Monday, 19 May 2014 08:55

የፊልማችን አገራዊ ፋይዳ

Written by  ፈለቀ የማርውሃ አበበ filmethiopia@yahoo.com
Rate this item
(1 Vote)

ACTION! “

… የመጀመሪያው የሕዝብ ሲኒማ ቤት በ1890 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተከፈተ። ሲኒማ ቤቱን የከፈተው አንድ ከአልጄሪያ የመጣ ፈረንሳዊ ነው። ይህን በዘመኑ የማይታመን ምትሀት መሰል ነገር የሚያየው ሕዝብ፤ የሲኒማ ቤቱን ‹‹ሰይጣን ቤት›› ብሎ ሰየመው። በተለይ ቀሳውስቱ #ሕዝቡ ከሰይጣን ቤት እየሄደ ሰይጣን እንዳያይ$ እያሉ ስላወገዙ ሲኒማ ቤቱ ከሰረ።$ (‹‹አጤ ምኒሊክ›› ከጳውሎስ ኞኞ - ገጽ - 337 - ‹‹ሲኒማ››)

          ስንት ውበት ጋረደን የነጎደው ዘመን ግዝት ሀይ ባይ አጥቶ የአዲስ ጥበብ ጥቅሻ ፀዳል ብርሃኗን ፈገግታዋን ፈርቶ አምናን የ ሀገር ሰው አ ይኑ ሲ ራብ ኖረ ቀ ድሞ! - ጭራ ቀርቶ! /‹‹ውበትና ዘመን›› - ያልታተመ።/ እነሆ፤ የፊልም ጥበብ፤ በየትም ስፍራ የመገኘት ልዩ ባህሪው፤ ከሰው ልጆች የእለት ተዕለት ህይወት ጋር ያለውን ቁርኝት ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶታል። በ2009 እ.ኤ.አ ፊልም በብዛት በሚታይባቸው ሀገራት የተደረገ ጥናት፤በአንድ አመት ብቻ 6.8 ቢሊዮን ያህል የፊልም መግቢያ ቲኬቶች መሸጣቸውን አረጋግጧል። ከአለም የህዝብ ቁጥር ጋ የሚስተካከል እንደማለት ነው። የቦክስ ኦፊስ ገቢውም 30 ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል። በዚያው አመት ከተለያዩ የቴሌቪዥን ቻናሎች የተሰባሰበውና 1.1 ቢሊዮን ብዛት ያላቸውን የዲቪዲና ብሉ ሬይን ሽያጭ ጨምሮ በአሜሪካ፣ ካናዳና አውሮጳ ብቻ 35 ቢሊዮን ዶላር አስገኝቷል።

የጥቁር ገበያው ገቢ ሲታከልበት ደግሞ ድምሩ አናት የሚያዞር አሀዝ ያመጣል። ትዝታ ለመምዘዝ ያህል፤እግረ መንገድም ለመነቃቃት፤ጥናቱ የተደረገበት ዘመን፤ኢትዮጵያዊው የፊልም ባለሙያ ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ፤ ‹‹ጤዛ›› በተሰኘው ፊልሙ ለበርካታ አለማቀፍ ሽልማቶች የታጨበትና ያሸነፈበት፤በተለይም የታላቁን የፓን አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል FESPACO AWARD ሽልማት፤በአፈ ታሪክ የስምንት ወንዶችን ጉልበት በሚያንበረክከው ጥንካሬዋ በምትታወቀው የምዕራብ አፍሪቃዋ ቡርኪናፋሶ ጥንታዊት ጀግና ንግስት ይኔንጋ እና ፈረሷ ምስል STALONE OF YENENGA በቡርኪናቤ ጠቢባን ቀጥቃጮች በነሀስ የሚሰራው ውብ ቅርፅ TROPHY በስፍራው የፊልማችን አገራዊ ፋይዳ በወኪልነት በተገኘችው እህቱ በወ/ሮ ሶሎሜ ገሪማ በኩራት ከፍ ብሎ የተነሳበት አመት ነበር - 2009 እ.ኤ.አ ።

ምንም እንኳ ትውስታው አሁን ከላይ ለጀመርነው ኢኮኖሚያዊ ንፅፅር ባይበጅም። እትዬ ሶሎሜም ይኸው የኢኮኖሚ መራራቅ ገብቷት ይመስላል፤ ሽልማቱን ስትቀበል በሰፊው የቡርኪናፋሶ ስታዲየም ለታደሙት ከአለም ዙሪያ ለተሰበሰቡ የፊልም አለም ሰዎች ባደረገችው ንግግሯ፤የነጻነት ታጋዩን የማርቲን ሉተርን I HAVE A DREAM ሀረግ ተውሳ ፤ ህልሟን ግን ‹‹አንድ ቀን አፍሪቃ የራሷ መገበያያ ገንዘብ እንዲኖራት›› ለመመኘት የተጠቀመችበት። የፊልም ሙያ፤ በሰው ልጆች የኢኮኖሚ ዑደት ውስጥ ያለው ፋይዳ ላቅ ያለ ነው። ለምሳሌ፤ የእንግሊዝ ካልቸር፡ሚዲያና ስፖርት ኮሚቴ፤ፊልም በብሄራዊው ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ግብአት አስመልክቶ ስለ ብሪቲሽ ፊልም ኢንዱስትሪ በ2001 እ.ኤ.አ ባቀረበው ሪፖርት ላይ…‹‹በ2001 እ.ኤ.አ ለጉብኝት ወደ ሀገሪቱ ከተመሙትና ለብሪቲሽ ቱሪስት ባለስልጣን visit britain መስሪያ ቤት 11.3 ቢሊዮን ፓውንድ ካስገኙለት 23 ሚሊዮን ቱሪስቶች መካከል 20 ከመቶው ስለ ሀገሪቱ ውበትና የህዝቦቿ ዘመናዊ አኗኗር፣ በፊልምና ቴሌቪዥን በቀረቡት መሳጭ ትእይንቶች ተማርከው የተጓዙ ናቸው።

እንዲሁም፤ በእንግሊዝ እያንዳንዱ ለፊልም ስራ የሚወጣ አንድ ፓውንድ በምላሹ የ1.50 ፓውንድ ትርፍ በማስገባት ኢኮኖሚውን ያስመነድጋል። ከ ራሳችን አ ንፃር ለ መመዘን የ ሚያበቃ አስተማማኝ የገቢና ወጪ መረጃ ቋት እስካሁን የለንም። ሆኖም ግን ይኼ ጊዜ፤ ከፋም ለማም፤ በሀገራችን የፊልም ሙያ በብዛት የተትረፈረፈበት ዘመንና መንግስት፣ ባለሞያዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ከየትየለሌ ተግዳሮቶቹ ጋ የየድርሻቸውን የሚቆነጥሩበት ጅማሬ ዘመን ለመሆኑ ምስክሩ ገሀዱ እውነት ነው… ዛሬ እዩት ምዕመኑን ወረፋ ሲጋፋ ‹‹ሰይጣን›› ማየት ሽቶ የሀገሬም ጠቢብ አምሮበት ተውቦ ‹‹ያይኔ ምሳ›› አምርቶ እዩት ‹‹ሴጣን ቤቱ››ም በሰዎች ሲሞላ መቶ አመት ቆይቶ። በመልካም ገፅታ ግንባታው በኩል ግን ፤ ዛሬ ዛሬ በአለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው የሚቆሙ የፊልም ጥበብ ውጤቶች ባመዛኙ ከይዘትና ቅርፃቸው አኳያ ቢበረበሩ ከመሆን አይድኑም። በተለይም፤ ችግሮችን በፊልም ሙያ አጉልቶ ማሳየት ተገቢነቱ ባይካድም፤ ስንትና ስንት ያልተነኩ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ እሴቶች ሞልተውን፤የበጃች ባዕዳንን ትኩረት ለማግኘት ሲባል ፤ የሀገርን ገመና የማስጣት ልምምዶች ባመዛኙ በጭብጥ ምርጫዎችና በተለይም ደግሞ የአጫጭር ፊልሞቻችን መልክ እስኪመስል ድግግሞሹ ተስተውሏልና።

ስለዬህም፤ለንባባችን ማንሸራሸሪያ የተሰደረው ስንኝ፤የሚጠቁም-የሚማፀነው፤ ዛሬም ድረስ በምዕራባዊያን የዜና አውታሮች ብቅ እያለ የሚያስበረግገን፤ ጆናታን ዲምቢልቢ የ1966ቱን ድርቅ አስመልክቶ ስለ ኢትዮጵያ ያቀረበው ዘጋቢ ፊልም፤ የአንድ ወቅት የድህነትና ጉስቁልና ምስል /Distorted Image/ እስከወዲያኛው ይቀረፍ ዘንድ ፤አልፎ አልፎ ጎልተው የሚወጡ የተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊያን የፊልም ባለሙያዎች ‹‹በፊልም የጠፋውን መልካችንን በፊልም እንቀይረው›› ድምፆች ከቁጭትም ባለፈ ተግባራዊ ምላሽ መሻታቸውን ነው። እልፍ ውግዘት ሰፍሮብን ኮድኩዶ ያኖረን ራዕይ አራቁቶ ከውበት ቆሌ ያራቀን የካቻምናን ክብር አመንምኖ አክስቶ አለሙም የሚያውቀን በተጠናገረው የዲምቢልቢ ፎቶ። የፊልም ጥበብ፤ ለባህል፡ለትምህርት፡ ለመዝናኛና ለፕሮፖጋንዳነት የሚውል ጡንቻማ መሳሪያ ለመሆን ችሏል። በ1963 እ.ኤ.አ ብሎዶን ዲሂንግራ ለዩናይትድ ኔሽን የትምህርት፣ ምርምርና ባህል ክፍል ባጠናቀሩት ሪፖርት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔህሩን ንግግር እንደጠቀሱት…‹‹በህንድ፤ የፊልም ሙያ በመላው ህዝብ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ፤ባጠቃላይ የጋዜጦችና መጻሕፍት ህትመቶች ሁሉ ተደምረው ያላቸውን አቅም ያስከነዳል።›› ብለዋል።

የህንድ የፊልም ገበያ በየሳምንቱ ለ25 ሚሊዮን ዜጎች ልዩ ልዩ የስራ ዘርፎችን አስገኝቶ፣ የዕለት ተዕለት ቀለባቸውን ይሰፍር የነበረው ገና ያኔ ከግማሽ ምእተ አመት በፊት ነበር። በ ቅርቡ በ ፊልምና ማ ህበረሰብ ዙ ሪያ በማጠንጠን የ ሚቀርቡ ጥ ናቶች ደ ግሞ፤ የ ፊልም ሙያ ከሰው ልጆች ስነ ልቦና ጋር ያለውን ግንኙነትም ዳስሰዋል። በ2005 እ.ኤ.አ ኖህ ሁህሪግ “‘Cinema is Good for You: The Effects of Cinema Attendance on Self-Reported Anxiety or Depression and ‘Happiness’” በሚል ርዕስ ለኢሴክስ ዩኒቨርሲቲ (University of Essex, UK) ባቀረቡት …የፊልም ጥበብ፤ያቀራረቡ ማራኪነትና ረቂቅነት በሰው ልጆች የአዕምሮ ጤና ላይ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል። ፊልም፤ በየትዕይንቶቹ የሚያቅፋቸው ድርጊያዎች ያላቸው ከድብርት የማላቀቅ፣ አእምሮን የማነቃቃትና መላ አካልን የማዝናናት ሀይል፤ ለተመልካቾች ነፃነትንና ዕድለኝነትን በመቸር /በህይወት ዘመናቸው በተአምር ሊደርሱበትና ሊያዩት እንደማይችሉ የሚያስቡትን አካባቢና አርዕስተ ጉዳይ ወይም በሩ…ቁ ያሉ ድንቅ ስብዕናዎችን… አይናቸው ስር ድቅን በማድረግ/ ላቅ ያለ የማይዳሰስ ስሜትና እርካታን ስለማጎናፀፉ ጉዳይ…ወዘተ::

በተጨማሪም ደግሞ ዘመኑ የፈጠረው ቴክኖሎጂ /ከአናሎግ - ዲጂታል/ ፊልምን ተደራሽነቱ በኢኮኖሚ ያልተገደበ እንዲሆን፤ ማንም ሰው ያሻውን ፊልም መርጦ የማየት እድልን አስገኝቶለታል ይላሉ። ሌላው እጅግ አስገራሚ የተባለውና በኮንላን፣ ቢግሬን እና ጆሀንሰን በ2000 እ.ኤ.አ የቀረበው የጥናት ውጤት ደግሞ ‹‹ፊልምን ደጋግመው የሚያዩ ሰዎች የመሞቻ እድሜያቸው የተራዘመ ነው። በዚሁም መሰረት ፊልምን የማያዩ ሰዎች ቢያንስ አንዳንዴም እንኳን ወደ ሲኒማ ቤት በመሄድ ከሚዝናኑ የፊልም ተመልካቾች ጋር ሲነፃፀሩ፤ የመሞት እድላቸው ስሌት በአራት እጥፍ የተራዘመ ነው።›› ይላል። የሦስቱ ምሁራን ጥናት የሚያመላክተው፤ሌሎች የማህበራዊ ተሳትፎዎቻችን በተገደቡበት ሁኔታ ውስጥ ሆነንም እንኳ፤ ከኪነ ጥበባት ውጤቶች ጋር ያለንን ትስስር መቀጠል መቻል፤ በህይወት ከመቆያ ተመራጭ መንገዶች አንዱ መሆኑን ነው። ‹የደላው ሙቅ ያኝካል›ን የሚተርት ቢኖር አይደንቅም። በአሜሪካዊያኑ ዘንድ በስፋት ተነባቢ በሆነው፤ ዛሬ ወጣቶቹ ኢትዮጵያዊያን የፊልም ባለሙያዎች እነ ዘረሰናይ ብርሀነ በተደነቀላቸው ‹‹ድፍረት›› በሯን ካንኳኩት ከአለም የፊልም መዲና ከሆሊዉድ አመሰራረት ጀምሮ፣ ስለ ፊልም ሙያ ዝርዝር መረጃ በተካተተበት An Empire of Their Own መጽሀፍ ደግሞ፤ ጥበቡ ከገንዘብ ምንጭነቱ ባሻገር በማህበረሰብ ላይ ስለሚያሳርፈው አሻራ ትንታኔ ይሰጣል።

ጸሀፊው ኒል ጋብለር፤ ‹‹በእኔ እምነት፤ የፊልም ሙያ በእለት ተዕለት ማህበራዊ ህይወት ላይ ተፅእኖ በማሳደር ማህበረሰቡን ክፉኛ ሊያንገዳግድ ይቻለዋል። እናም የዚህ ዘርፈ ቡዙ ተፅእኖ ጉዳይ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነገር ነው። ማህበረሰብ የተሸመነበትን የባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች እንዲያሰናስል እንጂ እንዳያነትብ ብርቱ ጥንቃቄን የሚሻና ይኸውም ባለሞያውን ግድ ሊለው የሚገባ ነው። የሆሊዉድን ነገር ስናየው ግን ይህን ኃላፊነት የዘነጋ ይመስላል። ዋናው ትኩረት ገቢ ማግኘቱ ላይ ሆኗል። የግብረገብ ጉዳይ ተዘንግቷል። የስነ ምግባር መመሪያዎች የሉም። ምን ያህሉ ፊልሞች ናቸው በጎ ምግባርን የሚሰብኩት?›› ሲሉ ይጠይቃሉ። በበኩሌ ምላሼ ‹‹አዎአይ›› ነው። ምክንያቱም፤ እንደ ኒል ጋብለር፤ አሜሪካዊያን የፊልም ባለሞያዎች ለመላው የሰው ልጆች በሚበጁ ፋይዳዎች ላይ እንዲጠመዱ ጫና ማሳደር መልካም ቢሆንም፣ ልናስገድዳቸው አለመቻላችን ተስፋችንን የተቀነበበ ያደርግብናል እንጂ ምኞቱስ ባልከፋ።ደግሞም አሜሪካዊያኑ የራሳቸውን በጎ መልክ ከፍ አድርገው ከማሳየት ቦዝነው አያውቁም። ባቀራረብም ሆነ በጭብጥ ምርጫ ለዚህ ይተጋሉ።

ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ሩቅ ሳንሄድ፤የዋይት ሀውስ ቀጭን ትዕዛዝ ፕሮዳክሽን ነው በሚባለውና መንታ ህንፃዎቻቸው በፈረሱ ማግስት አጣድፈው ባወጡት Flight 93 ፊልማቸው፤ ያልተፈጠረ ታሪክ አቀናብረው፤ የአይበገሬ አሜሪካዊ አርበኝነትን ስነ ልቦና በምስል ወ ድምጽ ጥበብ ከሽነው፤ በአስከፊው የአሸባሪዎች ጥቃት በርግገው የደነበሩ ምስኪን ዜጎቻቸውን ምን ያህል እንዳረጋጉና የአለም ህዝብንም እንዴት እንዳስደመሙ ያስታውሷል። በተረፈ፤ የስነ ምግባር መመሪያዎችና መሰል ጉዳዮች ከየዘመኑ ስልጣኔና የሰው ልጅ ኑሮ ተለዋዋጭነት ጋር፤ሳይቋረጡ፤ መልካቸውን እየቀያየሩ፤በምድሩ ዙሪያ፤ በየሀገራቱ የፊልም ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ጥልቅ ምክክርን የሚሹ የፊልም ሙያ አጀንዳዎች ሆነው የሚዘልቁ ናቸው። ዋናው ትኩረቱ ገቢ ማግኘቱ ላይ ብቻ ማነጣጠሩ ስለተባለው ግን፤የባለሞያው ምርጫ ነው። እንዲሁም የማንክደው የጥበቡም medium አይነት አስገዳጅነት። የፊልም ጥበብ፤ያነሱትን ሀሳብ አንዳች ‹‹ምትሀት››ን ፈጥሮ የማሳየት ጥበብ ነውና ስራውን ለመስራት ብዙ ገንዘብ ማስፈለጉን አይክዱትም። አልፎ አልፎ የሚከሰት ልዩ ዕድል /Fund/ ገጥሞ በጀት ካልተገኘ /Independent film making/ በቀር፤ፊልም ፕሮዲዩሰሩ ያወጣውን ገንዘብ ትርፋማ ለማድረግ መቆሙ ማንም ሊከለክለው የማይገባ መብቱ ነው። ቢዝነስ ነዋ! ሆኖም ግን በርካቶች የናጠጠ ገቢ ማግኘትን የማለማቸውና በሙያው የ‹‹መቆመራቸው››ን ያህል ደ ግሞ፤ ብዙ ፊ ልም ሰ ሪዎችም አሉ፤በማመቻመች፤ ገቢ ማግኛነቱን አምነው ለጥበባዊና የላቀ ፋይዳውም አብዝተው የሚጠበቡ። የዘርፉ ምሁራን ‹‹እኛ እንደደረስንበት ከሆነ›› ብለው እንደሚመሰክሩት፤ ‹‹የፊልም ጥበብ ውጤታቸው በማህበረሰቡ ማህበራዊ መስተጋብር፣ መንፈሳዊና ባህላዊ መዋቅሮች … ወዘተ ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ የማያምኑ ባለሙያዎች ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ›› ነው። እ ኒህ ፊ ልም ሰ ሪዎች፤ ም ንም እ ንኳን አዎንታዊውንም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖውን አናምንም ቢሉ፤ ቢያንስ፤ እጅግ በረቀቀ መንገድ አቀናብረው የሚያወጡት የፊልም ጥበባቸው ፤ተመልካቾች አለምን የሚገነዘቡበትንና ስለ ህይወት የሚያስቡበትን መንገድ ለመቀየድ ምን ያህል አቅም እንዳለው ግን አይክዱም።

ባለሞያዎቹ ተጽዕኖውን ላለማመን ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱበትንና ምሁራኑ በበኩላቸው፤ ሙግቱን ለመርታት የሚያቀርቡትን ማስረጃ በቀጣዩ ጊዜ እናይ ዘንድ ተስፋ እያደረግን፤ለዛሬው ከላይ ላነሳነው ‹‹በሞያችን ስለ ማህበረሰቡ እንጨነቅ ዘንድ ግድ ይለናል››ለሚለው ፅንፍ ማሰሪያ እናብጅለት። ፊልሞች፤ ታዳሚያቸውን /እያወቀም ይሁን ሳያውቀው/ ወደ በጎነት ወይም ወደ ጥፋት የመምራት እምቅ ኃይል አላቸው። ‹‹ልክ ህፃን ልጅን እንደመመገብ›› ነው። ጤናማ ወይም የተመረዘ ምግብ ልንመግበው እንችላለን። ህፃኑ ሁለቱን ለይቶ አያውቅም። ይኼ ማለት ግን ተመልካቹ ቀሽም ነው አያሰኝም። አይደለምም፡ ፡ያን ያህል ለመረዳትና ለማገናዘብ ደካማ ላይሆን ይችላል። ግን ደግሞ ሁሉም ተመልካቾች አንድ ናቸው ማለትም አይደለም። ‹‹አንድ ፊ ልም ከ መነሻ ን ሻጤው ( inspiration) ያቀራረቡ ዘዬ፣ ያተራረኩ (narration) ሂደት፣ ያሰራሩ የቴክኒክ አይነት፣ ይዘት፣ በውስጡ ሊያቅፋቸው የሚመርጣቸው ግብአቶቹ crafts እና የጥበባዊ ደረጃው ጉዳይ… ምርጫው በባለሞያው ችሎታና መብት የሚወሰን ስለመሆኑ (Artistic Freedom) ባንደራደርም፤ እንደየፊልሙ ዘውግና አውድ፤ ጭብጥ፣ ታሪክና መልዕክት…ሁለንተናዊ መልክ፤ ‹‹ፊልሙ ተሰርቶ የሚቀርበው እንዴት ያለ የግንዛቤ አድማስ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ነው?›› ወደሚለው አፍርሳታ ይመራናል። ምናልባት ፊልም ለተመልካች ከመቅረቡ በፊት ባለው የቅድመ ግምገማ /Prior restraint/ መስፈርትና ገደብ እስከ ጥግ እምነት ጥለን ካልተማመንን በቀር። ያም ቢሆን በቀጥታ ለዲቪዲ ሽያጭ የሚውሉትን አይመለከትም። የሚገርመው ደግሞ አደጋው ጎልቶ የሚታየው በእነዚህኛዎቹ /Popcorn productions/ ላይ መሆኑ ነው። እንግዲህ የፊልም ጥበብ በተመልካቹ ላይ ያለው ተፅእኖ መክረር ነው፤ በተለይ የባለሞያዎችን የኃላፊነት ጉዳይ ከፍ የሚያደርገው። ኋላ ከሚመጣ የዜግነትና የታሪክ ተጠያቂነትም ሆነ ከህሊና ተወቃሽነት /ከተስተናገደ/ ለመዳን። ህፃኑን በመመገብ መመሰሉም፤በምግቡ ውስጥ የተደባለቀ መርዝ ካለ የህፃኑን ህይወት ለመታደግ ያስቸግራል ለማለት ነው። የተሻለው መንገድ፤ቢቻልስ፤ ለህፃኑ ጤና ተስማሚ የሆነና ጣፋጭ ምግብን ሰርቶ ለማቅረብ መሞከር ነው።

ባጋጣሚ ‹‹ነፋስ ያመጣው›› ብናኝ ቢገባበት እንኳ አብላጫ ይዘቱ ብናኝ መርዙን ለማርከስ አቅም ያለው የጥበብ ማዕድ። በመጨረሻም፤‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት›› ይሏልና ወደ ራሳችን /የአሮጊቷ/ የዘመመች ታዛ ጎንብ ብለን ዘልቀን፤ ዝቅ ዝቅ ብለን እንሰነባበት። በመግቢያችን ላይ እንዳልነው፤ ዛሬ ዘመኑ በደረሰበት የዲጂታል ቴክኖሎጂና አማራጭ መገናኛ ዘዴዎች እገዛ፤ የፊልም ጥበብ ባንድ ጊዜ በየትም ስፍራ የመገኘቱ (ubiquity) እንዲሁም ማንኛውም የምስል ወ ድምጽ መረጃ በሰከንድ ክፍልፋዮች ከምድር አፅናፍ፣ አፅናፍ አሳብሮ ለመጓዝ መቻሉ፣ መልካም አጋጣሚነቱ ሀቅ ቢሆንም፤ ከየባለሞያው/ግለሰብና ቡድን ምኞት ጋር አብሮ በዘላቂነት ፀንቶ እንዲኖር የምንሻውን ትልቁን ስዕል፤ ሌሎች የማያውቁትን የተፈጠርንበትን ማህበረሰብ ምንነትና ክብር፤ ሌሎች የሌላቸውና ለእኛ የተቸሩ እፁብ ድንቅ ቅርሶቻችንን ፀ ጋ፤ የ እናት ሀ ገርን መ ልካም ገፅታ… ለአለም የማስተዋወቅ ፋይዳውን ማሰብ አለመተው ደግ ነው። ያኔ ነው የነጆናታን ዲምቢልቢ አይነቶቹ ዘመን ያስቆጠሩ ጥላሸቶች ታጥበው የሚጠሩት። እንዲሁም፤ በጋራ፤ የሌለንን የፊልም ፖሊሲ በመደማመጥና በትጋት በመቅረፅ፤ የጥበቡን አይነተኛ ፋይዳ (relevance) ባለፉት ዘመናት የተጣቡንን የማህበራዊ ቀውስ ነቀርሳዎች ሰንኮፍ የምንነቅልበት፤ዛሬን የምናጠይቅበትና ነጋችንን የምንተነብይበት፤ በአስተማማኝ መሰረት ላይ የቆመ ጥበብ (medium) ማድረግ ነው የሚበጀን።

እናም ለዘመናት ተሸክመናቸው የኖርናቸው ለእድገት ጸር የሆኑ ደዌዎች ታክመው የሚድኑበት እንጂ፤ረቂቅ ጥበቡን ተጠቅመን እንደመፈወስ፤ለጊዜያዊ ዝናና ጥቅም የሀገርን ውበት አጋንኖ ማጉደፍ ፤ከሁሉም በላይ ደግሞ ፤ ጭራሹኑ በነበረው ላይ ሌላ ለከርሞ የማይድን ነቀርሳ ፈጣሪ፣ አጥፊ አርአያን አጉልቶ በማሳየት፤ውል የለሽ ሴራ መጎንጎንና አረፋ ደፈቅ ስሜት ያግተለተላቸውን ረብ የለሽ የታሪክ ጉድፎችን እየለቃቀሙ መቆለል፤ትርፉ፤ አዳዲስ ችግር አምጪ ሀሳቦችን የምንቀፈቅፍበት ማህፀን ማበራከት እና ለነገው ትውልድ የማይወጣውን እዳ ማውረስ ነው። film is a truth twenty four times a second. ባለራዕይ ሲገኝ ለሀገር የሚቆም ራሱን ሰውቶ ፀጋን የተቸሩ የእምዬ ኢትዮጵያን እጆቿን ዘርግቶ ግዝቱን ትብታቡን ወዲያ መመንጠር ነው ባንድነት ተነስቶ! ለአለም አይን ማቅረብ ፈገግ ደርበብ ያለች የትልቋ እማማን የእውን ምስል አሁን በወል አበጅቶ። (የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም በሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል /ፑሽኪን/ አዳራሽ የቀረበ፤ ለአላቲኖስ የ ፊልም ሰ ሪዎች ማ ህበር ከ ተዘጋጀ የውይይት መነሻ ጽሑፍ።) CUT!

Read 2866 times