Monday, 19 May 2014 09:17

“አድናቂዎቼ ፍፁም ጤነኛ መሆኔን እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ” ድምፃዊ ዝናሽ ፀጋዬ (ያሃቢቢ)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በሶሻል ሚዲያ ላይ ስላንቺ የተፃፉ ነገሮች አሉ፡፡ ምንድነው ነገሩ?
በ”ቃል ኪዳን” መጽሔት ላይ የወጣውን መረጃ አይተሽ ይሆናል፡፡ መጽሔቱ ይዞት የወጣውን መረጃ ተመርኩዞ ነው ሶሻል ሚዲያውም የስም ማጥፋት ውንጀላውን የቀጠለው፡፡ አስገራሚው ነገር መጽሔቱ ከእኔ ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅም ሆነ የተለዋወጥነው መረጃ የለም፡፡ ዘገባው ሲወጣ፣ እኔ ከነአካቴው አዲስ አበባ አልነበርኩም፤ ለስራ አዳማ ሄጄ ነበር፡፡ የፋሲካን በዓል እንኳን ከቤተሰብ ጋር አላሳለፍኩም፡፡
በአሜሪካና በእስራኤል ኮንሰርት ለማቅረብ ከፕሮሞተሮች ጋር ጨርሼ፣ ኤምባሲ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነበርኩ፡፡ የአዳማ ስራዬን ጨርሼ፤ ፕሮሞተሬ ጋር ስደውል አስደንጋጭ መልስ ሰጠኝ፡፡
ምን አለሽ?
መፅሄቱ ያወጣውን ዘገባ ነው የነገረኝ፡፡ የአዕምሮ ጤንነቴ እንደታወከና ሰሜን ሆቴል አካባቢ የሚገኘውን ቤቴን ለቅቄ፣ ኦሎምፒያና ላፓሪዚያን አካባቢ እንደምውል ፅፎ ከእነፎቶዬ አውጥቶታል፡፡ ከአንድ ወር ስራ በኋላ ተመልሼ አዲስ አበባ ስመጣ፣ ጉዳዩን ለብሮድካስት ኤጄንሲ አመለከትኩ፡፡ ብሮድካስት ኤጀንሲም መፅሄቱ ማስተባበያ እንዲያወጣ ነገረው። ማስተባበያው ግን አልተሰራም፡፡ ይሄንንም አሳወቅሁኝ፡፡ ወሬው ቤተሰቤን ሁሉ ግራ አጋብቶ ነበር፡፡ እናቴ አሁንም ድረስ ታማ ተኝታለች። እኔ ቤተሰብ የማስተዳድር ሰው ነኝ፣ ሌሊት ሰርቼ ቀኑን ሙሉ የምተኛ ሰው አይደለሁም፡፡ ይሄው መጽሔት ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ላይም የስም ማጥፋት ውንጀላ ፈጽሞበታል፡፡ ለጎሳዬ እንደውም ማስተባበያ ሰርተውለታል፤ ያውም ከእኔ በኋላ ነው ለማንኛውም በመፅሄቱ ላይ ክስ ለመመስረት ሂደቱን ጀምሬአለሁ፡፡
የውጭ አገር ኮንሰርቱ ምን ደረሰ?
የተናፈሰው ወሬ ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ውጭ አገርም ደርሷል፡፡ አንድ ፕሮሞተር ደግሞ ለኮንሰርት ሰው ሲወስድ፣ ታሪኩን በደንብ አጥንቶ ነው እንጂ ዝም ብሎ ከፍተኛ ብር አውጥቶ ሪስክ አይወስድም፡፡ ፕሮሞተሬ ኤምባሲ ለቪዛ ከመግባቴ በፊት ማድረግ ያለብኝን ነገር እንደሚነግረኝ ገልፆልኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን ከእኔ ጋር ያሰበውን ኮንሰርት ሰርዞ፣ ከሌላ ድምፃዊ ጋር መዋዋሉን ነገረኝ፡፡ ምክንያቱን እንዲነግረኝ ጠይቄው ነበረ፡፡ ለጊዜው ትቼዋለሁ ብቻ ነው ያለኝ፡፡
ከዚህ ቀደም የውጭ አገር ኮንሰርቶች ሰርተሻል?
አረብ አገራት በሙሉ የቀረኝ የለም፡፡ አሜሪካና እስራኤል ግን የመጀመሪያዬ ጊዜ ነበር።
እስካሁን ስንት አልበሞችን ሰርተሻል?
“ሀቢቢ” የሚለውን ሙሉ አልበሜን ከሰራሁ በኋላ፤ አሁን ሁለተኛ ስራዬን ማስተሩን ጨርሻለሁ፣ እነ ይልማ ገብረአብ፣ መሰለ ጌታሁን፣ ሱራፌል አበበ፣ አዱኛ ቦጋለ የተሳተፉበት ሙሉ ስራ አልቆ ተቀምጧል፡፡ ምክንያቱም አሁን ሙዚቃ ቤቶች የኮፒራይት ጉዳይ ስለሚያሳስባቸው ስራዎችን አይቀበሉም።
አሁን ምን እየሰራሽ ነው ታዲያ?
አንድ የሱዳን ካምፓኒ ከሱዳን አገር መጥቶ፣ ሙሉ የሱዳንኛ ዘፈን ከፍሎ አሰርቶኛል፡፡
ምን ያህል ተከፈለሽ?
ለአስራ አንድ ዘፈኖች፤ አስራ ሶስት ሺህ ብር ነው የከፈሉኝ፡፡  ከእነ ባንዳቸው መጥተው እዛ አገር የሚወደዱ ሱዳንኛ ዘፈኖችን አሰርተውኛል።  
ከሙዚቃ ስራ ውጪ በምን ትተዳደሪያለሽ?
እኔ የስምንት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ፤ የምኖረው ከእናቴ ጋር ነው፡፡ “ሀቢቢ ባንድ” የሚባል የራሴ የሙዚቃ ባንድ አለኝ፡፡ አሁን ለጊዜው ስራው ስለቆመ ንግድ ጀምሬያለሁ። ኮስሞቲክሶችና ሌሎች የመዋቢያ ቁሳቁሶችን ይዤ ባዛር ላይ እሳተፋለሁ፡፡ አሁን ሙዚቃ ብዙም አዋጪ ስላልሆነ፣ ባለኝ አቅምና ችሎታ ወደ ንግዱ እየገባሁ ነው፡፡ በቅርቡ “ጥራኝ አዳማ” የሚል ነጠላ ዜማ ለቅቄያለሁ። ለመኖርም ለመስራትም የማስበው አዳማ ነው፡፡ አሁን ጥሩ ስሜት ላይ ስላልሆንኩ ትንሽ እረፍት እፈልጋለሁ፡፡ ቤተሰቤን ይዤ። በተሰራው ስራ በጣም ነው የከፋኝ፡፡ ስሜን ያጠፉት ኢትዮጵያዊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች ናቸው። እኔ ፍፁም ጤነኛና የስራ ሰው መሆኔን ማንም ኢትዮጵያዊና አድናቂዎቼ በዚህ አጋጣሚ እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ፡፡

Read 3854 times