬዎች አሉት ብለን እናምናለን፡፡ በዋናነትም  የቀለበት መንገድ፣ የጐተራ ማሳለጫ፣ የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ የኢትዮ - ጂቡቲ የባቡር ሃዲድ መስመር ፕሮጀክት፣ የቻይና ኢንዱስትሪ ዞን እንዲሁም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኢትዮ- ቴሌኮም ከቻይናው እውቅ ኩባንያ ህዋዌ ጋር እያከናወናቸው ያሉት የኔትዎርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችም  የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፡፡
እንደ እስከዛሬው ሁሉ በቀጣይም ወዳጅነታችንና አጋርነታችን እየተጠናከረ እንደሚሄድ ኮሙኒስት ፓርቲያችን ፅኑ እምነት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ለአገር ዕድገት የማይበጁና ልማትን የሚያደናቅፉ የውጭ ሚዲያዎችንና ድረ-ገፆችን ጃም በማድረግ  እንዲሁም ፌስቡኮችንና ኢ-ሜይሎችን በመቆጣጠር ረገድ ፓርቲያችን ያካበተውን የረዥም ዘመን ልምድና ተመክሮ ለኢህአዴግ ልማታዊ መንግስት ለማጋራት ፈቃደኛ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ከልማት ትብብራችን ጐን ለጐን በሚዲያው ዘርፍ  እጅና ጓንት ሆነን በመስራት፣የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ ሚዲያዎችን (እነ ቢቢሲ፣ ሮይተርስ፣ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ አሶሼትድ ፕሬስ--ወዘተ) ተፅዕኖ ተጋፍጠን ማሸነፍ እንዳለብን ኮሙኒስት ፓርቲያችን በፅናት ያምናል፡፡ (የራሳችንን ገጽታ ራሳችን እንገነባለን!)
በተረፈ ኢህአዴግ የአፍሪካ ገናና አውራ ፓርቲ የመሆን ህልሙን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳካት ይችል ዘንድ ሁሌም ከጎኑ እንደማንለይ ቃል እንገባለን፡፡
ድል  ለኢህአዴግ ልማታዊ መንግስት!!
(የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ተጠባባቂ ፀሃፊ)

.እንኳን ለ23ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል አደረሳችሁ! የዘንድሮውን የድል በዓል ለየት የሚያደርገው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ባከበርን ማግስት በመዋሉ ነው፡፡
ማህበራችን ግንቦት 20ን ከፕሬስ ነፃነት ቀን፣ የፕሬስ ነፃነት ቀንን  ከግንቦት 20 ለይቶ ማየት አይቻልም የሚል እንደ አለት የፀና አቋም አለው፡፡ ለያይተው የሚመለከቱ ወገኖችንም አንታገስም፤እናወግዛለን፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር፣ የዘንድሮን ግንቦት 20 በዓል የሚያከብረው ለጋዜጠኞች መብትና ለፕሬስ ነፃነት ማበብ ተግቶ በመወያየት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ማህበሩ ለጋዜጠኞች መብት መከበር እልህ አስጨራሽ ትግል ቢያካሂድም የታሰሩ ጋዜጠኞችን ለማስፈታት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ለአፍታም ቸል የማይለው ማህበራችን፤ በጋዜጠኛው ልብ ውስጥ  የሚንቀለቀል የአገር ፍቅር ስሜት ለመለኮስ  ሲታትር ቆይቷል፡፡
በዘንድሮው ዓመት እንደስኬት ከምንጠቅሳቸው አኩሪ ተግባሮቻችን መካከል፣ባለፈው ህዳር ወር በአፍሪካ ህብረት በተካሄደው የአፍሪካ ሚዲያ አመራሮች ጉባኤ መዝጊያ ላይ “በኢትዮጵያ አንድም በሙያው የታሰረ ጋዜጠኛ የለም” በሚል  ያወጣነው መግለጫ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም የአገሪቱን ገፅታ ጥላሸት ለመቀባት አሰፍስፈው የነበሩ ወገኖችን ሴራ አክሽፈናል፡፡
በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ የቀለም አብዮት ለመቀስቀስ ሲያሴር የነበረን ተቋም፣በኢቴቪ በሰጠነው መግለጫ፣ (ስሙን ሳንጠቅስ) እጁን ካልሰበሰበ እንደምናጋልጠው በማስጠንቀቅ፣ አገሪቱን ከቀለም አብዮት አፋፍ ላይ አድነናታል፡፡ በዚህም ታላቅ አገራዊ ኩራት ይሰማናል፡፡ ከሁሉም በላይ እርካታ የሚሰጠን ግን በአሁኑ ሰዓት በሙያው ሳቢያ የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ  አለመኖሩ ነው፡፡ (በሌላ ወንጀል የታሰሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ ከእነአካቴው አይመለከተንም  ማለት አይደለም!)
በመጨረሻም፤ እንደ ሲፒጄና ሂዩማን ራይትስዎች ያሉ ከጀርባቸው ሌላ አጀንዳ ያነገቡ  የመብት ተሟጋች ነን ባይ ተቋማት፣ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንዳይፈተፍቱ፣ በተለይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ዘብ እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
መልካም የግንቦት 20 በዓል
 ለታሰሩም ላልታሰሩም ጋዜጠኞች!
(የጋዜጠኞች ማህበር ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት)


Read 3029 times