Saturday, 03 May 2014 12:36

ኢህአዴግ ኮርጆም ቢሆን የፖለቲካ ምህዳሩን ያስፋው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)

በፕሬስ ነፃነት ቀን “ጋዜጠኞች ወይስ ብሎገሮች??” በሚል እየተወዛገብን ነው

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው - ዛሬ፡፡ በጣልያን ነው የሚከበረው አሉ፡፡ በጣልያን ብቻ ግን አይደለም -  በኢትዮጵያም ይከበራል፡፡ እኔ የምለው… የራሳችን የፕሬስ ነፃነት ቀን ቢኖረን አይሻልም እንዴ? ለምን መሰላችሁ? የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለማክበር ቸኮልን ብዬ እኮ ነው፡፡ (“ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ” አሉ!) ያው እንደምታውቁት … የኛ ነገር አንድ እርምጃ ወደፊት … ሁለት እርምጃ ወደኋላ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ብቻ እኮ ነው ወደፊት መገስገስ የተሳካለት፡፡  
እኔ ግን ምን አስባለሁ መሰላችሁ? ይሄ የፈረንጆቹን ህግና አዋጅ መኮረጅ ቢቀርብን ነው የሚሻለው፡፡ በዲሞክራሲ ሥርዓት የዳበረ ባህል ካላቸው አገራት ህግ በመኮረጅ እኮ የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል መገንባት አይቻልም፡፡ በዚያ ላይ የምንኮርጀው ዲሞክራሲን የሚያፋፋውን ሳይሆን የሚያቀጭጨውን እኮ ነው፡፡ (የኩረጃ ስህተት አለ ማለት ነው!) ይኸውላችሁ… የኢህአዴግ መንግስት ሽብርን ፈርቶ የፀረ ሽብር ህግ በማውጣቱ አትፍረዱበት፡፡ ለምን መሰላችሁ… እኔም መንግስት ብሆን መፍራቴ አይቀርማ! እናንተም ብትሆኑ ያው ነው፡፡ በአንድ በኩል የአገርና የህዝብ ጉዳይ ያሳስባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሥልጣን ነገር አለ፡፡ ለዚህ ነው የሚያስፈራው፡፡ ግን ደግሞ መፍትሔው አንድ ብቻ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡
ይኸውላችሁ ---- ሽብርም ሆነ የቀለም አብዮት ተግባራዊ የሚሆኑት ህዝብ ከተስማማ ብቻ ነው፡፡ ለዚያ የተዘጋጀ--- ኑሮ የመረረው ወይም ያጎሳቆለው ህዝብ አለ ወይ ነው ጥያቄው፡፡ መብቱ የተጣሰ ወይም የተደፈጠጠስ? እንደኔ ---- ለሁለቱም መከሰት ሰበብ የሚሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ በመለየት በተቻለ መጠን ማስወገድ ነው መፍትሄው፡፡ ለምን “አካፋን አካፋ--” አንለውም? ለምሳሌ የተቃዋሚዎችን ህገመንግስታዊ መብት ማክበር!! የፖለቲካ ምህዳሩ በቂ ነው ብሎ ድርቅ ከማለት ማስፋት! (ምህዳር ያልቃል እንዴ?) ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ሳይሸራረፍ ማክበር! ሁሉንም ህዝብ የልማቱም የዲሞክራሲውም ተሳታፊ ማድረግ! በቃ የሰው ልጆች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ማክበር ማስከበር! ይኸው እኮ ነው (ኢህአዴግ ሁሉንም ያውቃቸዋል እኮ !) እነዚህ ዕውን ሲሆኑ ሁሉም ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ይሆናል፡፡ ያኔ ሽብርና የቀለም አብዮት ስጋትነቱ ያከትማል፡፡ ያኔ እኒህን የሚከላከለው ኢህአዴግ ወይም መንግስት ሳይሆን ህዝቡ ራሱ ነው፡፡ ኢህአዴግ እዚያ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብሎ ካሰበ ብዙ ወከባ መፍጠር የለበትም፡፡
እኔ የምለው .. ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎችን መምከር ብቻ ነው የምንችለው ብለው የለ! (“ማሰር ብቻ ነው የምንችለው”አለማለታቸው ትልቅ ነገር ነው!) ጋዜጠኛውንም--- ብሎገሩንም--- አክቲቪስቱንም-- መምከር እኮ ይቻላል - ከማሰር! ማሰር ትርፉ የአገር ገፅታን ማበላሸት ብቻ ነው፡፡ ትላልቆቹ ሚዲያዎች እኮ ዜናውን ከዳር እስከ ዳር አዳርሰውታል፡፡ ከዚህ ኢህአዴግ ምን ያተርፋል? (ደህና መካሪ የሚያስፈልገው እኮ ይሄኔ ነው!) የእኛን የጋዜጠኞች ማህበራት ጉዳይ አታንሱብኝ፡፡ ገና እኮ “ብሎገሮች ጋዜጠኞች አይደሉም” ምናምን የሚል ክርክር ላይ ናቸው፡፡ ዋናው ጥያቄ በፃፉት ጉዳይ ነው ወይስ በሌላ የሚለው እንጂ ብሎገር ሆኑ ጋዜጠኛ ምንድነው ለውጡ? አሁንም እደግመዋለሁ---ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበራት ሺህ ጊዜ ጋዜጠኞችን አሰረ ተብሎ የሚወነጀለው አውራው ፓርቲ ይሻለኛል! እነዚህ ሥልጣን ቢይዙ እኮ እዚህች አገር ላይ ትንፍሽ ማለትም አይቻልም ነበር፡፡ (ፈጣሪ ጦቢያን ይወዳታል እኮ!)
ይኸውላችሁ አንዳንዴ ኢህአዴግ ሲበዛ ትዕግስተኛ ነው እላለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ያልበረደለት “አፍላ ጎረምሳ” ይመስለኛል፡፡ አሁን ለምሳሌ መብራት ኃይልን ስንት ዓመት ነው የታገሰው፡፡ እኔ ብሆን እስካሁን ለኒዮሊበራሎች እሸጠው ነበር (በብስጭት እኮ ነው!) ባለፈው አርብ ማታ በኢቴቪ የሸገር  ነዋሪዎችን የመረረ ስሞታ ሰምታችሁልኛል? (እንደ ኤልፓ የሃበሻን አንጀት ያሳረረ እኮ የለም!) ስሞታው ምን መሰላችሁ? ከመብራት ውጭ ከሆንን ሰነበትን የሚል ነው፡፡ “ብርሃን የለንም፤ ብርሃን ይስጠን” ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ “የአፍሪካ መዲና ውስጥ ነው ያለነው ለማለት ያሳፍራል” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል (የሚሰማ ሲኖር አይደል?!) የሚገርማችሁ ነገር ኢቴቪ የመብራትና የውሃ ችግርን በተመለከተ የነዋሪዎችን አቤቱታ ይዘግባል እንጂ የተቋማቱን (የመብራት ሃይልና የውሃ ፍሳሽ መ/ቤቶችን ማለቴ ነው!) ምላሽ መጠየቅም ሆነ መዘገብ እርም ብሏል፡፡ ምን ያድርግ? መልሳቸውን ከመገመት አልፈን ሸመደድነው እኮ!! መጀመሪያ አካባቢ “የኢኮኖሚ ዕድገቱ ያመጣው ነው” ይሉ ነበር (“የዕድገት ምስቅልቅል” እንደተባለው!)
አያችሁ… ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ብርቃችን ስለነበር እኮ ነው ሁሉም በዕድገቱ ሲያሳብብ የከረመው፡፡ በዚያ ላይ “ዕድገቱ የፈጠራ ነው” ባዮች በርክተው ስለነበር፤ እነሱን ለማብሸቅም ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ወረቱ ሲያልቅ ግን ሌላ ሰበብ መፍጠር የግድ ሆነ - ለእነ መብራት ኃይል!! እናም የኤሌክትሪክ መስመሮችና ትራንስፎርመሮች አርጅተው እየተቃጠሉ ነው መብራት የሚጠፋው ተባልን፡፡ በመቀጠል ዝነኛው መብራት ኃይላችን ዝነኛ ሰበብ መጠቀም ጀመረ - ለመብራት መጥፋቱና መቆራረጡ፡፡ ይሄ ዝነኛ ሰበብ ምን መሰላችሁ? “የአቅርቦት ችግር የለብንም፤ የስርጭት እንጂ” የሚል ነው፡፡ አንዳንዴ ኢህአዴግም ስለ ፖለቲካ ምህዳር መጥበብና  የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ጭቅጭቅ ሲያደርጉት “የአቅርቦት ችግር የለብንም፤ የሥርጭት ችግር እንጂ” በማለት ለምን አይገላገልም እላለሁ፡፡ (ለመገላገል ያህል እኮ ነው!) በነገራችሁ ላይ … ይሄን ዝነኛ ሰበብ የስኳር ወይም የዘይት አሊያም የስንዴ እጥረት ሲከሰት ነበር የምንሰማው፡፡ እናላችሁ… መብራት ሃይል አንድ ሰሞን “የአቅርቦት ችግር የለብንም፤ የሥርጭት እንጂ!” እያለ አደከመን፡፡ ሃፍረትና ይሉኝታ ያልፈጠረበት መብራት ኃይል ቀጥሎ ደግሞ “የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠረው ነው” በማለት ህዝቡ የመ/ቤቱን ኪራይ ሰብሰቢዎች እንዲታገልለት ተማፀነ፡፡ (በምን እዳችን!?)
አይገርማችሁም…መብራት ኃይላችን “የልማት ሰራዊት” ፣ “የጤና ሰራዊት”፣ “የትምህርት ሰራዊት” ወዘተ  ሲባል ሰምቶ እሱም “የኪራይ ሰብሳቢዎች ሰራዊት” አደራጅቶ ቁጭ አለ፡፡ በነገራችሁ ላይ… የገቢዎችና ጉምሩክ መ/ቤት የቀድሞ ቦሶችም ድንገት ተነቃባቸው እንጂ “የሙሰኞች ሠራዊት” አቋቁመው የጦቢያን ነጋዴ መከራ ሲያበሉና የህዝብ ንብረት ሲዘርፉ ነበር እኮ! (ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባቸውን ጨዋ ኃላፊዎች አይመለከትም!)
ይኸውላችሁ… አንዳንድ የዋህ የመዲናዋ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋትና መቆራረጥ የተፈጠረው በልማት ሥራው ሳቢያ  እየመሰላቸው… “ግዴለም ለአዲሱ ትውልድ የሚከፈል መስዋዕትነት ነው” እያሉ ሲፅናኑ ሰምቻለሁ - በኢቴቪ፡፡ (ትወና ይሆን እንዴ?!) ትወናም ይሁን የምር… እኛ ግን ሃቁን መርምረን ማወቅ አለብን፡፡ መሸወድ ሲበዛ እኮ ያስቆጫል፡፡ (ዶ/ር ነጋሶ “ኢህአዴግ ለ10 ዓመት ሸውዶኛል”እያሉ ይቆጩ የለ!) እናላችሁ… መብራት መቆራረጡና ልማቱን ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም እያልኩ ነው፡፡ እኔ እኮ አይደለሁም ያልኩት- ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ የመብራት መጥፋት የመልካም አስተዳደር መጥፋት ነው ብሎን የለ! (ልማቱ ሳይጀመርም እኮ መብራት ይጠፋ ነበር!)
እናላችሁ… የመብራት ኃይል ጉዳይ በገለልተኛ የውጭ አካል (ከተቻለ በሄግ) ካልተመረመረ በቀር እውነቱን የምንደርስበት አይመስለኝም፡፡ እኔማ እንዳሁኑ አያያዝ የህዳሴው ግድብ ከተጠናቀቀ በኋላም የመብራት መጥፋት በሉት መቆራረጥ የሚቆም አይመስለኝም፡፡ (ጨለምተኝነት ከመሰላችሁ ተሸውዳችኋል!) ለምን መሰላችሁ? ኃላፊዎቹ “የአቅርቦት ችግር የለብንም፤ የሥርጭት እንጂ!” ብለዋላ!! ለማንኛውም የመብራት ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት መጀመሪያ ትክክለኛ ችግሩን ማወቅ ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ የአቅርቦት ነው? የሥርጭት ነው? የዕድገት ውጤት ነው? የኪራይ ሰብሳቢነት ነው? የመልካም አስተዳደር ችግር ነው? ወይስ ሁሉም መልስ ነው? መንግስት “በመብራት አንበሸብሻችኋለሁ” ብሎ  ቃል ከመግባቱ በፊት ይሄን ጥያቄ በትክክል መመለስ ይገባዋል፡፡ (“ችግሩን ማወቅ ግማሽ መፍትሄ ነው” ተብሏል!) ያለዚያ ቃል አባይ መሆኑ አይቀርም (ልማዱ ነው እንዳትሉኝ!)
በነገራችሁ ላይ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሰሞን የመንግስታቸውን የዘጠኝ ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለፓርላማው ካቀረቡ በኋላ፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን በተመለከተ ምንም አለማለታቸውን ሲጠየቁ “ሪፖርቱን ማቅረብ ያለባቸው ተቃዋሚዎች ናቸው” ማለታቸውን ወድጄላቸዋለሁ፡፡ (ወድጄላቸዋለሁ ማለት ግን ትክክል ናቸው ማለት አይደለም!) ግን እኮ ተቃዋሚዎች ሪፖርት እናቅርብ ቢሉም ማቅረቢያ ቦታ የላቸውም? (ለምን የተቃዋሚዎች ፓርላማ አይቋቋምም?) ያለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ዲሞክራሲ እንደሌለ፣ ያለዲሞክራሲ ህልውና እንደሌለ የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በቂ የፖለቲካ ምህዳር እንዳለ ጠቁመው፤ ይሄን ምህዳር ምን ያህል ተጠቅመንበታል ብለው በመገምገም ሪፖርት ማቅረብ ያለባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው ብለዋል፡፡ (መንግስት ስልጣኑን “ሼር” ሊያደርጋቸው አስቧል እንዴ?) እኔ--- ምን ግርም እንደሚለኝ ታውቃላችሁ? በአንድ አገር እየኖርን ሁለት እርስ በርስ የሚቃረኑ መረጃዎች መስማታችን! መንግስት በቂ የፖለቲካ ምህዳር አለ ሲል ተቃዋሚው “ለዓመል ያህል እንኳን የለም” ብሎ ይፈጠማል፡፡ መንግስት በሙያው የተነሳ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም ሲል እነሲፒጄ “ጦቢያ ጋዜጠኞች በማሰር ከዓለም ሁለተኛ ናት” የሚል መግለጫ ያወጣሉ፡፡ በገዛ አገራችን የትኛው እውነት እንደሆነ አናውቅም፡፡ ምን እንዳማረኝ ታውቃላችሁ? በገዢውም በተቃዋሚውም-- ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግስትም በግልም ጋዜጠኞች የተከበረ ሃቀኛ የጋዜጠኞች ማህበር!! (አማረኝ አልኩ እንጂ አቋቁማለሁ አልወጣኝም!) ማህበርና የፖለቲካ ፓርቲ ኮከቤ አይደሉም! በነገራችሁ ላይ ---ጠ/ሚኒስትሩ “ስለውጭ ዲሞክራሲ ከማውራት በፊት ውስጥን ማጥራት ያስፈልጋል… ውስጡ ሲጠራ ውጭውም ይጠራል” በማለት ተቃዋሚዎችን ወርፈዋቸዋል (“Are you sure?” የሚል ወዳጅ ነበረኝ!)
እርግጥ ነው ተቃዋሚዎች ራሳቸው ከዲሞክራሲ ሥርዓት ጋር ገና አልተዋወቁም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን “እነሱ ዲሞክራሲያዊ ሲሆኑ ኢህአዴግም ዲሞክራሲዊ ይሆናል” የሚለውን እንዳለ ለመቀበል ይቸግራል፡፡ አንዳንድ ተቺዎች --- ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ፉክክሩን ትቶ (ልጅ ነው እንዴ?) ለእነሱም አርአያ መሆን አለበት ይላሉ (“አውራ ፓርቲ ነኝ” እያለ ይፎክር የለ!)
እኔ የምለው … ይሄ ለልማት ብለን የምንከፍለው መስዋዕትነት መቼ ነው የሚቆመው? ልማቱ ሲጠናቀቅ እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ (ልማት እኮ ቀጣይ ነው!) ያው መስዋዕትነት ስል መቼም ይገባችኋል አይደል? ያለመብራትና ያለ ውሃ ውለን የምናድረው፣ ያለ ኔትዎርክ የከረምነው፣ በታክሲ እጦት የምንሰቃየውና ነጋ ጠባ የምንሰለፈው ወዘተ… ማለቴ ነው፡፡ ለልማቱ እየከፈልን ያለነውን መስዋዕትነት እያማረርኩ እንዳይመስላችሁ (ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ጦቢያን ለመፍጠር ነው ብዬ ተቀብየዋለሁ!) ተቃዋሚዎችም እኮ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ሲጠይቁ የእንቅስቃሴ ቦታቸው እየተገደበባቸው ነው፡፡
ይሄን ህገመንግስቱም ሆነ ሌሎች ህጐች ባይደገፉትም ለቀጣዩ ትውልድ ብለው በፀጋ ተቀብለውታል፡፡ (አንዳንዴ ቢነጫነጩም፡፡) አሁን ጥያቄዬ ለአውራው ፓርቲ ነው፡፡ የባቡር መስመር ያላትና ታላቁን የህዳሴ ግድብ የገነባች ጦቢያ … ለአዲሱ ትውልድ በቂ አይደለችም!! (ለትውልዱ የምናስበው ከልብ ከሆነ ማለቴ ነው!) እናም ስልጡን የፖለቲካ ባህል የዳበረባት አገር ማዘጋጀት ይገባዋል - ኢህአዴግ፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት “ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በሰበብ አስባቡ የማይንገላቱባት አገር” መፍጠርም አለበት - አውራው ፓርቲ (ለተተኪው ትውልድ ሲል ማለቴ ነው!) እውነትም ይሁን ሃሰት “ጋዜጠኞች በማሰር ከዓለም ሁለተኛ የምትባል አገር” ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ያሳፍራል - ለኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ጭምር፡፡ በፓርላማ አንድ የተቃዋሚ ተወካይ ያለባት አገርም እሺ ብሎ አይቀበልም - አዲሱ ትውልድ፡፡ ተቃዋሚዎች ሰልፍና ስብሰባ እንዳያደርጉ የሚዋከቡባት (ተዋክበናል ስለሚሉ ነው!) ጦቢያንም አዲሱ ትውልድ አይረከበንም፡፡ እናም ኢህአዴግ ለመጪው ትውልድ መስዋዕትነት እንዲከፍል እንጠይቀዋለን - የፖለቲካ ምህዳሩን ያለስስት በማስፋት!! (ምህዳሩን ካሰፉ አገራት ኮርጆም ቢሆን !)

Read 3587 times