Saturday, 10 May 2014 12:39

“ኃይለኛ ነጋዴ ነኝ…የብርሌ አንገት ማነቅ አልወድም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(16 votes)

አዛውንቱ የትጋት ተምሳሌት!

“ኃይለኛ ነጋዴ ነኝ…የብርሌ አንገት ማነቅ አልወድም”

ወደ ንግድ ሥራ ሀ ብለው የገቡት መሬት ወድቆ ባገኙት ድፍን 50 ሳንቲም ነው


አቶ ጌትነት ጎሹ አበጋዝ ይባላሉ፡፡ በአማራ ክልል አዊ ዞን ቻግኒ ከተማ ተወልደው ማደጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት አስቸጋሪ ፈተናዎችን ተጋፍጠወ እንዳለፉ
የሚገልፁት የ59 ዓመቱ አዛውንት፤ ዛሬ በቻግኒ ከተማ ከሚገኙ ሆቴሎች የትልቁ የቀ.ኃ.ስ በር ሆቴል ባለቤት ናቸው፡፡
መሬት ላይ ወድቆ ባገኙት ድፍን ሀምሳ ሳንቲም… በዶሮ ንግድ ስራ የጀመሩት  አዛውንት አቶ ጌትነት፤ በአውራ ጎዳና መ/ቤት የመኪና ረዳት ከመሆን ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን ሳይመርጡ በመስራት ባለሀብት ለመሆን በቅተዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በህይወታቸው፣ በቢዝነስ ሥራቸውና ፍልስፍናቸው ዙሪያ ከአቶ ጌትነት ጋር አውግታለች፡፡

ከተማዋ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ሆቴሎች አንዱ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ በር (ቀ.ኃ.ሥ በር) ሆቴል ነው፡፡ መቼ ነው የተከፈተው?
በ1983 ዓ.ም በለውጡ ጊዜ ነው በትንሹ የተጀመረው፡፡
ሆቴሉን ቀ.ኃ.ሥ በር ብለው የሰየሙበት ምክንያት ምንድነው?
ቀ.ኃ.ስ በር የተባለበት ምክንያት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከእንግሊዝ ከስደት ሲመለሱ በሱዳን ካርቱም በኩል፣ አሁን ህዳሴው ግድብ በሚገደብበት አድርገው እዚህች ከተማ ነው ያረፉት፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ጃንሆይ፣ እዚህ ሶስት ሳምንታት አሳልፈዋል፡፡ ይህ አካባቢ በወቅቱ ጫካ ነበር፡፡ በእርሳቸው ትዕዛዝ መተከል አውራጃ፣ ቀ.ኃ.ስ በር ከተማ ተብሎ ተመሰረተ፡፡ በዚያን ጊዜ የከተማዋ ፕላን ራሱ ቀ.ኃ.ስ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ከዚህ ታሪክ በመነሳት፣ የእኔ ሆቴል ተከፍቶ ሲመረቅ፣ ለምርቃቱ የተጠሩት የአገር ሽማግሌዎች ቀ.ኃ.ሥ በር ሆቴል ብለው ሰየሙት፡፡
ከተማዋ አሁን “ቻግኒ” በመባል ነው የምትታወቀው፡፡ እንዴት ስሟ ሊቀየር ቻለ?
ይገርምሻል… ህዝቡ በወቅቱ ቀ.ኃ.ስ በር የሚባለው ስም እንዲቀየር አልፈለገም ነበር፡፡ ወቅቱ ደርግ ሥልጣን የያዘበት አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ ቀ.ኃ.ስ በር የሚለው ይቅር ተባለና ወደ ቻግኒ ተቀየረ፡፡
“ቻግኒ” የሚለው ቃል አገውኛ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ለመሆኑ ፍቺው ምን ማለት ነው?
ቻግኒ እንዳልሽው አገውኛ ቃል ነው፡፡ ብዙ ፍቺም አለው፤ “ቻ-ግኒ” ማለት “የነገ ቤት” ማለት ነው፡፡ “ቻግኒ” ማለት ደግሞ “የነገ ነገር” ማለትም ነው፤ ብቻ ብዙ ፍቺ አለው፡፡
በ1983 ዓ.ም ትንሽ ሆቴል ሆኖ ስራ መጀመሩን ነግረውኛል፡፡ አሁን ደግሞ ፎቅ እስከ መገንባትደርሰዋል፡፡ እስኪ ሂደቱን ያጫውቱኝ…
በ1983 ዓ.ም የነበረው ቤት ፈርሷል፡፡  በትንሽ አሮጌ ቤት ነው የተጀመረው፡፡ መነሻ ካፒታሉም 33ሺህ ብር ነበር፡፡ ከዚያ አንድ አስር ዓመት ከሰራሁ በኋላ፣ ይህን የምታይውን ሆቴል (ወደ ምግብ አዳራሹ እያሳዩኝ) ሰራሁ፡፡ አሁንም ሰርቼ ካጠራቀምኩ በኋላ፣ በ2002 ዓ.ም ይህን የምታይውን ፎቅ ሰራሁ፡፡ ሶስት ወለል አለው፡፡
የከተማዋ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ከተማዋ የንግድ ከተማ ናት፡፡ በአጠቃላይ ደረቅ ወደብ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ከሰባትና ከስምንት ያላነሱ መግቢያ በሮች አሏት፡፡
እስኪ መግቢያ በሮቹን ይጥቀሱልኝ?
ከወንበራ፣ ከዚጋም፣ ከጃዊ ስኳር ፋብሪካ፣ ከህዳሴው ግድብ፣ ከአዲስ አበባና ከባህርዳር መግቢያ አሏት፡፡ ያም ሆኖ፣ የንግድ ከተማም ሆና ፈጣን እድገት የላትም፡፡
ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ?
እኛ ምክንያቱን አናውቀውም ወይም ብዙ አይገባንም፡፡ በጣም የሚገርምሽ እንደውም እየቀዘቀዘች ነው የመጣችው፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ጎብኚዎች በዚህ ያልፋሉ፡፡ እኛም የጉብኝቱ አካል ነን!! በዚህስ መሻሻልና ጥሩ እንቅስቃሴ የላትም?
የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ያን ያህል አስተዋ    ጽኦ የለውም!! ለምሳሌ እናንተ እዚህ ምሳ በላችሁ፣ አረፋችሁ፣ እዚህ አድራችሁ በሌሊት ብትነሱ አሳምራችሁ የህዳሴው ግድብ ያለበት በጠዋት ትደርሳላችሁ!! ለምቾቱም ቢሆን ውሀውም አየሩም እዚህ ቀዝቃዛ ነው፤ ነገር ግን ሁሉም ግልገል በለስ ነው ማደር የሚፈልገው!! በዚህ የተነሳ ከተማዋ የንግድ ከተማ ብትሆንም ብዙ ተጠቃሚ አይደለችም፡፡
እስኪ እንዴት ወደ ሆቴል ስራ እንደተሰማሩ ያጫውቱኝ? ትምህርትስ ተምረዋል?
እኔ አልተማርኩም፡፡ ልጆቼን ግን አስሩንም አሳምሬ አስተምሬያለሁ፡፡ ኢንጂነር የሆነ አለ፤ በክልል ደረጃ ፋይናንስ ቢሮ የሚሰራም አለኝ፡፡ ሁሉንም አስተምሬያለሁ፡፡ ወደ ሆቴል ስራ ከመግባቴ በፊት በኢትዮጵያ አውራ ጎዳና መስሪያ ቤት ውስጥ የመኪና ረዳት ሆኜ እሰራ ነበር፡፡
በየአገሩም እዞር ነበር፡፡ ታዲያ ለአልጋና ለምግብ የሚሰጠኝን አበል መኪና ውስጥ እየተኛሁ አስቀምጥ ነበር፡፡ ያቺን አሰባስቤ 33 ሺህ ብር ሲደርስልኝ ነው ትንሿን ሆቴል የከፈትኩት፡፡ አሁን እንደምታይው የበፊቱ ሆቴል እንዳለ ሆኖ ወደ ላይ ሶስት ፎቅ ለመገንባት በቅቻለሁ፡፡
ስንት መኝታዎች አሉት?
ይሄ ትልቁ ፎቅ 27 መኝታ ሲኖረው፣ የቀድሞው ፊት ለፊት የምታይው አንድ ፎቅ አለው፡፡ ከላይና ከታች 33 መኝታዎች፣ በአጠቃላይ 60 የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡
የእርስዎ ሆቴል ከሌላው የከተማዋ ሆቴሎች ጋር ሲወዳደር እንዴት ነው?
እራ! ይሄማ ምን ተወዳዳሪ አለው! የእኔ እኮ በከተማዋ አይነተኛ ሆቴል ነው፤ ነገር ግን አሁን ሰው የሆቴል ቢዝነስ እየገባው ስለሆነ እየሰራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኔ ትልቅና የተሻለው ነው፤ በከተማዋ ካሉት ማለቴ ነው፡፡
አሁን እርስዎ ጡረታ አልወጡም ማለት ነው?
የምን ጡረታ አመጣሽብኝ! እኔ ገና የ59 ዓመት ጎረምሳ እኮ ነኝ፡፡  እስከ 70 ዓመቴ ድረስ እሰራለሁ፡፡
ጎበዝ ነጋዴ ነኝ ብለው ያስባሉ?
አሃ! ጎበዝ ብሆን አይደል ይህን ሁሉ ያስፋፋሁት። ጎበዝ ነጋዴ ማለት ገንዘብ  ሳያባክን አጠራቅሞ ቁም ነገር ላይ የሚያውል ነው፡፡ እኔ ያለ ቁም ነገር ገንዘብ ማውጣት አልወድም፡፡ የቢራ ጠርሙስ አንገት ወይም የብርሌ አንገት ማነቅም አልፈልግም አልወድም፡፡ ሁሉምን በስራ ላይ ነው የማውለው። ስራዬን ቀንም ማታም እሰራለሁ፤ አላርፍም፡፡ አሁን ጥሩ አቅም አለኝ፤ ጉልበቴ ሲደክም ልጆቼ ደርሰዋል፤ ለእነሱ አስረክባለሁ፡፡ ታዲያ ጎበዝ ነጋዴ  አይደለሁም?
በጣም ጎበዝ ነዎት! ባለቤትዎስ አሉ?
አሁን በፊት ለፊትሽ አለፈች እኮ! ገና 42 አመቷ ነው፤ ወጣት ናት፡፡
ለቤትዎ ጥሩ አባወራ ነዎት?
ይህንን መመስከር የምትችለው ባለቤቴ ነበረች። አሁን ቤተክርስቲያን ልታስ    ቀድስ ሄደች (ወቅቱ የሁዳዴ ፆም ነበር)፡፡ እኔ ግን ጥሩ ባል እና ጥሩ አባት ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ እራ! ጥሩ ባልሆንማ፣ ምሽቴስ አራግፋኝ አልነበር የምትሄድ ዋ!
ቻግኒ በጣም የምትታወቀው በዝነኛዋ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)ነው፡፡ ከእርስዋ ቤተሰቦች ጋር ይተዋወቃሉ?
አባቷ አያ ሽባባው፣ አባቴ ነው ማለት ትችያለሽ፡፡
በዕድሜ በጣም ትበላለጣላችሁ እንዴ?
ዋ! ያሳደገኝ አባቴ ነው እያልኩሽ፡፡ ልጅ ሆኜ የእሱን ጥጆች እጠብቅ ነበር፡፡
አቶ ሽባባው የሚኖሩት ባህርዳር ነው፡፡ እዚህ ከተማዋ መግቢያ ላይ “ጣና በለስ” የሚባል ሆቴል  የእነ ጂጂ ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ማነው የሚያስተዳድረው?
እናትየዋ ናት የምታስተዳድረው፤ ወ/ሮ ተናኜ ትባላለች፡፡ ከአቶ ሽባባው ጋር ከተለያዩ በጣም ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል፤ እሱም ወደ ባህርዳር ከሄደ በኋላ ወደዚህ ወጥቶ አያውቅም፡፡
ጂጂስ እዚህ መጥታ ታውቃለች?
እሷም መጥታ አታውቅም፡፡ እናቲቱ እትዬ ተናኜ ራሷ አሜሪካ ድረስ እየሄደች ነው የምትጠይቃት። ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ ሄዳለች እንጂ ሆቴል ብትሄጂ አታጫትም ነበር፡፡ ጎበዝ የስራ ሰው ናት። የባለስልጣን ልጅም አትመስልም፡፡ እትዬ ተናኜ፣ ማህበራዊ ኑሮ ላይ ጥሩ ግንኙነት አላት፤ ሰው መካሪና አስታራቂም ናት፡፡
የባለስልጣን ልጅ ነበሩ እንዴ?
አባቷ የቆላ ዳሞት አውራጃ (የፍኖተ ሰላም) አስተዳዳሪ ነበሩ፤ በጥሩ ኑሮ ነው ያደገችው፡፡
እስቲ ስለልጅነት ጊዜዎ ያስታውሱኝ… የሀብታም ልጅ ነበሩ? ወይስ ከደሀ ቤተሰብ ነው የተወለዱት? እንዴት ጠንካራ ሰራተኛ ሊሆኑ ቻሉ?
እንዳትስቂ ግን አንድ ነገር ልንገርሽ?
አትሳቂ ካሉኝ ምን ይደረጋል አልስቅም፡፡ እስቲ  ይንገሩኝ…
እኔ በ1964 ዓ.ም (ለራሳቸው ሳቃቸው እያፈናቸው) ቤታችን ከከተማው ጫፍ ላይ ነበር፡፡ ዘመዶቼ ወደ መሀል ከተማ ልከውኝ ስመጣ፣ እዚህ ከተማ መሀል አንድ ነጭ ሽልንግ (50 ሳንቲም) ወድቃ አገኘኋት፡፡ ቅዳሜ ቀን ነበር፤ ያቺን ሳንቲም ይዤ “ቅዳማጃ” የምትባል ከተማ አለች፤ ከቻግኒ 24 ኪ.ሜ ትርቃለች፡፡ አሁን አልፋችኋት ነው የመጣችሁት፡፡ እዚያ ያለ ዶሮ ተራ ሄድኩኝ፡፡ ከዚያም በጣም ትልቅ ዶሮ ገዛሁኝ፡፡
በ50 ሳንቲም
ዋ! ያን ጊዜ ዶሮ 10 እና 15 ሳንቲም አልነበር የሚገዛ! የእኔ እኮ ትልቅ ዶሮ ስለሆነ ነው 50 ሳንቲም ያወጣው፡፡ ከዚያ አንድ ጌሾ ነጋዴ አህያ ላይ ጫነልኝና ጉዞ ጀመርን መንገዱ አካባቢው ጫካ ስለነበር፣ አህያው እየሄደ ሳለ፣ የዶሮውን አንገት ሀረግ አንቆ ገደለብኝ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ የሞተ ዶሮ ተሸክሜ ጉዞ ቀጠልኩ። እያልኩ በመፀፀት አለቀስኩ፡፡ ደግነቱ ግን ስጋዴ የሚባለው አካባቢ የሚኖሩት ሰዎች የሞተም ይበላሉ። ባህላቸው ችግር የለበትም፡፡ እናም በምላጭ አርጄ፣ ላባውን አስወግጄ፣ ቆዳውን ገፈፍኩት፡፡ የዶሮው ስጋ ሰዎቹ በጣም ትልልቅ ነው፡፡ ያንን ስጋ በአንድ ብር ገዙኝ፤ 50 ሳንቲም በማትረፌ ለቅሶዬ ወደ ሳቅ ተቀየረ፡፡ እውነቴን ነው፣ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ በህይወቴ ይህን አልረሳውም፡፡
ሌላስ ገጠመኝ አለዎት?  
አውራ ጎዳና ውስጥ ረዳት ሆኜ እየሰራሁ እያለ አሰብ ነበርን፡፡ የእኛ መኪና ጎማው ፈነዳ፡፡ ቼርኬው ለብቻ ወደቀ፤ እኔ ደግሞ መኪናው ተገለበጠ ብዬ ደንግጬ ሄጄ ቸርኬውን ስይዘው እጄ እንዳለ ተገሸለጠና ጎማው ላይ ቀረ፡፡ አንደኛ፤ ቦታው አሰብ ስለሆነ ሞቃት ነው፣ ሁለተኛ ቸርኬው ግሏል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ያቃጠለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ለብዙ ጊዜ እንጀራ ቆርሼ የምበላበት አጥቼ ስሰቃይ ቆይቻለሁ፡፡ እነዚህን ነገሮች አልረሳቸውም፡፡
ያኔ ደሞዝዎት ምን ያህል ነበር?
አውራ ጎዳና ስሰራ፣ መንግስት የሚከፍለኝ በወር 48 ብር ብቻ ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ በ1973 እና 74 ዓ.ም ነው፡፡
የሞተውን ዶሮ ሸጠው ያገኟትን አንድ ብር ምን አደረጓት?
ዋ! የዶሮ ንግድ ጀመርኩና በወር ከ15 ቀን ውስጥ ካፒታሌን ወደ 4.50 ሳንቲም አሳደግሁት፡፡ (ሳ….ቅ….) አሁን ማግኘቴ መለወጤ ብዙ አያስደንቀኝም። የማስታውሰው የድሮውን ችግሬንና ከችግር ለመውጣት ያደረግሁትን መፍጨርጨር ነው፡፡ እኔ በባህሪዬ ገንዘብ ማባከን አልወድም፡፡ ልጆቼ ገንዘብ በብዛት እያወጡ ሲዝናኑ ስመለከት ይገርመኛል፡፡ እመክራቸዋለሁ ግን አይሰሙኝም፡፡
ጤናዎትስ እንዴት ነው? እድሜ ሲገፋ እኮ…
ስኳር አለብኝ፤ ግን በደንብ ተቆጣጥሬው ነው የምኖረው፡፡ ፈጽሞ ችላ አልለውም፡፡ ወደ 18 ዓመት ገደማ ከስኳር ጋር ኖሬያለሁ፤ ፈፅሞ ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን አልፈቅድለትም፡፡
ከቻግኒ ጀምሮ እስከ ህዳሴው ግድብ መስመር ድረስ ብቸኛ የሀረርና የበደሌ ቢራ አከፋፋይ መሆንዎትን ሰምቻለሁ…
አዎ! ያ መኪና ከነተሳቢው ይታይሻል? (ሆቴላቸው ጎን ባለ አንድ ትልቅ መጋዘን ፊት ለፊት ቢራ የሚያራግፍ መኪና ከነተሳቢው እያመለከቱኝ) አሁን እነ ሀረር ሶፊን፣ በደሌን እያወረደ ነው፡፡ ከዚህ አንስተሽ እነግልገል በለስና በዚያ መስመር ያሉት በጠቅላላ እነዚህን ቢራዎች ከእኔ ነው የሚወስዱት፡፡ መኪናውም መጋዘኑም የራሴ ነው፡፡ አየሽ፤ ሀይለኛ ነጋዴ ነኝ ያልኩሽ ለዚህ ነው፡፡  

Read 6819 times