Saturday, 03 May 2014 12:06

ሰራተኞች ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ያለ አግባብ ከስራችን አፈናቅሎናል አሉ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

  “ሥራቸውን በገቡት ውል መሰረት ባለመስራታቸው አሰናብተናቸዋል”- ሆቴሉ
    ከአምስት ወር በፊት ስራ የጀመረው የኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አራት የሴኩሪቲ ሰራተኞች፣መብታችንን በመጠየቃችን በማይመለከተን ጥፋት ወንጅሎ ያለማስጠንቀቂያ ከስራችን አባርሮናል ሲሉ በሆቴሉ ላይ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡ የሆቴሉ የሰው ሃይል አስተዳደር አቶ አሰፋ በየነ በበኩላቸው፤ሰራተኞቹ የተባረሩት የተሰጣቸውን ሃላፊነትና ተግባር ወደጐን በመተው በሆቴሉ ላይ ችግር በመፍጠራቸው ነው ብለዋል፡፡ እንደማንኛውም አመልካች ተወዳድሮና መስፈርቱን አሟልቶ በሴኩሪቲ ክፍል መቀጠሩን የገለፀው አቶ ሃዲስ በሪሁን፤ አማርኛህ ለሆቴሉ አይመጥንም፣ ሴት ፈትሸሃል፣ እንግዳ አቆላምጠህ ጠርተሃልና ሌሎች   የማይመስሉ ሰበቦችን በመደርደር አስተዳደሩ ከስራው እንዳሰናበተው ተናግሯል፡፡
“የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱል ሰላም ሲዮ ባሬንቶ፤ ከምሁር የማይጠበቅ ፀያፍ ንግግር ተናግረውኛል፣ የጓደኛዬን ሚስት አቆላምጬ በመጥራቴ “እሱ እስኪለቃት እየጠበቅህ ነው” በማለት ክብሬን የሚነካ ንግግር ተናግረውኛል፣ ለዚህም ምስክር አለኝ” ሲል ምሬቱን ገልጿል - አቶ ሀዲስ፡፡ “ሆቴሉ እንደማንኛውም ሰራተኛ ውል ያስገባን በቀን ለስምንት ሰዓት እንድንሰራ ቢሆንም እስከ 14 እና 16 ሰዓታት ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ ተገደን ሰርተናል” ያሉት ሰራተኞቹ፤ የህክምና ኢንሹራንስ ቢኖረንም መድሀኒት የምንገዛው በግላችን ነው፣ ከተቀጠርንበት የስራ መደብ ውጭ የማይመለከተንን ስራ ሁሉ እንሰራለን፤ በአጠቃላይ ከፍተኛ በደል ደርሶብናል ብለዋል፡፡ “ከዚህ በፊት ሆቴሉ በርካታ ሰራተኞችን በግፍ አባርሯል” የሚሉት ሰራተኞቹ፤አሁንም ሊያባርራቸው ያዘጋጃቸው እንዳሉ መረጃ አለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ በመስራት ልምድ እንዳካበተ የሚናገረው ሌላው ተሰናባች ሳሙኤል ደመመው፤ “የሴኩሪቲ ሰራተኞችን የፍተሻ ብቃት ለማረጋገጥ አንዳንድ ጊዜ ፈንጂና ቦንብን ጨምሮ መሳሪያ ታጥቆ የሚገባ እንግዳ ይላካል፣ ያንን በብቃት ፈትሾ ላገኘ የምስጋና ደብዳቤ ይሰጣል፣ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ይህን መሰል በርካታ የብቃት ማረጋገጫዎችን ስናልፍ እናመሰግናለን እንኳን አልተባልንም፣ ከስራ ለማባረር ግን በርካታ የማይመለከተኝን ታፔላ ለጥፈውብኛል” ሲል አማርሯል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ “ቡልሺት፣ ጋዴም” የሚሉ ስድቦችን ሰድበውን ሲያበቁ፣ “የትም ቦታ ብትሄዱ ምንም አታመጡም” በማለት በአገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረናል ብለዋል - ሠራተኞቹ፡፡
“በስራችን ተግተን ብንሰራም ደሞዛችን በጣም አነስተኛ ነው፣ ሰርቪስ ቻርጅ የለውም፣ የሚቀርብልን ምግብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ የብሔር ወገንተኝነት የተንሰራፋበት ድርጅት ነው” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ችግሮቹ እንዲስተካከሉ ፊርማ አሰባስበን ለሰው ሃይል አስተዳደር በማስገባታችን “ሰራተኛ አሳመፃችሁ” ተብለን ከሥራ ተፈናቅለናል ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ፕ/ር አብዱልሰላም ሲዮ ባሬንቶ፣ በመምህርነት በተለያዩ የአለም አገራት ለ37 ዓመታት ቢሰሩም ስለ ሆቴል ማኔጅመንት የሚያውቁት ነገር ስለሌለ ስራውን እያበላሹ ነው ሲሉም ሰራተኞቹ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ የሰራተኞቹን ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የሆቴሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱልሰላም ሲዮ ባሬንቶ በበኩላቸው፤ በስነ-ምግባር ጉድለት፣ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት እና መሰል ችግሮች ሰራተኞች መሰናበታቸውን እንደሰሙና ገና ሪፖርት አለማንበባቸውን ጠቁመው፣ “በሰራተኞቹና በእኔ መካከል ሌሎች በርካታ ማናጀሮች በመኖራቸው የትኞቹ እንደተሰናበቱ አላወቅሁም” በማለት ጉዳዩ  በቀጥታ የሚመለከተው የሰው ሀይል አስተዳደሩን እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የሆቴሉ የሰው ኃይል አስተዳደር አቶ አሰፋ በየነን በስልክ አግኝተን በሰጡን ምላሽ፤ ሆቴሉ አለም አቀፍ ሆቴል እንደመሆኑ በርካታ አለም አቀፍ እንግዶች እንደሚያርፉበት ጠቁመው፣ ከዚህ አንፃር የሴኩሪቲ  ስራ ከፍተኛ ጥንቃቄና ንቃት የሚጠይቅ ቢሆንም ሰራተኞቹ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው መሰናበታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ስንብቱም የተፈፀመው በገባነው ውል መሰረት ነው፤ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ደሞዝ ቅጣት ደርሰናል” ያሉት አቶ አሰፉ፤ ከሴኩሪቲ ሃላፊው በደረሰን መረጃ ጥፋታቸውን ባለማረማቸውና ባለማስተካከላቸው ተሰናብተዋል ብለዋል፡፡ የጥቅማጥቅም ጥያቄን በተመለከተም ሲናገሩ፤እንደማንኛውም ሰራተኛ ሰርቪስ ቻርጅ ይከፈላቸዋል ያሉ ሲሆን ህክምናን በተመለከተም ለዓለም ከፍተኛ ክሊኒክ ጋር በገቡት ውል መሰረት፤ሰራተኞች በክሊኒኩ አስፈላጊውን ህክምና እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ የብሄር ወገንተኝነት የተባለው ሃሰት መሆኑን የገለፁት አቶ አሰፋ፤በሆቴሉ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሀዲያ፣ ትግሬ፣ ወላይታ እና የበርካታ ብሄር ተወላጆች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ጠቁመው “እናንተም ጋ ለአቤቱታ ከመጡት ውስጥ አማራም ትግሬም ኦሮሞም አሉበት” ብለዋል፡፡
የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ ሰራተኞቹ ቀደም ሲል ይከፈላቸው እንደነበር ጠቁመው ሆቴሉ በትክክል ተከፍቶ ስራ ከጀመረ በኋላ ግን በርካታ የሰው ኃይል በመቅጠርና በሶስት ሽፍት በመደልደል ሁሉም ሰው በቀን ስምንት ሰዓት መስራት እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ስነ-ምግባር ይጎድላቸዋል፣ ከሆቴል ጋር የተገናኘ ሙያ የላቸውም በሚል የቀረበው ትችት ተቀባይነት እንደሌለው ሲያስረዱም “ዋና ስራ አስኪያጁ በአሜሪካ አገር ለ42 ዓመት ሲኖሩ ትምህርታቸው ሆቴል ስራ ላይ ነው ያተኮረው” ያሉት የሰው ኃይል አስተዳደሩ፤ በሆቴል ሙያ ዙሪያ ከፍተኛ ስልጠና እንደሚሰጡና በሆቴሉ ባለአደራ ቦርድ ብቃታቸው ታምኖበት መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ አንድ ሰራተኛ በተሰማራበት ሙያ ላይ የሚቀመጡ መስፈርቶችና ገደቦች እንዳሉ የተናገሩት አስተዳደሩ፤ “የሆቴሉ ማናጀር የሴኩሪቲ ሰራተኛው አንዲትን እንግዳ አቅፎ ሲስም አግባብ አለመሆኑን በመናገራቸው ስማቸውን ለማጥፋት መሞከር ትክክል አይደለም፣ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው በተወሰደው እርምጃ ገና ስራ ከጀመረ አምስት ወር ያልሞላውን ሆቴል ስም ለማጥፋት መሯሯጥ አግባብ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሰራተኞችን በግፍ ያባርራል፤ ሊያባርርም ተዘጋጅቷል መባሉም ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አቶ አሰፋ አስተባብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የሸራተን አዲስ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር 4ኛ አመት የምስረታ በአሉን ባለፈው ማክሰኞ በሆቴሉ ላሊበላ አዳራሽ የማህበሩ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳዊት ሣሙኤል ባደረጉት ንግግር፤ከዚህ ቀደም የሆቴሉ ሠራተኞች በአመት ለ27 ቀናት ያለ ክፍያ ማሠራትን ጨምሮ የተለያዩ በደሎች በማኔጅመንቱ ይፈፀምባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ከማህበሩ ምስረታ በኋላ ግን በሂደት ማኔጅመንቱ እና ማህበሩ እየተነጋገሩ የሠራተኛው ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡ አሁንም በርካታ ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ የፍርድ ቤት ውሣኔን የሚጠብቁ ጉዳዮችም እንዳሉ አመልክተዋል፡፡
በበአሉ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) ተወካይ አቶ ታመነ መኮንን ባደረጉት ንግግር፤ ሠራተኛው መብቱን ለማስከበር በማህበር መደራጀት ጠቀሜታ እንዳለው አሳስበው፣ የሸራተን አዲስ ሆቴል ሠራተኞች ማህበር ለአባላቱ መብት መከበር እያደረገ ያለው ትግል በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡   

Read 4091 times