Saturday, 10 May 2014 12:19

ብትናገር ያምናውን፣ ብትፈትል አንድ ልቃቂት (ተተዛረበት ናይዓሚ፣ ተፈተለት ፋእሚ)

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አንድ የኦሮሞ ተረት እንዲህ ይላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ ዘመቻ ይሄድ ኖሮ ቤተሰቡንና ቤት ንብረቱን ሁሉ ለጎረቤቱ አደራ ብሎ፤ ቀዬውን ተሰናብቶ ወደ ጦር ሜዳ ሄደ፡፡
ጦርነቱ ከሁለት ዓመት በላይ ፈጀ፡፡ ብዙ ሰው ከወዲህ ወገን ሞተ፡፡ ከጠላትም በኩል እንደዚሁ ስፍር ቁጥር የሌለው ሰው አለቀ፡፡ ይሄንን ሁሉ አልፎ ያ ዘማች ተርፎ ወደ መንደሩ ተመለሰ፡፡
ገና ወደ ቤቱ ሳይደርስ መንገድ ላይ ያገኘውን ሰው ሁሉ፤
“መንደራችን ሰላም ነው ወይ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
“ሰላም ነው፡፡ ምንም የደረሰ ነገር የለም” ይለዋል አንዱ፡፡
ሙሉ በሙሉ ለማመን ስለሚቸገር ሌላውን ሰው፤
“ጎበዝ፤ መንደራችን እንዴት ነው? ሰዉስ እንዴት ከረመ” ሲል ይጠይቃል፡፡ ሌላውም ሰውዬ፤
“ኧረ አማን ነው፡፡ ምንም የተፈጠረ ችግር የለም” ይለዋል፡፡
እንዲህ እየጠየቀ ሲጓዝ በመጨረሻ ያንን ቤተሰቡንና ቤት ንብረቱን አደራ የሰጠውን ጎረቤቱን አገኘው።
ተቃቅፈው ተሳሳሙ፡፡
“እንዴት ነህ?” አለ ዘማች፡፡
“ደህና!” አለ ጎረቤት፡፡
“ሁሉ አማን፣ ሁሉ ደህና?”
“ሁሉም አማን ነው፡፡ ሰላም ነው!”
“እርግጠኛ ነህ? ምንም ችግር አልገጠማችሁም?”
“ኧረ ምንም፡፡ ያ ያንተ ውሻ ብቻ ከመሞቱ በስተቀር ምንም የሆነ ነገር የለም”
“ውሻዬ እንዴት ሞተ?”
“አጥንት ሲግጥ አንቆት ሞተ”
“የምን አጥንት?”
“አንድ የታረደ በሬ ነበር የሱን አጥንት ሲበላ አንቆት ነው፡፡”
“በሬው ለምን ታረደ?”
“ለባለቤትህ አርባ”
ዘማች ኡኡታውን ለቀቀው፡፡ ጮኸ፡፡ ዕንባው ተንዠቀዠቀ፡፡ ጎረቤትዬው አባብሎ ቀና አደረገውና፤
“እቤት ስትደርስ ያደርስህ የለም ወይ? በቃ ዝም በል” አለውና መንገድ ይጀመራሉ፡፡
ከዚያም መቼም ባል የሚስቱን አሟሟት ማወቅ አለበትና፤
“ለመሆኑ ምን ሆና ሞተች?” አለው ፡፡
“በወሊድ ነው የሞተችው” አለ ጎረቤት፡፡
“በወሊድ?!” አለ ባል፣ በድንጋጤ፡፡
“አዎ በወሊድ ነው”
“ከማን አርግዛ?” አለ ባል፤ ዘመቻ የቆየው ሁለት ዓመት መሆኑን እያሰላሰለ፡፡
“ሰው ካንተ ነው ይለኛል፤ እኔ ግን እኔ አይደለሁም እላለሁ!” አለው፡፡
*       *       *
ዛሬ በሀገራችን፤ ትንሽ መገለቻዎች፣ የትልቁ ስዕል ምልክቶች ናቸው! ማናቸውንም የነገር አካሄድ ሥረ-መሰረቱን ደብቀን የምንጓዝበት ከሆነ፤ ውጤቱ አያምርም፡፡ እያንዳንዱ የተከማቸ ነገር ድንገት አንድ ጊዜ ለመፈንዳት ቅንጣት ሰከንድ ትበቃዋለች፡፡ የTipping Point (ፍንዳታዋ ነጥብ እንደማለት) ደራሲ ነገሩ እየደለበ ይሂድ እንጂ ለመፈረካከስ አንዲት አጋጣሚ ትበቃዋለች ይላል፡፡ ዕውነት ነው፡፡ ውስጥ ውስጡን የተጠራቀመ፣ የተነፋፋ ምሬት በየት እንደሚፈነዳ አይታወቅም፡፡ ምሬት ተጠራቅሞ ወደ አንድ ቦይ ሳይገባ በፊት ካልገደቡት፤ ውሎ አድሮ ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግር ሊሆን ይችላል፡፡
ብዥታና ዳፍንተኝነት አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው፤ ህሊናዊው (subjective) ሁኔታ ሲዘገይና ዕሙናዊው ሁኔታ (objective) እጅግ ሲቀድም ነው፡፡ ካለንበት ሁኔታ ተነስተን ስናስበው፣ ይህ ክስተት የሚመጣው፤ ምሬቱ እጅግ ሲበረክትና መፍትሔው እጅግ ሲዘገይ ነው ማለት ነው፡፡
የአሜሪካው የሲቪል መብቶች ትግል መሪ “እምቢ ብሎ መነሣት፣ ያልተሰሙ ድምፆች ቋንቋ ነው” ይለናል፡፡ ይህን ልብ እንበል፡፡ ትምህርት የረጋ አካባቢ፣ የተቀደሰ መንፈስና ንፁህ ልቦና ይፈልጋል፡፡ ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን፤
“ለእኔ፣ በመርህ ደረጃ፤ ትምህርት፤ ከፍርሃት፣ ከጉልበት እና ከአርቴፊሻል ሥልጣን ጋር የሚሰራ ከሆነ የመጨረሻ አስከፊ ነገር ነው፡፡ ይህ ዓይነት አያያዝ ድምፅን ያኮስሳል፣ ስሜትን ያቀዝዛል፣ ቅንነትንና የተማሪዎችን ሙሉ ልብ (ልበ-ሙሉነት) ያመነምናል፡፡ በዚህ ሁኔታ የምናፈራውም፤ እጁን የሰጠና ተምበርካኪ ትውልድ ነው” ሲል ጠቅልሎ ያስቀምጠዋል፡፡
በክፍል የምንማረውን ያህል ከህይወትም እንማራለን፡፡ ከአካባቢም እንቀስማለን፡፡ ስለሆነም ዕድሜ ልካችንን ተማሪዎች ነን፡፡
ነገር እስኪባባስ፣ እስኪጎመዝዝና እስከሚመር ተብሎ ታይቶ፤ ወደ ፍንዳታ ደረጃ እስከሚደርስ ማየት፤ በኋላን በመካያው ሰበብና ምክን ፈጥሮ “የአብዬን እከክ ወደምዬ ልክክ፤ አያዋጣም፡፡
ሁሉም ተማሪ የሰከነ፣ የተቀነባበረ፣ የበሰለ መልክ መያዝ ይገባዋል፡፡ ሁሉን ነገር በጥሞና መመርመር የመማር ዋንኛው አንጓ ነው፡፡ ግራ ቀኙን ማየት ክፉ ደጉን መለየት የማንኛውም ጉዞ መሰረታዊ መነሻ ነው፡፡ ዊሊያም አስበር የተባለ ካናዳዊ ሐኪም ስሞት መቃብሬ ላይ እንዲፃፍ የምፈልገው፤ ከዚህ በታች ያለው ነው፡-
‹እዚህ ለመድረስ ነው እንደዚያ የተጣደፍነው?!›
ጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ በማዕረግ ዲግሪ ለተሸለሙት የዬል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባደረጉት ንግግር፤ “የክብር ተመራቂ፤ ተሸላሚ እና የማዕረግ ተሸላሚ ለሆናችሁ ተማሪዎች እንኳን ለዚህ አበቃችሁ እላለሁ። በ‹ሲ›(ር) የተመረቃችሁም አይዟችሁ፤ እናንተም እንደኔ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን ትችላላችሁ” ብለዋል፡፡
ለሁሉም ተማሪ አገሪቱ እኩል እድል ትሰጣለች ነው ቁም ነገሩ፡፡ እኛስ? ብሎ መጠየቅ እንግዲህ የእኛ ፋንታ ነው፡፡ በየትም አገር፣ በየትም ጊዜ፤ ለሁሉ በሽታ አንድ ዓይነት መድኃኒት የለም ‹ፓናሲያ› እንዱሉ፡፡ ለሁሉ ችግር አንድ ብቸኛ መፍትሄም የለም፡፡ ሁሉም መንገድ ወደ አንድና አንድ ሰፈር ብቻ አያደርስም። የጉዳዮቻችን አፈራረጅ እንደወቅቱና ሁኔታው ተጢኖ ሳይሆን፤ ሁሉም በተለመደው መንገድ መሆኑ አሳሳቢ፡፡ “ይሄማ በዚህ በዚህ ሰበብ የመጣ ነው”፣ “ይሄማ ከጀርባ ይሄ ይሄ ነገር ቢኖረው ነው፡፡ ይሄማ ከተለመዱት ሰዎች ውጪ አይሆንም” (“Round up the usual suspect” እንዲል፤ ቃለ-ፊልም)፤ እያልን ብዙ መንገድ ለመሄድ አይቻለንም፡፡ በለሆሳስ እናስብ፡፡ ዙሪያ-መለስ ዕሳቤ ይኑረን። አገርና ህዝብ በማይጎዳ ፍትሀዊ ጎዳና እንጓዝ፡፡ አለበለዚያ “ብትናገር ያምናውን፣ ብትፈትል አንድ ልቃቂት” የሚለው የትግሪኛ ተረት እፊታችን ይደቀናል፡፡

Read 5149 times