Saturday, 24 May 2014 14:14

አኖሌ ሃውልት ፖለቲከኞችና የታሪክ ምሁራንን እያወዛገበ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

በምኒልክ ዘመን በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ተፈፅሟል የተባለውን የጡትና እጅ መቁረጥ ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና ጭፍጨፋ ለማስታወስ በሚል በአርሲ አኖሌ አካባቢ በ20 ሚሊዮን ብር የተሰራው ሃውልት፣ በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድርን ጨምሮ በርካታ የኦህዴድ ባለስልጣናት በተገኙበት ተመርቋል፡፡  
ሃውልቱን ያሰራው አካል ያለፈን ታሪክ መዞ ቂም በቀልን ለማውረስ ሳይሆን ቀጣዩ ትውልድ ከአስከፊው ድርጊት እንዲማርና ወደፊት ድርጊቱ እንዳይደገም ነው ሃውልቱ የተገነባው ብሏል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን በበኩላቸው ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ አንደኛው ወገን  ሃውልቱ በህዝቦች መካከል ቅራኔና ቂም በቀል የሚፈጥር ነው በማለት ሲቃወም ሌላው ወገን በበኩሉ ድርጊቱ ዳግመኛ እንዳይከሰት መማርያ እንጂ የበቀል አይደለም ሲሉ የሃውልቱን መቆም ይደግፋሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አወዛጋቢ በሆነው የአኖሌ ሃውልት ዙሪያ የታሪክ ምሁራንንና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡


“ጡት ስለመቆረጡ በፅሁፍ የተቀመጠ መረጃ አላገኘሁም”

ዶ/ር ነጋሲ ጊዳዳ (ፖለቲከኛና የታሪክ ምሁር)
ሃውልቱ ለምን እንደተሰራ የተጨበጠና ጠለቅ ያለ መረጃ የለኝም፡፡ የታሪክ መረጃዎች  እንደሚታወቀው አንድም በፅሁፍ ይተላለፋሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በአፋዊ ንግርት (አፈታሪክ) የሚተላለፍ ነው፡፡ እኔም የዶክትሬት ማሟያ ፅሁፌን የሰራሁት አፈ-ታሪክን  ተጠቅሜ ነው፡፡
በ1879 አፅመ ጊዮርጊስ የተባሉ የአፄ ምኒልክ ታሪክ ፀሃፊ (አንዳንዶች የኦሮሞ ታሪክ ፀሃፊ ናቸው ይሏቸዋል) በዚያን ጊዜ እንደሰላይ ነበረ የሚሰሩት፡፡ እኚህ ሰው የምኒልክ ጦር ከመንቀሳቀሱ በፊት የሚዘመትበትን ህዝብ ባህል፣ አኗኗሩን ካጠኑ በኋላ እንዴት መወገድ እንደሚችል ሃሳብ ያቀርቡ ነበር፡፡ እኔ ጋ ባለ አንድ መፅሃፋቸው ላይ ስለዚህ ስለ አኖሌ ጉዳይ ሲፅፉ፣ በአንድ በኩል አፄ ምኒልክ ከ1879 ዓ.ም በፊት ለአራት አመት አርሲን ለማስገበር ጦርነት ሲያካሂዱ እንደነበር ተርከዋል፡፡ መስከረም 1879 ላይ የምኒልክ የአባታቸው ወንድም የሆኑት ራስ ዳምጠው ናቸው የመጨረሻውን የአርሲ ጦርነት ያካሄዱት፤ ምኒልክ እንጦጦ ነበሩ፤ በዚያ ጦርነት ላይ የምኒልክ ሰራዊት ለሶስት ቀናት መዝረፍ፣ ማቃጠልን ጨምሮ ሽማግሌና ህፃናት ላይ ብዙ ጉዳት አድርሷል፡፡ የአፅመ ጊዮርጊስ ፅሁፍ እንደሚለው፣ በወቅቱ ራስ ዳምጠው “እኔ ተኩስ ሳልል እንዴት ሰራዊቱ ትዕዛዜን ሳያከብር ተኩስ ጀመረ” በሚል እንጂ በሰዎች እልቂት ሃዘን አልተሰማቸውም ነበር፡፡ ለአፄ ምኒልክ በላኩት መልእክትም ሰራዊቱ ከትዕዛዛቸው ውጪ በመሆኑ በእጅጉ ማዘናቸውን እንጂ ስለጠፋው የሰው ህይወት ሃዘን እንደተሰማቸው አልገለፁም ነበር፡፡ በዚህ የሦስት ቀን ጦርነት በወቅቱ “አዞሌ” አሁን “አኖሌ” በሚባለው ቦታ ላይ 12ሺህ ሰው ተገድሏል፡፡ ከዚህ መረጃና ጦርነቱ አሰቃቂ ነበር ከሚለው እውነታ ውጪ እኔ እስካሁን እጅ ቆርጠዋል፣ ጡት ቆርጠዋል የሚል የፅሁፍ መረጃ አላገኘሁም፡፡ በ1984 ወደ አኖሌ በሄድኩበት ወቅት፣ የአርሲ ሰዎች እጅና ጡት የተቆረጠበት አካባቢ ነው ብለው ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው አሁንም ድረስ እጅና ጡት ተቆርጧል የሚለው ታሪክ በሰፊው የሚነገር ነው፡፡ ሆኗል አልሆነም የሚለውን ለማረጋገጥ በደንብ ምርምር መደረግ አለበት እንጂ ለምን ታሪኩ እንዲህ ተነገረ ወይም ተባለ ብሎ ማውገዝ ከባድ ነው፡፡
ሌላው ማስታወስ ያለብን ለምሳሌ እነ ወለጋ የተወረሩት እስከ 1877 ዓ.ም ነበር፡፡ ነገስታቱ በሰላም ነው እጃቸውን የሰጡት ጅማም እንደዚሁ ነው፡፡ አርሲ ግን ለረጅም ጊዜ አልቀበልም ብሎ ስለነበር በጣም ብዙ አሰቃቂ ጦርነቶች ተካሂደው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ሁኔታው ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄንን ሃውልት ያቆሙ ሰዎች፣በአንድ በኩል በታሪክ የሰሙትን ለማስታወስ ብቻ ብለው ይሆናል፡፡ በኔ እምነት ሃውልቱ የነበረውን ሁኔታ ለማስታወስና ለወደፊት እንዳይደገም የተሰራ ይመስለኛል፡፡ እኔ መገንባቱ ምንም ችግር የለውም ነው የምለው፡፡ ታሪክን በሚገባ ካነበብን፣ አፄ ቴዎድሮስ የግዛት አንድነትን ለማምጣት የተጉ ተደርገው ነው የተቀረፁት፡፡ በአዲስ አበባም ያሰሩት መድፍ በስማቸው ከተሰየመው አደባባይ ላይ ተቀምጧል እንዲሁም ጎንደር ሃውልታቸው ቆሟል፡፡ ነገር ግን ሸዋ እና ወሎ ያሉ ሰዎችን ከንፈር መላጥ፣ እጅ መቁረጥ፣ ከነህይወት ገደል መክተት፣ ማቃጠል የመሳሰሉ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ፈፅመዋል፡፡ አፄ ዮሐንስ ደግሞ እነዚህን “ጋሎች እና እስላሞች” ክርስቲያን አድርጉ ብለው ወሎ ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈፅመዋል፡፡
በአጠቃላይ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ሃውልት ሲሰራ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፤ ነገር ግን ያለፈ ታሪክ ያስከተለው ጉዳት በቀጣይ እንዳይደገም በሚል እሳቤ ሃውልት ሲቆም ለበቀል ነው በሚል መደምደሙ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ሃረር ጨለንቆ ላይ ለተፈፀመው ጭፍጨፋ ሃውልት ተሰርቷል፡፡ የራስ መኮንን ሃውልት ደግሞ ሃረር ከተማ ላይ አለ፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ላይም የምኒልክ ሃውልት ተቀምጧል፡፡ በአንፃሩ በምኒልክ ጉዳት ደርሶብናል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ታሪክን በሃውልት ለማስታወስ የሚደረጉ ነገሮች በጥንቃቄ መቃኘት አለባቸው፡፡


“ሀውልቱ የኦሮሞን ህዝብ 100 ዓመት ወደ ኋላ የጎተተ ነው”
አቶ አበባው መሃሪ (የመኢአድ ሊቀመንበር)

የሃውልቱን መገንባት አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ጀግንነት የሰሩ የኦሮሞ ልጆች አሉ፡፡ የሚኒልክ አማካሪ ከነበሩት መካከል ወደ 80 በመቶ የሚሆኑ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ጣሊያን በተሸነፈበት ጦርነትም የኦሮሞ ልጆች ገድል ቀላል አይደለም። እነዚህን ታሪኮች ወደ ጎን ገፍቶ አኖሌ ላይ ብሄሮችን ሊያቃቅር የሚችል ሃውልት ከመገንባት ይልቅ የእነዚህን ጀግኖች ሃውልት አቁመው ቢሆን ኖሮ፣ ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ ይፀና ነበር፡፡ የታሪክም መገለጫ ይሆን ነበር፡፡ እንደኔ እይታ የአኖሌ ሃውልት የኦሮሞን ህዝብ ወደ ኋላ 100 ዓመት የጎተተ እንጂ ወደፊት ያራመደ አይመስለኝም።
በሌላ በኩል እኔ ይሄ ሃውልት የኦሮሞዎች ፍላጎት ያለበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ያሰሩት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአጠቃላይ ግን ሃውልቱ ሁለቱ ትላልቅ ብሄር ብሄረሰቦች- አማራና ኦሮሞው  እርስ በእርሳቸው ተጋጭተው  ትልቅ የነበሩት ትንሽ እንዲሆኑ ታልሞ የተደረገ ሴራ እንጂ የኦሮሞን ህዝብ ለመጥቀም የተደረገ ስራ አይደለም፡፡ ሃውልቱ ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ሳይሆን ጉዳት ነው የሚያመጣው፡፡ ከሌላው ብሄር ጋር ቅራኔ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ከፍተኛ ጉዳትም ያስከትላል፡፡
በዚህች ሃገር ታሪክ ውስጥ ብዙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተፈፅመዋል፡፡ እከሌ ይሄን አድርጓል እያልኩ መወንጀሉን አሁን ባልሻም በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉት አያሌ ግጭቶች የብሄር ተቃርኖ መሰረት ያላቸው አይደሉም፡፡ እኔ አገዛለሁ በሚሉ ከብሄረሰቡ የወጡ ነገስታት (ከሸዋ አፄ ምኒልክ፣ ከትግራይ አፄ ዮሐንስ፣ ከጎጃም ንጉስ ተክለሃይማኖት፣ ከጎንደር አፄ ቴዎድሮስ) ሃገሪቱን አንድ አድርገው ለመግዛት ባደረጉት ጥረት ብዙ ግፍ ተፈፅሟል፡፡ በወቅቱ ለግዛት አንድነት እምቢ ያለውን፣ ያመፀውን ቀጥተው ነው የሚያስተዳድሩት፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን ህዝቡን እየመገበ አይደለም ስልጣን የያዘው- እየገደለ፣ እያሰረ፣ እያባረረ ነው ስልጣን ላይ የተቀመጠው እና እንዲህ ያሉ ታሪኮች ባይነሱ መልካም ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ታሪኮች እንደታሪክ ተፅፈው ሊቀመጡ ይችላሉ፣ ነገር ግን እንዲህ ተደርገሃል በሚል ቂም በቀልን መቆስቆሱ ለዚህች ሃገር አይጠቅምም፡፡ የአኖሌ ሃውልትም የኦሮሞዎች ሃውልት ሳይሆን የካድሬዎች ሃውልት ነው፣ ስለዚህ የብሄሩን ታሪክ የማይወክል ሃውልት መቆሙን እቃወማለሁ፡፡ መቆም ያለበት ሃውልት የኦሮሞን ታሪክና ጀግንነት አጉልቶ የሚያሳይ ሃውልት ነው፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ገዳ ስርአት በሃገራችን የመልካም አስተዳደር ስርአት ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪኮች ተፅፈው ቢቀመጡ ጠቃሚ ነው፡፡ ሌላው አፄ ምኒልክ ጡትና እጅ ቆረጡ የሚለው ታሪክ ይወራል፡፡ በአንድ ወገን ደግሞ የኦሮሞ አባገዳዎች በግንባራቸው ላይ የሚያደርጉት የአማራን ብልት በመስለብ የተገኘ ነው የሚሉ የአማራ ካድሬዎችም አሉ፡፡ ስለዚህ ባህር ዳር ላይ ደግሞ ለዚያ ሃውልት ይቁም ከተባለ ምንድን ነው የሚሆነው? በአጠቃላይ እኔ የምመክረው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በካድሬዎች ሴራ አንድነቱን አሳልፎ እንዳይሰጥ ነው፡፡


“የሃውልቱ ፋይዳ ታሪክን ማስተላለፍ  ነው”
አቶ ቡልቻ ደመቅሣ (ፖለቲከኛ)

በአለም ታሪክ ውስጥ መጥፎም ጥሩም የሰሩ ሰዎች ሃውልት አላቸው፡፡ የጣሊያን ህዝብ ግማሹ ሙሶሎኒን አይወደውም ግን ሃውልቱ አለ፤ የሞስኮ ህዝብ ግማሹ ስታሊንን አይወደውም ግን ሃውልቱ አለ፡፡ የሚወደው ክፍል ሃውልቱን ያቆማል፣ የማይወደው ግን ሃውልት ሊቆም አይገባውም፣ ከቦታው አስወግድ ማለት አይችልም፡፡ እኛም የኦሮሞ ምሁራን የተሰራን ሃውልት፣ የተፈፀመን ታሪክ ተመልሰን እንለውጥ ማለት የለብንም፡፡ በሃውልቱ መገንባት ላይም ቅራኔ የለኝም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በአፄ ምኒልክ እጅግ በጣም ተበድሏል፡፡ ባሪያ ሆኗል፣ ተጎሳቁሏል ግን እሱ ታሪክ ነው፡፡ የአኖሌ እንደተባለው  ተፈፅሟል፣ በሰነድ ላይ የሰፈሩ ፅሁፎችን ባላነብም ታላላቅ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን አረጋግጠውልኛል፡፡
የሃውልቱ ፋይዳ ታሪክን ማስተላለፍ ነው፡፡ እኛ ከዚህ ታሪክ ነው የወጣነው፣ ከዚህ ታሪክ ነው የበቀልነው፣ ከታሪካችን እንማር--- በሚል ሃውልቱ መገንባቱ ነውር የለውም፡፡ ታሪክ በመፅሃፍ መልክም ለትውልድ ይተላለፍ የለም እንዴ? ሃውልቱ ይፍረስ የሚለውን ቅስቀሳ  አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ ሃውልቱ የበቀል ሳይሆን የመማሪያ ነው፡፡ መኖር አለበት፡፡


“እውነተኛ አርቲስት የጥላቻ መንፈስ አያንፀባርቅም”
ዶ/ር ሃይሉ አርአያ (ፖለቲከኛ)

ስለ አኖሌ ሃውልት የጠለቀ ግንዛቤው ባይኖረኝም በአጠቃላይ በሀገራችን የተገነቡ ሃውልቶችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ተናግሬያለሁ፡፡ በሃገራችን የታየው የሃውልት ግንባታ የሚያሳዝንና አደገኛም ነው፡፡ ምክንያቱም የእውነተኛ ሃውልት አላማ ህዝብን ማሰባሰብ፣ የብዙሃኑን ተጋድሎና መንፈስ የሚያንፀባርቅና ለመጪው ትውልድም ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ አሁን  በሃገራችን የማያቸው ሃውልቶች ግን ህዝብን የሚያሰባስቡ ሳይሆኑ የሚያራርቁ  ናቸው፡፡ ቂም በቀል አስታዋሽ፣ ቁስል ቆስቋሽ ናቸው፡፡ ስለዚህ ፋይዳቸው ዝቅተኛና አደገኛ ነው፡፡
በአጠቃላይ የሚገነቡትና የተገነቡት ሃውልቶች ገፅታ ከፋፋይ ነው፡፡ ወደ ኋላ የሚመልሰን ነው ስል፣ ከሃገሪቱ መፃኢ እድል አንፃር ተመልክቼው ነው። አሁን የሚያስፈልገን ያለፈውን ቁስል እያስታወስን በመካከላችን ቅራኔና ጥላቻ፣ ቂም በቀል ማናፈስ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ አዲስ ህይወትና ራዕይ ማምጣት ነው መሆን የነበረበት፡፡ ግጭትና አንዱ በሌላው ላይ በደል ማድረስ በኛ ሀገር አይደለም የተጀመረው፡፡ አሁን ታላላቅ መንግስታት ሆነው የምናያቸው አገራት ህዝቦች፣ በየዘመኑ ከፍተኛ እልቂትና በደሎች አሳልፈዋል፡፡ እነዚያ እልቂቶችና በደሎችን በማስታወሻ ፅፈው ያስቀምጧቸዋል እንጂ 24 ሰዓት ሙሉ ቂም በቀል የሚቀሰቅስ ሃውልት የሰሩ አይመስለኝም፡፡
ለምሳሌ 6 ኪሎ ያለው የሰማዕታት ሃውልት ያሳዝነኛል፡፡ ምክንያቱም ሃውልቱ የሚያስታውሰው መራራ ነገርን ነው፣ እልቂትን ነው፡፡ እርግጥ በውጭ ወራሪ የተፈፀመን ታሪክ ነው የሚያስታውሰው፣ ከዚያ አኳያ ምናልባት የወረራውን ግፍ የሚያሳይ ስለሆነ፣ ሃውልቱ ተገቢ ነው ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ያም ቢሆን ዛሬ አለማችን ትንሽ እየሆነች በመጣችበት ጊዜ፣ተበዳይና በዳይ ህዝቦች መቀራረባቸው አልቀረም፡፡ ዛሬ ጣሊያን  ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ በከፍተኛ ሁኔታ ህዝብና መንግስትን እየደገፈች ነው፡፡ ከዚያ አኳያ ሲታይ፣ ያ ሃውልት ጠቃሚ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ እኔ በግሌ እንዲህ ያለ ሃውልት ጠቀሜታው አይታየኝም፡፡ በሰዎች መካከል መተባበርን መቀራረብንና መፈቃቀርን የሚሰብክ ሃውልት ነው መገንባት ያለበት እንጂ ቂም በቀልን የሚያስታውስ መሆን የለበትም፡፡
አኖሌ ላይ እንደተባለው ጡት መቁረጥ የመሳሰሉት ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በሌሎች ሃገሮች እንደሚፈፀመው ተፈፅሟል ቢባል እንኳ የዛሬ 100 ዓመት ገደማ የተፈፀመ በደል፣ ዛሬ ላለነው ትውልዶች አብሮ መኖርና መስራት እንቅፋት መሆን የለበትም፡፡ ይሄ ሃውልት ግን የሚሰብከው መፈቃቀር ጠፍቶ፣ ጥላቻ ስር እየሰደደ እንዲሄድ ነው፡፡ የጥላቻና የቂም በቀልን ችግኝ የሚኮተኩት ነው፡፡
እኔ በግሌ በአፈታሪክ ጉዳዩን ሰምቻለሁ፣በፅሁፍ ግን አላጋጠመኝም፡፡ ከተፈፀመም በእውነት ታሪኩ አሳዛኝ ነው፡፡ በየትኛውም ጦርነት ሴቶች የተለየ ክብር እና ጥበቃ ነው የሚደረግላቸው፡፡ ጡት መቁረጥ የሚለውን እኔ ማመንም ይቸግረኛል፡፡ ይሄን ድርጊት የፈፀመው ምን አይነት ህዝብ ነው?
ከዚህ ሃውልት ማንም አይጠቀምም፡፡ ቂም በቀልን ማስታወስ እሳቱ የሚበላው አስታዋሹንም ጭምር ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሚያስፈልገን እንዲህ ያለው ነገር አይደለም። ታሪኩ አይረሳ ነገር ግን በመዝገብ ተመዝግቦ ይቀመጥ፣ ታሪኩ ተጠንቶ በትምህርት መልክ ይሰጥ፡፡ የኛን አብሮ መኖር ህልውና የሚፈታተንና መርዝ የሚረጭ ሃውልት ማቆም ግን ተገቢ አይደለም፡፡ መጥፎ መጥፎውን እናስብ ከተባለማ፣ መንቀሳቀስ የማንችል ሰዎች ነው የምንሆነው።
እኔ ይሄን ሃውልት የሰራው አርቲስትም ይገርመኛል። በእኔ እምነት አርቲስት አይደለም፡፡ እውነተኛ አርቲስት ይሄን የቂም በቀልና የጥላቻ መንፈስ ማንፀባረቅ የለበትም፣ ምክንያቱም አርቲስት የፍቅር ስሜት ያለው፣ ሩህሩህ፣ ህዝብን የሚያፈቅር ነው፡፡ ሰላምን፣ የህዝብ መተባበርን የሚፈቅድ ነው፣ እውነተኛ አርቲስት፡፡ እናም የሃውልቱን መገንባት አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡  



“ፖለቲካዊ ግብ ያለው ሃውልት ነው”
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የፍልስፍና ምሁር)

በዚህ 24 አመት ውስጥ የታሪክ ነጋሪ ነኝ በሚል ፈሊጥ፣ ብዙ መርዶ ነጋሪዎች በዚህች ሃገር ላይ ተበራክተዋል፡፡ ይሄም ሃውልት የመርዶ ነጋሪዎቹ ሃውልት ነው፡፡ ታሪክ በጣም ውስብስብ ነገር ነው፡፡ ብዙ ዓመት መጠናት አለበት፡፡ መርዶ ነጋሪዎች ግን ከየት እንደሚያመጡት ባይታወቅም፣ በእንደዚህ ያለ ጊዜ እንዲህ ተደርጓል የሚሉ ማስረጃ አልባ ታሪኮችን እያወሩ፣ሁልጊዜ በህዝቦች መሃል ግጭትና ፀብ ተንጠልጥሎ እንዲቀር የሚያደርጉ ሰዎች ሥራ ነው ብዬ ነው ሃውልቱን የምወስደው፡፡ የመርዶ ነጋሪዎች ሃውልት ነው፡፡ የታሪክ ውጤት አይደለም፡፡
ለምሳሌ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሃውልት መኖር ያለበት፣ ያ ታሪክ እንዳይደገም የሚያሳስብ አዎንታዊ ሚና ስላለው ነው፡፡ አውሮፓ፣ አሜሪካ --- ወዘተ እንዲህ መሰል ድርጊቶች የተፈፀሙበት ሃገር ሁሌ ተመሳሳይ ሃውልት አለ፡፡ ይሄኛው ጠብ ለመጫርና ህዝብን ለማለያየት የተሰራ ስራ ነው፡፡ ሃውልቱ የተሰራላቸው ወገኖችና የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑ በርካታ ዜጎችን ድጋፍ እንኳ ያላገኘ ሃውልት ነው፡፡ እንደው በደፈናው ሃውልቱ ፖለቲካዊ ግብ ያለው ሃውልት ነው፡፡ ለወደፊት ከዲሞክራሲውና ከሃገሪቱ እድገት ጋር ሁኔታዎች ይሻሻላሉ ከሚል እሳቤ በመነሳት፣ ምናልባት ይህ ሃውልት በሰፊው ህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ስለማይኖረው ቂም በቀልን የማስተላለፍ ሃይሉ ሊቀንስ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አርቆ አሳቢ ነው፡፡ ህዝቡ እንደ ካድሬዎቹ አይደለም የሚያስበው። ህዝቡ እንደዚያ ቢያስብ ኖሮማ፣ ከተለያየን ቆየን እኮ! በየክልሉ ያለው አብዛኛው ህዝብ አርቆ አሳቢ እና ለሀገሩ ቀናኢ ነው፡፡ አንዳንድ ወጣቶች የካድሬዎቹን መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ፡፡ ግን ግዴለም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንካራ ማህበረሰባዊ ትስስሮሽ ያለው ህዝብ ስለሆነ፣ይህን መሰል ሃውልት በድንጋይም ሆነ በብረት ተሰራ ዋጋ አይኖረውም፡፡ በጊዜው በብዛት በአርበኝነት የእዚችን ሃገር ባንዲራ በክብር ያቆሙት እኮ የብሄሩ ተወላጅ አርበኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሃውልቱ የጥላቻ ግንብ ቢሆንም መጪው ትውልድ ሊቀበለው አይችልም፡፡



“ሃውልቱ ቢገነባ ሌላው ምን ያንጫጫዋል?”
አቶ ገብሩ ገ/ማርያም (የመድረክ አመራር)

የኢትዮጵያ ችግር ዘርፈ ብዙ ሆኖ እያለ፣ሰሞኑን ለምን አኖሌ ላይ ሃውልት ተሰራ ብለው የሚንጫጩ ሰዎች ይደንቁኛል፡፡ የሰው ልጅ ጡት እኮ ነው የተቆረጠው! የሰው እጅ እኮ ነው የተቆረጠው! በጥይት ሲሆን እኮ ወዲያው ነው የሚሞተው፡፡ ባህላቸውን ለማክበር ወተት ተሸክመው የሄዱ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ጡታቸው የተቆረጠው፤ ይሄ ነው ታሪኩን ልዩ የሚያደርገው፡፡ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ድርጊት በዓለም ላይ ተፈፅሟል የሚሉ የታሪክ አዋቂዎች አላጋጠሙኝም፡፡ ታዲያ ዛሬ ለነዚህ ሰማእታት ሃውልት ቢገነባ የታሪክ ፀሃፊ ነን፣ አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች ምን ያነጫንጫቸዋል? እነዚህ የታሪክ አዋቂ ነን ባዮች እኮ በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት፣ ኦሮሞ ሸዋ ውስጥ ያልነበረ ብሄር ነው ብለው ሲፅፉ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱ እንደሚያወሩት፣ የሃውልቱ ፋይዳ ቂም ለማስተላለፍ አይደለም፡፡ በፊት እንደዚህ ነበረ ለማለት ነው፡፡ አሁን የድንበር ክለላዎችን እናስወግድ በሚባልበት በ21ኛው ክ/ዘመን ዘመን ቂም አይኖርም፡፡
ለምን የህውኃት ሰዎች ሃውልት ሲሰራ እነዚህ ሰዎች አልተንጫጩም? እኔ ይገርመኛል! ይሄኛውስ ከሰማዕትነት በምን ይለያል? ታሪኩን በሚገባ አውቃለሁ፡፡
ሰዎቹ አንድ በአል ለማክበር ወተት፣ ገንፎ፣ ቅቤ እና አባገዳዎች የሚይዙትን ተሸክመው በአላቸውን ለማክበር ሲሉ ነው ከበዋቸው፣ ዋና አዛዣቸውን መጀመሪያ ገድለው፣ ከዚያ በኋላ ሴቶቹን ጡታቸውን፣ ወንዶቹን እጃቸውን እየቆረጡ የለቀቁዋቸው፡፡ ይሄ በሌላ አለም የተፈፀመ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በወደቁበት ቦታ ላይ ሃውልት መስራት ምንድን ነው ነውሩ? መንጫጫቱስ ከምን አይነት ንቀት የመነጨ ነው? የብሄር ልዩነት አስፍቶ ግጭት ያመጣል የሚባለው የማይሆን ቅዠት ነው። ይልቅስ የምሁራኑ አስተሳሰብ ነው የሚያሰፋው፡፡ እኔ በአጠቃላይ የምለው ሃውልቱ መገንባቱ ጥሩ ነው፣ እነዚያን ሰማዕታት እናስታውስበታለን ነገር ግን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንደመሆናችን፣ ዘመኑ የሚፈቅደውን ስራ እንስራ ነው መባል ያለበት፡፡ መንጫጫቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንደህ አይነት ታሪክ ደርሶብናል የሚሉ ካሉም፣የራሳቸውን ይገንቡ ሌላውን ግን አይንኩ፡፡ የቀይ ሽብር ሃውልት ሲሰራ፣ በነጭ ሽብር ኢህአፓ የፈጃቸው ሰዎች ሃውልትስ? ዛሬም ድረስ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ታሪክ አዋቂዎች፣ ፕሮፌሰሮች የማስተላልፈው መልእክት፣ ወሬ በማናፈስ ይህቺን ሃገር አትበትኗት የሚል ነው፡፡


“ዛሬ የኦሮሞን ህዝብ እየበደሉ ያሉት እነሱ ናቸው”
ዶ/ር ሞጋ ፍሪሣ (የኦፌኮ አመራር፤ ፖለቲከኛ)


 ወደ ኋላ ሄዶ ታሪክ ጎልጉሎ ማውጣት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምኒልክ ግዛት ለማሰባሰብ ጦርነት አካሂደዋል፣ ይሄ የሚታወቅ ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ይሄ ተደረገ ብለው ታሪክ ለመንገር የሚሞክሩት እነሱ እነማን ናቸው? ዛሬ የኦሮሞን ህዝብ አንድነት በማናጋት ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው እኮ እነሡ! ታሪክን ለመንገር ብቁ አይደሉም፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የአኖሌ ታሪክን ማውጣቱ ትርጉሙ ምንድን ነው? ይሄን ለማድረግስ ምን የሞራል ብቃት አላቸው? ለወደፊት በሚገባ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚፃፍበት ጊዜ ለሃገራቸው ጥሩ የሰሩ ሰዎች ታሪክ ይወጣል፡፡ እነሱም ዛሬ ወንድሞቻቸውን እየገደሉ እኮ ነው? ታሪክ ለመፃፍ ብቁ አይደሉም፡፡ አሁን ታሪክ ብለው የሚያወሩ ሽማግሌዎችም እውነተኛ ኦሮሞ አይደሉም፡፡ በገንዘብና በጥቅም ተደልለው ነው፣ ታሪኩን ይሄ ነው ብለው የሚያወሩት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ በጣም ደግ ህዝብ ነው፡፡ በነሱ አካሄድ ቢሄድ ኖሮ፣ ኦሮሞና አማራው ተፋጅቶ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡን እያፋጀ፣ በሌላ በኩል ደርሰው ታሪክ ነጋሪ ነን ማለት አይገባቸውም፡፡ መጀመሪያ ራሳቸውን ከኢህአዴግ ምርኮ ነፃ ማውጣት አለባቸው፡፡ እኔ የልዩ ቀዶ ህክምና ባለሙያ (Special Surgeon) ነኝ፡፡ ታሪኩን አልተመራመርኩም ነገር ግን በጦርነት ጊዜ ብዙ ነገር ይፈፀማል፡፡ ለምሳሌ ድሬደዋ ላይ ብቻ የተፈፀሙ የድሮ ታሪኮችን ጎልጉለን ብናወጣ ብዙ ነገር እናገኛለን፡፡ ያሸነፈው አካል እንዲህ ያለ ነገር መፈፀሙ የተለመደ ነው፣ እነሱ አሁን የሚሰሩትን ጥፋትና ተንኮል ለመሸፈን ሲሉ ነው ይሄን ያመጡት፡፡ ሰዎች እርስ በእርሳቸው በሚናከሱበት ጊዜ ላይ፣ ይሄን ሃውልት መገንባቱ በእሳት ላይ ቤንዚን መጨመር ነው፡፡
ዛሬ መነገር ያለበት አንድነታችንን ስለምንጠብቅበት ሁኔታ ነው፡፡ ዛሬ ከወገኖቻችን ጋር ተስማምተን የሃገራችን የአንድ ኢትዮጵያን ጥቅም የምናስከብርበት ጊዜ መሆን አለበት እንጂ ወደ ኋላ ሄዶ ታሪክ እየመዘዙ እንዲህ ያለውን ነገር መፈፀሙ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ዛሬ እኮ የኦሮሞን ህዝብ እየበደሉ ያሉት እነሱ ናቸው፡፡    





Read 11291 times