Saturday, 03 May 2014 12:40

አውሮፕላን ተንጠላጥሎ ከአምስት ሰአታት በላይ የበረረው እናቱን ፈላጊ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(3 votes)

ወደ አየር ማረፊያው የገባው  በአጥር ዘሎ ነው
ዕሁድ ሚያዝያ 12 ቀን፣ 2006 ዓ.ም ምሽት…
“ቀን ለሰራዊት፣ ማታ ለአራዊት” ብሎ ነገር የማይመለከታት እንቅልፍ የለሽ አሜሪካ፣ እኩለ ሌሊት ቢያልፍም፣ እንደነቃች ናት፡፡ ጨለማ ስራ እማያስፈታው የካሊፎርኒያው ሚኔታ ሳንጆሴ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያም፣ ሂያጅና መጪውን በማስተናገድ የዘወትር ተግባሩ ተጠምዷል፡፡ አውሮፕላኖች ይነሳሉ፣  አውሮፕላኖች ያርፋሉ… መንገደኞች ይሄዳሉ፣ መንገደኞች ይመጣሉ…
ነጋ ጠባ በርካታ አውሮፕላኖችንና መንገደኞችን በአግባቡ በማስተናገድ የሚታወቀው የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው፣በዚህች ምሽትም የተለያዩ በረራዎችን በወጉ በማስተናገድ ስራ ተጠምዷል፡፡ ከደህንነትና ጸጥታ ሰራተኞች እስከ ቴክኒክ ባለሙያዎች፣ ከመንገደኛ አስተናጋጆች እስከ አብራሪዎች… በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ሰራተኞች፣ እንደተለመደው የተመደቡበትን ስራ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማከናወን ቀጥለዋል፡፡
ብዙ መንገደኞች አሉ… ከተለያየ አቅጣጫ በመነሳት፣ ሲጓዙ አምሽተው የደረሱ መጪዎች፡፡ ብዙ መንገደኞችም አሉ… ወደየራሳቸው አቅጣጫ ሊጓዙ፣ ከመሸ ጓዛቸውን የሸከፉ ተጓዦች፡፡ በፈካ ብርሃን የተጥለቀለቀው የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው የመንገደኞች መስተንግዶ ክፍል፤ የሚመጣውን ለመቀበል፣ የሚሄደውን ለመሸኘት በመጡ በርካታ ሰዎች ተሞልቷል፡፡
ከዚህ ብርሃናማ ክፍል ርቆ በሚገኝ ጨለማ ውስጥ…
አንድ መንገደኛ አለ፡፡ የሚሸክፈው ጓዝ የሌለው… “በል እንግዲህ ቸር ያድርስህ!” ብሎ በእንባ የሚሸኘው፣ የራሱ ሰው የሌለው መንገደኛ፡፡ ለመሄድ የሚፈልግ እንጂ፣ ወዴት ለመሄድ እንደሚፈልግ የማያውቅ ተጓዥ አለ፡፡ “ትኬት አለመቁረጥ ካሰቡት ለመድረስ አያግድም፣ ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው!” ብሎ የተነሳ፤ እንደሌሎች መንገደኞች ትኬት ያልቆረጠ…  ጨለማው ውስጥ ያደፈጠ መንገደኛ፡፡
የደህንነት ካሜራዎችንና በረቀቀ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ የታገዘውን ጥብቅ ፍተሻ፣ በአንዳች ዕጸ-መሰውር አልፎ፤ ሽቦ የተገጠገጠበትን አደገኛ አጥር እንደ እንሽላሊት ወጥቶ፣ እንደ እባብ መሬት ለመሬት እየተሳበ ወደ ማኮብኮቢያ ሜዳው ቅጽር ግቢ የዘለቀ ሰርጎ ገብ መንገደኛ…
ይሄን መንገደኛ፣ ከጨለማው በቀር ማንም አላየውም!... ዙሪያውን ከተደቀኑት የደህንነት ካሜራዎች፣ አንዳቸውም አልያዙትም፡፡ ዙሪያውን ከሚቃኙት የኤፍቢአይ ፖሊሶች፣ አንዳቸውም አላናዘዙትም፡፡ ማንም ሳያየው፣ ማንም ከጉዳይ ሳይጥፈው፣ ትንፋሹን እንደዋጠ፣ ጨለማውን ሰንጥቆ ወደ አንድ አቅጣጫ ሮጠ፡፡ እሱ እንደሌሎች መንገደኞች አይደለም፡፡ ጓዙን ተቀብሎ በክብር ወደተመደበለት አውሮፕላን የሚያደርሰው መሪ የለውም፡፡ እሱ ጓዝ የለውም… የተመደበለት አውሮፕላን የለውም… የሚያደርሰው መሪም የለውም!... ጓዙ ተስፋ፣ መሪው ደመ-ነፍስ ነው… ከእነዚያ፣ በቅርብ ርቀት ማኮብኮቢያው ላይ ተደርድረው ከሚያያቸው አውሮፕላኖች ወደ አንዱ የሚያደርሰው!
ሮጠ መንገደኛው… በቅርቡ ወዳገኘው አውሮፕላን፡፡
የትኛው ነው የኔ አውሮፕላን ብሎ የሚጠይቅበት፣ መብትም ፋታም የለውም፡፡ በፖሊሶች አይን ስር ገብቶ አሳር መከራውን ከማየቱ በፊት፣ በቅርቡ ያገኘው አውሮፕላን ጉያ ውስጥ መሸጎጥ ነው የፈለገው፡፡
ተሳካለት!...
ንጋት ላይ….
የዕለቱ መንገደኞች ከትተው መግባታቸውን ያረጋገጠው የሃዋይ አየር መንገድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን ለጉዞ ተዘጋጅቷል፡፡ በበረራ ቁጥር 45 የሳንጆሴን መሬት ለቆ ክንፎቹን ሊዘረጋ የሰከንዶች ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ ተሳፋሪዎቹ ቀበቷቸውን ሸብ አድርገው ለረጅሙ ጉዞ ታጥቀዋል፡፡ አብራሪዎቹ በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡ የበረራ ተቆጣጣሪዎች የመጨረሻዋን ሰከንድ ጠሩ!...
አውሮፕላኑ ማኮብኮቢያው ላይ ወደፊት ተንደረደረ፡፡ ከመሬት ተነስቶ ፍጥነቱን እየጨመረ በረረ፡፡ እግሮቹን አጥፎ፣ ክንፎቹን ዘረጋ፡፡ አፍንጫውን ወደጠቆረው ሰማይ ቀስሮ፣ ሽቅብ ተመነጠቀ፡፡
ረጅም ጉዞ… ከፓሲፊክ ውቅያኖስ በላይ፣ እስከ ሃዋይ በተቀየሰ የሰማይ መንገድ ላይ የሚደረግ ረጅም ጉዞ፡፡ ጉዞው አውሮፕላኑ ውስጥ ለሚገኙ እንጂ፣ አውሮፕላኑ ጉያ ስር ለተደበቀው መንገደኛ፣ ሩቅ በሚለው ቃል አይገለጽም!... ጉዞው ለዚህ መንገደኛ ከሩቅም በላይ ነው፡፡ ይሄን ያህል ማይል ተብሎ የማይሰፈር፣ የትየለሌ የሚረዝም፣ ዝንተ-አለም ያክል ጉዞ ነው - ለእሱ!...
አውሮፕላን አብራሪው፣ ጉዞው አምስት ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ያህል እንደሚፈጅ ለተሳፋሪዎቹ አወጀ፡፡ እርግጥ ነው፣ ምቹ ወንበር ላይ ተንፈላሰው ለተቀመጡት ለውስጠኞቹ ተሳፋሪዎች፣ ጉዞው የአምስት ሰኣት ከሰላሳ ደቂቃ ነው፡፡ ከታጠፉት የአውሮፕላኑ እግሮች ስር ተሸጉጦ ለሚርበተበተው፣ ኦክስጅን አጥሮት ጫን ጫን ለሚተነፍሰው… ለውጨኛው ተሳፋሪ ግን፣ ጉዞው የሰዓታትና የደቂቃዎች ጉዳይ አይደለም!...  ዘለለት የሚመስል፣ እስከ ዝንተአለም የሚረዝም ፍርሃትና ጭንቀት እንጂ!...
ከሚኔታ ሳንጆሴ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው አውሮፕላን፣ ሰማይ እየሰነጠቀ መክነፉን ቀጥሏል፡፡ እስከ 38 ሺህ ጫማ ከፍታ ሽቅብ እየጓነ፣ ቁልቁል እየወረደ ወደ ፊት ይገሰግሳል፡፡ ከዜሮ በታች 30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሚደርስ ፍጹም ቅዝቃዜ ውስጥ፣ ቆፈን ሳያደነዝዘው ክንፎቹን ዘርግቶ ይቀዝፋል፡፡ እግሮቹን አጥፎ ይከንፋል፡፡
በስተመጨረሻም…
ፓሲፊክ ውቅያኖስን አቋርጦ ለአምስት ሰአት ከሰላሳ ደቂቃ የተጓዘው አውሮፕላን፣ ከሃዋይ ሰማይ ስር እንደሚገኝ  የሚገልጸው የአብራሪው የብስራት ድምጽ ከተሳፋሪዎቹ ጆሮ ደረሰ፡፡ ከአውሮፕላኑ ጎማ ስር የተሸጎጠው ድብቅ መንገደኛ ግን፣ የት ስለመድረሱ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ዘለአለም በሚመስል ስቃይ ውስጥ ጠፍቶ ነበርና፣ ሲሆን ስለነበረውም ሆነ እየሆነ ስላለውም ነገር፣ አንዳች እንኳን የሚያውቀው አልነበረም፡፡
ረጅም ማይሎችን የተጓዘው የሃዋይ አየር መንገድ አውሮፕላን፣ ከፍታውን ቀንሶ ወደ ካሁሉኢ አውሮፕላን ማረፊያ ቁልቁል ወረደ፡፡ የታጠፉ እግሮቹን ዘርግቶ ማኮብኮቢያውን ረገጠ፡፡ ከአውሮፕላኑ መውረድ የጀመሩትን መንገደኞች እንጂ፣ ከአውሮፕላኑ እግሮች በላይ ያለውን ብረት ሙጥኝ ብሎ የተለጠፈውን ድብቅ መንገደኛ ልብ ያለው አልነበረም፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ፣ የካሁሉኢ አውሮፕላን ማረፊያ የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራ አንዳች ምስል ከሰተ፡፡ ከአውሮፕላኑ ጉያ ስር፣ ሁለት እግሮች ቁልቁል ተዘረጉ፡፡ እኒህ መሬት የረገጡ እግሮች፣ ከአውሮፕላኑ ጎማ በስተጀርባ ተደብቆ ለሰዓታት የበረረውና በለስ ቀንቶት እዚህ የደረሰው የስውሩ ጥቁር መንገደኛ ናቸው፡፡
ይሄ በደመ-ነፍስ ከወዲያ ወዲህ የሚለው ግራ የተጋባ ብላቴና፣ ያህያ አብዲ ነው፡፡ ጨለማን ተገን አድርጎ፣ የሳንጆሴ አለማቀፍ አውሮፕላን ጣቢያን አጥር አልፎ ከአውሮፕላኑ ጉያ ውስጥ የተወሸቀው፣ ለሞት ከሚዳርግ ፈታኝ የሰዓታት በረራ በኋላ በተዓምር በህይወት ተርፎ መሬት ለመርገጥ የታደለው ህገ-ወጡ መንገደኛ፣ ሶማሊያዊው ብላቴና ያህያ አብዲ ነው፡፡
የ15 አመቱ ሶማሊያዊ ታዳጊ፣ የሚያደርገው ጠፍቶት ይቅበዘበዛል፡፡ የት እንዳለ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡  የሚያውቀው ቢኖር፣ ከዚያች የሰቆቃ ኑሮን ይገፋባት ከነበረች የጠላት ከተማ፣ ከሳንታ ክላራ ርቆ እንደሚገኝ ብቻ ነው… እና ደግሞ፣ አንጀቱ በውሃ ጥም መቃጠሉን፡፡ ይሄ እረፍት ነስቶ የሚያቃጥለው ውሃ ጥም ነው፣ ያህያን ከአውሮፕላን ማረፊያው ሰራተኞች ወደ አንዱ የወሰደው፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው የመንገደኞች ዕቃ ተቆጣጣሪ ግለሰብ፣ ከበስተጀርባው አንዳች የሚቃትት የሲቃ ድምጽ ሰምቶ ዘወር አለ፡፡ ከየት መጣ ያላለው ጥቁር ልጅ፣ አለፍ ብሎ ራሱን ስቶ ሲዝለፈለፍ አየው፡፡ እንደምንም እየቃተተ በምልክት ጉሮሮውን የሚያረጥብበት ጠብታ ውሃ ይሰጠው ዘንድ ይለምነዋል፡፡
“ከየት የመጣ ጉድ ነው?!...” አለ ሰራተኛው ግራ በመጋባት፡፡ ይህ ጉድ ከየት እንደመጣ የታወቀው፣ ከቆይታዎች በኋላ ነው፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው የደህንነት ሰራተኞች፣ ድንገት ግቢው ውስጥ ስለተከሰተው ሶማሊያዊ ሰርጎ ገብ መረጃ ደረሳቸው፡፡ የሬዲዮ መገናኛዎች አንዳች ነገር መከሰቱን የሚጠቁም መልዕክት አስተላለፉ፡፡ የኤፍቢአይ ፖሊሶች አደጋ ከመከሰቱ በፊት ነገሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል በአፋጣኝ ከስፍራው ደርሰው ከበባ አደረጉ፡፡
እዚህ ክብ ውስጥ ራሱን ስቶ ከሚዝለፈለፍ ብላቴና በቀር፣ የጠረጠሩት አሸባሪ አልነበረም፡፡ ፖሊሶቹ ብላቴናውን አገላብጠው ፈተሹት፡፡ በደረት ኪሱ፣ የሆነ የሚጎረብጥ ነገር ነኩ፡፡ ሆኖም የጠረጠሩት ፈንጂ አልነበረም - ከፕላስቲክ የተሰራች አሮጌ የጸጉር ማበጠሪያ እንጂ!...
“እንዴት እዚህ ድረስ ልትመጣ ቻልክ?” በግርምት ተውጠው ልጁን ጠየቁት ፖሊሶች፡፡
ልጁ እንደምንም ብሎ እያቃተተ የሰጣቸው መልስ ቢኖር፣ እንዴት እንደመጣ ጭራሽ እንደማያስታውስ ብቻ ነው፡፡
“ምንድን ነው ነገሩ?” ሲሉ መልሰው ጠየቁ ፖሊሶች፣ የበለጠ ግራ በመጋባት፡፡
የኤፍቢአይ ቃል አቀባይ ቶም ሲሞን እንዳሉት፣ ነገሩ ግልጽ የሆነው ዘግይቶ ነው፡፡ ትንፋሽ አጥሮት ሲስለመለም የነበረው ያህያ፣ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል እንዲገባ ተደረገ፡፡ ነፍሱን ካወቀ በኋላም የሆነውን ሁሉ ለፖሊሶቹ ተናገረ፡፡ ከሳንጆሴ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራ ላይ ልጁ የኤርፖርቱን አጥር ዘሎ ወደ አውሮፕላኑ ሲሮጥ የሚያሳይ ቪዲዮ ተገኘ፡፡
ከሆስፒታል ወጥቶ ሃዋይ ውስጥ ወደሚገኝ የህጻናት ክብካቤ ማዕከል እንዲገባ የተደረገው ያህያ፣ አሁንም የአተነፋፈስ ችግር አልለቀቀውም፡፡ ያን ያህል ርቀት፣ በዚያ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ አውሮፕላን ላይ ተንጠልጥሎ የተጓዘው፣ ያህያ አብዲ የተባለው የ15 አመቱ ሶማሊዊ የዓለም ዜና ሆነ - እንደ ተዓምር የሚቆጠር አጀብ የሚያሰኝ ዜና!
የሳንጆሴ አውሮፕላን ማረፊያን ጥብቅ ፍተሻ በምን ተኣምር ሊያልፍ ቻለ?... በዚያ ቅዝቃዜ ውስጥ ለአምስት ሰኣት ተኩል ያህል አውሮፕላን ስር ተሸጉቶጦ መቆየት የቻለበት ሚስጥር ምንድን ነው?... ኦክስጅን በሚያጥርበት ከፍታ ላይ ረጅም ሰዓት ቆይቶ፣ እንዴት በህይወት ተገኜ?... እንዲህና እንዲያ ያሉ ጥያቄዎችን አስነሳ ልጁ፡፡
“ይሄን ለማድረግ ያነሳሳውስ ምንድን ነው?...” የሚለውም የብዙዎች ጥያቄ ሆነ፡፡
ለዚህ ጥያቄ መልሱ “ፍቅር!” ነው.... የእናቱ ፍቅር!...
የዛሬን አያድርገውና ያህያ አብዲ፣ ከእናት አባቱና ከአምስት እህት ወንድሞቹ ጋር በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ነበር ኑሮው፡፡ ከስምንት አመታት በፊት ግን፣ ቤተሰቡ የመፍረስ አደጋ ገጠመው፡፡ አባቱ አብዲላሂ የሱፍ አብዲ፣ ለሚስታቸው ለኡባህ ሞሃመድ አብዱላሂ “እዚህ ሄድኩ” ሳይሉ፣ ያህያንና ሌሎች ሶስት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ሱዳን ሄዱ፡፡ እናትም ከቀሪዎቹ ሁለት ልጆቻቸው ጋር ባዶ ቤት ታቅፈው ቀሩ፡፡
ይህ ከሆነ ከአመታት በኋላ፣ ሳይናገሩ የሄዱት አባት ሳይናገሩ ወደቤታቸው ድንገት ከተፍ አሉ፡፡ “ልጆቼን ይዤ አሜሪካ ለመሄድ አስቤያለሁ፡፡ ፈቃደኛ ከሆንሽ ትዳራችንን በይፋ እናፍርስና ልጆቼንም ስጪኝ?” ሲሉም ሚስታቸውን ጠየቁ፡፡ እናት ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ አባት አላባበሉም፣ ሱዳን ውስጥ ያቆዩዋቸውን ሶስቱን ልጆቻቸውን ይዘው በ2008 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ተሰደዱ፡፡ በካሊፎርኒያ አዲስ ትዳር መስርተው፣ ሌሎች ሶስት ልጆችን አፍርተው መኖር ጀመሩ፡፡
በአባቱ አስገዳጅነት ከእናቱ ጉያ ተነጥሎ ወደ አሜሪካ የተጋዘው ያህያ አብዲ፣ የአሜሪካን ኑሮ መልመድ ተስኖት ነጋ ጠባ ሲጨናነቅ ነው አመታትን የገፋው፡፡ የእንጀራ እናት ፊት እየገረፈው መኖሩ አንገሽግሾታል፡፡ የዚችኛዋ ጨካኝ እናት በደል፣ ሩቅ ካለች እናቱ ናፍቆት ጋር ተደምሮ ህይወቱን ሰላም ነስቶታል፡፡ ከእህትና ወንድሞቹ ተነጥሎ ሲቆዝም ውሎ ያድራል፡፡
እየቆየም፣ በሶማሊያ ያለችው እናቱ ናፍቆት ከሚችለው በላይ ሆነበት፡፡ ፊት ከማይሰጡት አባቱ ፊት ቆሞ፣ “እናቴ ናፍቃኛለችና አይቻት መምጣት እፈልጋለሁ” ብሎ ለመጠየቅ ደፈረ፡፡
“ያህያ… እናትህ እኮ፣ በሞቃዲሾ በደረሰ ፍንዳታ ህይወቷን አጥታለች!” ሲሉ መለሱለት አባቱ፡፡
ይህ ለያህያ ትልቅ መርዶ ነበር - ሊሸከመው የማይችለው ከባድ ጫና!... በዚህ መርዶ ቅስሙ ተሰብሮ፣ ቀሪ ዘመኑን በሃዘን ለመግፋት ጉዞ ጀመረ፡፡ የእናቱ ሃዘንና የእንጀራ እናቱ በደል ራሱን እንዲጠላ አደረገው፡፡ በዚህ መጥፎ ሁኔታ ረጅም ጊዜያትን የገፋው ያህያ፣ ለማመን ያቃተውን አንዳች የምስራች የሰማው ባለፈው አመት መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡
“እናትህ አልሞተችም!... ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው የምትኖረው!” ነበር ያለው፣ በአሜሪካ የሚኖር አንድ ዘመዳቸው፣ ከሰው ሰማሁ ብሎ፡፡ያህያ ለማመን ተቸግሯል፡፡ ሰማሁ ብሎ የነገራቸው አባቱም፣ የሰማውን እንዳያምን ለማሳመን ሞከሩ፡፡ እናቱ ከሞተች አመታት እንዳለፋት አስረግጠው ነገሩት፡፡ እሱ ግን፣ ከአባቱ ይልቅ የሰማውን ነገር ለማመን ፈቀደ፡፡ እናቱን አንድ ቀን እንደሚያገኛት ቀልቡ ነገረው፡፡ ያንን ቀን ሲጠብቅ ወራት አልፈዋል፡፡
 ሚያዝያ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት…
አባቱና የእንጀራ እናቱ እንደተለመደው በስድብ ያጥረገርጉታል፡፡ ያለ ጥፋቱ በግልምጫና በነገር ይጠብሱታል፡፡ ያህያ ከዚህ በላይ መታገስ አልቻለም፡፡ በቆሙበት ትቷቸው፣ እግሩ ወደመራው አቅጣጫ ሽምጥ ሮጠ!... ተመለስ ቢሉት አልሰማቸውም፡፡ ወደ እነሱ ከሚመለስ፣ ወደ ጨለማው ቢገሰግስ የተሻለ ነገር እንደሚጠብቀው አምኗል፡፡
ያህያ ሮጠ!... ከሶስት ማይል ሩጫ በኋላም፣ ራሱን ከሳንጆሴ አውሮፕላን ማረፊያ አጥር ስር አገኘው፡፡ ይሄን አጥር መዝለል፣ አፍሪካ ምድር ላይ ወዳለች እናቱ የሚደርስበት ረጅም ጉዞ መጀመሪያ ነበር - አልሞተችም ወዳላት እናቱ፡፡
እርግጥም እናቱ ኡባህ ሞሃመድ አብዱላሂ አልሞተችም፡፡እርግጥ ከባሏና ከሶስት ልጆቿ ተነጥላ፣ ያለረዳት ሁለት ልጆቿን በማሳደግ የምትገፋው ኑሮ፣ ከሞት የሚተናነስ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አገሪቱ በጦርነት እየታመሰች ነው፡፡ በሞቃዲሾ ምድር ላይ ደም እንደ ጎርፍ መፍሰስ ይዞ ነበር፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያንም፣ ከሞት ሽሽት አገራቸውን ጥለው ስደት እየወጡ ነበር፡፡ የኡባህ ዕጣም ከሌሎች ሶማሊያውያን የተለየ አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በሸደር የስደተኞች ካምፕ መኖር ጀመረች፡፡
ስደተኛዋ እናት፣ ባሏ ከእቅፏ ነጥቆ በወሰደባት ልጆቿ ናፍቆት ስትሰቃይ ነው የኖረችው፡፡ ደጋግማ ወደ አሜሪካ ስልክ ደውላ፣ “እባክህ አትጨክንብኝ!... ድምጻቸውን እንኳን አሰማኝ!?” እያለች በለቅሶ ባሏን ለምናዋለች፡፡ ስልኩን በጆሮዋ ላይ ደጋግሞ ዘግቶባታል፡፡ ደም እንባ አስለቅሷታል፡፡ ኑሮዋን የበለጠ መሪር አድርጎባታል፡፡ እያንዳንዷን ቀን ትርጉም አልባ፣ ህይወቷንም ስቃይ አድርጎባታል፡፡
ከእነዚህ ትርጉም አልባ ቀናት (ባለፈው ሳምንት) በአንደኛው… በካምፑ ውስጥ በሚገኘው ገበያ ለሽያጭ የምታቀርባቸውን አትክልቶች ስታዘገጃጅ፣ ስልክ እንደሚፈልጋት  ተነገራት፡፡ በአሜሪካ የሚኖር ዘመዳቸው ነበር ደዋዩ፡፡
“ልጅሽ ያህያ፣ ወደ አንቺ ለመምጣት በአውሮፕላን ተንጠላጥሎ ሲጓዝ ፖሊሶች አግኝተው ያዙት!” አላት ደዋዩ፡፡ኡባህ ሞሃመድ አብዱላሂ የስልኩን እጀታ ይዛ ተንቀጠቀጠች፡፡ መብረቅ እንደመታት በቆመችበት ደርቃ ቀረች፡፡ የሰራ አካላቷ እየተንዘፈዘፈ አለቀሰች፡፡
የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ወደ ኡባህ ደውለው የተሰማትን ጠየቋት፡፡ “እውነት ግን ልጄ በህይወት አለ!?... እባካችሁ፣ ስለ ወላድ ብላችሁ… ካልሞተ የልጄን ድምጽ አሰሙኝ!?” ስትል እንባዋን አጎረፈች፡፡ ለጊዜው በሆስፒታል ውስጥ ስለሚገኝ ልታነጋግረው ባትችልም፣ ልጇ ግን አሁንም በህይወት እንደሚገኝ አረጋገጡላት፡፡ የልጇን ወሬ ከሰማች ጀምሮ እህል በአፏ አልዞረም… የልጄን ድምጽ አሰሙኝ ብላ እያለቀሰች ለምናለች… ሁለት ልጆቿ በካምፑ አብረዋት አሉ፡፡“አደራችሁን… የልጆቼን አይን ሳላይ እንዳልሞት እርዱኝ!” ስትልም ለኢትዮጵያ መንግስትና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተማጽኖዋን በእንባ ታጅባ አቀረበች፡፡
 ቢቢሲ እንደዘገበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኡባህ ጥያቄ ቀና ምላሽ ሳይሰጥ አይቀርም፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው የሸደር የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የህግ ከለላ ሃላፊ የሆኑት አብድራዛቅ አባስም፣ ሁባህ በተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ በኩል ወደ አሜሪካ ለመሄድ የሚያስችላትን የመጀመሪያ ቃለ መጠይቅ ከቀናት በፊት በስኬት እንዳጠናቀቀች ተናግረዋል፡፡ ቀጣዩን ቃለ መጠይቅ ካለፈች፣ አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ አሜሪካ በማምራት  ከልጇ ያህያ ጋር እንደምትገናኝ ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል፡፡ ኡባህ ግን የልጇን ዜና ከሰማችበት ቅጽበት አንስቶ በጭንቀት ላይ ናት፡፡ የልጇን ዓይን ሳታይ እንዳትሞት በመስጋት፣ እንቅልፍ አጥታ ትባዝናለች፡፡
(እ.ኤ.አ ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ 105 ሰዎች በአውሮፕላን ተንጠላጥለው ለመሄድ ሙከራ አድርገዋል፤ በህይወት የተረፉት 25 ብቻ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ተከስክሰው ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል - ይላል ዋሽንግተን ፖስት፡፡ )Read 2693 times