Monday, 19 May 2014 09:09

ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዶ/ር መለሰ ተመስገን አህጉራዊ ሽልማት ተቀበሉ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(8 votes)

የፈጠራ ስራቸው የስንዴን ምርት ከ3 እጥፍ በላይ ማሳደግ አስችሏል ከ42 ሃገራት የተውጣጡ 700 ተመራማሪዎች በውድድሩ ተሳትፈዋል

            ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዶ/ር መለሰ ተመስገን፣ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለአፍሪካ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጡ የፈጠራና የምርምር ውጤቶችን ለሚያበረክቱ ተመራማሪዎች በየአመቱ የሚሰጠው ‘ኢኖቬሽን ፕራይዝ ፎር አፍሪካ’ የተባለው ታላቅ አህጉራዊ ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ዶ/ር መለሰ ለዚህ አህጉራዊ ሽልማት የበቁት፣ ‘አይባር ቢቢኤም’ የተባለውና በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ በመቅረብ ላይ የሚገኘው የኮትቻ አፈር ማጠንፈፊያ መሳሪያ የፈጠራ ስራቸው፣ የህዝብን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ለውድድር ከቀረቡ በርካታ የፈጠራና የምርምር ውጤቶች ብልጫ በማሳየቱ እንደሆነ በተለይ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለተመረጡና የላቀ የምርምር ውጤት ላበረከቱ ተመራማሪዎች በየአመቱ ሽልማት የሚሰጠው አፍሪካን ኢኖቬሽን ፋውንዴሽን (The African Innovation Foundation) የተባለው ተ ቋም ፣ ዘ ንድሮም ከ42 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 700 ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች በዕጩነት የቀረቡበት ውድድር በማካሄድ፣ ከተደጋጋሚ ምዘናና ማጣሪያ በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት በናይጀሪያ አቡጃ በተካሄደ ስነስርዓት ላይ ኢትዮጵያዊውን ዶ/ር መለሰን ጨምሮ ሶስት የአህጉሪቱ ምርጥ ተመራማሪዎች ሸልሟል።

ዶ/ር መለሰን ለዘንድሮው የ‘ኢኖቬሽን ፕራይዝ ፎር አፍሪካ’ ተሸላሚነት ያበቃቸው ‘አይባር ቢቢኤም’፣ የተባለው የቴክኖሎጂ ፈጠራቸው፤ ውሃማ አካባቢዎችን በቀላሉ ለማጠንፈፍ የሚያስችል ሲሆን፣ ቀደም ሲል ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዶ/ር መለሰ ተመስገን አህጉራዊ ሽልማት ተቀበሉ የፈጠራ ስራቸው የስንዴን ምርት ከ3 እጥፍ በላይ ማሳደግ አስችሏል ከ42 ሃገራት የተውጣጡ 700 ተመራማሪዎች በውድድሩ ተሳትፈዋል በአለም አቀፍና ሀገራዊ የምርምርና የትምህርት ተቋማት በምርምር የተሰሩት መሳሪያዎች ዉጤታማ ሳይሆኑ መቆየታቸው የተጠቀሰ ሲሆን የእሳቸው ፈጠራ ችግሩን ለመቅረፍ እንደቻለ ታውቋል። ተመራማሪውን ለሽልማት ካበቋቸው ምክንያቶች መካከል፣ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ ለየት ባለ አቀራረብ ሰርተው ያወጡት ይህ የኮትቻ አፈር ማጠንፈፊያ መሳሪያ፣ የግብርና ምርትን በማሳደግና የህዝቡን ኑሮ በመቀየር በኩል ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑ በተግባር መረጋገጡ ተጠቃሽ ነው።።

መሳሪያው በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ የሚቀርብ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑም ተፈላጊ እንደሚያደርገው የተናገሩት ዶ/ር መለሰ፣ እስካሁን በ ጥቅም ላ ይ በ ዋለባቸው ማ ሳዎች ላ ይም የስንዴ ምርትን ከሶስት እጥፍ በላይ ድረስ ለማሳደግ መቻሉንና በአመት ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ለማምረት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎችም የዝናብ ውሃን በማቆር ምርታማነትን ለማሳደግ እንደተቻለ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ለአነስተኛ መስኖና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚውልና በአለም ላይ ካሉ ተመሳሳይ መሳሪያዎች የተሻለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በኢትዮጵያ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ቦታ፣ ውሃ የሚተኛበት በመሆኑ የግብርና ስራ የማይከናወንበት ሲሆን የዚህ መሳሪያ መፈጠር መሰል ቦታዎችን ለእርሻ ስራ በማዋል በአገሪቱ ምርታማነትን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተነግሯል። ዶ/ር መለሰ ከያኔው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለማያ የግብርና ኮሌጅ በግብርና ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማእረግ ተቀብለው በግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት የሰሩ ሲሆን እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውካስል አፖንታይን፣ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወደ አገራቸው ተመልሰው በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በተመራማሪነት ለ15 አመታት ካገለገሉ በኋላም፣ ባገኙት የትምህርት ዕድል ኒዘርላንድ ውስጥ በሚገኘው ዴልፍት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ እና የዩኔስኮ የትምህርት ተቋም የውሃ ሃብቶች የትምህርት ክፍል፣ የፒኤችዲ ትምህርታቸውን ተከታትለው ተመርቀዋል።

ተመራማሪው፤ ብሄራዊ የግብርና ሜካናይዜሽን ምርምር ፕሮግራምን በማስተባበር የሰሩ ሲሆን በተለያዩ አገር አቀፍና አለም አቀፍ አውደጥናቶች ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማቅረብና ለህትመት በማብቃት ይታወቃሉ። ዶ/ር መለሰ ተመስገን፣ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አስር ያህል የምርምር ውጤቶችን በማውጣትም ጥቅም ላይ እንዲውሉም አድርገዋል። በሰኔ 2002 በኢፌዲሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አዘጋጅነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ጠቀሜታ ላይ በማዋል የላቀ ስኬት ላስመዘገቡ ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውን ብሄራዊ ሽልማት፣ ከቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እጅ የተቀበሉ ሲሆን ሁለት ጊዜ የሀገር አቀፍ ተሸላሚ በመሆንም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው። ዶ/ር መለሰ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት በማስተማር፤ እንዲሁም የማስተርስና የዶክትሬት ተማሪዎችን የምርምር ሥራ በማማከር ያገለገሉና በማገልገል ላይ ያሉ ከመሆናቸው ሌላ፣ ከ25 በላይ የጆርናልና ሌሎች ሳይንሳዊ ፅሁፎችን ያሳተሙ አንጋፋ ተመራማሪ ናቸው።

Read 3241 times