Saturday, 17 May 2014 14:53

“አርሬ አይተኸኝ ነው እንጂ እኔም ሸክላ ነበርኩ” አለ ጀበና

Written by 
Rate this item
(10 votes)

     በዓለም ላይ በተደጋጋሚ ዝናን አትርፈው ተጠቃሽ ከሆኑት ተረቶች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል። ደራሲ ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ በፃፉት “የሉሲ ከዋክብትና ሌሎችም” በተሰኘው የውርስ ትርጉም የልጆች መልካም ሥነ - ምግባር መጽሐፍ፤ ያገኘነውን ለዛሬ ባጭሩ አቅርበነዋል። በድሮ ጊዜ በአራዊትና በወፎች መካከል ጦርነት ተደርጐ ነበር። የሌት ወፎች ከወፎች ጋር ተሰልፈው ተዋግተዋል። ነገር ግን በመጀመሪያው ጦርነት ወፎች ክፉኛ ተሸነፉ። የሌት ወፎች በሁኔታው ስለሰጉ በየዛፉ አንጓ ላይ ተደብቀው፣ የጦርነቱን የመጨረሻ ውጤት ተጠባበቁ። ድል አድራጊዎቹ አራዊት ወደቤታቸው ሲሄዱ፣ የሌት ወፎች ተደባልቀው አብረው ሄዱ። ትንሽ ከተጓዙ በኋላ፣ አራዊቱ ነቁባቸው (አወቁባቸው)። “ይቅርታ! እናንተ ከወፎች ወገን ተሰልፋችሁ የወጋችሁን አይደላችሁም እንዴ?” በማለት የሌት ወፎችን ጠየቋቸው። የሌት ወፎችም እንዲህ ሲሉ መለሱ።

“ኦ! በፍፁም! እኛ እኮ እንደ እናንተ ነን። ጥፍራችንንና ጥርሳችንን ብትመለከቱ ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ ነው። ወንድማማቾች እኮ ነን። ወፎች እንዲህ እንደ እኛ አካል አላቸውን? በፍፁም! እኛ የአራዊት ወገን ነን! (አይጦች ነን!)” አራዊቱ ሁ ኔታውን ከ ሰሙ በ ኋላ ዝ ም አ ሉ። የ ሌት ወ ፎቹንም አ ብረዋቸው እ ንዲሆኑ ፈቀዱላቸው። ከአይጥ ተቆጠሩ ማለት ነው። በሌላ ጦርነት ወፎች ሲያሸንፉ፤ አይጦች ከወፎች ጋር አብረው ለመሄድ ወሰኑ። ዛሬ ደሞ ወፍ ሆኑ ማለት ነው። ሲጠየቁም፤ “እኛኮ እንደእናንተ ነን ክንፍ አለን” አሏቸው። ውሎ አድሮ ወፎችና አራዊት ሰላም ፈጠሩ። አራዊቱም የሌት ወፎቹን “ከእኛ ጋር አይደላችሁም” አሏቸው። ወፎቹም፤ “ከአራዊት ጋር ተሰልፋችሁ ወግታችሁናል። ሂዱልን እናንተ አይጦች! እነሱ ያዛልቋችሁ!” ብለው አገለሏቸው። የሌሊት ወፎች ከአራዊትም ሆነ ከወፎች ጋር መኖር ስላልተፈቀደላቸው፣ ከወፎችና ከአራዊት የተውጣጣው የጋራ ኮሚቴ “ከዚህ በኋላ፣ የሌት ወፎች ሆይ! ሌሊት በአየር ትከንፋላችሁ (ትበርራላችሁ)።

ምንም ጓደኛ አይኖራችሁም። ከእንግዲህ ከሚራመድም ሆነ ከሚከንፍ ተለይታችሁ ትኖራላችሁ” በማለት ወሰነባቸው። ስለዚህ ይኸው እስከዛሬም ድረስ የሌሊት ወፎች በጨለማ ይክነፈነፋሉ፣ በጨለማ ዋሻዎችም ውስጥ ይኖራሉ። የሌት ወፎች እንደ ወፎች ክንፍ ቢኖራቸውም በዛፎች አናትና ቅርንጫፎች ላይ አርፈው አያውቁም። ማንም ቢሆን ስለሌሊት ወፎች አፈጣጠርና ምንነት ደንታ የለውም።

                                                              * * *

በህይወታችን፤ በተለይም በፖለቲካ ህይወታችን ውስጥ ሁለት ቦታ መርገጥ፣ ሁለት አቋም መያዝ፣ በተለይም በፈጠነ ግልብጥብጦሽ ውስጥ እንደእስስት መቀያየር፤ ማንነትን የማጣትን ያህል አደጋ አለው። በኢትዮጵያውያን ዘንድ፤ አርበኛ ነን እያሉ የባንዳ ሥራ መሥራት በታሪክም በኑሮም የእርግማን ዒላማ መሆን ነው። “ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው” የሚለው የፉከራና የሽለላ ግጥም ያለዋዛ አልተገጠመም። ይሄ ግጥም፤ አይጥ ነው ብለው አቅርበውት የሌሊት ወፍ ሆኖ ለሚገኘውና፤ የሌሊት ወፍ ነው ብለው ሲያቀርቡት አይጥ ሆኖ ለሚገኝ ግለ-ሰብ፤ አልፎ ተርፎም ለሚያንሿክክና ለሚያሾከሹክ ሥራዬ ተብሎ የተፃፈ ሳይሆን አይቀርም። “የአድር - ባይነት ዥውዥው መቼም ማቆሚያ የለውም” ይላል ሌኒን። ዕውነት ነው። መወዛወዙ በራሱ ቢቀር ባልከፋ። ግን ወዲህ ሲመጣ ካንዱ ሲላተም፣ ወዲያ ሲሄድ ከሌላው ሲላተም ጦሱ ለሰው መትረፉ ነው ጣጣው።

ገጣሚና ፀሐፌ - ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤ ስለ አንድ ሚስቱ ስለምትደበድበው ባል ሲያወሱ፤ “ሰውዬውን ሚስቱ በትግል ጥላው፤ እላዩ ላይ ተቀምጣ በቡጢ ስታነግለው፤ ጐረቤት ይደርሳል። “ምነው ምን ተፈጠረ?” ይላል ጐረቤት። ይሄኔ ባል፤ የሚስቱን የበላይነትና ነውሩን አለመቀበሉን ለጐረቤቶቹ ለማስረዳት፤ “እስካሁን ከላይ ነበርኩኝ አዲስ ግልብጥ ነኝ! አዲስ ግልብጥ ነኝ!!” እያለ ጮኸ። አቶ መንግሥቱ ይሄን ጨዋታ ያመጡት፣ ባገራችን አዲስ መንግሥት መጥቶ ሁሉም “አሸወይናዬ” ማለት ሲጀምር ነው። ያኔ እንግዲህ “ስለ አዲሱ መንግሥት ለምን አትፅፉም?” ተብለው ሲጠየቁ፤ “እኔ አዲስ ግልብጥ አይደለሁማ!” ባሉበት ወቅት ነው። አዲስ ግልብጥ መሆንና በየጊዜው መገለባበጥ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። ከለየለት አድርባይነት ተለይተው አይታዩም። ከአንድ ፓርቲ ወጥቶ ለሌላ ፓርቲ መገበር አድር ባይነት ነው። ከአንድ መንግሥት ወጥቶ ለተቃራኒው መንግሥት እጅ ሰጥቶ ማገልገልም የአድርባይነትን ትርጉም ያሟላል። ከሁሉም በላይ ግን በልብ ማመንዘር ይከፋል። ከዚህ ይሰውረን። ከሀገራችን ችግሮች አንዱ፤ “ወደቀ ሲባል ተሰበረ” ማለታችን ነው። እንዲህ ካልሆነ ሞተን እንገኛለን ብለን ስናበቃ ያ ጉዳይ ከተከወነ፤ አዲስ ቦቃ ልናወጣለት ደሞ ሌላ ፀጉር ስንጠቃ እንጀምራለን።

ደግን ደግ ክፉን ክፉ ማለት መቻል ትልቅ ፀጋ ነው። እርግጥ፤ ዝም ማለትም ሌላው ፀጋ ነው። ቃል በማይከበርበት፣ ፕላን በወግ በማይተገበርበት አገር፣ “ካልታዘልኩ አላምንም” ማለታችን ትክክል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለውጥን ግን በውል ማስተዋል ተገቢ ይሆናል። “ውሃ ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን ድረስ ይጠፋል” ብሎ ቀድሞ ማሳወቅ፣ ውሃ አጠራቅሙ ማለት በትክክለኛ መረጃ አሰጣጥ ማመን ነው። በ ስልክም፣ በ መብራትም፣ በ ምርጫም፣ በ ሹም - ሽ ርም ወ ዘተ አ ስቀድሞ መረጃ እንድናገኝ ቢደረግ መተማመን ይበረክታል። ማንኛውም ወገናችን፤ የመከላከያ ባለስልጣን ይሁን የክልል፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ቀራቢ ይሁን ተራ ማሪ፤ ሙስና ከፈፀመ ሙሰኛ ነው! መረጃውን ማግኘትም መብታችን ነው፡፡ በተግባር ምን ማለት እንደሆነ በየቤቱ የሆነውን መቃኘት ነው። መረጃ መስጠት የመሻሻል ምልክት መሆኑን ግን በተቀዳሚ ማድነቅ መልካምነት ነው። ተግባሩ ካረካን መልካም። ውሸት ከሆነ ግን “አርሬ አይተኸኝ ነው እንጂ እኔም ሸክላ ነበርኩ” ያለውን ጀበና በማስታወስ ቸግሮን ነው እንጂ አንታለልም ማለት ግድ ይሆናል።

Read 7374 times