Saturday, 03 May 2014 12:43

አሰፋ ተክሌ የግጥምና የታሪክ ማኅደር!

Written by  ቢተው ዘገየ
Rate this item
(1 Vote)

ክፍል አንድ
የተወደዳችሁ አንባቢዎቼ! በዚህ ጽሑፌ የግጥምና የታሪክ መድበል ስለሆኑ አንድ አባት አስነብባችኋለሁ፡ ፶ አለቃ አሰፋ ተክሌ ይባላሉ፡፡ የታሪክ መጻሕፍትን ተከታትለው ያነብባሉ፡፡ ሥነግጥም ደግሞ ተሰጥኦዋቸው ነው፡፡ ራሳቸው ይገጥማሉ፡፡ ጊዜና ወቅትን መሠረት አድርገው የተገጠሙትንም አይረሱም፡፡ በልጅ ኢያሱ፣ በንጉሥ ተፈሪ፣ በንጉሥ ሚካኤል ወቅት ከቅራኔ የተነሣ የተነገሩ ግጥሞችን አንደዳዊት ይደግሟቸዋል፡፡  
ተወልደው ያደጉት እንደቀድሞው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት ወረኢሉ አውራጃ ካቢ ወረዳ ልዩ ስሙ መጐሳ መንደር ነው፡፡ የተወለዱት ታኅሣሥ 12 ቀን በ1928 ዓ.ም በዕለተ ሚካኤል ነው፡፡ እርሳቸው በታኅሣሥ ወር 1928 ዓ.ም እንደተወለዱ፣ በሚያዝያ ወር 1928 ፋሽስት ኢጣሊያ ሀገሪቱን ተቆጣጠረች፡፡
የ፶ አለቃ አሰፋ ተክሌ ወላጆች ይተዳደሩ የነበሩት በግብርና ነው፡፡ 10 ዓመት ሲሆናቸው እዚያው ወረኢሉ ጊዮርጊስ የቤተክህነት ትምህርት በጥቂቱ ተምረዋል፡፡ ወረኢሉ ዘመናዊ ትምህርት ቤትም ገብተው እስከ ሦስተኛ ክፍል ደርሰዋል፡፡
በየካቲት ወር 1948 ዓ.ም ደግሞ የጀመሩትን ዘመናዊ ትምህርት ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ያመጧቸው ወላጅ እናታቸው ወ/ሮ ክቤ ዮሴፍ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ክቤ የያኔውን ወጣት አሰፋ ተክሌን አዲስ አበባ ለሚኖሩት ለአክስታቸው ልጅ ለወ/ሮ ከፋይነሽ ኑርየ ሰጥተዋቸው ተመለሱ፡፡
በወቅቱ ወ/ሮ ከፋይነሽ ኑርየና ባለቤታቸው ቀኛዝማች ነጋ በየነ በዐርበኝነት የታወቁ ሰዎች ነበሩ፡፡ ወጣቱ አሰፋ ተክሌ መርካቶ አካባቢ በነበረው አክስታቸው ቤት ሆነው እስከ 5ኛ ክፍል ተማሩ፡፡ የተማሩበት ት/ቤት በአሁኑ ሰዓት የአዲስ ከተማ ት/ቤት ያለበት አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱም 5ኛ ክፍል የደረሰ ሰው የከፍተኛ ትምህርት እንደተማረ ይቆጠር ነበርና በ1950 ዓ.ም በወታደርነት ሙያ ለመሠልጠን ተመልምለው፣ ሐረር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጦር አካዳሚ ገቡ፡፡ በጊዜው ለወታደርነት የመለመሉዋቸው መኰንን ጄኔራል ሽፈራው ተሰማ ይባላሉ፡፡ አሠልጣኞቹም እንግሊዞችና ሕንዶች ነበሩ፡፡
ሕንዳዊው ጀኔራል ራውል በእንግሊዝኛ ከሚያስተምሩት ወታደራዊ የቀለም ትምህርት በተጨማሪ
“ተጠንቀቅ”
“አሳርፍ”
“ማርሽ ወደፊት”
“እጥፍ ማርሽ በሩጫ ርምጃ ሂድ”
“ቁም”
“ቀኝ ኋላ ዙር”
“ወደ ግራ ዙር”
“ወደ ቀኝ ዙር”
“ባለህበት ” እያሉ መሠረታዊ የወታደር ትምህርት አስተምረዋቸዋል፡፡ የብሪቲሽና የሕንድ መኰንኖች እስከ 1954 ድረስ ሐረር ጦር አካዳሚ በሚያሠለጥኑበት ሰዓት የኬንያ፣ የአልጀሪያ፣ የሱዳን፣ የሶማሊያና የሌሎች አገሮች መኰንኖች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ይሰለጥኑ ነበር፡፡ ለአብነትም ሶማሊያ ገና ነጻ ሳትወጣ ዶ/ር አብራሸክ አሊህ ሸህ ማርኬ አብረዋቸው የሠለጠኑ ሲሆን እኒህ ሰው ሶማሊያ ነጻ ስትወጣ በነጻይቱ ሶማሊያ ሥለጣን በመያዝ የመጀመሪያው ሆነዋል፡፡
የሕንድ አሠልጣኞች ሲቀየሩ ኢትዮጵያዊው ጄኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ የጦር አካዳሚውአዛዥ ሆነዋል፡፡ በዚያ ወቅትም ፶ አለቃ አሰፋ፣ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን ተከታትለው እስከ 8ኛ ክፍል ደርሰዋል፡፡
፶ አለቃ አሰፋ ተክሌ ተራ ወታደር ሆነው ሐረር ለ12 ዓመት (1950-1962) ኖረዋል፡፡ ከዚያ ወደ ምድር ጦር መሐንዲስ መምሪያ ተዛውረው፣ ሀገራቸውን ለ34 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ለአገልግሎታቸው የ15 ዓመት የብር፣ የ20 ዓመት የወርቅ ሜዳልያ ተሸልመዋል፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥትም የተዋጊ ምልክት ያለበት ሠርቲፊኬት ተሸልመዋል፡፡
፶ አለቃ አሰፋ በሠራዊቱ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ለኃላፊነት በየጊዜው ይመረጡና ለታማኝነት ቦታም ይታጩ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰውየው እንደሌሎች ሰዎች ለበላይ አለቆች የማያጐበድዱ፣ በምላስና በአስመሳይነት የማያድሩ፣ የዓይን ተገዥ ያልሆኑ፣ ለእውነት ብቻ የቆሙና የግንባር ሥጋ ስለሆኑ ሹመትና ዕድገት በየጊዜው ያልፏቸው ነበር፡፡
“እኔ ሕግንና ሥርዓትን ጠብቄ ነው የምሠራው፡፡ አለቆቼን አልለማመጥም፡፡ የሚፈለግብኝን ሥራ ብቻ አሸንፌ ነው የኖርኩት” ይላሉ፡፡
በ1956 ዓ.ም ሶማሊያ የሩሲያን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቃ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ፶ አለቃ አሰፋ ቶጎ ውጫሌ ላይ ተዋግተዋል፡፡ ሶማሊያ ድል ከተመታችና ጦርነቱ ከበረደ በኋላ ግርማዊ ጃንሆይ በተገኙበት ለተዋጊው ግብዣ ተደረገ፡፡
 በወቅቱ የሠራዊቱን ሞራል የሚያነቃቃ ግጥም በግብዣው ላይ እንዲቀርብ ውድድር ተደርጐ ከ20 ወጣቶች ግጥም የእርሳቸው 3ኛ ደረጃ ወጥቷል፡፡ ግብዣው ላይ ካቀረቡት ግጥም አንዱ ዘለላ የሚከተለውን ይመስላል፡
“ለሶማሌ ነወይ ለትንሽዋ ነገር፣
አይተነው መጥተናል የቻይናንም አገር፡፡”
በወቅቱ ቻይና ደቡብ ኮርያን ትወጋ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ክብር ዘበኛ ጦር ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት በኩል በደቡብ ኮርያ ጐን ተሰልፎ ተዋግቷል፡፡ ግጥሙ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡
ሁለተኛው ዘለላ ደግሞ፡-
“እያለው መሣሪያ ጥይቱ ሳያንሰው፣
እንዴት ለሶማሌ እጁን ይሰጣል ሰው፡፡” …ሲሉም ገጥመዋል፡፡
ሦስተኛው እንዲህ ይላል፡-
“መጥተው ነበር እነዚያ ሶማሎች
መጥተው ተመለሱ፣
ብልኃቱን አጡበት፣
የጠቅል አሽከሮች ጉድ ጉድ አሉበት፡፡”  
በወቅቱ ወታደሩ “የጠቅል አሽከር” እያለ ይፎክር ስለነበር ነው እንዲህ መግጠማቸው፡፡
“ግጥሙን እኔ ገጥሜ ሳነብ ወታደር እሸቱ እንዳይላሉ የተባለው ድምጻዊ በግጥሙ ይሸልልበትና ይፎክርበት ነበር፡፡ ያን ጊዜም እኔና ድምጻዊው ጓደኛዬ ከጃንሆይ አንድ አንድ ሺህ ብር ተሸልመናል” ይላሉ ፶ አለቃ አሰፋ፡፡
በደርግ ዘመንም በ1968 ዓ.ም ወደ ኤርትራ አሥመራ ተቀይረው እስከ 1970 ዓ.ም በውጊያ ላይ ቆይተዋል፡፡ በኃይለሥላሴ የ፲ አለቅነት፣ ማዕረግ ያገኙ ሲሆን የ፶ አለቅነትን ደግሞ በደርግ ዘመን ነው ያገኙት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በጡረታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የሆኑት ፶ አለቃ አሰፋ፤ ከንባብ ከልምድ፤ ከማኅበራዊ ኑሮ፣ ከወቅታዊ ሁኔታዎችና አባቶች ሲናገሩ በጽሞና በማዳመጥ ባገኙት እውቀት፣ ከታሪክና ከወቅት ጋር የተነገሩ ሕዝባዊ ግጥሞችን አብጠርጥረው ያውቃሉ፡፡ ምን? መቼ? እንደተነገረ ከቦታው ጋር እያገናዘቡ ይናገራሉ፡፡
በ1969 ዓ.ም አሥመራ ውጊያ ላይ እያሉ ከሻዕቢያ ጦር በዐረብኛ አንድ የኮድ መልእክት ይተላለፋል፡፡ እርሳቸው ደግሞ ዐረብኛ ስለሚችሉ አሥመራ ዙሪያ ያለውን ምሽግ ሻዕቢያ ሌሊት ሊመታ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው ጦሩ ቦታ እንዲለውጥ አድርገዋል፡፡
ሻዕቢያም የተለቀቀውን ባዶ ቦታ ሲደበድብ አድሯል፡፡ በዚህም የተነሳ የመሣሪያ ኪሣራ ደርሶበታል፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ የጦሩ ባልደረባ ሲፎክር፤
“አሰፋ ተክሌ የጥጃ ሣሩ፣
እንኳን ሲዋጋ ሲሸሽ ማማሩ”
ብሎ አድንቋቸዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አባታቸው አቶ ተክሌ አበጋዝ ከወረኢሉ ባላባት ከደጃዝማች ወልደጊዮርጊስ ጋር ማይጨው ዘምተው የተዋጉ ዐረብኛ ናቸው፡፡
ጐጃሞች “ያፈረሰ ቄስ አይቀድስም፣
የሸሸ ንጉሥ አይነግሥም” ያሏቸውና ወሎዎች ደግሞ
“ምን ያረጋል ቀሚስ አለቤቱ፣
አሽከሩ ሲዋጋ ሸሸ ባለቤቱ “ተብሎ የተዘፈነባቸው ጃንሆይ፤ ከስደት መጥተው ለዐርበኞች መሬት ሲሰጡ በስሕተት ለበግ ሌቦችና ለአጭበርባሪዎች ሁሉ መሬት እንዲታደላቸው አድርገው ለእውነተኛ ዐርበኞች ግን ሳይሰጣቸው ቀረ፡፡ አባቴም ሳያገኝ ቀረ፡፡ በወቅቱ የወረኢሉ አዝማሪ፤
“ለንጉሥ ንገሩዋቸው ባያውቁ ነው፣ በሉ፣
እንዴት መሬት ሰጡት ለበግ ሌባው ሁሉ” ብሎ ዘፈነ፡፡
ከዚህም የተነሣ በአዝማሪው ግጥም ዐርበኞች ተፈልገው መሬት ሲሰጣቸው አባቴም መሬት አገኘ” ይላሉ ፶ አለቃ፡፡ አባታቸውም በማይጨው፤
“የወታደር መቃብር፣
ከመንገድ በታች አጋም ሥር፣
እኔም ለእናቱ አልነግር፣
አለ እያለች ትኑር”
በማለት በማይጨው ጦርነት ስለቀሩት ጓደኞቻቸው አዘውትረው ሲያንጐራጉሩ ይሰሙዋቸው እንደነበር አጫውተውኛል፡፡ የእናታቸው አባት ባሻ ዮሴፍ አብርየም በዓፄ ምኒልክ ዘመን መንግሥት ከራስ ሚካኤል ጦር ጋር ዐድዋ ዘምተዋል፡፡ እርሳቸው ከጦር ሜዳ እንደተመለሱ፡-
“እያለ መሣሪያ ጥይቱ ሳያንሰው፣
እንዴት ለሶላቶ እጁን ይሰጣል ሰው፡፡
ፍሪዳም አልገዛ ሥጋውም ይቅርብኝ፣
እፊት የቀደመ የሥጋ እዳ አለብኝ፡፡
የሌሊቱ ዝናም ምንም አላለኝ፡፡
ቀን ጥሎ ነው እንጂ የደበደበኝ”
እያሉ በበገና ይጫወቱ ነበር፡፡     
በተለይም ኢጣልያ ከማይጨው ጦርነት በኋላ የልብ ልብ ስለተሰማት የዐድዋን ዐርበኞች እየፈለገች ማጥቃትና መግደል ጀምራ ነበር፡፡ ባሻ ዮሴፍንም ለመግደል ኢጣልያ ዒላማ አድርጋ ባንዳ በአሰለፈችባቸው ጊዜ፣ ባሻ ዮሴፍ ጊዜያቸውን ያሳለፉት ከቦታ ቦታ በመዘዋወርና በመደበቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው፡-
“የሌሊቱ ዝናም ምንም አላለኝ፣
ቀን ጥሎ ነው እንጂ የደበደበኝ፡፡”
ያሉት፡፡
በሌሊት ዝናም የመሰሉት የዐድዋን ጦርነት ሲሆን የቀን ዝናም ምሳሌ ያደረጉት ደግሞ የማይጨው ጦርነትንና ያስከተለውን አስከፊ ገጽታ ነው፡፡ እርሳቸውም ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ላይ እንዳሉ ሞተዋል፡፡
ባንዶች ልዩ ምልክት የነበረበትን የጣልያን ኮት ይለብሱ ስለነበር ዐርበኞች፡-
“የጣልያንን ኮት ሁሉ አጠለቀው፣
ቀውጤ ቀን መጥቶ ካላወለቀው” … ብለው ገጥመዋል፡፡
ወ/ሮ ሸዋረጋ፤ ምኒልክ የንጉሥ ሚካኤል ባለቤት፣ የዓፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ፣ የልጅ ኢያሱ እናት ነበሩ፡፡ ወረኢሉ (ቤተ አምሐራ) ሞቱና ወረኢሉ ላይ ለቅሶ ተደረገላቸው፡፡ በወቅቱም የሸዋ አልቃሽ፤
“ምነው በቀረባት የወሎ ጋብቻ፣
የወሎ ግዛት፣
ወጣ ብላ ቀረች የሸዋ እመቤት”
…ብላ ስታለቅስ በወሎ በኩል ያለው ሰው ከፋውና የሚቀጥለውን የለቅሶ ግጥም ገጠመ፡፡
ይቀጥላል፡፡

Read 3814 times