Monday, 19 May 2014 09:07

የመፅሐፍ ቅኝት

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(5 votes)

መንደርተኝነት፤ የስንኩል ፖለቲከኞች አስተሳሰብ ውጤት

ርዕስ - ዶክተር አሸብር እና ሌሎችም፤ / የገፅ ብዛት - 237 / የህትመት ዘመን - መጋቢት 2006 ዓ.ም / የሽፋን ዋጋ - በኢትዮጵያ 65 ብር፤ በአሜሪካ 10 ዶላር/ ህትመት - ኤች ዋይ ኢንተርናሽናል ደራሲ - አሌክስ አብርሃም / ዘውግ - አጭር ልብወለድ (መድበል)

/ ቅድመ ኩሉ

                       የሥነ ፅሁፍ ምሁራን፤ አጭር ልብወለድ ከክርስቶስ ልደት 3000 ዓመት በፊት እንደተጀመረ ማስረጃ እየጠቀሱ ያስረዳሉ። እንዲያውም አፍአዊ ስነቃል ወይም ተረትን እንደ አጭር ልብወለድ በመውሰድ ዘመኑን ከዚያም ያርቁታል። ስቴቨን ዊልከንስ የተባሉ የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪ እንደሚሉት፤ አንድን አጭር ልብወለድ ለመዳኘት ለማሄስ የሚከተሉትን አምስት መመዘኛዎች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ወጥነት (Originality) የደራሲው የፈጠራ ብቃት (creativity) ሴራ (Plot) ጭብጥ (theme) ፍጻሜ (ending) ከዚህ ሌላ አንድ አጭር ልብወለድ ከሰባት ሺህ እስከ አስር ሺህ በሚደርሱ ቃላት ብቻ መጻፍ እንዳለበት፤ ሆኖም አንዳንድ ምሁራን ከሁለት ሺህ እስከ አራት ሺህ በሚሆኑ ቃላት ብቻ መጻፍ አለበት ይላሉ። “ዶክተር አሸብር እና ሌሎችንም” ለማየት የተጠቀምሁት ከላይ የተዘረዘሩትን መመዘኛዎች ነው። ይህ ሲባል ሃያ አምስቱ ታሪኮች ሁሉ ተመዝነዋል ማለት አይደለም፤ ተነብበዋል፤ ግን ለማሳያ ያህል “ተሰቀለ ቢሉኝ ባርኔው ነው ብዬ” በሚል ርዕስ የተጻፈውን አጭር ታሪክ መርጨዋለሁ።

ለዚህ ምክንያቴ ከወቅቱ የአገራችን ሁኔታ ጋር ስለሚስማማ ነው። የትረካው ይዘት የታሪኩ ባለቤት (ተራኪው) አብርሃም የሚባል የአራተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው። በአንድ መኝታ ክፍል ውስጥ ስምንት ተማሪዎች ይኖራሉ፤ ከእነሱ ውስጥ ደግሞ “አስቻለው” የሚባል ጓደኛ ነበራቸው። አስቻለው “ሱስ” ከሚባል ነገር ሁሉ የሚቀረው አልነበረም፤ ያጨሳል፣ ይቅማል፣ ይጠጣል፣ ሃሽሽ ይጠቀማል፣ ይዘሙታል። ለዚህ ሁሉ ሱሱ ማስታገሻ ሲል ያገኘውን ሁሉ እየሸጠ ጓደኞቹን የሚያስመርር ሌባ ነበር። አንድ ቀን ምክንያቱ ባይታወቅም አስቻለው ራሱን ሰቅሎ ተገኘ። የተለያዩ ተማሪዎች እነ አስቻለው መኝታ ቤት እየመጡ ለቅሶ ደረሱ፤ እንዲያውም አንድ ቀን ከእነ መንደርተኝነት፤ የስንኩል ፖለቲከኞች አስተሳሰብ ውጤት ጨምሮ ብዙዎቹ ኮረዶች በቀላሉ ያፈቅሩት ነበር። የመጀመርያ ሚስቱን በ36 ዓመቱ ያገባው ፒካሶ፣ ሁለተኛ ሚስቱን በ79 ዓመቱ ነበር ያገባው - ያውም የ27 ዓመት ወጣት። አስቻለው መኝታ በር ላይ እንዲህ የሚል ሙሾ (የለቅሶ ግጥም) ተጽፎ ተገኘ “ተሰቀለ ቢሉኝ ባርኔጣው (የዲግሪ ቆብ) ነው ብዬ፣ ተሰቀለ ቢሉኝ ያ ሱሪው ነው ብዬ (የነበረው አንድ ያረጀ ጅንስ ሱሪ ብቻ ነበር)፣ ተሰቀለ ቢሉኝ “ግሬዱ” ነው ብዬ። ለካስ አስቻለው ነው ትልቁ ዱርዬ!!” ይህን ግጥም በደንብ ማየት ያስፈልጋል፤ ደራሲው ለታሪክ ማጓዣ የተጠቀመው ይህን ግጥም ነው። ግጥሙ የህዝብ ሲሆን የተገጠመውም ከሌሎች አርበኞች ጋር መራር መስዋዕትነት ከፍሎ ለዘውድ ያበቃቸውን በላይ ዘለቀን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በግፍ ከሰቀሉ በኋላ ነው።

“ተሰቀለ ቢሉኝ እንግቱ (ወታደራዊ ትጥቁ) ነው ብዬ፤ ተሰቀለ ቢሉኝ ሽጉጡ ነው ብዬ፤ ተሰቀለ ቢሉኝ ዝናሩ ነው ብዬ፤ ለካስ በላይ ኖሮአል ትልቁ ሰውዬ” የሚል ነው መሠረታዊው ግጥም። ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አንዱ ኳሽ ደግሞ ለጀግናው በላይ ዘለቀ የተገጠመውን ቀየረና ለዱርየው አስቻለው ተጠቀመበት፤ ግጥሙን ያነበበና አስናቀ የሚባል የጐጃም ልጅ እንዴት በጀግናው ይቀለዳል ብሎ አካኪ ዘራፍ ይላል፣ ደራሲው ይህንን ግጥም ነው የልብወለዱ የግጭት መነሻ ያደረገው። ከዚህ በኋላ ስቴቨን ዊልከንስ በአመለከቱን የአጭር ልብወለድ መመዘኛዎች መሠረት ልብወለዱን እንቃኘው። ወጥነት (Originality) “ተሰቀለ ቢሉኝ ባርኔጣው ነው ብዬ” ከወጥነት አንፃር ስናየው አዲስ ነገር ላናገኝ እንችላለን። ሆኖም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምን አይነት ሆደ ባሻ ትውልድ እያፈሩ እንደሆነ ትዝብቱን የገለጠበት መልካም ሃሳብ ነው። እርግጥ ነው፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ረብሻ ሊቀሰቀስ ይችላል፤ ሲቀሰቀስም ኖሯል።

ምክንያቱ ግን የመንደርተኝነት ጣጣ አልነበረም፤ ወይ ከምግብ ጋር የተያያዘ ቅሬታ ውጤት ነው፤ አለዚያም አገራዊ የፖለቲካ ጥያቄ ነበር ብቸኛውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲንጠው የኖረው። በሳል ጥያቄ ለማንሳት፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ፣ ንቁ አዕምሮ ያስፈልጋል፤ ንቁ አዕምሮ በሌለበት ህሊና ውስጥ ሊነሳ የሚችለው መናኛና እዚህ ግባ የማይባል እንቶ ፈንቶ ጣጣ ብቻ ነው። እንቶ ፈንቶ ሰው የጠራ ዓላማ የለውም፤ በአንጻሩ ለሽብር እና ግርግር ምቹ በመሆኑ፣ በሆነ ባልሆነው ከጓደኛው፣ ወይ ከጐረቤቱ፣ ወይም ከመ/ቤቱ ሰዎች ጋር አምባጓሮ ከመፍጠር አይመለስም። ለምን? እንዴት? ማን? ብሎ መጠየቅና መረዳት ሽንፈት ይመስለዋል። ስለሆነም ድክመቱን በረብሻ መጋረጃ ይሸፍነዋል፤ የእሱን ጣጣ የጐሳ ካባ ስለሚደርብበት ሌሎችን ያነካካል። ስለሆነም ልብወለዱ መናኛ በምትመስል ምክንያት የዘመናችንን እውነት የሚነግረን በመሆኑ ፍልስፍናው ወጥ ነው ማለት እንችላለን። የደራሲው የፈጠራ ብቃት (creativity) ደራሲው በበነነ በተነነው ሁሉ የሚጋጩ ወጣቶችንና ምስኪን ፖለቲከኞችን የታዘበው በጥልቅ ስሜት ነው። ይታዘባቸዋል፤ ይተቻቸዋል። ግን “ደካሞች፣ ስግብግቦች፣ መንደርተኞች…” ብሎ አይፈርጃቸውም። ይልቁንም እያዝናና፣ እያዋዛ ልክ ልካቸውን ይነግራቸዋል። በአንድ ክልፍልፍ ጐረምሳ ምክንያት፣ የሁለት ብሔረሰብ ተወላጆች ጐራ ለይተው ዩኒቨርሲቲውን በጥናትና ምርምር ፋንታ የብጥብጥ መስክ ሲያደርጉት ያሳየናል። በመሆኑም የቋንቋና የአገላለጥ ጥበቡ የደራሲውን ፈጠራ እንድናደንቅ ይጋብዘናል።

ሴራ (Plot) በልብወለዱ ውስጥ “ምን ይፈጠር ይሆን?” ብለን የምንጨነቅበት የተወሳሰበ ሴራ አናይም፤ ሴራው በጣም ቀላል ነው። የአገራችን የፖለቲካ ስርዓት ባመጣው ጣጣ ምክንያት መንደርተኝነት በመንገሱ፣ ለሀገር ዕድገት መሠረት መሆን የሚገባቸው ወጣቶች ምስኪኑን ድምር ህዝብ ጭምር ለመከራ ሲዳርጉት ማሳየት ነው፤ የልብወለዱ ሴራ። የአጭር ልብ ወለድ ዓላማ ደግሞ እንደ ረጅም ልብ ወለድ የተወሳሰበ ሴራ በመፍጠር ያንን ለመፍታት መቃተት አይደለም፤ ነጠላ ታሪክ መስርቶ ነጠላ ታሪኩን ሊያስኬድለት የሚችል ሴራና ውሱን ወኪል ባለ ታሪኮች (ገፀ ባህርይ የሚባለው) ብቻ የሚያስፈልጉት የጥበብ ዘርፍ ነው። በዚህ ስሌት ሲታሰብ፣ የልብ ወለዱ ሴራ የዘመናችን (የሀገራችን) ጉልድፍ መንደርተኛ አስተሳሰብ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ሴራው ከሁለት ብሔረሰብ በመጡ ወጣቶች መሃል የሚደረግ ድንገተኛ ፍልሚያ ነው። ጭብጥ (Theme) የልብወለዱ ጭብጥ ፖለቲካ ነው፤ ብላሽ የሆነ የመንደር ፖለቲካ። ብላሹ የመንደር ፖለቲካ ብዙውን (የሚመለከተውንም የማይመለከተውንም) የሚያነካካ ክፉ በሽታ ነው፤ ሊተላለፍ ይችላል። ሲተላለፍ ደግሞ ጦሱ ቀላል አይደለም።

እናም አንድ ትዕግስት የለሽ ተማሪ በጫረው የመንደርተኝነት እሳት የሁለት ብሔረሰብ አባላት የሆኑ ተማሪዎች ለከፍተኛ ብጥብጥና የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንመለከታለን። ይህ እውነት በየቀኑም ባይሆን፣ በየሳምንቱ፣ በየወሩ እና በየዓመቱ የሚከናወን ቋሚ የብጥብጥ አጀንዳ ነው። ቀሽም ፖለቲካና ግልብ ፖለቲከኛ ሲገናኙ እንዲህ ናቸው፤ ምንም የማያውቁ አርሶ፣ ተሸክሞ፣ ሰርቶ በሌዎችን ሁሉ ለመከራና እንግልት ይዳርጋሉ። በደቡብ ክልል በነበሩ የጉራፈርዳ አርሶ አደሮች ላይ የተወሰደውን የማሳደድ እርምጃ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተከሰተውን ተመሳሳይ የማሳደድ ጣጣ ልብ ማለት ያሻል። ሁሉም እርምጃዎች የግልብ ፖለቲከኞች የሥራ ውጤቶች ናቸው። በቅርቡ ባህርዳር ላይ ኳስ ሜዳ ውስጥ በተነሳ መለካከፍ ጉዳዩ ወደ አስቀያሚ የብሔር ግጭት መሸጋገሩም የዚሁ የግልብ ፖለቲካና ፖለቲከኞች የሥራ ውጤት ነው። ህዝቡማ በደርግም በኃይለሥላሴ ዘመንም በፍቅር የኖረ ክቡር ህዝብ ነው። ለትውልዱ የተዘጋጀለት መርዘኛ ወጥመድ ግን እጅግ አደገኛ ነው። አብሮ የኖረ ህዝብ ላይጫወት፣ ላይቀልድ፣ በአጠቃላይም እንደ ልቡ ላይንቀሳቀስ ነው ማለት ነው። ይህ ነው የልብ ወለዱ ሁነኛ ጭብጥ። ፍጻሜ (Ending) ልብወለዱ የሚጠናቀቀው “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ላማ፣ ሰበቅታኒ” ብሎ ነው።

ትርጉሙ “አቤቱ አባት ሆይ! ለምን ተውኸኝ” ማለት ነው፤ ቋንቋው ደግሞ እብራይስጥኛ። ይህ ታላቅ ልመና ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ሞቱን በተመኘበት ቅጽበት የተናገረው ነው። እኛንስ አምላክ ለምን ተወን? የሚል መልእክት አለው። የልብወለዱ ዋና ባለ ታሪክ፣ በረብሻው ምክንያት ክፉኛ ተደብድቦ፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኘው ክሊኒክ ራሱን ስቶ ከቆየ በኋላ ሲነቃ በፌደራል ፖሊሶች ተከብቦ በማየቱ ነው፣ ከላይ ያለውን ኃይለቃል የሚናገረው። እንደኔ እምነት ይህ ጥልቅ ፍልስፍና ነው፤ ፖሊስ ብጥብጥ እንዳይነሳ መከላከል እንጂ በዱላ ብዛት ራሱን ስቶ የወደቀ ምስኪን ተሰብስቦ መጠበቅ ምን የሚሉት ተግባር ነው? ያውም ተበዳዩን ወንጀለኛ በማድረግ። በአጠቃላይ “ዶክተር አሸብር እና ሌሎችም” የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ ሲሆን በምፀታዊ አቀራረቡ፣ ጥቃቅን በሚመስሉ የህብረተሰቡ የዕለት ተለት ጣጣዎች ላይ ትኩረት በማድረጉ፣ ጣፋጭ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ በመሆኑ ተነባቢነቱ፣ አስተማሪነቱና አዝናኝነቱ የጐላ እንደሚሆን አልጠራጠርም። ሆኖም በቋንቋ አጠቃቀም ላይ መጠነኛ ግድፈት ለምሳሌ “ከዚያ” በማለት ፋንታ “ከዛ” ዓይነት አጠቃቀም፣ “ነፍስ” በማለት ፋንታ “ነብስ” ማለት፣ “ኧረ ይሄ ነገር ይችን ሴትዮ ያሳብዳቸዋል (ገፅ 81)” አይነት አንድና ብዙ አጠቃቀም ስላለ ድጋሚ በሚታተምበት ወቅት ቢስተካከል (ቢታረም) መልካም ይመስለኛል።

Read 3524 times