Print this page
Saturday, 17 May 2014 15:39

ኢህአዴግ በኢኮኖሚ ያስመዘገበው “B+” ትልቅ ድል ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)
  • በሰብአዊ መብት አጠባበቅ “C” አምጥተሃል ቢባል በፀጋ ይቀበለው
  • በፕሬስ ነፃነት ውጤትህ “D” ነው ቢባልም ”ሙያ በልብ ነው“ ይበል

            እናንተ …. የሰሞኑ ጉድ ምንድነው? (የአንበጣ መንጋውን ማለቴ ነው!) ለመሆኑ ትርጉሙ ምንድነው? ትውፊት የሚጠቅመው ለዚህ ጊዜ እኮ ነው፡፡ እኔማ ከወደ ሶማሊያ ነው የመጣው ሲባል ክው አልኩላችሁ፡፡ እንዴ “አልሸባብ” ልኮብን ቢሆንስ? (በፈንጂ አንበገር ስንለው በአንበጣ ቢፈጀንስ!) ለማንኛውም ግን አልፈነዋል፡፡ እኔ የምለው--- እነዚህ የደቡብ ሱዳኖቹ መሪዎች መጨረሻቸው ምን ሆነ? ታረቁ ወይስ አገራቸው ገብተው እንደለመዱት ተጣሉ? ሌላው ቢቀር ከቻይና ድረስ እየተመላለሱ የሚያሸማግሏቸው የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን አያሳዝኗቸውም እንዴ? (ፖለቲከኛ ማዘን የት ያውቃል!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል --- --ደቡብ ሱዳኖችን ለማስታረቅና ለማደራደር እንደጦቢያ መንግስት የደከመ የለም፡፡

እንዴ ---- ኢህአዴግ በኢኮኖሚ ያስመዘገበው “B+” ትልቅ ድል ነው! እኛ የመንግስት ሹማምንቱን የመረጥናቸው እኮ እኛን እንዲያገለግሉን እንጂ ጎረቤት አገር ሲያስታርቁ እንዲኖሩ እኮ አይደለም፡፡ (ከልባቸው ቢታረቁ ደግሞ የአባት ነው!) ሰሞኑን በሁለተኛው ዙር የእርቅ ሂደት ላይ ጎንበስ ቀና ሲሉ የሰነበቱት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደ ሳለኝ፤ቢቸግራቸው “ የማትታረቁ ከሆነ እጃችሁን ይዤ ለዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍ/ ቤት አስረክባችኋለሁ!” ብለዋቸዋል አሉ። መሪዎቹ እንዴት ቴረር በቴረር እንደሚሆኑ አስቡት! (እዚያ እኮ ሥ ልጣን የ ለም!) ለ ነገሩ ጠ /ሚኒስትሩም አይፈረድባቸውም፡፡ ህዝባቸውን በጎሳ እያቧደኑ እርስ በእርስ አጨራረሷቸው እኮ! እኔ በጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ቦታ ብሆን ኖሮ፣ በማስፈራራት ብቻ አልመለስም ነበር። በቀጥታ ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (ICC) ነበር የማስረክባቸው፡፡

(የደቡብ ሱዳን ህዝብ አለቀ እኮ!) ይታያችሁ… ከጥቂት ወራት በፊት እዚህ ተጨባብጠው ታርቀናል ብለው ከሄዱ በኋላ፣ እንደገና ሌላ ግጭት፡፡ ሌላ ጦርነት፡፡ ሌላ እልቂት፡፡ ሁለት ለሥልጣን የሚፎካከሩ የአፍሪካ ፖለቲከኞች ባልተስማሙ ቁጥር ህዝብ ማለቅ አለበት? (Enough is enough ቀለጠች!) የራስህን ትተህ የሰው ትፈተፍታለህ እንዳልባል ስለፈራሁ፣ቶሎ ብዬ ወደ አገሬ ጉዳይ ተመለስኩ። ወደ ጦቢያ፡፡ ወደ ኢህአዴግ፡፡ ወደ ልማታዊው መንግስታችን፡፡ እናላችሁ-----23ኛ የልደት ወይም የስልጣን በዓሉን የሚያከብረው አውራው ፓርቲያችን፤ ሌላውን እየዞረ ሲያስታርቅና ሲሸመግል፣ የራሱን ጉዳይ እንዳይዘነጋው እያልኩ፣ነጋ ጠባ በስጋት እናጥላችኋለሁ። (“የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” አሉ!) ከምሬ እኮ ነው…. አንዴ ሶማሊያ፣ ሌላ ጊዜ ሩዋንዳ፣ ከዚያ ደግሞ ደቡብ ሱዳን እያለ ሲያካልል ምርጫውን በ96 ነጥብ ከምናምን ውጤት እንዲያሸንፍ ድምፅ የሰጠነውን እኛን ያበሻ ልጆች እርስት ቢያደርገንስ? (ተናድጄም አላባራ!) ሁ ሌም እ ንቆቅልሽ የ ሚሆንብኝ ም ን እንደሆነ ልንገራችሁ… ሰው አገር ድረስ ሄዶ ገዢ ፓርቲንና ተቃዋሚን የሚያስታርቅ አውራ ፓርቲ፤ እንዴት ከአገሩ ተቃዋሚዎች ጋር እጅና ጓንት መሆን አቃተው የሚለው ጉዳይ ነው።

የሱዳን ፖለቲከኞችን ሁለት ጊዜ ከማስታረቅና ከራስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አንዴ ከመታረቅ የቱ ይቀላል? ለደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የዲሞክራሲን ሀሁ ከማስተማርና በአገር ውስጥ የዲሞክራሲ ሥርዓትን ከማጎልበት የትኛው ይቀላል? (የትኛው ይቀድማል አልወጣኝም!) በእርግጥ… የ ጎረቤት ሰ ላም የ ራስም ሰ ላም ነ ው። የጎረቤት ዲሞክራሲ ግን ለሌላ አይተርፍም፡፡ ለራሱ ለጎረቤቱ ብቻ ነው፡፡ የኢህአዴግን የሽምግልና ሚና እያጣጣልኩ እንዳይመስላችሁ፡፡ (ምን ቁርጥ አድርጎኝ!) መፅሃፉም ቢሆን እኮ “ዋሽተህም ቢሆን አስታርቅ” ይላል፡፡(አይልም እንዴ?) ይልቅስ ከገዛ ወንድሙ ጋር ተናቁሮ፣ ጎረቤቱን ሊያስታርቅ ስለሚተጋ የዋህ መፅሃፉ ምን እንደሚል አላውቅም (ኢህአዴግም የሚያውቅ አይመስለኝም!) እኔ የምለው… ግንቦት 20 ደረሰ አይደል? 11 ቀናት ብቻ እኮ ነው የቀሩት፡፡ ግንቦት 20ን ሳስብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ሚያዚያ 29 የተቃዋሚዎች ቀን እንዲሆን ተጠይቆ ነበር እኮ! ለመሆኑ መልስ አገኘ? (ይሄም በልማቱ ተሳቦ እንዳይከለከል ብቻ!) ወደ ግንቦት 20 ልመልሳችሁና … እኔ የግንቦት 20ን በዓል የማከብረው ከዛሬ ጀምሮ ነው፡፡

እንዴት መሰላችሁ የማከብረው? የግንቦት 20 ፍሬዎችን እያጣጣምኩ! በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ትንሽ ሰፋ ቢያደርገው እኮ ግንቦት 20 የተቃዋሚዎችም በዓል ይሆን ነበር፡፡ (የዲያስፖራ ተቃዋሚዎችን አልወጣኝም!) የዳያስፖራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ምህዳሩ የኢትዮጵያን ያህል ቢሰፋለትም አይበቃውም፡፡ (እንኳን የጦቢያ ምህዳር የአሜሪካም አልበቃውም!) እናላችሁ… የግንቦት 20ን ፍሬዎች ለማጣጣም ስል ትንሽ ደፈር እያልኩ ነው የምፅፈው፡ ፡ (“ለግንቦት 20 ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ!”አሉ) ባለፈው ረቡዕ ማታ በኢቴቪ እንደሰማሁት፤ ሁለት የእንግሊዝ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መዝነው B+ እና B አግኝታችኋል ብለውናል፡ ፡ (ሌላ የግንቦት 20 ፍሬ አትሉም!) ባለፈው ጠ/ ሚኒስትሩ በፓርላማ ሲናገሩ፤ 8 ከ10 አግኝተናል ያሉት ከምራቸው እንደሆነ የገባኝ አሁን ነው፡ ፡

ያኔማ ራሱ ኢህአዴግ ያወጣውን ፈተና፣ ራሱ ተፈትኖ፣ ራሱ እያረመ እንዴት ልመነው ? አሁን ግን በገለልተኛ አካል ስለታረመ ለማመን እገደዳለሁ፡ ፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ይሄን የሰሞኑን ውጤት አምነው መቀበል አለባቸው፡ ፡ የ ኢህአዴግ መ ንግስትም በ ኢኮኖሚ ም ዘናው B+ እና B ሲሰጠው ደስ እንዳለው ሁሉ፣ በሌሎች ኮርሶች የሚሰጠውን ውጤትም (Grade) በፀጋ ሊቀበለው ይገባል፡፡ (ማለቃቀስ የፋራ ነው!) ደህና ውጤት ሲያገኙ መፈንጠዝ፣ በውጤት ደከም ሲሉ.. ማለቃቀስ የፍሬሽ ተማሪ ምልክት ነው፡ ፡ ከዚያም አልፎ ውጤት የሰጠውን ወገን ---- የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ፣ ክንድ ጠምዛዦች፣ የኢትዮጵያን ገፅታ ጥላሸት ለመቀባት የሚሯሯጡ ወዘተ… በሚል መፈረጅና ነጋ ጠባ መዝለፍ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከሚገኝ መንግስት አይጠበቅም ( “አይጠበቅም ካ ንቺ!” አ ለ ዘ ፋኙ!) እናም ኢህአዴግ ነፍሴ… አንድም ቀን ጥሩ ውጤት አምጥቶ በማያውቅበት የሰብዓዊ መብት አያያዝ “C” አገኘህ ቢባል (መባሉ ደሞ አይቀርም!) አገር ይያዝልኝ ማለት አይጠበቅበትም፡፡ ይኸውላችሁ.. አውራ ፓርቲው ኢህአዴግ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ልባዊ ፍላጎት እንዳለው “ሁላችንም” እናውቃለን፡፡

ግን በየትኛው ጊዜው ያስከብር?! (ልማት አላፈናፍን አ ለው እኮ!) እና ም.. የባቡር ሃዲድ መዘርጋትና የዜጎች የሰብዓዊ መብት ማስከበር ለየቅል ስለሆኑበት፣ የተሰጠውን “C” በፀጋ ተቀብሎ ምናልባት ለከርሞ ለማሻሻል ይሞክር፡፡ (ይሄ የባቡር ሃዲድ ካላለቀ ግን የሚሆንለት አይመስለኝም!) ለኢህአዴግ ደግሜ ደጋግሜ ላሳስበው የምፈልገው… በተለያዩ ኮርሶች የሚሰጠውን ግሬድ “Personal” እንዳያደርገው ነው፡፡ እስቲ አስቡት… ዩኒቨርሲቲ እየተማራችሁ ሳለ፣ ውጤታችሁ “C” እና “D” በሆነ ቁጥር “የእኔን ዕድገት የማይመኝ ምቀኛ አስተማሪው ስለሆነ ነው እንጂ በደንብ ነበር የሰራሁት…” እያላችሁ ብትንጨረጨሩ ምን ታተርፋላችሁ? (“ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” አሉ!) በፕሬስ ነፃነትና በጋዜጠኞች አያያዝ ደግሞ ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅም የወረደ ግሬድ ሊያገኝ እንደሚችል መገመት አለበት፡፡ (ፈታኞቹ እነሲፒጄ እኮ ናቸው!) እናም… ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ (CPJ) ወይም ሌላ ፈታኝ በፕሬስ ነፃነትና በጋዜጠኝነት አያያዝ ለኢህአዴግ “D” ቢያሽረው፣ ተጯጩሆ ላልሰማው ማሰማት የለበትም፡፡

ይልቁንም በእልህና በቁርጠኝነት ተግቶ በመስራት፣ የቀጣይ ዓመት ግሬዱን ማሻሻል እንጂ! (በአንድ ቀን ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የብሎገር ፀሐፊዎች ታስረዋል ሲባል ሰምቶ “F” አለመስጠቱም እሱ ሆኖ ነው!) ሲፒጄ “ጋዜጠኞች የታሰሩት በሙያቸው ነው አይደለም?” የሚል ሙግት አይመቸውም፡፡ በመድብለ ፓርቲ ሥርአትና በተቃዋሚዎች የመንቀሳቀስ ነፃነት ደግሞ አውራው ፓርቲ “C-” ሊያገኝ እንደሚችል እርግጠኛ ባይሆን እንኳን ሊጠረጥር ይገባል፡፡ በፓርላማ አንድ ተቃዋሚ ብቻ ተወክሎ፣ የተቃዋሚዎች ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ፣ የሞት ሽረት ጉዳይ እየሆነ --- ከዚህ በላይ ውጤት መጠበቅ ፌር አይደለም፡፡ ለነገሩ ይሄን ኮርስ ኢህአዴግ እንደሜጀር ኮርስ ሳይሆን እንደ ኮመን ኮርስ ነው የሚቆጥረው፡፡ ልቡ ግን ያውቀዋል - ሜጀር ኮርስ እንደሆነ (“ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” አሉ!) ፈታኞቹ ወይም መዛኞቹ ደግሞ ሁሌም ግራ እንደተጋቡ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ… ኢህአዴግ በየመድረኩ “ዲሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” እያለ ሲምል ሲገዘት ነው የሚያውቁት፡፡

እናም በውጤቱ ማሽቆልቆል ለኢህአዴግ እነሱ ይጨነቃሉ፡፡ እርሱ ግን በልቡ የቻይና ኮሙኒስት ሪፐብሊክ መንግስትን እያለመ ልማቱ ላይ ይተጋል፡፡ እናም እንደሰሞኑ የኢኮኖሚ ውጤቱ በB እና B+ ግሬዶች ይንበሸበሻል። የአገር ውስጥ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ይሄ አካሄዱ ያሰበበት ቦታ አያደርሰውም ባይ ናቸው። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም፡- “የቻይናና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለየቅል ናቸው” ይላሉ፡፡ እናም አውራው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ በማዕረግ መመረቅ ከፈለገ ከኢኮኖሚ ውጭ ባሉት ኮርሶችም በርትቶ መስራት አለበት ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ። ለኢትዮጵያ ህዝብ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ብቻን አያረካውማ! የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን ዕድገትም አጥብቆ ይሻል፡፡ ተራ በተራ ሳይሆን እኩል፤ በተመሳሳይ ጊዜ! (ያኔ የግንቦት 20 ፍሬዎችን በእርግጥም ማጣጣም ይቻላል!)

Read 3284 times