Saturday, 10 May 2014 12:21

አሁን የሚያዋጣው ከቻይናው CCTV ጋር መወዳጀት ብቻ ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(10 votes)

ጆን ኬሪ “ታሳሪዎቹን ሳያስፈቱ አይመለሱም” ብሎ የተወራረደው 5ሺ ብር ተበላ
ተጠያቂነትን መሸሽ የለበትም (መንግስት ነዋ!)

አዲስ አበባና በዙሪያዋ የኦሮሞ ከተሞችን በማካተት የተዘጋጀው የጋራ ማስተር ፕላን፣ ለተቃውሞ መነሻ ይሆናል ብዬ ለማሰብ ያዳግተኛል፡፡ (ሊሆን አይችልም ግን አልወጣኝም!) ለምን መሰላችሁ? አብረን እንደግ እኮ ነው የተባለው፡፡ ወይስ ተቃዋሚዎቹ ለኛ ያልደረሰን መረጃ ደርሶአቸው ይሆን? (አሻጥር ቢጤ ማለቴ ነው!) ግን ደግሞ መንግስት ወይም የአዲስ አበባ መስተዳድር አሻጥር ምን ይሰራለታል? (መንግስት በራሱ ላይ አሻጥር ይሰራል እንዴ?) እንደሚባለው፣ በልማት ስም ከኦሮምያ ከተሞች መሬት ወይም የፖለቲካ አስተዳደር ቆርጦ ለመውሰድ ቢያስብ እንኴን ህገ-መንግስቱ አይፈቅድለትም፡፡ (የምናወራው ስለሶማሊያና ኢትዮጵያ መሰለኝ እኮ!)
የሆኖ ሆኖ ግን የጋራ ማስተር ፕላኑን የሚቃወሙ የክልሉ ተማሪዎች፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ባካሄዱት ተቃውሞ፣ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ (ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን!) መንግስት እንደሚለው እንግዲህ… ረብሻው የተቀሰቀሰው በሁለት መንስኤዎች ነው፡፡ በውጭ የፖለቲካ ድርጅቶች ድብቅ አጀንዳ እና የጋራ ማስተር ፕላኑን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ በሌላቸው ተማሪዎች በተፈጠረ መደናበር ወይም መደናገር! መንግስት በመንስኤነት የጠቀሳቸውን ጉዳዮች ሳንጠራጠር እንቀበላቸው ብንል እንኳ ጨርሶ ተጠያቂ ከመሆን አይድንም-መንግስት፡፡ (ተጠያቂነትን ማን ይወዳል?!) ግን እኮ መንግስት መሆን በራሱ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ሌሎች ወገኖች ሊጠየቁ ቢችሉም ሥልጣን የያዘው ኢህአዴግ ነውና የበለጠ ተጠያቂው እሱ ነው ባይ ነኝ፡፡ በረብሻው፣ በሞቱት ሰዎች፣ ሁከቱን ለማርገብ በተጠቀመበት ዘዴ ወዘተ… ይጠየቃል፡፡ ተጠያቂነት መቼም ቢሆን አይቀርለትም፡፡ የመንግስትነት ዕዳ ነዋ!! እናም መንግስት ቀደም ብሎ የቤት ስራውን በአግባቡ ተወጥቶ ነበር ወይ? የሚለውን መጠየቅ የአባት ነው፡፡ ግን የቤት ስራው ምንድነው? ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የክልሉ ተማሪዎችና ነዋሪዎች፣ በጋራ ማስተር ፕላኑ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ ጥርጣሬዎችንና ብዥታዎችን ማስወገድ ነው፤ የቤት ሥራው፡፡ ሁሌም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዓይነት ሙሉ ድጋፍና ተቀባይነት አገኛለሁ ብሎ መደምደም አያዋጣም፡፡ (ያውም ያለ ጥናት በዳበሳ!)
እኔ የምለው… ችግሩ ከተከሰተ በኋላ በኢቴቪ የምንሰማቸው ተከታታይ የባለስልጣናት ማብራሪያ ትንሽ የዘገየ አይመስላችሁም? (አሁን አያስፈልግም አልወጣኝም!) የጋራ ማስተር ፕላኑን ይፋ ለማድረግ ከመጣደፍ በፊት፣ ከህዝብ ጋር የሚካሄደውን ውይይት ማስቀደም አይገባም ነበር? የውስጥ ኃይሎችን ተፅዕኖም ሆነ የውጭ ሃይሎችን ግፊት እንዲሁም መንግስት በወሬና በአሉባልታ ሰበብ ተፈጠሩ ያላቸውን መደናበሮች ማስቀረትስ አይቻልም ነበር? ኢህአዴግ የቤት ስራውን በአግባቡና በወቅቱ ሰርቶ ቢያጠናቅቅ ኖሮ ይቻል ነበር፡፡ (ከኦህዴድ ባላውቅም!)
ሌላም ጥያቄ አለ፡፡ ሰው ሳይሞት ረብሻውን መግታት አይቻልም ነበር ወይ? ሌላው ቢቀር የሟቾችን ቁጥር መቀነስስ? (የመጠየቅ መብት አለን ብዬ እኮ ነው!) በ97 ዓ.ም ከምርጫው ቀውስ ጋር ተያይዞ ለተገደሉት ዜጎች፣ በኋላ ላይ ከመንግስት የተሰጠው ምላሽ፣ “የሰለጠነ አድማ በታኝ ፖሊስ ስለሌለን ነው” የሚል እንደነበር አስታውሳለሁ (ተሳሳትኩ እንዴ?) በነገራችሁ ላይ ረብሻው በአድማ በታኝ ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋል ይችል ነበር ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሆኖም የሰለጠነና የተደራጀ አድማ በታኝ ፖሊስ አለን ወይ?  ብሎ መጠየቅ ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ሳይጠቅመን አይቀርም (እስካሁን ካልታሰበበት ማለቴ ነው!) ይኸውላችሁ.. ተቃውሞ ወይም ረብሻ ሲነሳ የሰው ህይወት ሳይጠፋ መቆጣጠር የሚቻልበትን ማናቸውንም መላዎች መዘየድ ምንጊዜም የመንግስት የቤት ሥራ ነው፡፡
እንዴ… ስንቱን አወዛጋቢ ህግና አዋጅ ከባህር ማዶ ኮረጅኩ ብሎ ኩምጭጭ ይል የለ? ለምን የሰዎችን ሞት የሚያስወግድ ወይም የሚቀንስ የረብሻ መቆጣጠርያ ስልቶችንም አይኮርጅም? (መኮረጅስ ለዚህ ለዚህ ነበር!)
ወደ ተቃውሞው ስንመጣ ግን እውነት የጋራ ማስተር ፕላኑ ተቃውሞ የሚያስነሳ ነውን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ የአፍሪካ መዲና የምትባለው ሸገር፣ በዙሪያዋ ካሉ የኦሮምያ ልዩ ዞን ከተሞች ጋር በልማት ብትተሳሰርና በጋራ ቢበለፅጉ ችግሩ ምንድነው? መቼም አዲስ አበባ እንደ ሱዳንና ኤርትራ ጎረቤት አገር አይደለችም (ያልሰማነው ነገር ካለ ይነገረን!) ኢህአዴግ እንደሚለው፤ ይሄ ሁሉ ድካምና ልፋትስ የማታ የማታ አንዲት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አይደል እንዴ? አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር! በዚህ አጀንዳ ላይ ጥልቅ ውይይትና ሃሳብ ማንሸራሸር የግድ ይላል፡፡ ልማቱና እድገቱ እንደሆነ መቀጠሉ አይቀርምና!
እኔም እንደመንግስት ሰበብ ልፍጠርና፣ የዚህ ተቃውሞ ወይም ረብሻ ቀስቃሾች መሬት ሲቸበችቡ የከረሙና ይሄ ጥቅማቸው እንዳይጎድልባቸው የሰጉ አንዳንድ ባለስልጣናት ቢሆኑስ? (የግል ጥርጣሬዬ እኮ ነው!) ለነገሩ እኮ… የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች አንዳንድ ከንቲባዎችና ኃላፊዎች ከመሬት ዘረፋ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው መያዛቸውና ወህኒ መውረዳቸው በሚዲያ መዘገቡ ይታወቃል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ጉዳዩ (የጋራ ማስተር ፕላኑን ማለቴ ነው!) ውይይት ይሻል፡፡ የአመለካከት ለውጥም ይፈልጋል፡፡ (ኦህዴድ ውስጥ 1 ለ 5 አልተጀመረም እንዴ?)
አሁን ደግሞ እስቲ ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴና የእስር ሁኔታ ትንሽ እናውጋ፡፡ ሃሜትም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ያለ ቡና ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “35 የሰማያዊና የአንድነት አባላት ታሰሩ” የሚል ዜና አነበብኩ፡፡ (አገር ሰላም አይደለም እንዴ?) ሁለትና ሶስት የተቃዋሚ አባላት መታሰራቸው ሲገርመን 35?? (አደገኛ ነውጥ የተፈጠረ እኮ ነው የሚመስለው!) ሁሉም ደግሞ ታሰሩ የተባሉት ፈቃድ ላገኙበት ሰላማዊ ሰልፍ በራሪ ወረቀት ሲበትኑ ነው - በዜናው ላይ እንደተዘገበው፡፡ ቅስቀሳ ማድረግ ወይም በራሪ ወረቀት መበተን ባልተፃፈ ህግ ተከለከለ እንዴ? (ከተከለከለም ይነገረና!) ይኸውላችሁ… የሰማያዊም ሆነ የአንድነት ፓርቲ አባልም ደጋፊም አይደለሁም (ማን ተናዘዝ አለህ አትሉኝም?) የፓርቲ ደጋፊ ልሁን ብልማ… የመጀመሪያ ምርጫዬ ኢህአዴግ ነበር (ልማታዊ ነዋ!) ግን ከፓርቲዎች ጋር ኮከቤ አይገጥምም፡፡
ሃቁን ልንገራችሁ አይደል… ወደፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የመብት ተሟጋች የመሆን ህልምና ራዕይ ስላለኝ ነው ጉዳያቸውን በትኩረት የምከታተለው፡፡ በዚያ ላይ እንጀራዬ እንደሆነ ይታወቃል - ፖለቲካ መፃፍ፡፡ እናም አትፍረዱብኝ ለማለት ያህል ነው፡፡ ግን ደግሞ ለገዢው ፓርቲ አበክሬ ልነግረው የምፈልገው… በሆነው ባልሆነው የተቃዋሚ አባላትን እየያዙ ማሰር፣ የመንግስትን ብሎም የአገርን መልካም ገፅታ ከማበላሸት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ነው፡፡ በኢህአዴግ በኩል የተቃዋሚ አባላትን በማሰርና በማዋከብ አርፈው እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ የሚል ግምት ካለ፣ በከባዱ ነው የተሸወደው፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እኮ መታሰርን እንደዓላማ ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ለምን ሲባሉ? “እኛ አገር እንደ Hero የሚታየው የታሰረ ነው” ባይ ናቸው፡፡ (የባሰ አታምጣ አሉ!)
በነገራችሁ ላይ የቻይናው ጠ/ሚኒስትር አገራችንን መጎብኘታቸው አሪፍ ነው፡፡ ከዲፕሎማሲም ትስስር ባሻገር፣ የኢኮኖሚ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ ስለማስብ እኮ ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በኩል ግን ኢምንት ለውጥ እንደማያመጣ ይታወቃል (ቻይናን እያወቃችኋት!) እናም ለአውራው ፓርቲያችን የምመክረው (ባይሰማኝም መምከር መብቴ ነው!) የፖለቲካ ስርአት ጨርሶ ከቻይና ለመኮረጅ እንዳይዳዳው ነው፡፡ (ኮሙኒዝም ምኑ ይኮረጃል!)
እርግጥ ነው ዳቦ ያስፈልገናል፡፡ እርግጥ ነው ድሃ ህዝቦች ነን፡፡ ግን ከአንደኛው በፊት ሌላኛው ይቅደምልን ብለን አናውቅም፤ ወደፊትም አንልም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ሁለቱንም እኩል ነው የተራብነው፡፡ ሁለቱንም እኩል ነው የምንፈልጋቸው-ዳቦውንም ኦኮኖሚውንም (የፖለቲካውንም የኢኮኖሚውንም ነፃነት ማለቴ ነው!) እርግጠኛ ነኝ… የታላቋ ኮሚኒስት ቻይና ጠ/ሚኒስትር፤ በእንዲህ ያለው ጉብኝት ከአንደበታቸው ፈፅሞ የማይወጡ ቃላት ቢኖሩ፣ የዲሞክራሲ ሥርአትና የሰብዓዊ መብት አከባበር የሚሉት ናቸው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ግን ቀንደኛ አቀንቃኝ ናቸው (እቺንስ ማን አየባቸው!) እኔ የምለው … 3 ጋዜጠኞችና 6 የ“ዞን 9” ብሎገሮች መታሰርን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ (ታሳሪዎቹን ሳያስፈቱ አይመለሱም ብሎ የተወራረደ ወዳጄ 5ሺ ብር ተበላ!) በበኩላቸው፤ ዲሞክራሲና ዕድገት አይነጣጠሉም ብለዋል፡፡ ጎሽ! እኛም እንዲነጣጠሉብን አንፈልግም፡፡ ዳቦና ዲሞክራሲ እኩል እንፈልጋለን፡፡ ደሞም እኮ ኢህአዴግ ለበርካታ ዓመታት የታገለው መጀመሪያ ዳቦ፣ በኋላ ነፃነትን ለማስፈን አይደለም፡፡ እንደውም በዋናነት የታገለው እኮ ለመብትና ለነፃነት ነው (ከቻይና ጋር እየዋለ፣ ካልዘነጋው በቀር!) ከምሬ እኮ ነው… ቻይና የራሷ ታሪካዊና ባህላዊ ዳራ ስላላት፣ የእሷን ነገር ኮፒ ፔስት ማድረግ አይመከርም ብቻ ሳይሆን ጎጂም ነው፡፡ ከእሷ ኮፒ ፔስት ማድረግ… የሥራ ባህልን፣ የባቡር መስመር ዝርጋታን፣ ፋብሪካ ማስፋፋትን ወዘተ… ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ቻይና ከምዕራባውያኑ ይልቅ ለአውራው ፓርቲ ትመቻለች (እጅ ጥምዘዛ አታውቅማ!)
ዲሞክራሲያችሁ ምን ያህል ጎለበተ፣ የፕሬስ ነፃነት ተከብሯል?… ወዘተ ጣጣ ፈንጣጣ አታውቅም፡፡  እኔ የምፈራው ግን ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የታገለለትን ዓላማ ቻይና እንዳታስቀለብሰው ነው፡፡ በክፋት እኮ አይደለም፡፡ “የእኔን መንገድ ሞክሩት፤ ያዋጣል” በሚል ቀና ስሜት! ምን ጥርጣሬ እንደገባኝ ታውቃላችሁ? 30 ምናምን የተቃዋሚ አባላት፣ እንዲሁም 9 ጋጤኞችና ብሎገሮች  በራሪ ወረቀት በተናችሁ ተብለው የታሰሩት፣ ቀጥተኛ ባልሆነ የቻይና ተፅዕኖ ቢሆንስ? (እስራትና አፈና የኮሙኒዝም መለያ ነዋ!) በነገራችሁ ላይ… የእሁዱ የአንድነት “የእሪታ ቀን”፤ በብዙ መልኩ ለየት ያለ ሲሆን የብዙዎችንም ትኩረት ስቧል፡፡ አንዳንዶች የፈጠራ ጥበብ የታከለበት የመጀመርያው የተቃውሞ ሰልፍ ነው ሲሉ አድንቀውታል፡፡ “ከተሰለቸው ሰልፍ በስንት ጣዕሙ” ያሉም አልጠፉም፡፡ ሰልፉም ያለረብሻና ያለ እስር በሰላም የተጠናቀቀው በፈጠራ የታጀበ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ እናላችሁ… በመብራት፣ በውሃ፣ በኔትዎርክ፣ በታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች የመብት ጥያቄ ላይ ያተኮረው የእሪታ ቀን፤ ለአንዳንዶች ድራማ እንደመሰላቸው ሰምቻለሁ-የጎዳና ትርኢት፡፡ ምን ያድርጉ? የተገለበጠ እንስራ ያዘለች ሴት፣ ቱታ የለበሱ ወጣቶች፣ የጠቆረ አምፑል ወዘተ… በሰልፉ ላይ ለተቃውሞ መግለጫነት ውለዋል፡፡ ባለ እንስራዋ ያስፈለገችው የውሃ እጥረትን ለመግለፅ ነው-በተገለበጠ እንስራ፡፡ ጥቁሩ አምፑል ጨለማን ማመላከቻ ነው-የመብራት መጥፋትን፡፡ በተረፈ ደግሞ “እኔም ዞን 9 ነኝ!”፣ “እኔም ጋዜጠኛ ነኝ!” “እኔም ርዕዮት ዓለሙ ነኝ” ወዘተ የሚሉ ቲሸርቶችን የለበሱ ሰልፈኞችም ተሳትፈውበታል፡፡ የሙስሊም ሻርፕ የተከናነቡ ሰዎችም አፋቸው ተለጉሞ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ታይተዋል- የመናገር መብታችን ታፍኗል እንደማለት፡፡
ይሄንን Creative Protest (በፈጠራ የታገዘ ተቃውሞ) በፎቶና በወሬ ካየሁና ከሰማሁ በኋላ፣ አንድነት ለምን አዳዲስ የተቃውሞ ሰልፎችን  (ሰላማዊ የበለፀጉ ማለቴ ነው!) በተቃውሞ ባህል የዳበረ ልምድ ካላቸው የምዕራብ አገራት አይኮርጅም ስል አሰብኩ፡፡ ወዲያው ደግሞ ስጋት ገባኝ፤ “ተቃውሞ ለመኮረጅ ባህር ማዶ የሄዱት በምስጢር ነው” ተብለው የክስ ቻርጅ ቢቆረጥላቸውስ የእስረኛ አባላቱን ቁጥር ማብዛቱ ነው የሚሆነው!)
ዘመኑ በእጅጉ ጥንቃቄን የሚፈልግ ሆኗል፡፡ (ከዓለም ልንፋታ ነው እንዴ?) ለምን መሰላችሁ? ትላንት ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ነው ተብሎ ከመንግስታችን ጋር “ሲሞዳሞድ” የነበረ ተቋም፤ በአንድ ጀንበር “አሸባሪ ነው” ሊባል ይችላል፡፡ (ተብሏል አልወጣኝም!) እናም መረጃዎች ግልፅ እንዲሆኑልን እንጠይቃለን፡፡ የቀለም አብዮተኞች የትኞቹ ናቸው? ነውጠኞችስ? የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች አሸባሪዎችስ? የአሻንጉሊት መንግስት ማቋቋም የሚሹትስ? (ካሉ ማለቴ ነው!) እንዴ… ሌላ መዘዝ ካለው እኮ ስልጠናውንም፣ ጉብኝቱንም፣ ትውውቁንም፣ የልምድ ልውውጡንም፣ ወዘተ… እርም ልንለው እንችላለን፡፡ (አንዳንዶች መጪው ምርጫ የፈጠረው ትርምስ ነው የሚሉን አልተቀበልኩትም!) ለማንኛውም ግን ሌላውን ሁሉ ትተን ለምን ከቻይናው ቴሌቭዥን CCTV ጋር አንወዳጅም?! (ጎመን በጤና አሉ!) እነቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስ፣ አሶሼትድ ፕሬስ፣… አሸባሪዎች ናቸው ሰላማዊ! (ድሮስ … ኒዮሊበራሎች አይደሉ?!) ደጉን ጊዜ ያምጣልን! (ለጋዜጠኞች ብቻ አይደለም!)

Read 4698 times