Saturday, 10 December 2011 12:26

ኤልክላሲኮ ለምን ይለያል?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከ200 ሚሊዮን በላይ የቲቪ ተመልካች 
እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ
ከ100 ዓመታት በላይ የደርቢ ታሪክ
ሪያል ማድሪድ ከባርሴሎና ዛሬ እኩለ ሌሊት በሳንቲያጎ በርናባኦ ሲገናኙ አስደናቂ ፉክክር እንደሚያሳዩ ተጠበቀ፡፡ ሁለቱ ክለቦች በላሊጋው በ3 ነጥብ ልዩነት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው የሚገናኙ ይሆናል፡፡ በጨዋታው ባርሴሎና ካሸነፈ ምንም እንኳን ሪያል ማድሪድ አንድ ጨዋታ ቢቀረውም የደረጃ ሰንጠረዡን በእኩል 37 ነጥብ የሚተናነቁበት ሲሆን ሪያል ማድሪድ ካሸነፈ ደግሞ በውድድር ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ በመሪውና በተከታዩ ክለብ የ6 ነጥብ ልዩነት ይፈጠራል፡፡

ከ100 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው የሁለቱ ክለቦች የደርቢ ፍልሚያ ከዛሬው 216ኛ ጨዋታ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደው ከወራት በፊት በስፔን ሱፐር ካፕ ሲሆን ባርሴሎና 3ለ2 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
የኤልክላሲኮ ግጥሚያ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝበትና በዓለም ዙርያ ከ200 ሚሊዮን በላይ ተመልካች በቲቪ እንደሚታደመው የሚጠቅሱ መረጃዎች የዛሬ ሌሊቱን ግጥሚያ በስፍራው በመገኘት ከአለም ዙርያ ከተለያዩ 28 አገራት 159 የሚዲያ ተቋማትን በመወከል የተሰባሰቡ 891 ባለሙያዎች በስፍራው ተገኝተው እንደሚዘግቡት ያመለክታሉ፡፡
ሪያል ማድሪድ 13.2 ሚሊዮን ባርሴሎና ደግሞ 10.4 ሚሊዮን ደጋፊዎች በአለም ዙርያ እንዳላቸው ሲገመት፤ ይህንኑ በመንተራስ በየውድድር ዘመኑ ታላላቆቹ የስፔን ጋዜጦች አስ፣ ማርካና ሙንዶ ዲፖርቲቮ ኤልክላሲኮውን የዓለማችን ምርጡ ደርቢ ብለው ማዳነቅ ልምድ አድርገውታል፡፡ በእንግሊዝ ማን ዩናይትድ ከሊቨርፑል፤ በጣሊያን ኤሲ ሚላን ከኢንተር ሚላን፤ በአርጀንቲና ሪቨር ፕሌት ከቦካ ጁንዬረስ፤ በብራዚል ፍላሚንጎ ከቫስኮ ደጋማ የሚገናኙባቸው ጨዋታዎች በደርቢ ትንቅንቃቸው ከኤልክላሲኮ በጣም የራቁ ናቸው፡፡
በዚህ ውድድር ዘመን ሁለቱ ክለቦች በአገር ውስጥና በአውሮፓ ደረጃ ባደረጓቸው ግጥሚያዎች በግብ መንበሻበሻቸው ሲያመሳስላቸው ሪያል ማድሪድ 49 ባርሴሎና 47 ጎሎችን አስመዝግበዋል፡፡ በዚህም በላሊጋ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም ለቀረበው 57ኛው የውድድሩ ዋንጫ አስፈሪ ተቀናቃኝ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ሁለቱን ክለቦች በውድድር ዘመኑ አውሮፓን በከፍተኛ ብልጫ መቆጣጠራቸውን ያመኑት የአርሰናሉ ቬንገር የዘንድሮውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከመካከላቸው መንጠቅ ከባድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዛሬው የኤልክላሲኮ ፍልሚያ የሚመዘገብ ውጤትን ከገመቱ የመጀመርያው “ሜሲ” ተብሎ የሚጠራው ኦክቶፐስ ሲሆን ድሉ የባርሴሎና መሆኑን ጠንቁሏል፡፡ በባርሴሎና ተከላካይ መስመር ወሳኝ ተሰላፊ የሆነ ፍቅረኛዋን ጄራርድ ፒኬ ለማበረታት ሳንቲያጎ በርናባኦ መድረስ ያልቻለችው ኮሎምቢያዊቷ ሻኪራ በበኩሏ በቦጎታ ግጥሚያውን እንደምትታደም ሰሞኑን ስትገልፅ ድሉ ለምትደግፈው ባርሴሎና እንዲሆን ተመኝታለች፡፡ ሻኪራ እንደ ፖል ዘ ኦክቶፐስ አይነት ጠንቋይ እንስሳ ቢኖረኝ ውጤቱን አስቀድሜ እተነብይ ነበር ብላለች፡፡
ማድሪድ ለ3 ባርሳ ለ6 ዋንጫዎች በላሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ የመጀመሪያውን ስፍራ የያዘው ሪያል ማድሪድ የውድድር ዘመኑን የጀመረው በስፔን ሱፐርካፕ በባርሴሎና ዋንጫ ተነጥቆ በሁለተኛ ደረጃ ነበር፡፡ ከላሊጋ የሻምፒዮናነት ክብር ውጪ በኮፓ ዴለሬይ በ32 ቡድኖች የዙር ጥሎ ማለፍ፤ በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ምእራፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን በውድድር ዘመኑ ለ3 ዋንጫዎች እየተወዳደረ ይገኛል፡፡
በላሊጋው 2ኛ ደረጃ የያዘው ባርሴሎና በበኩሉ በኮፓ ዴላሬይ በ32 ቡድኖች ጥሎ ማለፍ፤ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ እንዲሁም በፊፋ የአለም ክለቦች ሻምፒዮና ግማሽ ፍፃሜ ላይ ሲሆን በውድድር ዘመኑ አስቀድሞ ካገኛቸው የስፔን ሱፐር ካፕ እና የአውሮፓ ሱፕር ካፕ ሁለት ዋንጫዎች ጋር በዓመቱ ለ6 የዋንጫ ክብሮች ተሰልፏል፡፡
ወቅታዊ አቋም ሪያል ማድሪድ በሁሉም ውድድሮች 22 ጨዋታ አድርጎ 18 ድል ፤ 2 አቻ፤ 2 ሽንፈት እንዲሁም 72 ጎሎች በማስመዝገብ ሲሆን የማሸነፍ እድሉ በሁሉም ውድድሮች 81.82 በመቶ እንደሆነና በሜዳው 90 በመቶ ድል እንደሚያደርግ ተተምኖለታል፡፡ ባርሴሎና ደግሞ በውድድር ዘመኑ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 14 ድል አድርጎ በ5 አቻ ሲወጣ አንድ ብቻ ተሸንፏል፡፡ 71 ጎሎችንም አስመዝግቧል፡፡ ለባርሴሎና የማሸነፍ እድል በሁሉም ውድድሮች 82 በመቶ ሲሆን ከሜዳው ውጪ 90 በመቶ ድል ይቀናዋል፡፡ በላሊጋው ባርሴሎና 259 የጎል ሙከራዎች አድርጎ ኢላማቸውን የጠበቁት 45.6% ሲሆን 256 ሙከራዎች ያደረገው ማድሪድ ኢላማውን 42.2% ይመታል፡፡ በብዙዎቹ ጨዋታዎች የሚከተሉት አሰላለፍ ሪያል ማድሪድ 4- 2- 3- 1 ባርሴሎና 4 3 3 ነው፡፡
የውጤት ታሪካቸው ከዛሬ ጨዋታ በፊት ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና በኦፊሴላዊደረጃ 215 ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን በ86 ሪያል ማድሪድ 361 ጎሎች አስመዝግቦ ሲያሸንፍ ባርሴሎና በ84 ድል የቀናው 347 ጎሎች አግብቶ ነው፡፡ በቀሪዎቹ 45 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በላሊጋው ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ ማድሪድ 69 ባርሳ ደግሞ 63 ጊዜ የተሸናነፉ ሲሆን 31 ግጥሚያዎችን አቻ ተለያይተዋል፡፡ በታሪካቸው በሁሉም ውድድሮች ማድሪድ 74 ዋንጫዎችን ሲሰበስብ ባርሴሎና 72 ዋንጫዎችን አግኝቷል፡፡ ሪያል ማድሪድ 9 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና 31 የላሊጋ የዋንጫ ክብሮች ሲኖሩት ባርሴሎና 20 የላሊጋና 3 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ተጎናፅፏል፡፡
የፋይናንስ ንፅፅር የሪያል ማድሪድ ዋና ቡድን የተዋቀረው በ458.5 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ሲሆን የባርሴሎና ዋና ቡድን በ209.5 ሚሊዮን ዩሮ ተሰርቷል ፡፡ በዘንድሮ የተጨዋቾች ዝውውር የሁለቱ ክለቦች ወጪ እኩል ከ55 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ነው፡፡ ባርሴሎና ለአንድ ተጨዋች በአማካይ 7.9 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ደሞዝ ሲከፍል ማድሪድ የሚያወጣው 7.4 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
በ2010 እኤአ ዴልዮቴ ይፋ ባደረገው መረጃ በአመት 438.6 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ በማስመዝገብ የአለም ክለቦችን የሚመራው ሪያል ማድሪድ ሲሆን ባርሴሎና በ398.1 ሚሊዮን ዩሮ ገቢው ይከተለዋል፡፡ ሁለቱ ክለቦች እስከ 2013 እኤአ በቴሌቭዝን ስርጭት መብት በየውድድር ዘመኑ እያንዳንዳቸው የ120 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ያገኛሉ፡፡
የኤልክላሲኮው ዋናዎቹ ትንቅንቆች
ሞውሪንሆ ከጋርዲዮላ
ሁለቱም በፊፋ የአለም ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ ከመጨረሻዎቹ 3 እጩዎች ተርታ ገብተዋል፡፡ ሞውሪንሆ አምና ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው የተሸለሙ ነበሩ፡፡ ሁለቱም ከዛሬው የኤልክላሲኮ ፍልሚያ በፊት በቃላት አልተራኮቱም፡፡ ትንቅንቃቸውን በሜዳ ውስጥ በሚያሰልፏቸው ላይ ለማሳየት ሳያስቡ አልቀረም፡፡ በዛሬው ጨዋታ የሞውሪንሆ ሪያል ማድሪድ 4-4-2 አሰላለፍ እንደሚይዝ ሲጠበቅ የጋርዲዮላ ባርሴሎና በ4-3-3 ሊገባ ይችላል፡፡ ጆሴ ሞውሪንሆ በላሊጋው መስራት ከጀመሩ በሁለተኛ የውድድር ዘመናቸው ባርሴሎና በጋርዲዮላ አሰልጣኝነት ላለፉት 4 የውድድር ዘመናት በስፔንና በአውሮፓ ደረጃ ያለውን ልዩነት በማጥበብ ዘንድሮ ከፍተኛ ለውጥ አሳይተዋል፡፡
ኦዚል ከኢኒዬስታ
በኤልክላሲኮው የግራ ክንፍ መስመር ወይም በአማካይ ስፍራ ከሚጠበቁ ትንቅንቆች ዋንኛው በማድሪዱ ሜሱት ኦዚልና በባርሳው አንድሬይስ ኢኒዬስታ መካከል የሚደረገው ነው፡፡ ኦዚልና ኢኒዬስታ በኤልክላሲኮው ያለውን የፉክክር ሚዛን በማቃናትና በመቆጣጠር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡
ቫልዴዝ ከካስያስ
ሁለቱ በረኞች በኤልክላሲኮ ያላቸው ልምድ የትንቅንቁን መጨረሻ በመወሰን ግንባር ቀደም ሚና አለው፡፡ በውድድር ዘመኑ በ10 ጨዋታዎች ጎል ስላልገባበት የባርሴሎናው ቫልዴዝ በ7 ጨዋታዎች ጎል ካልስተናገደው የማድሪዱ ካስያስ የተሻለ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ካሲያስ ያለቀላቸው የግብ ሙከራዎችን በማዳን ከቫልዴዝ በእጥፍ ተሽሎ ይገኛል፡፡
አልቬዝ ከራሞስ
በኤልክላሲኮው ከሚጠበቁ የክንፍ መስመር ትንቅንቆች በማድሪዱ ሰርጂዮ ራሞስና በባርሴሎናው ዳንኤል አልቬዝ መካከል ይሆናል፡፡ ሁለቱም ተጨዋቾች ከዓለማችን ምርጥ የቀኝ ክንፍ መስመር ተሰላፊዎች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ራሞስ በሁለገብ ቅልጥፍናው እና በጠንካራ ታክሎቹ የሪያል ማድሪድን የመከላከል አቅም በማጎልበት፤ አልቬዝ ደግሞ በፍጥነቱ የባርሴሎና የማጥቃት ሃይል በማጠናከር በሚያሳዩት እንቅስቃሴ ኤልክላሲኮውን ሊያደምቀው ይችላል፡፡
ሮናልዶ ከሜሲ
አንዳንድ ዘገባዎች ለእያንዳንዱ ፔሌ ሌላ ማራዶና እንዳለ ሁሉ ለእያንዳንዱ ሜሲ ሌላ ሮናልዶ መኖሩን በመጥቀስ የሁለቱን ተጨዋቾች አስደናቂ ፉክክር እየገለፁ ናቸው፡፡
በፊፋ የ2011 የአለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ የመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች ሜሲ እና ዛቪ ከባርሴሎና እንዲሁም ሮናልዶ ከሪያል ማድሪድ ቀርበዋል፡፡ በዛሬው ኤልክላሲኮ በላሊጋው የኮከብ ግብ አግቢ ፉክክር በእኩል 17 ግቦች የተያያዙት ሮናልዶና ሜሲ በግብ አዳኝነት ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
ክርስትያኖ ሮናልዶ የቡድኑ ኮከብ ግብ አግቢ ሲሆን በላሊጋው በ17 ጎሎች እየመራ ከመሆኑም በላይ በሁሉም ውድድሮች 21 ጎሎች አስመዝግቧል፡፡ የባርሴሎና ክለብ ኮከብ ግብ አግቢ በላሊጋው 17 ጎሎች ያሉትና በሁሉም ውድድሮች 27 ያገባው ሊዮኔል ሜሲ ነው፡፡
ዣቪ
ዣቪ ሄርናንዴዝ ክሬየስ ለ14 አመታት ለባርሴሎና ዋና ቡድን ሲጫወት በሁሉም ውድድሮች 458 ጨዋታ አድርጓ 67 ጎሎችን አግብቷል፡፡ የግብ እድሉ በስድስት ጨዋታ አንዴ ነው፡፡
6 የላሊጋ፤ 1 የኮፓ ዴላሬይ፤ 5 የስፔን ሱፐር ካፕ፤ 3 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ያገኘው ዣቪ ከ2008 በኋላ ደግሞ ከስፔን ብሄራዊ ቡድን ጋር የአውሮፓና የአለም ዋንጫዎችን ለማንሳት በቅቷል፡፡ በ2009 እና 2010 በፊፋ የአለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ 3ኛ ደረጃ ያገኘው ዣቪ ዘንድሮ ለመጨረሻ ፉክክር ከገቡ ሶስት እጩዎች አንዱ ነው፡፡
በፊፋ የአለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ የቀረቡት ሶስት የመጨረሻ እጩዎች ዛሬ በኤልክላሲኮ ሁለቱ ለባርሴሎና አንዱ ለሪያል ማድሪድ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ተጨዋቾቹ ያስመዘገቡት ስኬት ለወርቅ ኳስ ሽልማት ያለውን ፉክክር የሚወስን ይሆናል፡፡ አምና በላሊጋው 40 ጎሎችን በማስቆጠር ሮናልዶ 31 ጎሎችን ያስቆጠረውን ሜሲ ቢመራም ሁለቱም ተጨዋቾች በሁሉም ውድድሮች እኩል 53 ጎሎችን አስመዝግበዋል፡፡ የባርሴሎናው ዣቪ በበኩሉ በጎል አስቆጣሪነት ከሮናልዶና ከሜሲ እኩል የሚፎካከር ባይሆንም በኳስ ማቀበል ችሎታው 90 በመቶ ትክክለኛ በመሆን የትኛውም ተጨዋች የማይስተካከለውን ብቃት ሲያሳይ ቆይቷል፡፡

 

br /

Read 6610 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 12:34