Saturday, 26 April 2014 12:31

በአንዳንድ ትራፊክ ፖሊሶች ጎጂ ድርጊት መሞት ይብቃ!!!

Written by  በአሲዮ ዳን
Rate this item
(0 votes)

በዕቁብ ስም የሚሰበስቡት ገንዘብ ደመወዝ ነው የበረሃ አበል?

ይህ ዕድሜው ከ14 ዓመት የማይበልጥ ልዩ የትምህርት ፍቅርና አቅም ያለው ሕፃን የሥራ ቦታ ነው - መስቀል አደባባይ፡፡ ከትምህርቱ ሰዓቱ ውጪ ባለው ጊዜ ከጫማ ማሳመር ሥራ የሚያገኛትን ገቢ እንደወትሮው ለ’ራሱና ለአቅመ ደካማ እናቱ አንጀት መለጎሚያ እንዳትውል የሚያደርጋት ክስተት ተፈጠረ፡፡ አንድ ሚኒባስ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከጊዮን ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ ይነጉዳል፡፡ ለሌሎች አሽከርካሪዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚያስገድደውን የትራፊክ ምልክት ጥሶ ተፈተለከ፡፡ ከለጋሃር ወደ መስቀል አደባባይ የሚጓዝ የከተማ አውቶብስ አለአግባብ ወደ መስመሩ የገባበትን ይህንን ሞገደኛ ሚኒባስ ላለመግጨት መሪውን ጠቅልሎ ወደ አደባባዩ ጥግ (አሁን ታክሲዎች ወደሚቆሙበት ቦታ) በጭንቀት አመራ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ላዳ ታክሲዎችን ገጭቶ 70 ሜትር ድረስ ተንሸራቶ ኤግዚቢሽን ማዕከል መግቢያ ደረጃ ጋ ሲደርስ ቆመ።
ከዚህ ሁሉ አደጋ መካከል ተዓምር በሚባል ሁኔታ ሚኒባሱና አውቶብሱ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ቀላል እና መካከለኛ ጉዳት ብቻ ደረሰባቸው፡፡ ከመንገድ ውጪ የሥራ ቦታው ላይ የነበረው ሕፃን ግን በአውቶብሱ ጎማ ተዳምጦ ብርኩ ደቀቀ - የአልጋ ቁረኛም ሆነ፡፡ በሰሙት ነገር ልባቸው የደማው የሕፃኑ ደንበኞች፤ የሚኖርበትን ቤት አፈላልገው ለሕክምና እና ለመቋቋሚያው ይሆነው ዘንድ ለሕፃኑ ካሳና ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ያደርጉ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ለደረሰበት አደጋ ምንም አስተዋፅዖ የሌለው ታዳጊ አጭር ታሪክ እዚህ ላይ ተቋጨ፡፡
አንድ ወጣት የታክሲ ሹፌር የመኪናውን ማርሽ ወደኋላ አስገብቶ ብዙ ተሳፋሪና ታክሲ ከሚበዛበት የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ሥፍራ በጥድፊያ ለመውጣት ሲሞክር ታክሲ በመጠበቅ ላይ የነበረች ወጣትን በመኪናው ገፍትሮ በመጣሉ ክስ ቀርቦበት ምርመራ ተጀመረ፡፡ በወጣቷ ላይ ምንም አካላዊ ጉዳት አለመድረሱ በሕክምና ማስረጃ በመረጋገጡ በከሳሽና ተከሳሽ መካከል በተደረገ ዕርቅ እልባት አገኘ፡፡ ሹፌሩም ከስህተቱ እና ካየው ውጣ ውረድ በመማሩ፣ ዳግም ያለጥንቃቄ (በእሱ አገላለፅ ያለወከባ) እንደሚነዳ ተገዝቶ ወደ ስራው ተመለሰ፡፡
ከዚህ አደጋ ሁለት ሳምንት በኋላ ወጣቷን ከገጨበት ቦታ በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ተሳፋሪ ጭኖ የሚበርበትን መስቀለኛ መንገድ በማቋረጥ ላይ የነበረ የ18 ዓመት ወጣትን በመኪናው ገጭቶ፣ የእግረኛ ማቋረጫ መስመሩ ላይ ዘረረው፡፡ ሹፌሩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ‘ራሱን የሳተው ወጣት ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ፡፡ ከገባበት ሰመመን ነቅቶ የደረሰበትን ጉዳት ለማወቅ አድል ያላገኘው ወጣት ከጥቂት ቀናት በኋላ በሆስፒታል አልጋ ውስጥ ሳለ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ሹፌሩ የቀረበበትን በቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል ክስ ሲከታተል ቆይቶ ለፍርድ መቀጠሩን አስታውሳለሁ፡፡ ቀድሞ ካደረሰው አደጋ አንዳችም ትምህርት ያልወሰደ፣ ፍፁም ኃላፊነት የማይሰማው ሹፌር አጭር ታሪክ እዚህ ላይ ተቋጨ።
አንጋፋው አየር መንገዳችን ካፈራቸው ምርጥ ወጣት አብራሪዎች አንዱ የሆነው ካፒቴን ትምህርቱን አጠናቆ በበረራ ሥራ የተሰማራ ቢሆንም እናት አገሩ ዕውቀቱን እና ትጋቱን ለመጠቀም፣ ወላጆቹም የልጃቸውን ስኬት ለማጣጣም እምብዛም አልታደሉም፡፡ ከሥራ መልስ ምሽቱን ሲዝናና አምሽቶ፣ ተሽከርካሪውን እየነዳ ወደቤት በመመለስ ላይ ሳለ ዋናውን መንገድ ስቶ ለግንባታ በተገለበጠ ጠጠር አልያም አሸዋ ላይ በመውጣቱ መኪናው ተገለበጠ፡፡ ክቡር ሕይወቱም በአደጋው ምክንያት አለፈች፡፡ መኪና ከማሽከርከሩ በፊት ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ባለማከናወኑ፣ ሕይወቱን በማጣቱ በቤተሰቦቹ ላይ የሐዘን ከል የወረደ ወጣት አጭር ታሪክ በዚህ ተቋጨ፡፡
 እነዚህን እና መሰል የትራፊክ አደጋ ዜናዎችን መመልከት፣ ማዳመጥ፣ ማንበብ ወዘተ ከደማችን ጋር የተዋሀደ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም አንዱ ማረጋገጫ ከዓመታት በፊት ኮልፌ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የደረሰው ዘግናኝ እልቂትም ሆነ በቅርቡ ዘነበ ወርቅ አካባቢ ገደል ውስጥ ተገልብጦ ከፍተኛ አደጋ ያስከተለው የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አደጋ የደረሱት በሰለጠኑ አገራት ቢሆን ብሔራዊ ወይም ከተማ ዓቀፍ የሃዘን ቀን ሊያሳውጁ የሚችሉ መሆናቸው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
የትራፊክ አደጋ እያስከተለ ያለውን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና ክስረት፣ ዕንባና ሳግ እየተናነቃቸው ለረዥም ዓመታት ሲገልፁልን በነበሩት ነፍስ-ሄር ሳጅን ዳንኤል እግር የተተኩት ረዳት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ የአደጋው መበራከት፣ አሰቃቂነቱ እና አሁንም ድረስ ከአሽከርካሪዎችም ሆነ ከእግረኞች የሚፈለገው ለውጥ በሚፈለገው መጠን አለመምጣቱ እያስቆጫቸው በተመሳሳይ ስሜት ዘወትር ተለወጡ ይሉናል፡፡ ለዚህም ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡
በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ በሚሰራጩ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ የመንገድ ደህንነት ዘጋባዎች የትራፊክ አደጋ መንስዔዎች ናቸው ተብለው በአብዛኛውን የሚጠቀሱ ነጥቦች አሉ - የአሽከርካሪ ጥፋት፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ማነስ፣ የእግረኛ የጥንቃቄ ጉድለት እና ከመንገድ ጋር የተያያዙ ችግሮች፡፡ ከዚህ ሁሉ ጎልቶ የሚታየው የአሽከርካሪ ጥፋት ነው፡፡ የዛሬው ፅሑፌ ርዕሰ ጉዳይም አይነኬ ከሆኑት ጉዳዬች አንዱ ስለሆነው ነው - እየገደሉን ስላሉ አንዳንድ የትራፊክ ፖሊሶች ጎጂ ድርጊቶች፡፡
3ኛው የትራፊክ አደጋ ሳምንት ከሚያዚያ 06 ቀን ጀምሮ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ከመሆኑ አንፃር፣ ይህንን አይነኬ ሃሳብ በማንሳት፣ የትራፊክ አደጋን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በማሰቤ የግል ምልከታዬን እነሆ፡፡

ማሳያ አንድ - ትርፍ ሰው መጫን
አንድ ተሽከርካሪ ከመጫን አቅሙ በላይ ሠው ወይም ዕቃ ከጫነ እንደ ፍሬን እና ጎማ ያሉ የተሽከርካሪው አካላት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ስለማይችሉ፣ ተሸከርካሪው ለአደጋ የመጋለጥ እንድሉ ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ከሆኑት ተሽከርካሪዎች ውስጥ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባሶችና ሌሎች የህዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ግንባር ቀደሞቹ እንደሆኑ ሲገለፅ በተደጋጋሚ እንሰማለን፡፡
የህዝብ ማመላለሻዎች ትርፍ የሚጭኑበት ዋነኛ ምክንያት ብዙ ሰው በመጫን የገንዘብ ጥቅማቸውን ከፍ ማድረግ እንደሆነ መገመት ባይከብድም ከሐዋሳ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ በዝዋይ በኩል ቡታጅራ፣ ከባሕርዳር አዲስ አበባ፣ ከሻሸመኔ ሶዶ፣ ከመቀሌ አክሱም፣ ከአዳማ አዋሽ አርባ ባደረግኳቸው ጉዞዎች ስለጉዳዩ የጠይቅኳቸው ሹፌሮች የሠጡኝ መልስ  ትርፍ የሚጭኑበት ሌላም ምክንያት እንዳላቸው ያስገነዝባል፡፡ ብዙዎቹን የሚያስማማው መልስ የመጀመሪያው ሲሆን አጠቃላይ ሐሳባቸው በግርድፉ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ምክንያት አንድ፡- ለምሳሌ አንድ ሹፌር በሰው 25.00 ብር በሚከፈልበት መስመር አራት ትርፍ ተሳፋሪ ቢጭን 100.00 ብር ያገኛል፡፡ ከዚህ ብር የተወሰነውን ለሚያስቆመው ትራፊክ ቢያካፍል ቀሪዋን ለኪሱ ከማድረጉ ባሻገር፣ በዛው ቀን ትርፍ ጭኖ ሲሄድ እንዳይቀጣ ከትራፊኩ ጋር “ደንበኝነትን” መመስረቻ ስለሚሆነው የቀን ገቢውን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ምክንያት ሁለት፡- አንድ ሹፌር በሚሰራበት መስመር በሚገኙ ሆቴሎች፣ ግሮሰሪዎች ወይም ሱቆች ውስጥ ዕቁብ ጥሎ ስሙን ካስመዘገበ፣ በዛ መስመር የሚገኙ የዕቁቡ አደራጅ ትራፊኮች ትርፍ ቢጭንም ታርጋውን ከሩቅ በማየት ብቻ ሳይቀጡ ያሳልፉታል፡፡ ብቻ ከሱ የሚጠበቀው ዕቁቡን ሳያቋርጥ መጣል ነው፡፡
ዕቁብ በሹፌሮቹ ቋንቋ “አንዳንድ” የትራፊክ ፖሊሶች በቡድን እና በግል ተደራጅተው በዕቁብ ስም በወኪሎቻቸው አማካኝነት የሚሰበስቡት ግብር መሆኑ ነው፡፡
ምክንያት ሶስት፡- በዚህ መስመር የሚሰራ ሹፌር “ዕቁብ” የማይጥል ወይም በሹፌሮቹ ቋንቋ “የማይገባላቸው” “የማይወርድላቸው” ከሆነ የዕቁቡ አደራጅ “ትራፊኮች” እየተቀባበሉ በረሃ መሐል አለአግባብ የመኪናህን ጥሩንባ በተከለከለ ቦታ ነፋህ ወይም በጠራራ ክረምት ዝናብ መጥረጊያህ አይሰራም ብለው የክስ ወረቀት ይሰጡታል፡፡ አልያም ትክክለኛ ስለመሆኑ አንዳችም የሚያጠራጥር ነገር የሌለበትን መንጃ ፍቃድ ሐሰተኛ ሳይሆን አይቀርም በማለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዱታል፡፡ ስለዚህ ምርጫው ሁለት ነው ፤ “ዕቁብ መጣል” ወይም ስራውን ማቆም፡፡
ሥራውን ማቆም ስለማይታሰብ “ዕቁብ ይጥላል”፡፡ ዕቁብ ከጣለ ደግሞ አሁንም በሹፌሮቹ ቋንቋ “ዘጭ አድርጎ” (ብዙ ትርፍ ተሳፋሪ ጭኖ) ይጓዛል፡፡
ምክንያት አራት፡- አስተውላችሁ ከሆነ ትራፊክ አስቁሞ መንጃ ፍቃድ ሲጠይቃቸው የመኪናውን የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር (ሊብሬ) ብቻ እየመዠረጡ በልበ ሙሉነት አሳይተው መንገዳቸውን ያለክስ የሚያልፉ አንዳንድ ሹፌሮች አሉ፡፡ መሰል ሹፌሮችን “የባሉካ ሹፌር”፣ “የሳጅን ሹፌር” ወይም “እርገጥ” ይሏቸዋል፡፡ እርገጥ የሚሏቸው ያለ ጭንቀት ነዳጃቸውን ጥግ ድረስ እየረገጡ መንገዱ ስለሚጓዙ ነው፡፡ ሊብሬ የሚያሳዩት የተሽከርካሪው ባለቤት በዛ ወይም በአቅራቢያ መስመር ትራፊክ ፖሊስ፣ የትራፊክ ፖሊስ የቅርብ ቤተሰብ ወይም የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ፣ ሥምሪት ኃላፊ ወይም የቅርብ ቤተሰቡ መሆኑን ለማሳወቅ ነው፡፡ እነዚህ ክስ የማይነካቸው (Charge Proof) ተሽከርካሪዎች ናቸው - ዘጭ አድርገው ሰው የሚጭኑ፡፡      
መደምደሚያ አንድ
ከላይ ያየናቸው እና በቦታ ውስንነት ያልገለፅኳቸው ሌሎች ምክንያቶች ሲጠቃለሉ፣ ሙሰኛ ትራፊክ ፖሊሶች በመኖራቸው ምክንያት ሹፌሮች ትርፍ ሰው ለመጫን ይደፋፈራሉ፣ ይበረታታሉ ወይም ይገፋፋሉ የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሱናል፡፡ ትርፍ መጫናቸው ደግሞ የተሽከርካሪውን ለአደጋ የመጋለጥ ዕድል ከፍ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡

Read 2647 times