Saturday, 10 May 2014 12:31

ያልተጠቀምንባቸው እንቁ የቱሪስት መስህቦቻችን

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)

የውጫሌ ስምምነት የተፈረመበት ሥፍራ 30 ሚ. ብር የሚፈጅ ፕሮጀክት ከተቀረፀለት 6 ዓመት ቢሞላውም መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም

           ይስማ ንጉሥ ምንድነው? ብዬ ብጠይቅ፤ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከጉዳዩ ጋር አግባብ ካላቸው ጥቂት ሰዎች በስተቀር፣ የተቀረው ኢትየጵያዊ እምብዛም ያውቀዋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ስለ ይስማ ንጉሥ በሚዲያ ሲነገርም ሆነ ሰዎች ሲያወሩ ሰምተን ስለማናውቅ ነው፡፡
ይስማ ንጉሥ ትልቅ የታሪክ ስፍራ ነው - ለአድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌ ስምምነት የተፈረመበት ቦታ፡፡ ነገር ግን ትልቅ የቱሪስት መስህብ መሆን የሚችል ስፍራ ቢሆንም፤ እንደተቀሩት በርካታ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎች ሁሉ ትኩረት ስላልተሰጠው መሬት ላይ ያለ ስፍራ በመሆኑ ዳነ እንጂ መጥፋቱ አይቀርም ነበር፡፡
ስፍራው ድሮ ስሙ አቤይደብሮ ነበር፡፡ ታዲያ አሁን እንዴት ይስማ ንጉሥ ተባለ? የውጫሌው ውል ሲፈረም እቴጌ ጣይቱ ብጡል በስፍራው አልነበሩም፡፡ የተፈራረሙት አፄ ምኒልክና ኮነት ፒየትሮ አንቶኔሊ ነበሩ፡፡ ተርጓሚ ደግሞ ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሴ ነበሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱ የውጫሌው ውል አንቀጽ 17 ሲነበብላቸው፣ አራስ ነብር ሆኑ፡፡ ከዚያም ባለቤታቸውን አፄ ምኒልክን “ይስሙ ንጉሥ” አሏቸው፡፡ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፡፡ ከዚህ መሳይ ውል ግን ጦርነት እመርጣለሁ” በማለት ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ “ይስሙ ንጉሥ” የሚለው ሃረግም በሂደት ወደ “ይስማ ንጉሥ” ተለውጦ የውጫሌ ውል የተፈረመበት ስፍራ መጠሪያ ሆነ፡፡
ከአዲስ አበባ 400 ኪ.ሜ ተጉዘው ደሴ ከተማ ከደረሱ በኋላ፣ ወደ ወልዲያ ሲያቀኑ፣ ከደሴ 60 ኪ.ሜ ላይ ውጫሌ ከተማን ያገኛሉ፡፡ ከዚህች ትንሽ ከተማ 6 ኪ.ሜ ያህል ዝቅ ብሎ በአምባሰል ወረዳ በ 03 ቀበሌ፣ የሮቢት መንደርን አቋርጠው፣ ከአምባሰል ተራራ ግርጌ ባለው ትንሽ አምባ ላይ ይስማ ንጉሥን ያገኛሉ፡፡ ይህን ስፍራ ሲያዩ በጣም ያዝናሉ፡፡ ምክንያቱም አፄ ምኒልክና ኮንት ፒየትር አንቶኔሊ ስምምነቱን ሲፈራረሙ የተቀመጡበት ነው ከሚባል ድንጋይ በስተቀር አንዳች ምልክት እንኳ የለውም፡፡
ስፍራው በአካባቢው ገበሬዎች ስለሚታረስ ከ6 ዓመት በፊት ከግማሽ ሄክታር ያነሰ ነበር በዛፍ የተከለለው፡፡ በሚሊኒየሙ ሰሞን የአምባሰል ወረዳ አስተዳደር ገበሬዎች በማሳመን፣ ሦስት ከግማሽ ሄክታር ስፍራ መከለሉን ይናገራል፡፡ አስተዳደሩ፣ ይስማ ንጉሥን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ፣ ከ10-15 ዓመት እንኳ ተግባራዊ የሚሆን የማይመስል፣ የመዋኛ ገንዳ፣ መኝታ፣ ካፌና ሬስቶራንት፤ መዝናኛ፣… ለመገንባት ከ25-30 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት መቅረፁን ይገልፃል፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቱ ከተቀረፀ 6 ዓመት ቢሆነውም መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም፡፡
ዘንድሮ ሚያዝያ 25 ቀን 2006 ዓ.ም የውጫሌ ውል የተፈረመበት 125ኛ ዓመት በይስማ ንጉሥ በድምቀት ተከብሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት፣ የአካባቢው ጥቂት ሰዎች ከሚያስቡት በስተቀር ዕለቱ ተከብሮ እንደማያውቅ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ዓመት ትኩረት ያገኘው በአድዋ ተጓዦች ምክንያት ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡-
አምስት የአድዋ ተጓዦች፣ ከ1000 ኪ.ሜ በላይ በእግር ተጉዘው፣ የአድዋ ድል በሚከበርበት ዕለት የካቲት 23 ቀን 2006 በአድዋ ከተማ ለመገኘት፣ ከአዲስ አበባ ተነስተው ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ተጓዦቹ ውጫሌ ከተማ ሲደርሱ የተቀበሏቸው ሰዎች “ለአድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነው ውል የተፈፀመበት ይስማ ንጉሥ ከዚህ ነው” ይሏቸውና ያሳዩዋቸዋል፡፡ ተጓዦቹም ባዩትና በሰሙት ነገር በጣም አዝነው፣ የዘንድሮውን 125ኛ ዓመት አብረዋቸው እንደሚያከብሩ ነግረዋቸው ወደ አድዋ ጉዞ ቀጠሉ፡፡
ተጓዦቹም በገቡት ቃል መሰረት ሶሎራዮ በተሰኘው ድርጅታቸው አማካይነት ከተለያዩ ሚዲያዎች ጋዜጠኞችን ጋብዘው ይዘው በመሄድ ዕለቱን አምባሳደል ወረዳ አስተዳደሩና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በድምቀት አክብረዋል፡፡ በቀጣይም በየዓመቱ እንደሚገኙና ይስማ ንጉሥን የታሪክ መስህብ ለማድረግ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ህፃን ሽማግሌው፣ አሮጊት፣ ጎልማሳውና፣ ልጃገረዶች ተኳኩለውና አምረው፤ ኮበሌዎች ጎፈሬያቸውን አበጥረውና ዱላ ይዘው፣ በመተጫጫ ወቅት የሚዘፍኑትን እሆለሌ እየተጫወቱ ዕለቱን አክብረውታል፡፡
የአካባቢው ነዋሪ ይስማ ንጉሥ እንዲለማ፣ ቱሪስቶች እየመጡ የሚጎበኙት ታሪካዊ ስፍራ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ፍላጎቱንም ከሮቢት መንደር እስከ ስፍራው ያለውን ጥርጊያ መንገድ በጉልበቱ በመስራት አሳይቷል፡፡ ይህ ስፍራ ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ ለቱሪስቶች ትልቅ መስህብ ነው፡፡ አካባቢው ሌሎችም ታሪካዊ ቦታዎች አሉት፡፡ አፄ ቴዎድሮስ “እጄን ለእንግሊዝ አልሰጥም” ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተው የወደቁባት እንዲሁም በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የነበረችው መቅደላ አምባ፣ የአፄ ቴዎድሮስ መቃብርና ሁለት መድፎች የሚገኙበት፣ የአፄ ቴዎድሮስ ጄነራል ገብርዬ፣ ከጄነራል ናፒየር ጋር የተዋጋበት የእሮጌ መስክ የሚገኝበት ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በኦሪት ጊዜ መስዋዕት ይደረግባት እንደነበር የሚነገርላት ታሪካዊቷ ተድባበ ማርያም፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል የሚገኝባት ግሼን ደብረ ከርቤ፣ በሀገራችን የመጀመሪያው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የነበረውና አባ ተክለ ሃይማኖትና አባ ኢየሱስ ሞሃ የተማሩበት ሐይቅ ገዳም፣ ከ40 በላይ መፃሕፍት የፃፉት የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም፣ ቦሩ ሜዳ የሚገኘው አበራ ሥላሴ፣… በይስማ ንጉሥ አካባቢ የሚገኙ በመሆኑ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራባቸው ማለፊያ የቱሪስት መስህብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የውጫሌ ውል የተፈረመበት 125ኛ ዓመት በይስማ ንጉሥ ሲከበር የጉዞ አድዋ መሪ፣ ጋዜጠኛና የፊልም ባለሙያ ብርሃኔ ንጉሤ ባደረገው ንግግር፤ “አኒማል ፋርም የተሰኘውና የሌሎች በርካታ መጽሐፍት ደራሲ እንግሊዛዊው ጆርጅ ኦርዌል ህንድ ውስጥ አንድ ሌሊት ያደረባት ክፍል (አልቤርጎ) የቱሪስት መስህብ ሆና፣ በብዙ ቱሪስቶች ስትጎበኝ፣ ሦስት የኢጣሊያ ጄነራሎች የሞቱበትና አንዱ ጄነራል የተማረከበት እንዲሁም የአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነችው ይስማ ንጉሥ፣ የቱሪስት መስህብ አለመሆን አስገራሚ ነው” ብሏል፡፡    

Read 6296 times