Saturday, 17 May 2014 15:56

አሰፋ ተክሌ - የግጥምና የታሪክ ማኅደር

Written by  ቢተው ዘገየ
Rate this item
(7 votes)

በንጉሥ ሚካኤል በኩል የወሎ ጦር በፊታውራሪ ሥራው ብዙ ገብሬ (የዐድዋ ዐርበኛ የነበሩ) የተመራ ሲሆን በንጉሥ ተፊሪ ረገድ ጦሩ፣ በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ እዝ ሥር ነበር። ጦርነቱ ሊጀመር ሲል በወሎ በኩል ግጥም ተገጠመ፤ “እኔስ ፈራ ሆዴ እኔስ ፈራ ሆዴ፣ የተፈሪን ሽጉጥ የኢያሱን ጎራዴ

           ውድ አንባብያን:- ባለፈው እትም ስለ፶ አለቃ አሰፋ ተክሌ ታሪክ ማስነበባችን ይታወሳል። በዛሬው እትማችን የወሎ ሰው ስለ ወ/ሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ከገጠመው ግጥም በመነሣት እንቀጥላለን፡- “አሁን ምን ያደርጋል የሴት ወየው ባይ፣ ወሎ የመጣው ሞት ሸዋ የለም ወይ? ተይ አንቺ ሴትዮ ነገር አታጥብቂ፣ እኛ አልገደልናትም እግዜርን ጠይቂ።” ለሰገሌ ጦርነት ዋና መነሻው ልጅ ኢያሱ፣ በሸዋ ሤራ ከሥልጣን በመወገዳቸው ነው። ከሥልጣን ተወግደውም የመታሰርና ከቦታ ቦታ የመንከራተት ችግር ደርሶባቸዋል። በጊዜው ልጅ ኢያሱን ይደግፏቸው የነበሩት የጎጃሙ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ሲሆኑ የድጋፉ መነሻም ልጃቸውን ወ/ሮ ሰብለወንጌል ኃይሉን አግብተው፣ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ኢያሱን ስለወለዱ ነው። በመጨረሻ ልጅ ኢያሱ፣ ከራስ ካሣ ግዛት ሥላሴ እንዲታሰሩ፣ በራስ ኃይሉ አማካይነት ከእሥር እንዲያመልጡ የተደረገውም ለዚሁ ነው። የእስር ቤት ጠባቂያቸው ደጃዝማች አበራ ካሣ ሲሆኑ በኋላም ፈትቶ ለቋቸዋል። በጊዜውም፡- “አበራ ምን አለ አበራ ምን አለ፣ ፈትቶ ለቀቀና አላየሁም አለ” ተብሎ ተዘፈነ። ልጅ ኢያሱ ከእስራት አምልጠው፤ መቅደላ ደርሰው፣ ከቀ.ኃ.ሥ ጦር ጋር ሲዋጉ አሽከራቸው፤ “የዘጠኝ ንጉሥ ልጅ አሥረኛው እሱ፤ መቅደላ ላይ ሆኖ ያስካካል ፈረሱ” ብሎ አድንቋቸዋል። በመጨረሻም በደጃዝማች አርኣያ ዮሐንስ ግዛት፣ ትግሬ ውስጥ ቢደበቁም ደጃች አርአያ እጃቸውን ይዞ ለመንግሥት ሰጥቷቸዋል። በሰገሌ ጦርነት ወሎ የታጠቀው ጎራዴ ሲሆን ሸዋ የታጠቀው ደግሞ ለበን ነው። በዚህ ምክንያት ንጉሥ ሚካኤል ለምን ልጄ ታሰረ? ለምንስ ከሥልጣን ወረደ? የምኒልክ ኑዛዜስ አለ አይደለም ወይ? ብለው ከሸዋ ጋር ለመዋጋት ወደ ሰገሌ መጡ።

የሸዋ ጦር አሰፋ ተክሌ - የግጥምና የታሪክ ማኅደር ለበን መሳሪያ ታጥቆ የነበረው፣ በዓፄ ምኒልክ ውል መሠረት ከፈረንሳይ ስለመጣ ነው። በንጉሥ ሚካኤል በኩል የወሎ ጦር በፊታውራሪ ሥራው ብዙ ገብሬ (የዐድዋ ዐርበኛ የነበሩ) የተመራ ሲሆን በንጉሥ ተፊሪ ረገድ ጦሩ፣ በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ እዝ ሥር ነበር። ጦርነቱ ሊጀመር ሲል በወሎ በኩል ግጥም ተገጠመ፤ “እኔስ ፈራ ሆዴ እኔስ ፈራ ሆዴ፣ የተፈሪን ሽጉጥ የኢያሱን ጎራዴ።” ጦርነቱ ቀጠለ። አሰላለፉ የጎራዴና የዘመናዊ ለበን መሳሪያ ሆነና ንጉሥ ሚካኤል ድል ሊሆኑ ሲል የገጠሙት ግ ጥም የ ሚከተለው ነ ው። በ ወቅቱም ጎጃምና ጎንደር ይረዱኛል የሚል ሐሳብ ነበራቸውና ሳይመጡ ስለቀሩ፤ “በጎጃም በጎንደር ደመናው ዘለቀ፣ ዘርያላችሁ ዝሩ የእኔስ ዘር አለቀ።” ብለው አዋጅ አስነገሩ። ቃላቸው ከጊዜ በኋላ ጎጃምና ጎንደር በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ “ምነው ምነው የሚያዘምተን ሰው የለም ወይ? ብሎ ተናደደ፤ ተቆጣ፤ ወዲያው ተማረኩ መባልን ሰምቶ ነው እንጂ የጎንደርና የጎጃም ሕዝብ ከጎናቸው ተሰልፎ ተፈሪን ለመውጋት ሐሳብ ነበረው። የወሎ ጦር አዝማች የነበሩት ፊታውራሪ ሥራህ ብዙ፤ በጀግንነት ሲዋጉ ድል ስለአልቀናቸው በዘዴ የሸዋን ጦር ሰብረው ለማምለጥ ችለዋል። የሸዋም ጦር በስለላ ተከታትሎ፣ ደሴ ከተማ በአገኛቸው ጊዜ ተኩስ ከፍተው ብዙ ሰው ገደሉ።

በመጨረሻ ራሳቸውም በእሩምታ ጥይት ሞተዋል። አስከሬናቸው ከንጉሥ ሚካኤል ጋር ሆነው በአሠሩት ደሴ መድኃኔዓለም ተቀብሯል። በወቅቱም፤ “ሥራህ ብዙ ገብሬ ሥራው መሰከረ፣ በሰራው ከተማ ደሴ ተቀበረ።” ተብሎ ተገጠመ። ፊታውራሪ ሥራህ ብዙ ገብሬ፤ ሰገሌ ላይ ተዋግተው ድል እንደሆኑ ሲያውቁና ሲያመልጡ የወሎ አዝማሪ ስለጀግንነታቸው እንዲህ ብሎም ነበር። “የመሣሪያ እጦት ነው ሰው የሚያስደነግጥ፣ ጀግናስ ተቀምጧል ተመዝኖ እንደ ጥጥ” ወደ ወሎ ተግተልትሎ የገባው የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ጦርም፣ እኛ እምንፈልገው ልጅ ኢያሱን እንጂ ንጉሥ ተፈሪን አይደለም ብሎ ያመፀውን የወሎ ሕዝብ፣ አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ አሰቃየው። በግድ እንዲገብርም አደረገው። የወሎ ሕዝብ በሬውና ላሙ እየታረደበት፣ የጎተራ እህሉ ለበቅሎ እየተሰጠበት በሥቃይ ላይ እንዳለ፣ ሕዝቡ አማርሮ ያለቅስና ያዝን ጀመር። የወቅቱ የወሎ ገዥ የነበሩት ራስ ደምስም፤ “ወሎ ተበደልኩ ብሎ ያስወራል? እስቲ በደሉ የት አለ? እስቲ ስለሕዝቡ በደል ልጃገረዶች በዘፈናቸው ምን እንደሚሉ ይናገሩ…” ምን ይላሉ?” አሉ። ከ13 ዓመት በታች የሚገኙ ልጃገረዶች ሲዘፍኑ፣ ቄስ መነኩሴው ሳይቀር ተሰባሰበ።

በተለይ ተዋበች የተባለችው የዘፈኑ አቀንቃኝ ስትዘፍን፡- “ላሚቷ ታረደች ወተትዋ ሲፈስስ፣ በሬውም ታረደ ትልሙን ሳይጨርስ፣ ምን ትጠቀማለህ ሀብተ ጊዮርጊስ አንተራስ ደምስ” ትላለች። ንጉሥ ሚካኤል ሰገሌ ላይ ተማርከው ሲያዙ አዝማሪያቸውም አብሮ ተማርኮ ታሥሮ ነበር። ከመኻል ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ፤ “እስቲ ዝፈን አሉት። “እኔ አ ልዘፍንም ም ርኮኛም አ ይዘፍንም ጌ ታዬ ተማርኳል” ይላል። በግድ ዝፈን ተባለ። አዝማሪው ማሲንቆውን አንሥቶ እየገዘገዘ እንዲህ አለ፤ “እንዲሁ በከንቱ ደም ተፋሰስን እንጅ፣ አልጋው መች ይወጣል ተሚካኤል እጅ።” ይህንን ግጥም የሰሙት አንድ ነገር አዋቂ ሽማግሌ፤ “ፊታውራሪ! ይኸ አዝማሪ ሰደበህ‘ኮ” ይላሉ “ምን ብሎ?” “አንተ አነፍናፊ ነህ ከዳር ትቀራለህ፤ በመኻል የንጉሥ ሚካኤል ልጅ ወ/ሮ መነን ስለአለች የእርስዋ ልጆች ይነግሣሉ፤ አንተ ግን ዳር ቀሪ ነህ ነው ያለህ፤ ዞሮ ዞሮ አልጋው የእኛ ነው እያለህ ነው።” ሲሉዋቸው “አከና” ብለው ሊገርፉት ተነሱ። በዚህ ጊዜ መነን ነበሩና “አትንካው፤ አይሆንም ዝፈን አልከው ዘፈነ። እንደገና እንዴት ልግረፍ ትላለህ? ብለው ከግርፋት አስጥለውታል።

ንጉሥ ሚካኤል በመማረካቸው ምክንያት እየተብሰለሰሉ አዲስ አበባ ውስጥ በመኖር ላይ ሳሉ በጽኑ ይታመማሉ። በዚያው ወቅት ጳጳሳትና ትላልቅ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አድርገው፤ “ወደ ሀገሬ ወሎልሂድና መቅደላ ሚካኤል ልቀበር” ብለው ለንጉሥ ተፈሪ ነገሩዋቸው። ንጉሥ ተፈሪም የቁጣ ፊት እያሳዩዋቸው፤ “እኔ ምንድነኝ! ሸዋን ጠይቁና ይሂዱ” ብለው ይከለክሏቸዋል። የትኛውን ሸዋ መጠየቅ እንዳለባቸው ግራ የተጋቡት ንጉሥ፣ ሚካኤልም ንጉሥ ተፈሪን በቀሉት ዓይኖቻቸው እየተመለከቱ፤ “በእኔ እድሜ በደረስክ ጊዜ ሸዋ ጭራቅ ሆኖ ይዋጥህ” ብለው ንጉሥ ተፈሪን እንደረገሙዋቸው ፶አለቃ አሰፋ ከሚያውቁት ታሪክ ተነሥተው አውግተውኛል። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በመጨረሻ ዘመናቸው ሌባ ሌባ ተብለው ከቤተመንግሥታቸው መወገዳቸውና ዐጽማቸው ተደብቆ እንዲኖር የተደረጉት ምናልባትም በንጉሥ ሚካኤል ኀዘን ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፤ ፶አለቃ አሰፋ። ንጉሥ ሚካኤል 10ሺህ ሠራዊት ይዘው፣ ዐድዋ ዘምተው በሠሩት ጀግንነት፣ የሀገር ባለውለታ እንዲሆኑ ቢያስችላቸውም፣ እዚሁ ሸዋ ሞተው የተቀበሩበት ሳይታወቅ ቆይተዋል። በኋላም በራስ እምሩ ምክር ዐፅማቸው ፈልሶ ወደ ወሎ ይሄዳል። ዐጽማቸው መቅደላ ደርሶ በተቀበረበት ሰዓት፣ የወሎ ሕዝብ በብዛት ተሰብስቦ ነበር።

ከሸዋም እስኩቢኒ (መረጃ ተከታታይ) ይሄዳል። እስኩቡኒዎች የራስ ሚካኤልን ዐፅም አጅበው ወደ መቅደላ የሄዱበት ምክንያት በለቅሶ ላይ ኃይለ ሥላሴን የሚወቅስ የለቅሶ ግጥም እንዳይገጠም፣ ከተገጠመ ሰዎቹ እንዲያዙ ተብሎ ነው። በኋላ የተፈራው አልቀረም። ወ/ሮ ጣይቱ አብርሃም የተባለች አስለቃሽ፣ ደረቷን እየተመተመችና የለቅሶ ግጥም ገጥማ እያዜመች ሕዝቡን ማስለቀስ ትጀምራለች፡- “ምን ንጉሥ አለና አቤት ትላላችሁ፣ ምን ጳጳስ አለና ትባረካላችሁ፣ ሰይጣን በቅሎ ጭኖ ሲከንፍ እያያችሁ።” በዚህ ጊዜ ሸዋዎች፤ “ያዟት ያዟት” ሲሉ ወሎዎች አሾልከው አጠፏትና አመለጠች። በዚያ ወቅት የንጉሥ ሚካኤል ባለሟል የነበረ “ልግጠምና ላልቅስ” ብሎ ፈቃድ ጠየቀ። መረጃ ሰብሳቢዎች “አንድ አሽሙር ብትናገር ቂጥህን ትገረፋለህ” ይሉታል። ከዚያም የ ንጉሥ ሚ ካኤል የ ፈረስ ስ ም “ አባ ሻንቆ ማሜ ይባል ነበርና፡- “አባ ሻንቆ ማሜ ቤትህ አፈሰሰ፣ ተከዳኙ ነወይ? ወይስ ሣሩ አነሰ? ተክዳኑም አይደል ሣሩም አላነሰ፣ ያባ ሻንቆ ቤቱ ምሰሶው ፈረሰ” ብሎ ገጠመ። ወ/ሮ መነንን ለራስ ተፈሪ የዳሩላቸው ልጅ ኢያሱ ናቸው። መነን ለንጉሥ ተፈሪ ሲዳሩ፤ “መቼም ልጅ ኢያሱ ልጅ አይወጣለት፣ ልቅም እንደ ስንዴ ጥሩ እንደ ወተት ያቺን መሳይ ቆንጆ ሰጧት ለድመት። አይገባም እንጂ ያዩትን መናገር፣ መነን ለተፈሪ አትገባም ነበር”

ተብሎ ተዘፈነ። እቴጌ መነን በሞቱበት ዘመን የወረኢመኑ ሰው የሆነ፣ ከወሎ (ከአምባሰል) የመጣ አዲሴ ፈጅር የተባለ አልቃሽና የለቅሶ ግጥም ገጣሚ ነበር። በለቅሶው ላይ፡- “ጎጃሞች ተነሡ እንግባ አገራችን፣ ጎንደሮች ተነሡ እንግባ አገራችን፣ ወሎዎች ተነሡ እንግባ አገራችን፣ በቴጌ ነበረ ሸዋ ዝምድናችን።” ሲል ወሎ፣ ጎጃምና ጎንደር አንድ ላይ ተሰብስበው ማልቀስ ጀመሩ። በዚያ ጊዜ የለቅሶውን ሥነ-ሥርአት የሚቆጣጠሩ ሦስት ትላልቅ ሰዎች በአጃቢ ይዞሩ ነበርና አዲሴ ፈጀርን ጠርተው ማስጠንቀቂያ ሰጡት። ማስጠንቀቂያውም እቴጌ ውጭ ሀገር ድረስ ተሰድደው ሄደው አገሪቱን በክርክር ያስከበሩ፣ ያዳኑ የኢትዮጵያ ንግሥት እንጂ ለእነዚህ ለሦስቱ አገሮች ብቻ የቆሙ አይደሉም። እ ና ሌ ላ ግ ጥም ግ ጠም” አሉት። ሰዎቹም ወፋፍራሞች ስለነበሩ አዲሴ ፈጅር እንዲህ ብሎ በግጥም ሰደባቸው፡- “ሞት አለብኝ ብሎ ያዳም ልጅ ቢሰጋ፣ መች ይሸከም ነበር ይህን ወደል ሥጋ።” ይህን ሲል እንዳያስገርፉት ወሎ ለለቅሶ ብንመጣ ተገረፍን ሊል ነው፣ ብለው ስለሰጉ በለቅሶኛው መኸል የዶርዜና የኦሮሞን ሰው ሰገሰጉበት። ዶርዜው እየዘለለ ሲፈርጥ፣ ኦሮሞው ሀሌሌ ሲል ለቅሶው ቆመ። ወዲው የአምባሰል አልቃሽ፤ “እንደ እኔስ ከሆነ እንደ እኔስ እንደ እኔ፣ ንጉሥ ስልጣን ትተው ይሂዱ ምናኔ።” ብላገጠመች። የመንዝ አልቃሽ ደግሞ፤ “ኧረ ወሎዬዋ ምነሻ ምነሻ፣ ንጉሥ አሰናባች ማን አደረገሻ።” አለቻት። በዚያ ዘመን ለአጋፋሪነት መልክ ያለው ሰው ይፈለግ ነበር። አለባበሱ፣ አቋቋሙ የሚያምር ይመረጥ ነበር። እና የወረኢሉ ባላባትና የወለጋ ገዢ ለነበሩት ለራስ ሀብተ ማርያም ሰው ተመርጦ፣ ለአጋፋሪነት ተሰጣቸው። ሰውዬው ግን መልክ ብቻ እንጂ በሥራ አልተስማማቸውም ነበርና፤ “እኛ ጠጅ መስሎን በርሜሉ ቢከፈት፣ ጠላነው መልሱት ወደነበረበት።” ብለው ሰውዬውን አስቀየሩት።

Read 7127 times