Saturday, 26 April 2014 12:28

ኢህአዴግ ራሱ ጥያቄ አውጥቶ፣ ራሱ ተፈትኖ፣ ራሱ ያርማል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)

ፓርላማው እንዲሟሟቅ ትኩስ ቡናና ሳቅ ያስፈልጋል!

        ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለፓርላማ ያቀረቡት በፋሲካ ማግስት ነው ማለት ይቻላል- ባለፈው ሐሙስ፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ከሌላው ጊዜ በተለየ እንቅልፍ እንቅልፍ ያላቸው (የበዓል ማግስት እኮ ይጫጫናል!) ለነገሩ … ያንን ሁሉ ሰዓት አዳራሽ ውስጥ መሰብሰብም እኮ እንቅልፍ ያመጣል፡፡ ምናልባት በጣም የባሰበት እኮ ጥያቄውን ለጠ/ሚኒስትሩ ከአቀረበ በኋላ፣ “ለሽ” ሊል ይችላል፡፡ ደግነቱ እኛ እንሰማዋለን (“እኛ” ወካዮቼ ማለቴ ነው!) በነገራችሁ ላይ በበቀደሙ ፓርላማ  እንቅልፍ ያስቸገራቸውን የምክር ቤት አባላት ለመውቀስ አይደለም - የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲያፈላልግ መተንኮሴ ነው (የግምገማ ተጠሪውን ሳይሆን የሪፍሬሽመንት ክፍሉን!)  
ከምሬ ነው--- ለምን አጭር የቡና ሰዓት አይኖርም? (“ኖሮ አያውቅም ወይም አልተለመደም” እንዳትሉኝ!) ለነገሩ ብትሉኝም አልቀበልም፡፡ ይኼውላችሁ---- ድሮ የሌሉ አሁን የተጀመሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እናም ----- ድሮ የቡና ሰዓት የሌለው ምናልባት ዘመኑ ስለማይጫጫን ይሆናል፡፡ አሁን ግን ይጫጫናል እያልን ነው፤ስለዚህ መፍትሄ የግድ ነው፡፡ በእርግጥ መፍትሄው ትኩስ ቡና ብቻ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ትኩስ ቀልድ ሊሆንም ይችላል፤ ዋናው ነገር ከእንቅልፍና ከድብርት ስሜት ማነቃቃቱ ነው፡፡ ያለዚያ እኮ ጠ/ሚኒስትሩ ከስንት አንዴ ተገኝተው የሚያቀርቡት ሪፖርትና ማብራሪያ ከንቱ ሆነ ማለት ነው! (እንቅልፍ ወስዶት “ገና” እንዳመለጠው ትንሽ ልጅ!)  እናላችሁ --- አባላቱ ሁሉን ነገር በንቃት እንዲከታተሉ ከፈለግን coffee break ቢኖር አይከፋም፡፡ አሊያም ደግሞ አንድ ሁለት ሞቅ ያለ ሳቅ የሚያጭሩ ቀልዶች ያስፈልጋሉ - በየመሃሉ፡፡ (ፓርላማው ቀልድ ለምዷል እኮ!) የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና) በቀልድና በተረብ እያዋዙ ነበር እንዲህ ያሉ የፓርላማ ጉባኤዎችን የሚመሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የግድ ኩምክና ይጀምሩ እያልኩ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ የተዋዛ “ስፒች” የሚፅፍላቸው----ከንግግራቸው ጋር የሚጣጣም ተረትና ምሳሌ የሚነግሯቸው ----- ሰሞነኛ ቀልዶችን የሚያሰሟቸው ቀልድና ጨዋታ አዋቂዎች አማካሪዎች ያስፈልጓቸዋል፡፡
   በዲሞክራሲ የበለፀጉ አገራት መሪዎችም እኮ እንኳንስ ቀልድ ንግግርም ተለማምደውና ሰልጥነው ነው የሚቀርቡት፡፡ (በጎውን መኮረጅ ክፋት የለውም ተብሎ የለ!) እኔ የምለው----የእንግሊዝ ፓርላማን የክርክር ሥርዓት አይታችሁልኛል? ቀውጢ እኮ ነው! (እንኳን ሊጫጫን የተኛንም ይቀሰቅሳል!) ይገርማችኋል----ወረቀት ይዞ የሚያወራ እንኳን አታዩም! ሁሉም በቃሉ ነው የሚያንበለብለው፡፡
በነገራችሁ ላይ ---- የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እርጋታ ይማርከኛል፡፡ (መማረክ መብቴ ነው!)  የቱንም ያህል የሚያስቆጣ አስተያየት ቢሰነዘርም በቁጣ ማዕበል አይወሰዱም፡፡ ተገቢ የመሰላቸውን መልስ ተረጋግተው ይሰጣሉ እንጂ! ይሄ መቼም በልምምድ የሚመጣ አይመስለኝም - በተፈጥሮ እንጂ!! (በምንም ይምጣ ብቻ ተመችቶኛል!)
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመጣ፣ በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ---ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው በአሽሙር የተጠቀለለ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ “አሁንም የትራንስፎርሜሽንና እድገት እቅዱ በዋና ዋና መስኮች ይሳካሉ ብለው ያስባሉ ወይንስ ልምድ ተቀስሞበታል ብለን እንድንወስድ ነው የሚፈልጉት?” (ቃል በቃል ሳይሆን መንፈሱን ነው!) በዚህ አስተያየት ትንሽ ሳይከፉ አልቀሩም - ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ (ተከፉ እንጂ ተቆጡ አልወጣኝም!)
ጠ/ሚኒስትሩ ከሰጧቸው መልሶች መካከል ይበልጥ ትኩረቴን ይበልጥ የሳበው--- “አንድ ተማሪ 10 ጥያቄዎች ቀርበውለት 8ቱን በትክክል መልሶ ሁለቱን ቢሳሳት እንዴት ሰነፍ ይባላል?” ሲሉ የጠየቁበት ነው፡፡ በእርግጥ ራሳቸው ናቸው የመለሱት፡፡ “ጎበዝ ተብሎ ይበረታታል እንጂ!” በማለት፡፡ (መንፈሱን እንጂ ቃል በቃል አይደለም!) እንግዲህ ተማሪው ኢህአዴግ ነው ወይም ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፡፡ አስሮቹን ጥያቄዎች ያወጣውም ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ ፈተናውን የተፈተነውም ኢህአዴግ ነው፡፡ ፈተናውን ያረመውም ራሱ ኢህአዴግ! እኔ የምለው--- ኢህአዴግ ራሱ ፈተና አውጥቶ፣ ራሱ ተፈትኖ፣ ራሱ አርሞ---- እንዴት ይችለዋል? (እርማቱ የምር ከሆነ ማለቴ ነው!)
ከዚያው ከፓርላማ ጉዳይ ሳንወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽንን የገለፁበት መንገድ አንጀቴን እንዳራሰው ልገልፅ እወዳለሁ፡፡ (መብራት መጥፋቱ ስለማይቀር አንጀቴን ላርስ እንጂ!) “ደንበኞችን ማበሳጨት ዓላማው ያደረገው መብራት ኃይል!” ሲባል የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ “ማበሳጨት” ግን አይገልፀውም “ማጨስ” የሚለው ይሻላል!! አንድ ጥያቄ አለኝ - ባለፈው አንድ ወር ለአፍታም ቤቱ ወይም ቢሮው መብራት ጠፍቶበት የማያውቅ ካለ ይሸለማል (ቤተመንግስትና የከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖሪያ ቤቶችን አይመለከትም!)
በነገራችሁ ላይ ---- ሰሞኑን በኢቴቪ የሰማሁት አንድ ዜና እንዴት  በግርምት እንደሞላኝ አልነግራችሁም!  በኢትዮጵያ ውስጥ የግል ሚዲያውን የሚያሰራ በቂ ነፃነት መኖሩን የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ድርጅት አረጋገጠ ይላል- ዜናው፡፡ ወደ ኋላ አስር አመት ግድም ተመልሼ አንድ ነገር ላስታውሳችሁ፡፡ ይሄም በ97 የምርጫ ቀውስ ማግስት በኢቲቪ የሰማሁት ዜና ነው፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ---- ለሁለት ይሁን ለሶስት ቀን ታክሲዎች አድማ መተው ነበር (ያኔ ማህበርና ታፔላ አልነበረማ!) ሲበቃቸው ወደ ሥራ ገቡ፡፡ አገልግሎት ሲሰጡም ዋሉ፡፡ ማታ ታዲያ ኢቴቪ ምን ብሎ ቢዘግብ ጥሩ ነው? “ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ታክሲዎች አገልግሎት ሲሰጡ እንደዋሉ ሮይተርስ ዘገበ” አይገርማችሁም --ኢቴቪ በገዛ አገሩ የተከሰተውን ሁነት የመዘገብ ልበሙሉነት አጥቶ ሮይተርስን በእማኝነት አቀረበ፡፡ (በእርግጥ የተቃዋሚው ጎራ “ዓይንህን ላፈር” ብሎት ነበር!) የሰሞኑም ዜና ተመሳሳይ ነው፡፡ “አላልኳችሁም----የግል ሚዲያዎች ለመስራት የሚያስችል ነፃነት አላቸው---ይኸው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች መሰከሩ” የሚል ዓይነት መንፈስ ያዘለ ነበር - የኢቴቪ ዜና፡፡ እኔ የምለው---- እኛ ባለቤቶቹ ብንጠየቅ አይሻልም ነበር፡፡
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል----በፍርድ ቤት የተመሰከረብን ነው የመሰለኝ፡፡ ከስንት አገር አውሮፕላን ተሳፍሮ መጥቶ “ለመስራት የሚያስችል ነፃነት አላችሁ” ብሎን ሄደ (ሳንጠይቅ እኮ ነው!) ለነገሩ እኛ ባንጠይቅም የሚጠይቅ ይጠፋል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ራሳቸውን “የቀለም አብዮት ተከላካዮች” አድርገው የሚቆጥሩ አንዳንድ አገር በቀል ማህበራት ጠይቀው ሊሆን ይችላል፡፡ ለማንኛውም ግን የነፃነቱም ይሁን የአልቦ ነፃነቱ ባለቤቶች እኛ ነን፡፡ በተለይ መንግስትና ኢህአዴግ ስለኛ ነፃነት ከእኛው ቢሰሙ ነበር የሚሻላቸው፡፡ (እውነቷን ከፈለጉ ማለቴ ነው!) የሚገርመው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ባለፈው ህዳር ወር ላይ የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት  ሲካሄድ፣ የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን እንጂ ምዕራባውያን እንዲናገሩልን አንፈቅድም የሚል ሃሳብ ሲንፀባረቅ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የግል ሚዲያ በነፃነት እየሰራ ይሁን አይሁን የሚያረጋግጡልን ግን እነሱ ሆነው አረፉት! (ያሳዝናልም ይገርማልም!)  

Read 4111 times