Saturday, 24 May 2014 14:07

“ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ሱዳንና ግብፅ መተባበር ነበረባቸው”

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(6 votes)

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የህዳሴ ግድብ፤ በሱዳን፣ ግብፅና ኢትዮጵያ ትብብር መሠራት ነበረበት (ያሉት የሱዳን የውሃ ኤክስፐርት ዶ/ር ሳልማን አህመድ ሳልማን፤ “ወደፊትም ተመራጩ መፍትሔ የሦስቱ አገራትና የሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ትብብር ነው” ብለዋል፡፡
“ሱዳን እና የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መልካም እድሎች እና ፈተናዎች” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በሱዳን በተዘጋጀ ወርክሾፕ ላይ ጥናት ያቀረቡት ዶ/ር ሳልማን፤ የተፋሰሱ አገራት በወንዙ ላይ እኩል መብት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ “በዚህ መንገድ የተቃኘ የትብብር ሀሳብ፣ ስድስት አገራት ተስማምተውበት ፈርመዋል፤ በኢትዮጵያ ፓርላማም ፀድቋል” ያሉት ዶ/ር ሳልማን፤  “አምስት ፈራሚ አገራት በፓርላማ ካፀደቁት በአለም አቀፍ ህግ መሰረት አስገዳጅነት ያለው ህግ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የትብብር ማእቀፉ ታሪካዊ መብታችንን ያሳጣናል በሚል ግብፅና ሱዳን የሚያሰሙትን ተቃውሞ መሰረተቢስ ነው ሲሉም አጣጥለውታል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቴክኒክ፣ በኢኮኖሚም ሆነ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የሚደገፍ ነው ያሉት ኤክስፐርቱ፤ ግድቡ በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ ትብብር መሰራት ነበረበት፤ ቀድሞ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ግብፅና ሱዳን ባለፉት ዓመታት  ያጋጠሟቸው ችግሮች አይፈጠሩም ነበር ብለዋል፡፡ ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል በመግዛት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ትሆናለች  ያሉት ዶ/ር ሳልማን፤ ሱዳን በ1959ኙ ስምምነት መሰረት  ከተመደበላት ኮታ ውስጥ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ ለምን እንዳልተጠቀመች  የመስኖና ተፈጥሮ ሀብቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሹመኞቿ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የግብፅ የኢንፎርሜሽን አታሼ አብዱራህማን ናስር፤ የተፋሰሱ አገራት የሌሎችን አገራት ፍላጎት በማይነካ መልኩ የሚያካሂዱትን ልማት ግብፅ ትደግፋለች  ሲሉ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

Read 2439 times