Saturday, 10 May 2014 12:37

“የሥራ ፈጠራ ጥበብ ተቋም ቢኖርና ቢስፋፋ ኖሮ፣

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(13 votes)

ፀረ - ሙስና ኮሚሽን አያስፈልግም ነበር”
ዓላማ ይዘው የሚሰሩ የኢትዮጵያ ህዳሴ አስተማማኝ መሰረቶች ናቸው
የኢንተርፕረነሮች መመዘኛ-ተነሳሽነት፣ ማቀድና መፈፀም
ዶ/ር ወረታው በዛብህ በሙያ ኢኮኖሚስት ናቸው፡፡ በሙያቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲዎችና ኮሌጆች አስተምረዋል፤ በተለያዩ መ/ቤቶችም ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመበልፀጊያ ወይም የሥራ ፈጠራ ጥበብ (ኢንተርፕረነርሽፕ) እያሰለጠነ ያለው ጂንየስ ማሰልጠኛ ባለቤትና አሰልጣኝ ናቸው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ስድስት የፈጠራ ጥበብ ባለቤት መሆኛ ዘዴ መጻሕፍትና ሰባት የኢንተርፕረነርሽፕ ዲቪዲዎች ያዘጋጁ ሲሆን፣ በማኅበራቸው ቤርቴክ ቢዝነስ ሶሳይቲ በኩል ደግሞ 110 የቢዝነስ ፅንሰ ሐሳብ ማስጨበጫ ምሽት ፕሮግራሞች ላይ አስተምረዋል፡፡ አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅና ጂንየስ ማሰልጠኛ በጋራ በመሆን “የብልፅግና ቁልፍ” በሚል ርዕስ በሳተሙት ስድስት መጻሕፍት ላይም ተሳትፈዋል፡፡
ሥራቸውን ለቀው ወደ ግል ሥራ ለመግባት የተነሳሱት የ6ሺ ብር ደሞዝተኛ ሳሉ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶ/ር ወረታው፤ ኢትዮጵያ በሥራ ፈጠራ ጥበብ ኋላ ቀር መሆኗ በኢንተርረነርሽፕ እንዳሰለጥን አድርጎኛል ይላሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ ከእኚህ የሥራ ፈጠራ ባለሙያ ጋር ማራኪና አነቃቂ የሆነ ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

የሥራ ፈጠራ ጥበብ ወይም ኢንተርፕረነርሽፕ እንዴት ይገለፃል?
እኛ በምናሰለጥንበት መንገድ፣ ኢንተርፕረነርሽፕን “የሥራ ፈጠራ ጥበብ” ብለን ነው የምንተረጉመው፡፡ ኢንተርፕረነርሽፕ (የሥራ ፈጠራ) ሦስት ዋና ዋና ግብአቶች አሉት፡፡ አንደኛ ከሥራ ፈጠራነቱ ተጨማሪ፣ ፈጣንና የማያቋርጥ የሀብት መፍጠር ሂደት፣ ሌላው መሬት፣ የሰው ኃይል፣ ካፒታል፣ ሐሳብ፣ ቴክኖሎጂ ላይ ያለውን ኋላ ቀር የአሰራር ድርሻ መለወጥ፣ ሦስተኛው ደግሞ የተጠና ኃላፊነትን ወስዶ፣ ስራውን በግልም ይሁን በጋራ፣ የሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶችን ሁሉ ተቋቁሞ ስኬታማ የማድረግ ሂደት ነው-ኢንተርፕረነርሽፕ፡፡
ይኼ ግብአት ከተገኘ (ከታወቀ) 215 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚያ በፊት በየሥርአተ ማኅበሩ የተወሰደው ሌላ ሌላ ግብአት መሬትን በወረራ መያዝ፣ የሰውን ልጅ እንደዕቃ መሸጥ ….  ነበሩ፡፡
ከ215 ዓመት በፊት ግን ሁኔታዎች ተለወጡ። አሜሪካ፣ አውሮፓና ጃፓን የሰለጠኑት የኢንተርፕረነርሽፕ ግብአቶችን በመጠቀም ነው። በኢንተርፕረነርሽፕ ሐሳብ፣ አዲስ ነገር መፍጠር፣ የተፈጠሩትን በማሻሻል ብዙኃን እንዲጠቀሙበት ማድረግ፣ ይቻላል በማለት የሚያቀራርብ ማኅበራዊ ሂደት ሆነ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮ የሰጠችው ሀብት በውስጡ አለ፡፡ ያንን ሀብት ወደ ምርትና አገልግሎት ለውጦ በርካታ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ማድረግ፣ የባለራዕዮች ህልምና ዓላማ ነው፡፡
ኢንተርፕረነርሽፕ መመዘኛ አለው?
አዎ! አለው፡፡ ኢንተርፕረነሮች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ውልሰን ሃሮልድ የተባሉ አሜሪካዊ የንግድ ሰው፣ በ2004 እ.ኤ.አ ባሳተሙት መጽሐፍ፣ ከ215 ዓመት በፊት አሜሪካ ከነበሯት 22 ሚሊዮን የቢዝነስ ሰዎች መካከል፣ ኢንተርፕረነሮች ከመቶ ሰዎች አምስት (1,100,000) ብቻ እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡ ሕንድ ደግሞ በ20 ዓመት ውስጥ ከጠቅላላ ሕዝቦቿ፣ ከመቶ ሰው መካከል አንድ ኢንተርፕረነር ለማግኘት ዘመቻ ጀምራለች፡፡
እያንዳንዱ ሰው ውስጥ ትልቅ አቅም አለ፡፡ ኢንተርፕረነርሽፕ ይህንን አቅም አውጥቶ መጠቀም ማለት ነው፡፡ ቻይናን ለአብነት ብንወስድ፣ ኢንተርፕረነርሽፕ በመፍጠር፣ ባለፉት 30 ዓመታት የት እንደደረሰች እያየን ነው፡፡ ኢንተርፕረነርሽፕን ተግባራዊ በማድረጋቸው ፋብሪካውም ሆነ እርሻው ካፒታል ፈጥሮላቸዋል፡፡
በአገራችን በጣም ብዙ ሰዎች በየወሩ ደሞዝ ያገኛሉ፡፡ የኢንተርፕረነርሽፕ ራዕይ በውስጣቸው ስለሌለ ያገኙትን ጨርሰው ቀጣዩን ወር ይጠብቃሉ። እነ አቶ በቀለ ሞላ ግን የመሻሻልና የመለወጥ የኢንተርፕረነር ራዕይ ስለነበራቸው፣ ሻይና ዳቦ እየበሉ በመቆጠብ፣ 15 ሆቴሎች በመስራት ለብዙዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡
ኢንተርፕረነሮች ሦስት መመዘኛ አላቸው፡፡ ተነሳሽነት፣ ማቀድና መፈፀም ናቸው፡፡ ብዙዎቻችን ተነሳሽነት የለንም፡፡ በሚቀጥለው ዓመት እዚህ ደረጃ እደርሳለሁ፣ ግቤ ይኼ ነው… የሚል ነገር የለንም። እንደፈለገው ይሁን ብለን እንተወዋለን እንጂ ተነሳሽነት አይኖረንም፡፡ ተነሳሽነት ያላቸው ሰዎች “የዛሬ ዓመት፣ ከ5 እና ከ10 ዓመት በኋላ… እዚህ እደርሳለሁ” ብለው ያቅዳሉ፡፡  
በውሳኔያቸው መሠረት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ የሌላቸውን ሙያ ይቀስማሉ፣ የሌላቸውን ገንዘብ ይቆጥባሉ፡፡ ገንዘብ ለማበርከት የተሻለ ሥራ ይሰራሉ፣ በዚህ መሰረት ወደሚቀጥለው ደረጃ ይሸጋገራሉ፡፡ ተነሳሽነት፣ እደርሳለሁ ላሉት ነገር ታማኝ መሆን፣ አጋጣሚዎችን መጠቀም፣ ቃልን ጠብቆ በፅናትና በጥራት የመፈፀምና የመጓዝ ችሎታ ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደለም - በጣም አድካሚ ነው፣ መሰናክል ሊበዛበት ይችላል፡፡ ነገር ግን እልህ አስጨራሽ ትግልና ፈተና ሲገጥም፣ እንደ በቀለ ሞላ፣ እንደ ተካ ኤገኖ፣ እንደዘነበ ፍሬው ለራዕይ ታማኝ ሆኖ፣ በትዕግስትና በብልሃት እክሉን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ የአቶ ተካ ኢገኖ ተነሳሽነት ዛሬም አልበረደም፡፡ ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረት ሁሉ ቢወረስም ተስፋ ቆርጠው አልተቀመጡም፡፡ ዛሬም በ85 ዓመታቸው ከዘራ ይዘው ባለፋብሪካ ናቸው። ሀብት ያለው፣ በግል ተነሳሽነትና አመለካከት ላይ ነው፡፡ የሰው ሀብት 90 ከመቶ አመለካከቱ ነው። ኢንተርፕረነሮችን ሁሉ ስንመለከት ከባዶ ነው የተነሱት፡፡ መነሻቸው ተነሳሽነታቸው ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ከዓለም ቱጃሮች ከ1-3ኛ ያለውን ደረጃ የሚይዙትን አሜሪካዊ ዋረን ቡፌ እዚህ ላይ መጥቀስ አስፈላጊ ነው፡፡ ዋረን ቡፌ 6 ዓመት ሲሆናቸው “በ35ኛ ዓመቴ ሚሊዬነር እሆናለሁ” ሲሉ ነበር ያቀዱት፡፡ አሜሪካ እ.ኤ.አ 1933 ዓ.ም በታሪኳ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ በነበረችበት ጊዜ፣ ሰው የሚበላና የሚላስ በተቸገረበት ጨለማ ዘመን፣ ቡፌ ግን ሚሊዬነር የመሆን ህልም ነበራቸው፡፡ ይህ ነው ራዕይ ማለት፡፡
ከተነሳሽነት ቀጥሎ ያለው፣ ያቀዱት ዓላማ ላይ ለመድረስ የሚጓዙበትን መንገድ ማቀድ ወይም ካርታ መንደፍ ነው፡፡ በ10 ዓመት አንድ ሚሊዮን ባለራዕዮችን ለማፍራት ብናቅድ፣ እንዴትና ምን ብናደርግ፣ ምን ዘዴ ብንጠቀም፣ ህልማችን ላይ መድረስ እንችላለን? በማለት ማቀድ፣ በወረቀት ላይ ካርታ መንደፍ ነው፡፡ በየዓመቱ ስንት ማፍራት እንዳለብን ማቀድ፣ የትኛውን ችግር ማሸነፍና መወጣት እንዳለብን… በስሜትና በችኮላ ሳይሆን ትክክለኛና ግልጽ መረጃ ላይ በመመስረት ማቀድ ነው፡፡ ከ5 ወይም ከ10 ዓመት በኋላ አሁን ከውጭ የሚመጣውን አገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛ አድናለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ውጭ በመላክ ለአገሬ የውጭ ምንዛሩ አፈራለሁ፣ ለእንዲህ ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ… በማለት ማቀድ ነው ራዕይ፡፡ እንደ አቶ ዘነበ ፍሬው “በየሁለት ዓመቱ አንድ ፋብሪካ ካላቋቋምኩ፣ ለዚህን ያህል ሰራተኞች የሥራ ዕድል ካልፈጠርኩ፣… ያመኛል” ማለት ነው እቅድ፡፡
የመጨረሻው የኢንተርፕረነሮች መመዘኛ በወረቀት ላይ የታቀደውን መሬት አውርዶ መተግበር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሶስቱ ነጥቦች የጎደለው ተነሳሽነቱ ነው፡፡ ሰው፤ ካስገደድከው ይነሳሳል፡፡ ተገዶና በፈቃደኝነት መነሳሳት ግን ለየቅል ናቸው፡፡ ከ85 በመቶ የገጠር ነዋሪ ውስጥ 17 በመቶ የሆነው አርብቶ አደር፣ ያለ እቅድ ዝም ብሎ ከብት ያረባል፡፡ ወደ ከተማ ስንመጣ አብዛኛው ሰራተኛም ያለምንም እቅድ እየሰራ ይኖራል፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው ለዓላማቸው የሚሰሩት፡፡ እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ሕዳሴ አስተማማኝ መሰረቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ውስጥ 3ሺ ችሎታ (ሀብት) አለ፡፡
እያንዳንዱ ሰው ውስጥ ይህን ያህል ሀብት ካለ ለምን ከድህነት አልወጣንም?
ኢትዮጵያ በጣም የተጎዳችውና የደኸየችው እያንዳንዱ ሰው 3ሺ፣ ሀብት፣ እውቀትና ችሎታ ይዞ መቃብር ስለሚወርድ ነው፡፡ የሰው ኃይል ከፍተኛ የልማት መሰረት ቢሆንም፣ በውስጡ የያዘውን እምቅ ሀብትና እውቀት፣ በዕቅድና በራዕይ ስለማይጠቀምበት ነው አገራችን የደኸየችው። ተነሳሽነት ካለና እያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለው ችሎታ ቢወጣ፣ ኢትዮጵያን አይደለም አፍሪካን ይለውጣል፡ታዲያ በዚህ እምቅ ሀብት ለመጠቀም ምን መደረግ አለበት?
ህብረተሰቡ ያለውን እምቅ ሀብትና ችሎታ እንዲጠቀም ለማድረግ፣ ማሳመንና ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ እኔ በኢንተርፕነረነት ማሰልጠን ስጀምር፣ ማንም አስገድዶኝ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የፈጠራ ሥራ ጥበብ ክፍተት መኖሩን አይቼ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የምትመራባቸው ፕሮግራሞች በውጭ ፈንድ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ የራሷ ፕሮግራም የላትም፡፡ ለኢትዮጵያ እጅግ በጣም ጠቃሚው የራሷ ፕሮግራም ነው፡፡ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶች የማያሳትፈው ለዚህ ነው። ይህን ወጣት ኃይል ለማሰልጠን ነው የተነሳሁት፡፡ ሀገር እንድታድግና እንድትለወጥ ተነሳሽነት፣ ማቀድና መፈፀም የኢንተርፕረነሮች መመዘኛ ነው፡፡
አንድ ሰው ራሱን ከብክነት ካዳነ፣ ለራዕይ ከኖረው፤ ራዕዩን ለማሳካት አስፈላጊውን እውቀት፣ ችሎታ፣ ጥበብ ከሸመተ፤ መቆጠብ ከቻለ፣ የቆጠበውን ካባዛ፣ ብዙ ሰዎች በዓላማው ስር እንዲሰሩ ካደረገ፣ ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ይህንን ባህል ነው መፍጠር ያለብን፡፡
በቢዝነስና በኢንተርፕረነር መካከል ልዩነት አለ?
አለ! ሁሉም ኢንተርፕረነሮች የቢዝነስ ሰዎች ናቸው፡፡ ሁሉም የቢዝነስ ሰዎች ግን ኢንተርፕረኖች አይደሉም፡፡ ኢንተርፕረነሮች ከፍ ሲል የጠቀስናቸውን መመዘኛ የሚያሟሉት ናቸው፡፡
ኢንተርፕረነር ለኪሳራ ኃላፊነት (ሪስክ) መውሰድ አይፈራም ይባላል፡፡ ለምንድነው?
አዎ! ይኼ እውነት ነው፡፡ ኃላፊነት መውሰድ፣ ከኢንተርፕረነር 10 ችሎታዎች አንዱ ነው፡፡ የመክሰርና የማትረፍ አማራጮች እንዳሉ ቢታወቅም፣ ገንዘብን፣ እውቀትን፣ ጉልበትን ለመሥራት ያሰቡት ነገር ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ የሚያጠራጥሩ ነገሮች ቢኖሩ እንኳ፣ ችግሩን አጥንቶና ተረድቶ፣ ግብአቶቹን (ገንዘብ፣ ጉልበት፣ እውቀት) ፍሬ በሚያፈራ ነገር ላይ በማዋል ለሚገኘው ትርፍም ሆነ ኪሳራ ኃላፊነት የመውሰድ ችሎታ ነው፡፡ ሲያተርፍ፣ መቶ ፐርሰንት ተጠቃሚ፤ ሲከስር ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተጐጂው ራሱ ኢንተርፕረነሩ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሥራ ከጀመራችሁ 13 ዓመት ሆናችሁ? ትምህርት አሰጣጡና የሕዝቡ አቀባበል እንዴት ነው?
እንደ አጀማመራችን ከዚህ መፍጠን ነበረብን። በ1993 ዓ.ም ጂኒየስ ማሠልጠኛ ስንከፍት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኢንተርፕረነሽፕ ማስተማሪያ መጽሐፍ ፈልገን አንድም ቦታ ማግኘት አልቻልንም ነበር፡፡ አሁን ግን ከውጭ እየገቡና በተለያዩ ቋንቋዎችም (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ…) እየተተረጐሙ ናቸው፡፡ በቀጣይ 5 ዓመት ደግሞ የበለጠ ይሆናል፡፡ እስካሁን የነበረው የመሬት ውስጥ (የመሠረት) ዕድገት ነበር፡፡
አገሪቱ ሥራ ፈጠራ አንዱ የኑሮ አማራጭ መሆኑን አውጃለች፡፡ ስለዚህ፣ ከመሬት በላይ ዕድገት ተጀምሯል ማለት ነው፡፡ ወጣቱን በሙያ እያሠለጠነች ነው፡፡ ወጣቱም ከቀሰመው ሙያ አንዱን መምረጥ አለበት፡፡ ኢንተርፕረነርሽፕን አንዱ የዕድገት አማራጭ ማድረግ ግዴታ ነው። አሁን ማሠልጠኛ ማዕከሎች እየተቋቋሙና በየኮሌጁ የፈጠራ ክህሎት ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ በማስተማሪያ ረገድም፣ ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) እንዲሁም የዩኤንዲፒ… ማስተማሪያዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችም ማስተማሪያ እያዘጋጁ ነው፡፡ እስካሁን የነበረው የዝግጅት ጊዜ ነው፡፡ አሁን ወደ ተግባር ስለተገባ፣ በቀጣይ አምስትና 10 ዓመት ዕድገቱ በእጥፍ ይጨምራል፡፡ በዚህ ሥልጠና የተማረ እንጀራ ጋጋሪ ይፈጠራል፣ ብዙ ሰዎች ይቀጥራል፣ እንጀራውን አሻሽሎ ወደ ውጭ አገር ይልካል፣ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡
ኅብረተሰቡ ስለ ሥራ ፈጠራ ጥበብ ያለው የግንዛቤ ደረጃ እንዴት ነው? እንዴትስ ነው የዕድገት አማራጭ የሚሆነው?
የኅብረተሰቡ ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ግን በመጠኑም ቢሆን እየጨመረ ነው፡፡ የሥራ ፈጠራ ጥበብ ፈጣን ለውጥ ከሚያመጡ ግብአቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን እጅግ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት በኅብረተሰቡ ውስጥ በጣም መስረፅ አለበት፡፡ እኔ፣ በውስጤ የነበሩትን የተሳሳቱ የሕይወት ቀመሮች (ፎርሙላዎች) ጠራርጌ ለማውጣት ብዙ ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡
ቤተሰብ፣ ት/ቤት፣ አካባቢ፣ ጓደኛ፣ ጐረቤት፣ በነበረው ሥርዓትና ወግ ቀርፀውኛል፤ መላው ኅብረተሰብም እንደዚያው ነው፡፡ በተለይ ያለፉት 40 ዓመታት (በተለይም የደርግ አገዛዝ) መጥፎ ሰንኮፍ ተክሎብን ነው ያለፈው፡፡ የዕድገት ፎርሙላችን ተናግቷል፡፡ የሠሩ ሰዎች፣ ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል፤ ያልሠሩ ሰዎች በቀላሉ ቤት አግኝተው እየኖሩ ነበር፡፡ ሁላችንም ስንፍናንና ድህነትን ተካፍለናል፡፡
አሁን ግን ግሎባላይዜሽን በአንድ በኩል፣ ሥራ አጥነት በሌላ በኩል፣ ስደትም ተጨምሮበት ማኅበራዊ ቀውስ አፍጥጦ መጥቷል፡፡ ይህችን በርካታ የሥራ ኃይል፣ ምንም ያልተነካ እምቅ ሀብት ያላትን አገር፣ ሐሳብ በመፍጠር፣ ብዙ በማስተማርና በማሠልጠን፣ በ40 ዓመታት እጅግ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣችው ሲንጋፖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሲንጋፖር ለዚህ የበቃችው፣ ከአሜሪካ በኮረጀቻቸው አራት ነገሮች ነው፡፡ እነሱም የፈጠራ ጥበብ (ኢኖቬሽን)፣ የሥራ ፈጠራ ጥበብ (ኢንተርፕረነርሽፕ) እጅግ የመጠቁ የሌሎች የፈጠራ ሞዴሎች ልምድ የመማር ጥበብ (ሜንደርሽፕ) እና የቀሰሙትን እውቀትና ልምድ ለጀማሪዎች ማስተማርና ማካፈል (ሱፐር ሜንደርሸፕ) ናቸው፡፡
ጃፓንም ያደገችው እንደ ሲንጋፖር የዕድገት ምሥጢሮችን ከአሜሪካ ኮርጃ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ብናይ፤ እኛ ለጃፓን ቡና እንሸጣለን፡፡ የጃፓን ሠራተኞች ቡናውን ሲያጠሩ፣ ሲያጥቡ፣ ሲቆሉ፣ ሲፈጩ፣ ሲያደቁ፣ አሽገው በመላው ዓለም ሲልኩ፣ ዓመቱን ሙሉ ፋብሪካ ውስጥ ናቸው፡፡ እነሱ ዓመት ሙሉ የቆዩበት የቡና ሥራ፣ ለእኛ የአንድ ወቅት የለቀማ ሥራ ነው፡፡ ቡና በጣም ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጉዞ የሥራ ዕድል ሲፈጥር፣ የቡና መገኛ ለሆነችውና በጥሬው ለሸጠችው አገር ምንም አልፈየደም፡፡ ቆዳው፣ ጥራጥሬው፣ የቅባት እህሉ፣… ተመሳሳይ ነው፡፡ የሥራ ፈጠራ ጥበብ ማለት፣ ኅብረተሰቡ እነዚህን የቡና የሥራ ሂደቶች በፋብሪካ ውስጥ በማሳለፍ እሴት ጨምሮ በመሸጥ፣ የውጭ ምንዛሪ ማፍሪያ ዘዴ ነው፡፡
አገራችን የሥራ ፈጠራ ጥበብ ባለማጐልበቷ፣ መደህየቷን ሳስብ በጣም ይቆጨኛል፡፡ ሌሎች አገሮች፤ አርቴፊሻል ነገር ሠርተው በመሸጥ ገቢ ያገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ አሜሪካ በቺካጐ ግዛት አንድ ረዥም ሕንፃ አለ፡፡ ሕንፃው፣ የቺካጐን ከተማና አካባቢውን ጥሩ አድርጎ ከማሳየት በስተቀር ሌላ ምንም የሚታይ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በቀን 25ሺ ጐብኚ ቢያንስ 40 ዶላር ከፍሎ ያንን ሕንፃ ይጐበኛል፡፡
እስያዊቷን ትንሽ አገር ሲንጋፖርን በዓመት 15 ሚሊዮን ሕዝብ ይጐበኛታል፡፡ እነዚህን ቱሪስቶች ለመሳብና ለማስተናገድ ከ12 ሚሊዮን በላይ መኝታ ያላቸው ሆቴሎች አሉ፡፡ ምንም የሚጐበኝ ተፈጥሯዊ ነገር የላትምኮ፡፡ ቱሪስቶች ወደዚያች በውሃ የተከበበች ትንሽ አገር የሚጎርፉት እንዴት እንዳደገች ለማየት፣ በባህሯ ላይ በመርከቦችና ጀልባዎች ለመዝናናት ነው፡፡ እጅግ በጣም የተማሩ አስጐብኚዎች ስላላት፣ ቱሪስቶች አይደናገሩም፡፡ የሚጠራጠሩት ባህል፣ የፀጥታ ችግር፣ ሌባ፣ ለማኝ፣ የለም፡፡ እኛ ግን ተፈጥሮ የቸረችን የዱር አራዊት፣ አዕዋፍ፣ ፓርኮች አባቶች ያቆዩልን ላሊበላ፣ ፋሲለደስ፣ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሀውልት፣ የሶፍ ኦማር ዋሻ፣… እያለን መሸጥ ባለመቻላችን በድህነት እንማቅቃለን፡፡ የሥራ ፈጠራ ጥበብ ተቋም ያለመኖሩ እጅግ በጣም ጐድቶናል፡፡ አገሪቷ ፀረ - ሙስና ኮሚሽን እስከ ቀበሌ ድረስ ከማቋቋም፣ የሥራ ፈጠራ ተቋም እስከ ቀበሌ ድረስ ብታቋቁም ኖሮ፤ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አያስፈልጋትም ነበር፡፡ ራዕይ ያለው ሰው እንዴት ከሚገነባት አገር ላይ ይሰርቃል? ከአገሩ የሚሰርቅ ራዕይ የሌለው ሰው ነው፡፡ ፖሊሱ፣ ፍ/ቤቱ፣ አልበቃ ብሎ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋም አሳፋሪ ነው፡፡ ጃፓን፤ ሲንጋፖር፤… የመሳሰሉ አገሮች ፀረ - ሙስና ኮሚሽን የላቸውም፡፡ ለአገር ዕድገት ትልቁ መሳሪያ ኢንተርፕረነርሽፕ ሆኖ ሳለ፣ እኛ ግን ፀረ ሙስና እናቋቁማለን፡፡
በመጨረሻም ዶ/ር ወረታው፣ እያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያለውን ወደ ምርትና አገልግሎት የሚቀየረውን ጥሬ የሀብት ምንጭ መጠቀም አለብን። እዚህ ላይ ብዙ እንድናነብ፣ ብዙ እንድንማር፣ ብዙ እንድናውቅ ነው ወገኖቼን የምጋብዘው፡፡ ይህ ጥሬ ሀብት ካደገ፣ ኢትዮጵያ ከማንም አገር በተሻለ አስተማማኝ ሁኔታ ፈጥና የምታድግና ለዜጐቿ የምትመች አገር ትሆናለች ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Read 4988 times