Saturday, 17 May 2014 15:49

የከተማ አስተዳደሩ አፍንጫ የለውም እንዴ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

               የልጆች እናት የሆነችው ፋጡማ፤ ላለፉት ሰባት ዓመታት ፒያሳ በተለምዶ “አላሙዲ ያጠረው” እየተባለ የሚጠራው የቆርቆሮ አጥር ስር ከማለዳው 12፡30 ጀምሮ ተቀምጣ፣ ለታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶቻቸው ፓስቲና ሻይ እንዲሁም ቡና ታስተናግዳለች። ሆኖም የአካባቢው መቆሸሽና በመጥፎ ጠረን መሞላት ግን እየባሰበት እንጂ እየተሻለው አለመምጣቱን ትናገራለች። “ይህም እንጀራ ሆኖ እኔ ተቀምጬ የምሰራበት ቦታ ላይ ተፀዳድተውበት አገኛለሁ፤ እንጀራ ሆኖብኝ ቦታውን አፅድቼ እቀመጥና ሻይና ብስኩት ለሹፌሮችና ለረዳቶች መሸጥ እጀምራለሁ” ትላለች - ፋጡማ። በእርግጥ በአካባቢው ሽታ ተማርራ ለመልቀቅ ሁሉ አስባ እንደነበር አልሸሸገችም። ሆኖም ልጆቼን ጦማቸውን እንዳላሳድራቸው ሰጋሁ የምትለው ፋጡማ፤ ከአካባቢው የሽንትና ሰገራ መጥፎ ጠረን ጋር መኖሩን ለመድኩት ብላለች። አቶ ምናለ ጌታቸው የተባሉ የ56 ዓመት ጐልማሳ፤ መገናኛ አካባቢ ከሚገኘው የሥራ ቦታቸው በትራንስፖርት ተሳፍረው ሲመጡ የሚወርዱት ፋጡማ የምትቀመጥበት ሥፍራ ነው - ፒያሳ፤ ከአራዳ ህንፃ ጀርባ። “እዚህ ቦታ ላይ የአስኮ ታክሲ ለመጠበቅ ረጅም ሰዓት እቆማለሁ፤ በዚህ የተነሳ ሳይነስ የሚባል የአፍንጫ በሽታ ተጠናውቶኝ በስቃይ ላይ እገኛለሁ”

ያሉት ጐልማሳው፤ “ለመሆኑ የከተማዋ ራስ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከንቲባው የሚገኙበት አካባቢ እንዲህ አፀያፊያ የበሽታ መናኸሪያ ሲሆን እንዴት ሀይ ባይ ይጠፋል?” ሲሉ አበክረው ይጠይቃሉ። ጊዮርጊስ አካባቢ ከሚገኙ አትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ መደብሮች ተነስተው ቀኝዎን በመያዝ በጊዮርጊስ (በቶታሉ በኩል ፊት ለፊት) ቤተክርስቲያኑን ሲዞሩ፣ አፍንጫዎ ተነቅሎ የሄደ እስኪመስልዎት ድረስ የሚሰነፍጠው የሽንትና የሰገራ ሽታ መፈጠርዎን ሊያስጠላዎት ይችላል። እዚህ አካባቢ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለግንባታ ያጠረው ቦታ ራሱ፣ የቆሻሻ መከማቻና የበሽታ መናኸሪያ ሆኗል። ከውስጥ ግንባታ የሚያካሄዱት ሠራተኞች፣ ከአጥር ውጭ ያለው ሽታ እንዴት እንደሚያሰራቸው ግራ ያጋባል። አሁን በባቡር መንገድ ዝርጋታው የተነሳ ግማሹ ቦታ በቆርቆሮ ተሸፈነ እንጂ ቀደም ሲል በመጥፎ ጠረንና በቆሻሻ ክምችቱ የምኒልክ ሀውልትን ዙሪያ የሚፎካከረው ማንም አልነበረም።

“ሰው መንገድ ላይ መፀዳዳትን እንደነውር መቁጠር ካልጀመረ ከተማዋ ከዚህ በሽታዋ አትድንም” ይላል፤ ኢብራሂም (ስሙ ተቀይሯል) የተባለ የአካባቢው ነጋዴ። በቆርቆሮ አጥሩ ስር ታክሲዎች ተደርድረው ከሚቆሙበት ሥፍራ ፊት ለፊት፤ ሸራ ወጥሮ ሶፍት፣ ማስቲካ፣ የሞባይል ካርድ፣ የታሸጉ የፕላስቲክ ውሃዎች፣ ሲጋራ እና ሌሎች ሸቀጦችን በመሸጥ የሚተዳደረው ኢብራሂም፤ ከዚሁ ጎን ለጎን 50 ሳንቲም እያስከፈለ ለውሀ ሽንት በተዘጋጀው ተንቀሳቃሽ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ተጠቃሚዎችን ያስተናግዳል። ሆኖም ተጠቃሚው ብዙ አይደለም ይላል። “ስሙኒና ሃምሳ ሳንቲም ከፍሎ እዚህ መፀዳዳት እየቻለ፣ ከእኔ አለፍ ብሎ አጥር ስር ሲሸና ታይዋለሽ” በማለት ትዝብቱን የሚናገረው ነጋዴው፤ መንገድ ላይ መፀዳዳት የሚያስከትለውን መዘዝ እያወቁ፣ ሆን ብለው አካባቢውን የሚበክሉ የአዋቂ አጥፊዎች ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ጠቅሶ፤ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ካልተቀየረ ለውጥ እንደማይመጣ ይናገራል። አንድ ቀን ለሥራ ጉዳይ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ሄጄ ነበር። መግቢያው በር አካባቢ ስደርስ፣ አንድ ጎልማሳ መስተዳድሩ ግቢ ውስጥ ያሉ ፖሊሶች እያዩት፣ አጥሩ ስር ሽንቱን ሸንቶ ሲሄድ አየሁት። እኔም “እዚህ ቁጭ ብላችሁ አጥራችሁ ሥር ሲሸናዝም ትላላችሁ?” ስል ፖሊሶቹን ጠየቅኋቸው። ምላሻቸው ግን አስደንጋጭ ነበር።

“የሚሸናበት መፀዳጃ ቤት አዘጋጅተሽለታል? ወይስ ይፈንዳልሽ” አሉኝና ኩም አደረጉኝ። አያሌው ሙዚቃ ቤት ፊት ለፊት ያለው ደጎል አደባባይም የቆሻሻ መናኸርያ ከሆነ ከራርሟል። አደባባዩ ውስጥ ያለው የሳር መናፈሻ ሰገራና ሽንት ብቻ ነው። ለደቂቃዎች በዚህ አካባቢ መቆም ራስን የማጥፋት ሙከራ እንደማድረግ ይቆጠራል። ለዚህ አደባባይ መቆሸሽ ተጠያቂዎቹ፣ መኖርያቸውን በዚያ ሥፍራ ያደረጉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ናቸው። በጠባብ መተላለፊያ መንገድ ላይ ጓዛቸውን ይዘው ይኖራሉ፤ ልጆቻው እዚያው ይፀዳዳሉ። በከለመዳሪ ጎማ ልብሳቸውን አጥበው፣ እጣቢውን እዚያው ይደፉታል። አካባቢው በበጋ ሳይቀር ሁሌ እርጥበት የማያጣውና ቆሻሻ የማይለየው ነው። “መሽናት ክልክል” ወይስ “መሽኛ ክልል” አትክልት ተራን ጨምሮ መላው የፒያሳ ዙሪያ፣ የከተማዋ ጠቅላላ ቆሻሻና ሽንት የሚጠራቀምበት ሥፍራ ነው የሚመስለው።

የሚገርመው ደግሞ በየአጥሩ ላይ “መሽናት ክልክል ነው” የሚል ማሳሰቢያ (ማስጠንቀቂያ) መኖሩ ነው። ሁልጊዜ ሰው እዚያው ፅሁፉ የተለጠፈበት ቦታ ላይ ሲሸና ስመለከት፤ “መሽናት ክልክል ነው” የሚለውን “መሽኛ ክልል ነው” እያሉ እያነበቡት ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ይህ ሁሉ ቆሻሻ ያለው ደግሞ የአፍሪካ መዲና እየተባለች በምትጠራው፣ ያውም የከተማዋ አስተዳደርና ከንቲባው በሚቀመጡበት የማዘጋጃ ህንፃ ዙሪያ መሆኑ ይበልጥ ግራ ያጋባል። ታዲያከንቲባው የሚኖሩበት የከተማው እምብርት፣ ይህን ያህል ከቆሸሸ፣ ሌላው አካባቢ መቆሸሹ ምን ያስገርማል?! ያሰኛል። የከተማዋ ቆሻሻ “የክብር ስፖንሰሮች” አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፤ ለከተማዋ መቆሸሽ የክብር ስፖንሰር እየሆኑ ያሉ አንዳንድ ባለሀብቶች አሉ። ለምሳሌ ፒያሳ ወደ 20 ዓመት ገደማ ታጥሮ የተቀመጠው የባለሀብቱ ቦታ,ኧ ለከተማዋ መቆሸሽ የክብር ስፖንሰር እንደሆነ ይነገራል። “ቦታው በምንም ምክንያት ታጥሮ ሊቆይ ይችላል፤ ነገር ግን አንድን ቦታ አጥረው ሲያስቀምጡ ዙሪያውን ከእንዲህ አይነት የብክለት አደጋ መጠበቅ የባለቤቱ ኃላፊነት ነው” ይላሉ አንድ የአካባቢ ጥበቃ ኤክስፐርት።

“የውጭ አገር ዜጎች፣ ዲፕሎማቶችና ቱሪስቶች በከተማዋ ይዘዋወራሉ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ከተማ አስተዳደሩና ወደ ከንቲባው ጽ/ቤትም ጎራ ማለታቸውም አይቀርም፤ ያኔ ይሄን ሁሉ አፀያፊ ነገር አልፈው ነው የሚገቡት” የሚሉት ኤክስፐርቱ፤ ከንቲባውና የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች፣ ዙሪያቸውን እንደ ወታደር በከበባቸው ቆሻሻ መሀል ሆነው እንግዳ ሲቀበሉ ሊያፍሩና ሊሸማቀቁ ይገባል ብለዋል። ራሱ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያንም ከቶታል ፊት ለፊት ያጠረው ቦታ፣ በሽንት የተጥለቀለቀ ሲሆን የሚሰነፍጠው ሽታ ራስን የሚያስት ነው። አራዳ ጊዮርጊስም ለ ከተማዋ መ ቆሸሽ የ ክብር ስ ንፖሰር ሆኗል ይላሉ፤ አስተያየት ሰጪዎች። ሜክሲኮ አካባቢ ለምን ዓላማ እንደሆነ ባይታወቅም ለዓመታት የታጠረው ሥፍራ እንዲሁ ለከተማዋ መቆሸሽ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል። እስቲ የከተማዋ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ራስ የሆነው ቤተመንግስት ስር በቆርቆሮ ወደ ታጠረው ግቢ ጎራ ይበሉ። አስገራሚውን የቆሻሻ ትርኢት ይመለከታሉ። እድሜ ለዚያ የቆርቆሮ አጥር… ምን ያልደበቀው ጉድ አለ! ወደ ከተማ አስተዳደሩ ዙሪያ ስንመለስ፣ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዙሪያ በተለይም አሁን በጀርባው በኩል ህዝቡ እንደ አማራጭ መንገድነት የሚጠቀመው ቦታ፣ በፈርስት ካይሮፕራክተር ዌልነስ ክሊኒክ” በኩል ያለው አካባቢ፣ ወደ ገዳም ሰፈር ሊታጠፉ ሲሉ ያለው ቦታ… ጠቅላላ በመጥፎ ሽታ የተበከለና የህዝቡን ጤንነት የሚያውክ ነው።

ታዲያ ከንቲባው እና የከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ይህንን ጉዳይ እንዴት ተቋቋሙት? መላ ካላቸው ለእኛም ያካፈሉን። ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ማህበረሰብ ሳይንስ (ሶሲዮሎጂ) በድግሪ የተመረቁ አንድ ባለሙያ እንደሚሉት፤ ለፒያሳ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የከተማዋ መቆሸሽ ምክንያቱ የከተማዋ መኖሪያ ቤቶችና የህዝብ ብዛት አለመመጣጠን ነው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት ለጎዳና ተዳዳሪነት ትልቁ ምክንያት እንደሆነ የገለፁት ባለሙያው፤ መንግስት በዚህ በኩል ያለውን ችግር ካልቀረፈ፣ በቂ መፀዳጃ ቤቶችን ካልገነባና የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ካላስፋፋ፣ የከተማዋ መቆሸሽ እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ እንደማይመጣ ይናገራሉ። “በእርሻ መሬት መጥበብ፣ በህዝብ ብዛት፣ በዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመዝነብና በሌሎች የተፈጥሮ ችግሮች አርሶ አደሩ ወደ ከተማ በየጊዜው ይፈልሳል፤ሲመጣም ልጅና ሚስቱን አስከትሎ ነው” ያሉት የስነ-ማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያው፤ አርሶ አደሩ ከየክልሉ ስራ ፍለጋ ሲመጣ ማረፊያው ጎዳና በመሆኑ፣ መፀዳጃውም ጎዳና ይሆናል። እልባት ካልተገኘለት፣ ከተማዋ ከስሟ ጋር የማትጣጣምና ከቆሻሻ የማትፀዳ እንደሆነች ትቀጥላለች በማለት መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።

Read 1423 times